ሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ

መንግስታት በሚያስተዳድሩት የሀገር ህጋዊ ወሰን ወይም በተወሰነ አከባቢ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥማቸው በልዩ ጥንቃቄ ተግባራዊ የሚደረግ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጃሉ፤ የሁኔታው መሻሻል ሲረጋገጥም አዋጁ እንዲነሳ ያደርጋሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዋላጅ ምክንያቶች ናቸው ተብለው በስፋት የሚታወቁት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የሚከሰቱ አደጋዎች ቀዳሚ ምክንያቶች ተደርገው ቢወሰዱም ዲሞክራሲና ማህበራዊ ፍትህ ባልዳበረባቸው እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሀገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለመብትነት የሚሰጠው አብዝቶ ለሚያስጨንቃቸው የግለሰቦች የስልጣን ጉዳይ ነው፡፡ እነኚህ መንግስታት አብዛኛው ጊዜያቸውን የሚያጠፉት በተፈጥሮ ለሚደርሰው አደጋ ለመቋቋም የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ አቅምንና እውቀትን በማስተባበር ችግሩን ማስታገስ ወይም በዘላቂነት መፍታት ሳይሆን ተቀናቃኝ ለማጥፋት፤ የሀገርን እድገት በሚያቀጭጭ ተግባር ስራ ላይ የሚውሉ አዋጆች ማርቀቅና ማጽደቅ ለአፈፃፀሙም ከፍተኛ የሰው ሃይልና በጀት በመመደብ እንደሆነ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተዛማጅ የሆኑ የታሪክ ድርሳናት እንረዳለን፡፡

ኢትዮጵያም አንድ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያውጀው የመንግስት መደበኛ ስራዎች ሲታወኩና በመደበኛ የህግ አግባብ ለማከናወን አዳጋች ሆነው በሚገኙበት ሁናቴ የሚፈፀም በመሆኑ ነውና ለታወጁት አዋጆች ምክንያት የምንላቸው ለጊዜው ገታ አድርገን የብልጽግና መንግስት ባለፉት አምስት አመታት ከህዝብ እየገጠመው ያለው ሀቀኛ ተግዳሮትና ፈተና እንደዚሁም ራሱ በፈጠረው መደላድል የተፈለፈሉ ቡድኖች ለሚያነሱት ጥያቄዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቸኛና አማራጭ የሌለው መፍትሄ አድርጎ መውሰዱን እንገነዘባለን፡፡ ከአምስት አመት ወዲህ በኢትዮጵያ መንግስት የሚኒስትሮች ምክርቤት በኩል ተረቀው የተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ያፀድቃቸው አዋጆች ቀደም ብለው ከነበሩት አመታት ጋር ሲነፃፀሩ ለቁጥር አታካች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በነኚሁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አመታትም ምን ያህል የሀገሪቱ ሀብት እንደወደመ፣ የምን ያህል ወጣት ህይወት እንደተቀጨና ተስፋው እንደተኮላሸ፣ የህዝቡ የእለት ተእለት ስራ እንደተቃወሰ፣ ስራ ብቻም ሳይሆን ምን ያህል ህዝብ ወጥቶ የመግባት መብት ተነፍጎት መሽቶ በነጋ ቁጥር ሲቃትት እንደሚውል፣ ምን ያህሉ ደስተኛ ህይወት ለመምራት እድል እንደተነፈገ፣ ምን ያህሉ ማህበራዊ መስተጋብሩ ተበጥሶ አንዱ በአንዱ ላይ የቂምና በቀል እንዳረገዘ የሚመልስ ጥናት ወደፊት እንደሚኖር ተስፋ በማድረግ ለጊዜው ግን ቤቱ ይቁጠረው ማለት የሚሻል ይመስለኛል፡፡

ወደ ዋናው የዛሬ አጭር መጣጥፌ ስመለስ ነሃሴ 06/2015 የኢትዮጵያው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደለመደው አንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያፀድቅ በሚኒስትሮች ም/ቤት በኩል ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡ ይህ አዋጅም የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው፡፡ ምክርቤቱ የቀረበለትን ጉዳይ ከመመልከቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አዋጁ እንደይጸድቅ በሚፈልጉ ሃይሎች የተለቀቀ የእያንዳንዱ የአማራ ክልል ተወካይ የስልክ ቁጥሮች የያዘና አዋጁ እንዳያፀድቁ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ መልእክት በስፋት ሲዘዋወር ተስተውሏል፡፡ ያም ሆነ ይህ ጥረቱ አዋጁን ከመጽደቅ አልታደገውም፡፡ መጽደቁ ተከተሎም በርካታ ሚዲያዎች የእለቱ የምክርቤት ውሎ አስተጋብተዋል፣ ከነኚህ መካከል ግን የአንድ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስምና ንግግር በተለየ መልክ ሲዘገብና ሲተነተን ተመልክቻለሁ፡፡ ለምሳሌም አንድ ሚድያ “ከሙታን መካከል ህያው ሰው ተገኘ” በማለት ተጠቃሹ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ሲያንቆለጳጵስ አድምጫለሁ፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለባቸው ጥቂት ግን መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ጠቆም አድርጌ ልለፍ፡፡ 1) የአቶ ገዱ የቀድሞ ስብእና ዋቢ በማድረግ አሁን በምክር ቤቱ ካደረገው ንግግር ጋር በማነፃፀር እውን አቶ ገዱ ከሙታን መካከል የተገኘ ህያው የሚያስብል ጀብድ ፈጽሟል ወይ? 2) ከንግግሩ ጀርባ ያለው ገፊ ምክንያትስ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ ነኝ ለሚል ሁሉ ጠቃሚ ንግግር ነበር ወይ? 3) በሌላ አነጋገር ግለሰቡ በፊት ሲያንፀባርቃቸው የነበሩት አቋሞች አሁን በተወካዮች ምክር ቤት ውሎው ካደረገው ንግግር ጋር በማወዳደር ይህ የገዱ ንግግር ከምር መወሰድ የሚገባው ጉዳይ ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ የሚገባ ይመስለኛል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኢህአደግን በአባልነት ከተቀላቀለ ጊዜ አንስቶ በአማራ ክልል በተለያየ የስራ የሃላፊነት ደረጃዎች አልፎ እስከ የክልሉ ከፍተኛ ቦታ የሆነውን የርእሰ መስተዳደርነት የሃላፊነት ቦታ መድረሱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ትልቅ የሃላፊነት ቦታ ተመድቦም በርካታ በጎ እና ጎጂ የሆኑ ስራዎች እንዳከናወነ ይገመታል፡፡ ከበጎ ስራዎቹ ከሚጠቀሱት መካከልም በወልቃይት ላይ ሲነሳ የነበረውን የማንነት ጥያቄ ከብዙ ልፋት በኋላም ቢሆን በኢህአዴግ የስልጣን የመጨረሻ አመታት ገደማ ከትግራዩ አቻው አቶ አባይ ወልዱ ጋር በመሆን በቴሌቪዠን መስኮት በመቅረብ “ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈተነዋል፤ እንካን ደስ አላችሁ” የሚል የማብሰሪያ ንግግሩ ማስታወስ ይበቃል፡፡ ከጎጂ ስራዎቹ መካከልም ትልቅ ሰህተት ተደርጎ መወሰድ የሚገባው ጉዳይ ህዝብን እንደህዝብ በመጥላት ትግራይ የሚባል አንድን የጎረቤት ክልል ህዝብ መንገድ በመዝጋትና ውስጥ ውስጡን ሃይል በማደራጀት የቅድመ ከበባ ስራዎችን ያስጀመረ፤ ከዚያም ቲም ለማ የሚባል ቡድን በማደራጀትና በመምራት ሀገርና ክልሉ አሁን ለገቡበት ጥልቅ ችግር ብኮውን በማቡካትና በመጋገር በኋላም ወደ ፌዴራል መንግስት የስልጣን እርከን በመዛወር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትና ከዚያም ቀጥሎ የአብይ አህመድ አሊ የፀጥታ አማካሪ ሚኒስትርነት ከስልጣኑ በሚመነጭ የቀጥታ ተሳታፊነት የተጫወተው ሚና እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ የገዱ ፖለቲካዊና ግለሰባዊ ስብእናውን ስንመረምር እንደ አንድ የመንግስት ቁንጮ አባል የሀገር ጠላት የሆነው የውጭ መንግስትን በጄኖሳይዳል ጦርነት እንዲሳተፍ ከጥንስሱ በመሳተፍ ፣ በጋራ በማቀድና በተግባርም ተሳታፊ በመሆን ጦርነቱም ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር የበኩሉን ከፍተኛ ሚና የተጫወተ፣ የገዛ ወገኑ ያስገደለ፣ ያስጨፈጨፈ፣ በፓርላማ ያስወሰነ፣ ለጦርነት ዝግጅቱ ህዝብን ያነሳሳ፣ በጦር ሜዳ ላይ በመገኘት የቀሰቀሰ፣ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ (ዲፕሎማቶችንም ይጨምራል) የተሳሳተ መረጃ የሰጠ ሰው እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት መሰል ሰብእናዎች የአንድን በክህደት፤ በማታለልና በአደርባይነት መታወቂያው ካደረገ ሰው የምናገኛቸው መለዮዎች ናቸው፡፡ እንግዲህ ይህ አይነት ስብእና የተላበሰ ሰው ነው ከሙታን መሃል  ህያው ሆኖ ተገኘ የሚሉን፡፡

እዚህ ላይ ይህንን መሰል አስተያየት የሚሰነዝሩትን ለመሞገት አንድ ቀላል ጥያቄ ማንሳት በቂ ይሆናል፡፡ በወርሃ ነሃሴ 2015 የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ያፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአማራ ክልል ውጭ በሆኑ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ወይም ክልል እንዲታወጅ የቀርበ ጥያቄ ቢሆን ኖሮ ገዱ በምክርቤቱ መድረክ ላይ አሁን ያሰማው መራር ተቃውሞ አይነት ንግግር ያደርግ ነበር ወይ? ለኔ አይመስለኝም!! ምክንያቱም በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በቤንሻንጉልና በመጨረሻም በትግራይ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የህዝብ ተወካዮች ተብየዎቹን ተግባር ታዝበናል፣ ገዱም ድምጹ ሲያስተጋባ አልተሰማም፡፡ ለምን በዛን ወቅት አልተቃወምክም ተብሎ ቢጠየቅ ምናልባትም በምክር ቤቱ አልነበረኩም ወይም ሌላ ምክንያት ከመስጠት ይቆጠባል ብዬ ለማሰብ አይገደኝም፤ ምክንያቱም ከፖለቲካዊ የተሳትፎ ሰብእናው የምረዳው ሲምልለትና ሲገዘትለት የነበረውን ኢህአደግን ከኋላው ሆኖ በመውጋት፤ አሁን ደግሞ አብሮና ተነባብሮ ብዙ ግፍ ሲፈጽምና ሲያስፈጽም ለነበረው ብልጽግና በመክዳት የዥዋዥዌ ትእይነት አሳይቶናል፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ጉዳይ በህገመንግስቱ መሰረት ፌዴሬሽኑ ከመሰረቱት ክልሎች መካከል ከ60 በመቶ በላይ በሆኑ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ረስቶ በ “ነግ በኔ” ስም የሸነቀረው ማስፈራሪያው ቃሉ ነው፡፡ በበኩሌ ለየትኞቹ ክልሎች ይሆን ይህ መልእክት የተላለፈው? ብዬ ብጠይቅ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ ይህ ሰው ለሰውልጆች ልእልና፣ በመፈቃቀድ የተመሰረተ እኩልነት፤ ዲሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት ቀናኢና የማይነወጽ እምነትና ስብእና ባለቤት ቢሆን ኖሮ በየትኛውም መድረክ ላይ የሚናገራቸው ንግግሮች፣ በተግባር ሲያራምዳቸው የነበሩ አቋሞች ተመሳሳይነትና ወጥነት ይኖራቸው ነበር ብለን ልንከራከር እንችላለን፡፡ ባህርያዊ ማንነቱ የሚያሳየው በአንድ ወቅት ያራመደውን ሃሳብ በሌላ ሃሳብና ተግባር ሲያፈርስና ሲዋዥቅ ነው የተመለከትነውና ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ ቀድሞውንም የሞተ ሰው ከሞቱት መካከል ተነስቶአል ብሎ በባትሪ ለመፈለግ መሞከር፤ ዳንኪራ መምታትና ለዝና ለማብቃት ጥረት ማድረግ፣ ዘፋኙና ተከታዩ የሚያስተዛዝብ፣ ለሚዘፈንለትም ሰው ቤቱን አይገጥምለትምና ቢቀር ይሻላል ባይ ነኝ፡፡

በቸር እንሰንብት  

By aiga