08/06/2023

ከሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በትግራይ መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያካሄደውን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ላይ ለመምከር የጠቅላላ ሲኖዶስ ስብሰባ ለሃምሌ 25/2015 መጥራትዋ ሲነገር ከትግራይ እስከ ኦሮሚያ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ባህርዳር፤ ከአሜሪካ አስከ አውሮፓ ያለ ህዝበ ክርስቲያን በሁለት ጎራ ላይ የተንጠለጠለ መላምት ሲመታ ከርሟል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የገባችበት ምስቅልቅል በቅጡ የተረዳ ወገን “ሁሉም ወገኖች ተቀራርበው ችግሮቻቸው የሚፈቱበት” ጊዜ አሁን ነው እያለ መጪውን በተስፋ ተሞልቶ መልካም ምኞቱን ሲገልጽ በሌላ በኩል ደግሞ “የሚያስፈልገው ማውገዝ ብቻ ነው” በማለት የከረረውን ሲባጎ ሲገዘግዝ አድምጠናል፡፡ እኔም ባለፈው በስነበብኩት ጽሁፌ ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና ተከታዮችዋ መልካምና ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብዬ ነበር፡፡ በጽሁፌም ይህንን እድል በመልካምነቱ ከተጠቀመችበት ቤተክርስቲያኒቱ ወደተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር በሩ ይከፍትላታል የሚል ምክረ-ሃሳብ ጠቃቅሼ ነበር፡፡ ታሪካዊ አጋጣሚ ስል ከምር ነበር፡፡ ቤተክርስቲያንዋም ጊዜው የምርጫ ምርጫ የሌለው ኮስታራና መራራ ሃቅ ነው ብላ ከምር ትወስደዋለች ብዬ አስቤ ነበር በሃምሌው 26 የሆነው ግን በሚያንገራግጭ ኮሮኮንች መንገድ ሂዳ እንደምትቆም መኪና እሷም በሩ ላይ ደርሳ ቆመች፡፡ በተቋማዊ የልማት አቅጣጫ እሳቤ ቤተክርስቲያኒቱ የተከተለቸው መንገድና አተያይ “የተቋሞች የክስረት መንገድ” ይለዋል፤ አጋጣሚው አለመጠቀም እንደ ባከነ ጊዜ ይቆጠራል፡፡ ተቋሞች ድቅድቅ ጨለማ ሲያጋጥማቸው ተጠባቂው መፍትሄ የጥሞና ጊዜ ወስደው “ጥልቅ ፍተሻ” ማካሄድ ወይም በሃይማኖታዊ የአጠራር አቻው የአርምሞ ጊዜ ወስደው “ንስሃ” መግባት ተመራጭ መንገድ ይሆናል፡፡ ይህ ተቋማዊ “የፍተሻ” ወይም ”የንስሃ“ ጊዜ መልካም አጋጣሚ የሚባልበት ዋናው ምክንያትም ሀ) በስራ ላይ ያሉትን ህጎች፤ የአሰራር መመሪያዎችና ደንቦች (ቀኖና፤ ዶግማ) የመፈተሽ እድል ይኖራቸዋል ለ) የተቋሙ ተሿሚዎችና (ሊቃነጳጳሳት፤ ካህናት፤ ዲያቆናት) መላው ሰራተኞች በተቋሙ ተልእኮ አፈጻጸም ላይ ያላቸውን ሚናና ተሞክሮ የመገምገም አጋጣሚ ይኖረዋል ሐ) ልዩ ልዩ ተግዳሮቶችን በመለየት ዘመኑን የዋጀ አዳዲስ ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ የሚያስችል እድል ያገኛሉ፡፡ በዚህ የተነቃቃ ተቋም ወደ ጠንካራ ተቋምነት ለመቀየር ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል ተብሎ ይታመናል፡፡  

ማንኛውም ተቋም በተቋቋመበት አላማና ተልእኮ ልክ የሚያበረክተው አገልግሎት ተደራሽነት፤ ፍትሃዊነት እና ጥራት በአገልግሎት ተጠቃሚውና ቀጥታ ድርሻ ባላቸው አካላት ይለካል፤ ይመዘናል፤ ይገመገማል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም በጋህዱ አለም ያለች ተቋም እንደመሆንዋ መጠን ከዚህ እውነታ ውጭ ልትሆን አትችልም፡፡ ብትፈልግም አስተሳሰቡ ጊዜው ያለፈበት ከመሆኑም በላይ ተቀባይነቱ የሳሳበት ዘመን መድረሳችን ማወቅ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ለማወቅም የግድ ነቢይ መሆን አይጠይቅም፡፡ ከኛ የሚጠበቀው ትንሹ ነገር በዓለም ላይ የተከሰቱ ተቋሞች ውልደት፤ እድገትና ሞት ከታሪክ ድርሳናት መፈለግ ብቻ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስትና እምነት ጠብቃ ለረዥም ዘበናት የቆየች ሀገር መሆንዋን ማንም አይክደውም፡፡ በአማኙም በኩል ከሱ የሚጠበቀው ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አላለም፡፡ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፤ ከሶማሌ እስከ ወለጋ በሃይማኖት አባቶች የሚቀርብለትን ጥያቄ ያለምንም ማንገራገር ሲቀበል ኖርዋል፡፡ ቅዱስ መጽሃፉ በሚልክያ ምእራፍ 2፡7  “ካህኑም የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሄር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል ፥ ሰዎችም ህግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል” ብሎ እንደሚያዘው አማኙ ለቤተክርስቲያንዋ፤ ለካህናትዋና ለጳጳሶችዋ በፍጹማዊ ታዛዥነት ታማኝነትና ራሱን በማስገዛት ሲታዘዝ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ ተነስ ሲባል ይነሳል፤ ተኛ ሲባል ይተኛል፡፡ ሥራ ሲባል ይሰራል፤ አትሥራ ሲባል አይሰራም፡፡ ብላ ሲባል ይበላል፤ አትብላ ሲባል አይበላም፡፡ አዋጣ ሲባል ያዋጣል፤ አታዋጣ ሲባል አያዋጣም፡፡ እንዳውም በቅርቡ እንዳየነው ዝመት ሲባል ይዘምታል፤ ግደል ሲባል ይገድላል፡፡ እዚህ ላይ ማንሳት የሚገባን ጥያቄ አማኙ ለሃይማኖት አባቶቹ ይህንን ያህል ቀናኢ ከሆነ፤ የዛሬዋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህን በእግዚአብሄር መልእክተኛነቱ ከንፈሮቹ እውቀትንና እውነትን ለዚህ ታማኝ አማኝ ያፈልቃሉ ወይ? የሚል ይሆናል፡፡ ይህ ጥያቄ ለመመለስ በየጓዳና ጎድጓዳው የሚነገር በርካታ ጆሮን ጭው የሚያደርግ የንቅዘት፤ የብልሹ አሰራር፤ እና የስነምግባር ጉድለት ታሪኮች ቢኖሩም ጽሁፉ ለተነሳለት አላማ የሚረዳ በተቋሙ እውቅና አግኝተው እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ኢ-ሃዋርያዊ ህፀፆች ላይ ማተኮር ነው፡፡ እነኚህ ህፀፆች ደግሞ የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንዲሉ የላእለዋይ መዋቅሩ ነፀብራቅ መሆኑ መረዳት ይገባል፡፡ ፀሃፊው ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት በተለያየ ጊዜ የተሰጡ የሲኖዶስ መግለጫዎች፤ የመንግስት ባለስልጣናት መግለጫዎች፤ የሲኖዶሱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሚዲያ ጋር ያደረጉዋቸው ቃለመጠይቆች፤ ሊቀነ-ጳጳሳት በአውደምህረት ተገኝተው ለመእመናን ያስተላለፉዋቸው ሰበካዎች በመረጃ ምንጭነት ተጠቅሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንደተቋም ያላት ተልእኮ ሃዋርያዊና መንፈሳዊ ብቻ  መሆኑ በፍትሃነገስቷ፤ በ ቃለ አዋዲ እና በመሳሰሉ ሌሎች ተዛማጅ መመሪያዎችና ደንቦቿ ይደነግጋል፡፡ ይህ ሃዋርያዊ ተልእኮ  ወንጌልን ፤ ሰብአዊና ሰብአዊ ክብርን ፤ መልካምነትን፤ ሰላምን፤ ወንድማማችነትን የመሳሰሉ መርሆዎች መሰረት ያደረገ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ከነኚህ መርሆዎች በተጻራሪ የቆሙ ማንኛውንም ድርጊቶች ተፈጽመው ሲገኙ መኮነን፤ ተላላፊዎቹም ዘንድ ውግዘት ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ጽሁፌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንደተቋም የተልእኮዋን ዋና ሃዲድ የሆኑ አበይት አእማዳት ማለትም በወንጌል፤ በሰብአዊነትና በፍትህ የሳተችበት ጉዳዮች ያስረዱልኛል የምላቸው ላይ ብቻ አተኩሬ አብራራለሁ፡፡ እግረመንገዱም የቤተክርስቲያኒቱ ሹመኞችና ሰራተኞች የተቋምዋ ተልእኮ እንዲያስፈጽሙ በእምነት በሰጣቻቸው የሃላፊነት ማእቀፍ ስር ሆነው ያደረሱባት  ኪሳራ ክብደት ለመገንዘብ ያስችለናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በቅድሚያ ወደዝርዝር ጉዳይ ከመግባቴ በፊት በቅርብ ቀን ከአንድ ወዳጄ ጋር በቤተክርስቲያኒቱ ስለተከሰተው ጉዳይ የተነጋገርነው ላስቀድም፡፡ ይህ ወዳጄ ለእምነቱ ተማኝ መሆኑ አውቃለሁ፡፡ በሲኖዶስ አባላት የተደረገውን መንፈሳዊ ግድፈት አንስተን ስንጨዋወት “ይህማ የግላቸው ነው ሲኖዶሱን የሚመለከት አይደለም” በማለት ይህንን የመሰለ ግዘፍ ያለ ስህተቶቻቸውን ለመሸፋፈን የተጓዘበት ርቀት ሳጤን በእርግጥም ሰፊው አማኝ በሚያሳየው የየዋህነትና ግብዝነት አቋም ተቋምዋ የገባችበት ምስቅልቅል ለመፈወስ የማይጠቅም ከመሆኑም በላይ ተቋምዋ ንስሃ ገብታ የማስተካከያ እርምጃ ልውሰድ ብላ ብትንቀሳቀስ አማኙ ራሱ ከተልእኮ ፈጻሚዎቹ ጋር የተጋመደበት የእውር አፍቅሮት እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችልም ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካልዋት አጠቃላይ የሲኖዶስ አባላት መካከል በሀገር ውስጥ ከስምንት ያላነሱ ሊቃነ-ጳጳሳት፤ ውጭ በተልእኮ ካሉት ደግሞ አስራ ሁለት ሊቃነ-ጳጳሳት በድምሩ ሃያ የሚደርሱ ሊቃነ-ጳጳሳት የተሳተፉበት ኢ-ሃዋርያዊና ኢ-መንፈሳዊ ተልእኮ ተቋማዊ ከመሆን ውጭ ሌላ ምን ስም ሊወጣለት ይችላል?  

1.ወንጌል

ክርስቶስ “እኔ እውነትም፤ ህይወትም መንገድም ነኝ” ይላል፡፡ ይህ ቃል ክርስቶስ ለሰው ልጆች ከተናገረው ውብ፤ እጹብና ወድ ቃሎች መካከል የላቀ ቃል ነው፡፡ በክርስቶስ የምታምንና ስለክርስቶስ መልካሙን ሁሉ የምትሰብክ፤ ወንጌሉን የምታስፋፋ ቤተክርስቲን ይህ ቃል ሃዋሪያዊ ተልኦኮዋ ብቻም ሳይሆን በዘመናት ሁሉ ከዚህ መሰረታዊ አቋም (ዶግማ) ጋር ተጣጥማ መሄድ እንደሚገባት ህገ-እግዚአብሄርና ህገ-ቤተክርስቲያኒቱ ያዛል፡፡ በቅርብ ጊዜ ከታላላቅ ሹሞችዋ “የሰው ልጅ ከሚገዛን ሰይጣን ይግዛን” እና “ጅብ በልተህ ተቀደስ” ሲሉ አዳመጥን፤ አፍችን በእጃችን ከደን፡፡ “አለም ያልፋል ቃሌን ግን አያልፍም” የሚለውን የጌታችን የመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል አጥብቀን የያዝን አማኞች እነኚህ ሰዎች ምን ማለታቸው ነው ብለን በየቤታችን ስናጉተመትም አንዳንዶቹም እስካሁን ከተማርነው መካከል ያላወቅነው ሃቅ ይኖር ይሆን እንዴ ብለን ለማወቅ የባዘንበት ሆኖ አልፏል፡፡ አጠቃላይ ምእመንዋም ግራ ተጋብቶ፤ ቤተክርስቲያንዋም በሁለት መንታ አስተምህሮት መካከል እየናወዘች ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡

በመሰረቱ እንደዚህ አይነት ተልእኮአዊ ክስረት ወይም የተፋለሰና የተሳከረ አስተምህሮት ሲያጋጥም የቤተክርስቲያኒቱ ሊቀ ሊቃውንት ጊዜ ሳይወስዱ ተሰብስበው መምከር፤ መመርመር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንኳን በአደባባይ (በአውደምህረቱ) የተነገረ ጉዳይ ቀርቶ በሚስጥር የተደረገ ሃይማኖታዊ ተልእኮን የሚሸረሽር ነገር ካለ አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ በቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና እና ዶግማ በሚፈቅደው መሰረት በሊቃውንቱ ሰፊ ክርክር ይደረጋል፤ ይመከራል መግባባት ላይ ይደረሳል፡፡ እንደዚሁም ከታሪክ፤ ከተመክሮ እና ከሌሎች መሰል እህት አብያተክርስቲያናት አስተያየት ይሰበሰባል፡፡ በስተመጨረሻም የተደረሰበት ፍሬ ሃሳብ ከውሳኔ ጋር ለምእመኑ ይገለጻል፡፡ እንግዲህ “ሰይጣን ይግዛን” “ጅብ በልተህ ተቀደስ” ተብሎ በሊቃነ-ጳጳሳቱ አንደበት የተነገረው ቤተክርስቲያኒቱ ዝም መጽሃፉም ዝም እንዲሉ እስካሁን ድረስ የተባለ ምንም ነገር የለም፡፡ ከማንም በላይ የሚመለከታት ቤተክርስቲያኒቱ ሆና እያለች ሊቃነ-ጳጳሳቱና ካህናቱ የተናገሩት ልክ ነው ወይም የተሳሳተ ነው ብላ ስታውጅ አልተሰማም፡፡ ከእግዚአብሄር ክብር ዲያብሎስ ክብር የሚያስበልጡ ሊቃነ-ጳጳሳቱም ታቅፋ ትኖራለች፡፡ እንዲህ የመሰለ የተጣረሰ እምነት ማራመድ አስተምህሮቱ ከስሩ የሚሸረሽር፤ አማኝም የሚያሸሽ፤ ህብረትን የሚያፋልስ እንደሚሆን ለማንም ግልጽ ነው፡፡

ሌላው ሃይማኖታዊ ታሪክ መፋለስ አንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መገለጫ እየሆነ የመጣ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን በቅርቡ የሰማናቸው ትረካዎች ያረጋግጡልናል፡፡ ስምን ግብር ይከተለዋል እንዲሉ በቅርቡ አንድ አስተሳሰባቸው ህፃን ስማቸው (አባ) ህፃን የሚባሉ ሰውዬ በቴሌቪዥን ቀርበው ሰላማ የሚባል ነገር የለም ሲሉ ታሪክን ሲክዱ አድምጠናል (በቴሌቪዠን ቃለመጠይቅ ባደረጉት ምልልስ ባሰዩት ለከት የሌለው የስብእና መቃወስ ችግር እሳቸው በአንቱታ መጥራት ያላስተማሩን ክርሰትያናዊ ትህትና ገበያ ሄዶ የማያገኙትን ሸቀጥ ፍለጋ ሲንከራቱ መዋል መሆኑን ባውቅም ቅሉ በከበሬታ ጠርቻቸዋለሁ)፡፡ እውነታው ግን በ4ተኛው ክፍለ ዘመን የወቅቱ የአክሱም ንጉስ ኤዛና ክርስትና እምነት እንዲቀበል በማድረግ ረገድ ሶርያዊው ፈሬሚነስ ከፍተኛ ሚና መጫወቱ በኋላም አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በሚል የመጠሪያ ስም የመጀመሪያው ጳጳስ እንደሆኑ ታሪክ ይነግረናል፡፡ እንደዚህ አይነት የታሪክ አረዳድ የተበላሸበት ወይንም በታሪክ መነፅር ውስጥ አለማለፍ፤ በተጨማሪም “ሰው ከሚገዛን ሰይጣን ይግዛን” ካሉት ሊቃነ-ጳጳሳት ጋር ተዳምሮ እነኚህ ሰዎች የእውቀት ምንጫቸው ከየት እንደሚቀዳ እንድንመረምር ጊዜው አሁን መሆኑን ለኦርቶዶክስ አማኞች ወንድሞቼና እህቶቼ ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡  

ከታሪክ አረዳድ ሸውራራነት ባሻገር የወንጌል ተልእኮ መንሸራተት የምናይበት ሌላኛው አውድ ቢኖር ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጎራ መቀላቀል ነው፡፡ ይህንን ተልእኮ በተቋማዊ ቅርጽ ውስጥ አጭቃ በማስገባት ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ረዥም ርቀት የተጓዘችበትና ለአሁናዊ የቤተክርስቲያኒቱ ሰንጥቃት መነሻ ችግር የዳረጋት አቢይ ክስተት ተደርጎ በታሪክዋ ሊከተብ የሚችል መጥፎ የታሪክ አሻራ ይመስለኛል፡፡ እግረመንገዴም በዚህ ሂደት የመእምናኑ ሁሉን አሜን ብሎ የመቀበል አባዜ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በኋላ ላይም ለጦርነቱ መቀጣጠልም ትልቅ ሚና እንደነበረው ሳንረሳ ነው፡፡ እዚህ ላይ ይህ የፖለቲካ ዥዋዥዌ በተልእኮዋ ውስጥ አጋምዳ መሄድዋ ትክክል ነበር ለሚሉ ልበ የዋሃን የሁለት ጦርነቶች እያወዳደርኩ ላስረዳ፡፡ አንድ ሀገር በእርስ እርስ ጦርነት በምትታመስበት ወቅት ጦርነቱ አንዱ ከሌላው በልጦ ለመገኘትና ሌላውን በመድፈቅ ማሳነስ የሚደረግ ጦርነት ይሆናል፡፡ በእንዲህ የመሰለ የጦርነት አይነት እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያሉ የእምነት ተቋማት ሚናቸው የሚሆነው ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ሳይመርጡ “ከጦርነት የሚገኝ ቢኖር ጥፋትና ውድመት ብቻ ነው” በማለት ሌትና ቀን ብርቱ ጥረት አድርገው በሁለቱ ወንድማማቾች የተፈጠረውን ስሜት ማርገብ ይገባቸዋል፡፡ በአንጻሩ ወረራው በውጭ ሃይሎች የተፈፀመ ከሆነ ወራሪውን በማግኘት የእርቅ ሂደት ለማድረግ ፍፁም የማይታሰብ ከመሆኑም በላይ ጥፋቱ የከፋና የባሰ ሁሉንም ነዋሪ እከሌ ከእከሌ የዚህ እምነት ወይም የዚያ እምነት ሳይመርጥ የሁሉ ህይወት የሚያመሳቃቅለብት ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ መላውን አማኝ ራሱን እንዲከላከል የሃይማኖት አባቶችም ጦርነቱን የሚቆምበት ጊዜ አምላካቸው እንዲያመጣ በመፀለይ ያሳልፋሉ፡፡ በትግራዩ ጦርነት የታየው ሁለቱም አይነት ጦርነቶች ያዳቀለ በመሆኑ ጥፋቱም እጅግ የከፋ ሆኗል፡፡ ይህ ጦርነት ወንድማዊ ጦርነት በመሆኑ ከቤተክርስቲያኒቱ የሚጠበቀው የማስታረቅ ሚና እንጂ ካበደው ወገን ጋር ሆና ድጋፍ ለማድረግ ማኮብከባ በስተመጨረሻም በሙሉ ሃይላ ተዘፍቃ ስንመለከት በየትኛውም ስነአመክንዮ ተቀባይነት የለውም ለማለት እንገደዳለን፡፡ እንደውም ያየነው አሳፋሪ ተግባር ተጋብዞ የመጣው የባእዱ መሪ እንኳን  የአክሱም መእመንና ቀሳውስት ወገኖቻችን ፈጀህ፤ እንኳን ንዋያተ ቅዱሳናችን ዘረፍክ፤ ለዚህም የአክሱም ሃውልት መሸለም ይገባሃል ብሎ አቡነ አብርሃም ኤርትራ ድረስ ተጉዘው የጌታችን መድሃኒታችን መስቀል አውሬውን ማሳለምና ሽልማት መስጠት ሆነ፡፡ ይህ ራሱ ግራ የሚያጋባና እንግዳ ነገር በመሆኑ እስካሁን ድረስ አእምሮአችን መቀበል ካልቻላቸው ጉዳዮች ከመሆኑም በላይ፤ የትግራይ ጦርነት ባስታወስን ድቅን የሚል የምን ጊዜም ጥያቄ ሆኗል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለመሆኑ ይህ ሁሉ ድፍረት ከየት መጣ? ምንስ ቢፈጠር ባእድና ጠላት የሆነው ከወገንህና ያንተን እምነት ከሚከተል አንድን ህዝብ እንዴት ይበልጥብሃል? ለኛ እነኚህ ጥያቄዎች መልስ ያላገኘንላቸው የዘወትር ጥያቄዎች ሲሆን ለእነ አባ አብርሃም ለመሳሰሉት ደግሞ ማለፍ አይቀርምና ይችን ምድር እስኪሰናበቱ ድረስ ሁሌም በበጎቻቸው ባደረጉት ክህደት ዘወትር የሚያባንናቸው ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል፡፡      

ሃገሪቱ በ1987 ባፀደቀችው አሁንም በምትመራበት ህገመንግስት ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ መሆኑን፤ አንዱ በአንዱ ላይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ይህንን ህገ-መንግስት ተከትሎ የሆነውን እስቲ ወደ ኋላ ጥቂት መለስ ብለን እንቃኝ፡፡ የደርግ መንግስት ወድቆ ኢህአደግ ስልጣኑን በተረከበበት ማግስት በቤተክርስቲያኒቱም የስንጥቃት ምልክቶች መታየት ጀመሩ፡፡ ይህ ስንጥቃት ሄዶ ሄዶ የአገር ቤቱ ሲኖዶስ እና ስደተኛው ሲኖዶስ  በሚል ሁለት ተቋሞችን ፈጠረ፡፡ ስደተኛው ሲኖዶስ ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ የራሱ ሊቃነ-ጳጳሳት በመሾም ተቋማዊ ቅርፅ ፈጥሮ ስራውን ሀ ብሎ ጀመረ፡፡

ይህ ሲኖዶስ የሃገርቤቱን ስልጣን በማዶ አሻግሮ እየተመለከተ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ በአንደኛው መንገድ በመእመኑና በሀገርቤቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ጥላቻና አለመተማመን እንዲፈጠር የሚችለውን ሁሉ ማድረግ  ሲሆን ሁለተኛው መንገድ ደግሞ መንግስትን ለመጣል ከተቋቋሙት የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በሚስጥርና በገሃድ በመመካከርና ድጋፍ በመስጠት ከፍተኛ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ለአብነት ያህልም የአቶ ሃይለማርያም የአስተዳደር ዘመን ከማብቃቱ ጥቂት አመት ቀደም ብሎ የኢሳት ቴሌቪዥን ያቀረበውን ዜና ማስታወሱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ዜናው በስደተኛው ሲኖዶስና በግንቦት ሰባት የጋራ ጥምር ግብረ-ሃይል ተዘጋጅቶ የቀረበለትን በአሁኑ ሰአት የጄኖሳይድ አቀጣጣይ ስም የወጣለት መሳይ መኮንን ነበር የተነበበው፡፡ “የጎጃምና የጎንደር ካህናትና መነኮሳት በብጱእ አቡነ ማቲያስ የሚመራውን የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ከዛሬ ቀን ጀምሮ እንደማይቀበል አስታውቋል” ብሎ ሲያውጅ የውጪው ቡድን ዋና አስተባባሪ የሆኑት የኒውዮርኩ ሊቀጳጳስ አቡነ ጵጥሮስ  “ወያኔ ለስራው የሚያስፈልጉት አቡነ ማቲያስ ከእስራኤል ገዳም ከነበሩት መነኮሳት መካከል መርጦ ሾመ” በማለት ከግነቦት ሰባቱ ጋር የተናበበ መግለጫ ሰጡ፡፡ እንደዚህም ሆኖ በሁለቱም ሲኖዶሶች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ረዥም ርቀት ሄዶ እንደነበር ሁሉም የሚያስታውሰው ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ንትርክ ቀጥሎም መሰረታዊ ችግሩን ከስር ለመፍታት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ህይለማርያምን ተክቶ ወደ ስልጣን የመጣው አቢይ አህመድ አሊ አመካኝነት እርቅ ወረደ ተብሎ የውጪው ሲኖዶስ አባላት ሀገር ቤት ገቡ የሚል ዜናም ተነገረ፡፡ መታረቅ ተገቢ ቢሆንም ያለያዩዋቸውን ጉዳዮች ከስር መሰረቱ በሚገባ ፈትሾ በማከም ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን እንዳይከሰቱ ይቻል ነበር ባይ ነኝ፡፡ ያም ሆነ ይህ ቂም በቀል የነገሰበት በሴረኝነቱ የተካነው ወደ አገር ቤት የገባው እንግዳው ሲኖዶስ እንመለስና ጥቂት ልበል፡፡ ይህ የሰብስብ ሃይል የሃዋርያዊና የፖለቲካ ልምዱን አንግቦ ወደ ሀገር ቤት ገባ፡፡ የፖለቲካ ፍላጎቱን በአቢይ ወደ ስልጣን መምጣት በከፊልም ቢሆን ማሳካት እንደቻለ ነገር ግን ያላገባደዳቸው ቀሪ ስራዎች እንዳሉት የሚጠቁም ተግባራት ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ተቋምዋ መጠቀሚያ በማድረግም ቤተክርስቲያኒቱ ከወንጌል ሃዲድ የሚያስወጣትን ቀን ቀን በአውደምህረቱ በመጠቀም፤ ማታ ማታ ደግሞ ከፖለቲካ ባለሟሎች ጋር እየተገናኙ ህይማኖትን ብቻ ሳይሆን ከሞያሌ አሰከ መቀሌ፤ ከመተማ እስከ ደወሌ ሀገሪቱን የሚያምሱ ግልጽ የሆኑ ፖለቲካዊ እቅዶች ሲያወጡና ሲያስተባብሩ ቆይተዋል፡፡ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ከሀገሪቱ መከላከያ ሃይል፤ ከባእድ ወራሪዎች እንዲሁም ከጽንፈኛ ሃይሎች ጎን ተሰልፋ በገንዘብ፤ በሎጂስቲክስ እና የሞራል ድጋፍ የማድረጉ ሚስጥርም ይኸው ነው፡፡ አሁንም በአማራ ክልል በተፈጠረው ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ባደረገችው የጦርነት ጠመቃ ከመጠየቅ ከቶ ልታልፍ ልታመልጥ የምትችል አይመስለኝም፡፡        

2.ሰብአዊነት

ቸሩ ፈጣሪያችንና አምላካችን ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ “ምን ያህል ትወደኛለህ”? ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ በመጎናፀፊያ ውስጥ የነበሩትን ሁለቱ እጆቹን  እስከሚችለው ድረስ በስፋት በመዘርጋት “ይህንን ያህል” ነበር ያለው፡፡ ልብ ላለን ይህ በራሱ የሰብአዊነት ጥልቅ ሚስጥርና ጥበብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰብአዊነት ሲባልም ፍቅር፤ ወንደማማችነት፤ ሰላም፤ መከባበርና መረዳደትን ያጠቃልላል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቁጥር የበዙ ሊቃነ-ጳጳሳትና ዲያቆኖች ይህ ክርስቶስ የሞተለትን ሰብአዊነት በሚጻረር መልክ ሲያደርጓቸው የነበሩትን ለከት የለሽ ኢ-ሰብአዊ ሰብከቶች መነሻ በማድረግ በርከት ያሉ ጥያቄዎች በተቋማዋ ላይ ማንሳት ይቻላል፡፡ ለምን ተቋምዋ ይህንን የአምላካችን ጥልቅ የሰብአዊነት መርህ ወደ ጎን ገፋ አደርጋ አእምሮአቸውን የሳቱ በከፈቱት ጄኖሳይዳል ጦርነት ፍቅር ክንፍ ብላ ወድቃ ለአላማቸው ማሳኪያ (ለሰው ልጅ  መፍጂያ) የሚውል ገንዘብ አሰባሰባ አስረከበች?፤ እንዴትስ “እነኚህ ሰዎች ከሰው ህሊናና ከታሪክ መፋቅ አለባቸው”፤ “የትግሬ ደም በውስጤ ቢኖር ኖሮ በስሪንጅ አስመጥጥ ነበር”፤ እና ጎራ እየለዩ “ለነኚህ አልፀለይኩላቸውም፤ ፀለይኩባቸው እንጂ” የሚሉ ሊቀጳጳሳት፤ ዲያቆናትና ካህናት በውስጥዋ አረም ሆነው ሊበቅሉ ቻሉ? ለምንስ መነኩሴዎችዋና ጠባቂዎችዋ እንዲህ በመሰለ ሰብአዊነት የጎደለው ንግግርና ጥላቻን ሰብከው ጥላቻ ሊያዋልዱ፤ ሊያብዱና ሊቅነዘነዙ ፈቀዱ? የሚሉ ተከታታይነት ያላቸው ጥያቄዎች ለቤተክርስቲያኒቱ ማድረስ ይቻላል፡፡

እነኚህ ከላይ የተነገሩ ሃሳቦች ማንም ይናገራቸው ማንም የሰብአዊነት ሽታ የሌላቸው፤ ተናጋሪዎቹ በሰው ልጅ ላይ ያላቸውን ጥላቻና ክፋት የገለጹበት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይ ደግሞ ይህ አይነት ንግግር በቤተክርስቲያኒቱ ዋና ሹመኞች አፍ ሲነገር ማዳመጥ በእጅጉ ያሳምማል፤ ያሳዝናልም፡፡ ሲነገረን ካደግነው ፍቅር፤ መከባበር፤ እና መረዳዳት ወግና እሴት ያፈነገጠ ሆኖብን ዝብርቅርቅ ይልብናል፡፡ የህገ አራዊት መመሪያ ሆኖ ስናገኘው ቤተክርስቲያኒቱ ለምን በዚህ ያህል የወረደና የረከሰ ምእራፍ ልትገኝ ቻለች ብለን እንድንጠይቅ ይኮረኩረናል፡፡ ከዚህም አልፎ መድረክ ሳይለይ ስለጦርነት ሰበካ ማካሄድ፤ በውጭ ሃገር ኮንግረስ አባላት ፊት በመቅረብ ጦርነት እንዳይቆም ተማጽኖ ማቅረብ፤ በሃገር ውስጥ ጦር ሜዳ ድረስ በመሄድ መባረክ፤ ማወደስ፤ ማበረታት፡፡ በአንድ በተወሰነ ማህበረሰብ በጥላቻ ላይ ያነጣጠረ መልእክት በየአውደምህረቱ፤ በየሰብሰባ አዳራሹ፤ በሚዲያ ቃለመጠይቅ እየፎከሩና እየተጎማለሉ መናገር፤ “ሀገር ሊበትኑብን ነው!” ፤ “ዘመቻው የህልውና ዘመቻችን ነው!” እያሉ በአንድነት ስም እየሰበኩ በገቢር ግን ውስጥ ውስጡ አንድነትን የሚቦጠቡጡ ከላይ የገለጽኩዋቸው የድውያን ቡድኖች አመካኝነት እየተቀነባበረ ያለ በሰብአዊነት ላይ የሚያቄምና ፤ ህዝብን በመጨፍጨፍ ላይ ያነጣጠረ እኩይ ሴራ ውጤት መሆኑን ስንረዳ ምን እንላለን?፡፡     

3. ፍትህ

ማንኛውም ተቋም ተልእኮውን በተሳካ ለማስኬድ ተቋማዊ ፍትህ  የማስፈን ስራዎች መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ተቋማዊ ፍትህ ሲባል 1) የተቋሙ ተቀጣሪዎች እርስ በራስ የሚኖራቸው ተቋማዊ የስራ ግንኙነትና ጓዳዊነት፤ 2) ለተቋሙ ተልእኮ ውበትና ስኬት ሲባል በተቋምዋ የሚገኙ የስራ ዘርፎችና አደረጃጀቶች እርስ በርሳቸው ተናበውና ተመጋግበው ስራቸውን የሚያከናውኑበት አውድ፤ 3) ከተቋሙ አገልግሎት ቀጥታ ተቋዳሾች እና በስራ ሂደት ከሚገናኝዋቸው አካላት ጋር ተልእኮውን በመፈፀም ረገድ ተቋሙ መከተል የሚገባው ስነምግባር የሚያካትት ነው፡፡ እዚህ ላይ የተጠቀሱት አበይት ማንፀሪያ አቅጣጫዎችና ሌሎች መለኪያዎች ተጠቅመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቋማዊ ፍትህ ለማስፈን ረዥም ርቀት የሚቀራት፤ በተለይም መንፈሳዊ ተቋም ከመሆንዋ አንፃር እየተጓዘችበት ያለው መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

“ከፍተኛ ጥቅም የምታገኝበት ቦታ እንድትመድብ ከፈለግክ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ አምጣ ብሎ መደለያ መጠየቅና መቀበል”፤ “ቤተሰብ ለማስቀጠር አማላጅ ሆኖ መቅረብ”፤ “ምእመኑ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ ለቤተክርስቲኒቱ የሚሰጠው አስራትና መባ ለምዝበራ በሚያጋለጥ ስርአት መሰብሰብ” ፤ “ፍትሃዊነት በጎደለው የበጀት አመዳደብ በርካታ ቤተክርስቲያኖች እጣን መግዣ አጥተው ደጃቸውን እንዲዘጉ ማድረግ” ፤ “በማንነታቸው ብቻ ለዘመናት በሰሩበት ተቋም ከስራ በማባረር ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በረሃብ አለንጋ እንዲሰቃዩ መፍረድ”፤ “የቤተክርስቲያን ንብረት የሆኑ ቅርሶችን ዘርፎ (የያሬድና የሙሴ ንዋያት ጨምሮ) ሊቀጳጳስ በተገኙበት አውደምህረት ላይ በማቅረብ የጦር ሜዳ የጀግና ውሎ በሚያስንቅ ሽለላና ፉከራ እየዘመሩ ዘራፊነትን ማበረታት” የመሳሰሉት የመልካም አስተዳደር እጦትና አስተዳደራዊ በደሎች ቤተክርስቲያኒቱ በአገልጋዮችዋና በመእመኑ ላይ የምትፈፅመው ጭካኔ ማየት የሚያም ነገር ነው፡፡

በመጨረሻም ስለ ውግዘት ጥቂት ልበል፡፡ ማንኛውም ተቋም ተልእኮዬን ያሰኩሉኛል ብሎ በመደባቸው ተቀጣሪ ሰዎች የተሰጣቸው ሃላፊነት ተገን በማድረግ ተልእኮዬ አበላሽተዋል ብሎ ባመነ ጊዜ በሰራተኞቹ ላይ ተጨባጭነት ባላቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች በማስደገፍ ደረጃው የጠበቀ ቅደም ተከተል ያለው የስነስርአት እርምጃ ይወስዳል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም እርምጃ የምትወስድበት አግባብ ይኖራታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከእርምጃዎቹ አንዱ የሆነው በተለይም አሁን አሁን ተደጋገሞና ገኖ የምንሰማው ማውገዝ የሚሉት ውሳኔ ነው፡፡ ከላይ ሳስረዳ የመጣሁትን ማጣቀሻዎች መሰረት በማድረግ ማን በማን ላይ ውግዘት ቢያደርግ ያምርበታል? የውግዘቱ ውጤት ተቀባይነትስ ምን ሊሆን ይችላል? በውግዘቱ የውሳኔ መግለጫ ላይ ምን አይነት ክርስቲያናዊ ቃላቶች መጠቀም ይገባል? የሚሉትን የወቅቱ ጥያቄዎች እዚህ ላይ ገታ አድርጌ ቤተክርስቲያኒቱ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ “ማንኛውም ክርስቲያን ሊከተለው የሚገባ የህይወት መርህ” እያለች በየቀኑ የምትሰብክለት አንድ መሰረታዊ ጉዳይ አንስተን እንመልከት፡፡ ይህ የህይወት መርህ 10ሩ ትእዛዛት ይባላል፡፡ ይህ የእውቀት መጀመሪያ የሆነውን እነሱም እየሰበኩት ያለ 10ሩ ትእዛዛት በእውቀት በመመርመር የእለት መርሃቸው ቢያደርጉ ኖረው በቤተክርስቲያኒቱ ያሉ ሊቃውንቶች እየደረሰ ያለውን ይህ ሁሉ የእምነት መጣረስ፤ የጥላቻ ስብከት፤ አይኖርም ነበር ብለን ልንከራከር እንችላለን፡፡ እነሱም ጥላቻ ሰብከው ጥላቻ ለማዋለድ በልደፈሩም ነበር፡፡ ቤተክርስቲያንዋም ይህ ሁሉ ምስቅልቅል ውሰጥ ባልከተታት ነበር፡፡ ክህነተ ልብስ ለብሶ ከሃይማኖታዊ ተልእኮ ውጭ የሴራ አውጠንጣኝ የሃይማኖት መሪ ቅዱስ ከሆነው አውደምህረትና ቤተልሄም ከቶውንም ሊቆም አይገባም፤ ይወገዝ ብለንም ልንከራከርና ልንሞግት እንችልም ነበር፡፡ እረኛ ይሆኑኛል ብሎ አምኖ የኖረውን መእመን በተደረገበት ከበባ ከሰው ደረጃ ወጥቶ ህይወቱን ለማትረፍ እንደእንስሳ ሳርና ቅጠል እየተመገበ ለኖረ መእመኖቻቸው፤ ለተደፈሩት መነኮሳትና አይናቸው እያየ ሚስቶቻቸው ለተደፈሩባቸው የቤተክርሲያኒቱ አገልጋዮች፤ ቅርስና ንዋየ ቅድሳን ለመዝረፍ በመጣው ወራሪ ሃይል በዘግናኝነቱ ወደር የሌለው ግፍ የተፈፀመበት እጅግ የበዛ አገልጋይና መእምን፤ ንብረታቸው ለወደመባቸውና ለተዘረፈባቸው ቤተክርስቲያናት ሲባል በመጀመሪያ ውጭ ሀገር ሆኖ አሁን ደግሞ ቤተክርስቲያንዋ ውስጥ መሽጎ ለአማኙና ለሀገር ጠንቅ የሆነው ቡድን ንስሃ ተፀያፊ ሆኖልና ገለል ማለት ይኖርበታል፡፡ 

በኢዮአብ መሰሪ እጆች የተገደለውን የአበኔር ንጽህና ለመግለጽ በቀብር ላይ ተገኝቶ ለህዝብ የተናገረውን የንጉስ ዳዊት ንግግር በመጥቀስ ጽሁፌን ላብቃ “ልብሳችሁን ቅደዱ፤ ማቅም ልበሱ፤ በአበኔርም ፊት አልቅሱ” መጽሃፈ ሳሙኤል ካልእ ምእራፍ 3፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኝ የሆነ ሁሉ በአባቶቹ የወንጌል፤ የሰብአዊነትና የፍትህ ሴራ አፍሮ እና አዝኖ ልብሱን መቅደድ፤ ማቅም መልበስ ካለበት አሁን ነው፡፡ ይህ እድል ቤተክርስቲያኒቱ ወደ ጤናማ የወንጌል አገልግሎት፡ የሰብአዊነት፤ ፍትህ የወንድማማችነት ተልእኮዋ የሚመልሳት መሆኑን መረዳት ያሻዋል፡፡ ጊዜው ከረፈደ በኋላ እየየ ብሎ ማልቀስ ጥቅም የለውም፡፡

አበቃሁ

By aiga