ለአስተያት ሆነ ትችት፡- [email protected] ይፃፍ፡፡
- መግቢያ
የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ለውጥ ፍላጎት የንግስናው ስርወ-መንግስት ማብቅያ አከባቢ እንደነበር ግልፅ ነው። ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውን የንግስና አገዛዝ እንዲያበቃ አብዮታዊ እንቅስቃሴ በመጀመር ስርወ-መንግስቱ በዝባዥ፣ አድሃሪ፣የብሄር እኩልነት እና መሬቱም ለአራሹ የሚሉ የዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች አንግበው ወደ ግልፅ የትግል እንቅስቃሴ ገብተው ነበር። እነዚ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ያለውን አገዛዝ ለማስወግድ ይረዳናል ያሉትን የሌሎች ሃገሮች አብዮት በማጣቀስ ብዙ እንደ “ማኦ” እንደ ቸኮ ቬራ እንደ ሆቺሚኒ አንቱ ለመባል እና በሚመጣው ለውጥ ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች በበቂ ትንታኔ ሳይጠኑ በቁጭትና በስሜት በወለዳቸው ታጋዮች ስርዓቱ ገረሰሱት። ይህ ስርወ- መንግስት ከተገረሰሰ ብኋላ የመጣው አብዮታዊ ሃይል የህዝቡን “የለውጥ” ፍላጎት ግምት ውስጥ ሳያስገባ የራሱን የመበዝበዝ ስልቱ ዘረጋ። የደርግ ስርዓት ንጉሱን አስወግዶ ስልጣን ከያዘ በኋላም ቁጥራቸው የማይናቅ የአድሃሪው ስርዓት ቅሪቶች እና እንቅስቃሴውን ሲመሩ የነበሩ አብዮተኞች ቅርጥፍ አድርጎ በልቷል። ከደርግን አብዮት ያመለጡ ሌላ የለውጥ ሃይል ኢህአዴግ በሚል የሰላም፣ የዲሞክራሲ እና የልማት አርበኛ ለመሆን መፈክሩን አንግቦ ሌላ የለውጥ ሂደት ለመምራት በትጥቅ ትግል ተተካ። በዚህ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ መቻቻልን ሳይሆን ሁሉም የራሱ የፖለቲካ ስልት ብፁእ አድርጎ የሌላውን ሰይጣናዊ አስመስሎ በማቅረብ ግልፅ የዜሮ ድምር ፖለቲካ አራምደዋል። የዲሞክራሲ ጥያቄ እና የተደረጉ ትግሎች ፍሬ ሳያመጡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከበዝባዥ አድሃሪያን ወደ በዝባዥ አብዮታውያን እጅ ወደቀ እንጂ እንደ ዓላማ ተደርገው ተይዘው የነበሩት ሰላም፣ ልማት እና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን እዉን ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ ምክንያቱም የመዋቅራዊ ለውጥ ተግባራዊ ሳይደረግ ስልጣኑም ባንክም ታንክም በሌላ ተረኛ እጅ መግባቱ ነው፡፡
ደርግም ሆነ ኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣን ለመቆጣጠር የተጠቀሙት ስልት ቢለያይም ግቡ ግን ፖለቲካዊ ስልጣን ታንክና ባንክ በመቆጣጠር በዝባዥ ስርዓት ገንብተው ነበር፡፡ በዚህ የፖለቲካ ሂደት ያደገው እና ‘’ለውጥ’’ አመጣሁኝ ያለው ብልፅግናም ቢሆን ተመሳሳይ ሂደት ተከተሏል፡፡ ሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎም በምርጫ ስልጣን ለመያዝ ቢያሸንፉም ያዉ ታንኩም ባንኩም ለመቆጣጠር እንደማለት ነው። “አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ” የሚለውን ገላጭ ይሆናል። የአማራ ሊሂቃን የበላይነት ስትመራ የነበረችው ኢትዮጵያ መዋቅራዊ ለውጥ ሳታመጣ በዝባዥ አካሄድን ተከትለው የሄዱበትን ሂደት በትግራይ ሊሂቃን የበላይነት በመተካቱ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የአማራ ሊሂቃን ላይ የደረሰው ውድቅት በትግራይ ሊሂቃን መደገሙ የግድ ሆኗል። ምክንያቱም ሁለቱም ሊሂቃን ባህላዊና ማህበራዊ መሰረታቸው በመሳት ለስልጣን ሲሉ በዝባዥ መዋቅራቸውን በመዘርጋት ህዝባዊ መሰረት በማጣታቸው ነበር የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ። ይህ አካሄድ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር አሁን በስልጣን ያለዉ ብልፅግናም እጣ ፈንታው ተመሳሳይ የመሆን እድል አለዉ፡፡
2. መስመር እዩ ሓይልና እና የህወሓት አደርባይነት
የኢትዮጵያ ሊሂቃን ስልጣንን ለመቆጣጠር ህዝባዊ ይመስሉ እና ወደ ስልጣን ኮርቻ ከወጡ ብኋላ ወደ በዝባዥነት ይለወጣሉ። ህዝቡም ብሄራዊ ጥቅሙን የሚያሳኩለት መስሎት ውድ ህይወቱ በሃርበኝነት ይሰጣል። የትግራይ ህዝብ የነበረውን አገዛዝ ለማስወግድ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ብሄራዊ ጥቅሙን ለማስጠብቅ እና አንድ ሉአላዊትና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ላይ ክቡር ህይወቱን እንዲከፍል ያስቻለው በዲሞክራሲያዊ ሂደት በምትገነባ ኢትዮጵያ ላይ ተጠቃሚነቱን አረጋግጣለሁ በሚል ነው። ይህ ማለት የትግራይ ህዝብ ብሄራዊ ጥቅም ግልፅ ነው “ሓርነት” ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ። ይህን ሃረግ ነው መስመር በሚል የሚጠራው እና ህዝባዊ መሰረት ያለው ነው የሚባለውም። ይህ መስመር የህወሓት ብቻ ሳይሆን ማንኛው የትግራይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ልያሳኩት የሚገባው ብሄራዊ ጥቅም ነው። ብሄራዊ ጥቅምህን ለማሳካት ሁሉም የጋራ ብሄራዊ መግባባት(National Consensus) ይኖረዋል ማለት ነው ። በዚህ ሂደት ላይ ብሄራዊ ጥቅምን ለማስፈፀም የሚረዱ መሳርያዎች (tools) ማስፈፀምያ ስርዓት በመዘርጋት የሚመለከተው ዜጋ ብሄር፣ አከባቢ ፣ጎጥ እና ሃይማኖት በማይለይ መንገድ የተጣለበትን ሃላፊነት ይወጣል እንደማለት ነው። ይህንን ማስፈፀምያ መሳሪያዎች ማለትም ታንኩም ባንኩም ፖለቲካ ስልጣን ግቡ ለሆነ ፓርቲ መስጠት ማለትም በስልጣን ለመቆየት የሞት ሽረት ትግል ማድረጉን እና ተፎካካሪዎችን ዓቅም ማሳጣት ስራ ላይ ያውለዋል ማለት ነው። በዚህ ሂደት የሚፈጠሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደግሞ ገዢ ፓርቲው በመጣል በስልጣን የሚቆዩበትን አወቃቀር በመዘርጋት የመወነጃጀል እና የመጠፋፋት የዜሮ ድምር ፖለቲካ ውስጥ መኖር ነው የሆነውም እየሆነም ያለዉ። በሌላ አባባል የህዝቡ ህይወት ጉልበት ሃብት ንብረት በእጁ በማስገባት ወደ በዥባዝነት ስርዓት በመቀየር የህዝቡ ብሄራዊ ጥቅም እና ለዚህ ሲል የከፈለዉን ሃርበኝነትና አደራ ቅርጥፍ አድርጎ በላው ማለት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ያለችው ሃገር ናት ኢትዮጵያ የምንላት። የጠራ ብሄራዊ ጥቅምና ብሄራዊ መግባባት የሌለባት ሃገር ታድያ ሃገራዊ ስትራቲጂዋን ማሳካት አትችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ብሄራዊ ጥቅምን ለማሳካት ሳይችል ወይም አፍሪካ ውስጥ ብሎም መረጋጋት በማይለይበት ምስራቅ አፍሪካ የምትገኝ ሃገር በመሆንዋ ለቀድሞ ገዢዎች ስትራቴጂካዊ ጥቅም ከራስ ጥቅም ጋር በማጣጣም ሳይቻል ወራሪ ሃይል መጣብህ በሚል ሊሂቃኑ ህዝቡን እንደ ላባራቶሪ ጥቅም ላይ አዉለዉት ስያበቁ ከገባበት አዙሪት ውስጥ ሊያወጡት ግን አልቻሉም።
ይህ ብቻ ሳይሆን ያለንበት አከባቢ ባለው የተፈጥሮ ሃብት፣ የአባይ ተፋስስ እንዲሁም የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንደመሆኑ ስትራቴጂክ ፍላጎት ያላቸው ሀገራት ስትራቴጂያዊ ፍላጎታቸውን ለማረጋገጥ ሲባል በአከባቢው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትግል ሲደግፉም እየደገፉም ይገኛሉ፡፡ ከተቻለም የራሳቸውን አሻንጉሊት የሚመለሙሉበት እና በስልጣን ኮርቻ ላይ የሚያስቀምጡበት ሂደትም ተከትሏል፡፡ ይህ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ችግር የሆነው በአከባቢው የሚገኙ ሊሂቃን በአጠቃላይ የህዝባቸው ብሄራዊ ጥቅም በመለየት እና የሌሎች ስትራቴጂክ ፍላጎት ካላቸው ሀገራት ወይም ድርጅቶች ጋር በማቻቻል ብሄራዊ ጥቅም እና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አቅም አለመኖር ነው፡፡ በዚህም መሰረት የአገራችን ሊሂቃን ወይም ለህዝባቸው ብሄራዊ ጥቅም ቁርጠኛ ሆኖ አለመገኘት ወይም ለቀጠርዋቸው ታማኝ ሆነው መስራት ሳይችሉ እሱ ገራ ዘመም ነው ወይ የምዕራቡ ዓለም ቡችላ ነው እየተባባሉ እርስ በእርስ በመወነጃጀል ላይ ተደርሷል አሁንም እየቀጠለ ይገኛል፡፡ መወነጃጀሉ አገር በሚመሩ አመራሮች ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም እርስ በእርስ መጠራጠር እንዲሰፍን ያደረገ ነው፡፡
ህወሓትም በዚህ አፍሪካ ቀንድ ኢህአዴግ መር በመሆን ያደረገውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በዚህ አዙሪት ውስጥ ያለፈ በመሆኑ የአገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም ለማሳካት ይቅር ውግንና አለኝ ለሚለው የትግራይ ህዝብ የሓርነት ጥያቄ እንኳን ሳይመልስ ራሱን ለማዳን በአቋም ደረጃ መታገልን አቅቶት አብዛኛው የህዝቡን የሓርነት ፍላጎት ለማስፈፀም በሌላ በኩል ቀሪውን ደግሞ የስልጣን መጉዚትነት ርስት ለማስቀጠል ችግሩ በሽምግልና የሚፈታበት የሚያስመስሉ እንቅስቃሴዎች ያሉ ይመስላሉ፡፡ ህዝባዊ መስመሩን ወደ ጎን ብሎ ስልጣን የሞት ሽረት ያደረገው አደረጃጀት የሚመሩ ግለሰቦች ገበያው ከደራ በስልጣን ለመቆየት የትግራይ ህዝብ እንጦርጦስ ቢወርድም በስልጣን ኮርቻ ሊያቆያቸው የሚመጣ ማንኛውም ሃይል ጋር በጋራ የማይሰሩበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር መገንዘብ ይቻላል፡
3. የህወሓት አፈጣጠር እና ወቅታዊ ሁኔታ
የትግራይ ህዝብ ባህልዊና ማሕበራዊ ውቅሩ ፍትሃዊ ፣እኩልነት፣ ሓርነት እና ነፃነት የሚያምን ሲሆን ለዘመናት በህዝቡ ጫንቃ ላይ የተመሰረቱ ፊውዳልና ጭሰኛ አመለካከትና ተግባር ከነበረበት የአክሱም ስልጣኔ ወደቆ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ምክንያት ሆነ የሚል አስተሳሰብ ኣለኝ፡፡ በማሕበራዊ እሴቶቹ ማለትም በፀሎት፣ በሃዘን፣ በደስታ፣ የሽምግልና ሂደት ንቡር እና ነውር ለይቶ የሚሄድ ማህበራዊ ስብእናውን ጠብቆ ለዘመናት እንደህዝብና እንደ ሃገር እስካሁ በዚህ እሴት የመጣ ነው፡፡ እሴቶቹን ለመጠበቅም የሌላ ሞግዚትነት የማይቀበልና ራስ በራስ የማስተዳደር ፍላጎት ያለው ህዝብ ነው፡፡ ለዚህም ነው እሴቶቹን ተጠብቀው እንዲሄዱ ከውስጥም ከውጭም ለሚጫኑበት አደጋዎች ለመከላከል በአንድነት የሚታገለው፡፡ የአጭር ጊዜ ታሪኩም ለፍትህ፣ እኩልነት፣ ሓርነት እና ነፃነት በነበረው ፍላጎት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር ለሓርነቱ ለመታገል የተለያዩ ፖለቲካ ሃይሎችን በማደራጀትና በማቋቋም ወደ ሰለማዊ ትግል የተቀላቀለው፡፡ ከዚህ ብሄር አብራክ በተገኙ ወጣቶች የተመሰረቱ ብሄራዊ እና ሃገራዊ ፖለቲካ ፓርቲዎችም እንደነበሩ በታሪክ የሚታወቅ ነው፡፡
ህወሓት በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ጊዜ የተፈጠረ ‘’ብሄራዊ ፓርቲ’’ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ እኔ ህወሓት ፓርቲ ወይም ግንባር ነው በሚለው ሃሳብ አልስማማም፡፡ ህወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) ማለት በግርድፉ የትግራይ ህዝብ ለሓርነት ያካሄደውን አብዮታዊ እንቅስቃሴ መሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ TPLF የሚለውን የኢንግሊዝኛ አህፁረተ ቃል የያዘው ደግሞ የትግራይ ህዝብ የነፃነት ግንባር የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ የሓረጉ የትርጉም ፍች ላይ ሳይሆን ግንባር የመሰረቱት ፓርቲዎች የት ገቡ? ይህ ጥያቄ አልተነሳም ሳይሆን አብዮቱን እንዳይሳካ እንቅፋት ናቸው በሚል ግማሹ በርግጫ ሌላው በቁልምጫ ደብዛቸው እንደጠፉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የኢንግሊዝኛው ሃረግ ለውጨው ዓለም ድርጅቱ የተለያዩ ሃሳቦች አቃፊ ለማስመሰል ነው እንጂ እውነታውን በተፃራሪ ነው፡፡ አብዮት ልጆችዋን ትበላለች የሚለው ለትግራይ ህዝብ ግን ልጆቹን ሳይሆን አስተሳሰቡን እና የፖለቲካ አማራጩን ማለትም ብሄራዊ ጥቅሙን ቅርጥፍ አድርጎ የበላው ነው፡፡
ህወሓት የትግራይን ህዝብ የሓርነት ጥያቄ አንግቦ የደርግን ስርአት ከገረሰሰ ብኃላ እና የሽግግሩ ስርዓት መርቶ ወደ ዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ለመሳተፍ ፓርቲ ሆኖ ተመዘገበ፡፡ የህዝብ ብሄራዊ ጥቅምን አንግቦ ለፓርቲ ፖለቲካዊ ስልጣን የተመዘገበም ቀዳሚ ፓርቲም ሳያደርገው አይቀርም፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ ለዚህ እንቅስቃሴ እውን እንዲሆን ውድ ህይወታቸውን ለማበርከት የተነሱትን የድርጅቱ አርበኛ ሰራዊትም ማለትም ሰራዊት ትግራይ የድርጅቱ የስልጣን ጥም ለማስጠበቅ የጀርባ አጥንት ተደረገ፡፡ እውነታው ይህ እያለ በሰራዊቱ እና በህዝቡ የትግል እንቅስቃሴ ተሳታፊ ነበሩ ታጋዮች እስካሁን ድረስ የህወሓት ታጋዮች አድርገው ነው የሚቆጥሩት፡፡ ምንም ስህተትም የለባቸውም እስካሁን ድረስ ለትግራይ ህዝብ የሓርነት ጥያቄ የሚታገሉ መሆናቸው ነው የሚያምኑ ቅሉ ግን ለግል ስልጣን ጥም ላላቸው ግለሰቦች አገልጋይ መሆናቸውን ግንዛቤ እየተወሰደበት ያለ ይመስላል፡፡
የህወሓት አመራር በትግራይ ህዝብ የሓርነት ትግልን ለማሳካት ከውጭም ሆነ ከውስጥም የሚደቀኑ ስጋቶችን ለመከላከል የሚጠቅሙትን ስትራቴጂያዊ ተቋማትን ማለትም ወታደራዊ፣ የመረጃና ደህንነት፣ ሲቪል ሰርቪስ እንዲሁም የፓርቲ የንግድ ተቋማትን በድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎችን እደራጅቶ ነበር፡፡ እነዚ ስትራቴጂያዊ ተቋማት እና ፈፃሚ አደረጃጀቶች ከፓርቲ ውግንና ወጥተው ለህዝቡ ብሄራዊ ጥቅም ዘብ መሆን ነበረባቸው፡፡ ይህን ሳይሆኑ ቀርተው ለአንድ ፓርቲ አመራር የስልጣን ጥም ለማርካት ሲባል ዜጎች ሀገራቸውን ለማገልገል ባላቸው አቅምና እውቀት ተወዳድረው ሳይሆን በፖለቲካ አመለካከታቸው ሆነ፡፡ እነዚህ ስትራቴጂክ ተቃማትን በብቃት ያላቸው ዜጎች መያዝ እያለባቸው በፓርቲ ታማኞችን በማደራጀት እንዲሞሉ በማድረግ ህዝቡ ለሚያነሳው የፍትህ፣ የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄን ለመመለስ ሲያቅተው በውስጠ ዲሞክራሲያዊ መድረክ በሚደረጉ ግምገማዎች እንደየወቅቱ የሚያቀርባቸው የመከላከል ሃሳቦች አንዴ የአቅም ማነስ ነው ወይም የኪራይ ሰብሳቢነት ወይም አደርባይነት በሚል አመክንዮ እነዚህን ለማረም እስከ ጥልቅ ተሃድሶ ወይም ሪፎርም እርምጃዎች በመውሰድ ለማስተካከል ተሞከረ፡፡ ህወሓት አሁን ደግሞ ስትራቴጂክ ጥቅሙን ወደ ስልጣን ጥቅም ከቀየተረ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ስትራቴጂክ አመራር ችግር ገጥሞኛል ብሏል፡፡
እውነት ለመናገር ስትራቴጂክ አመራር የሚገኘው በስትራተጂክ ተቋማት ግንባታ ሂደት እንጂ የስትራቴጂክ ተቋማት በፖለቲካ ታማኝነት እና ስልጣን መያዝ ግባቸው ላደረጉ አባላትና ደጋፊዎች ሞልተህ እንዴት ስትርቴጂክ አመራር ይገኛል፡፡ ብሄራዊ ጥቅም ወደ ስልጣን ጥቅም በተቀየረበት ፤ ብሄራዊ መግባባት በሌለበት የፖለቲካ ታማኝነትን እንደመስፈርት በሚወሰድበት ወቅት የፓርቲ አባላት ለብሄራዊ ጥቅም ሳይሆን ለፖለቲካ ስልጣን ለያዙ ግለሰብ ተገዢ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የምናገኘው አመራር ስትራቴጂክ ከበርቴ እና ስትራቴጂክ ጭሰኛ ነው የሚሆነው፡፡ አበው እንደሚሉት ይህ ሂደት ‘’ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’’ መሆኑን ነው፡፡ እውነት ድርጅቱ ለማዳን እና ፓርቲና ህዝብ ወይም የፓርቲ ፍላገት እና የህዝብ ጥቅም ለማሳካት የመዋቅር ለውጥ እንዲገነባ ከተፈለገ አሁን ድርጅቱ የገጠመዉ ጎጠኝነት ነው፡፡ ድርጅቱ ላለፉት 64 ቀናት ባደረገው ግምገማ ይህን ድርጀት ላለፈው ግማሽ ክፍለዘመን የመሩት ሄዶ ሄዶ ወደ አንድ ጎጥ መጠቃለሉ አይቀርም፡፡ ህወሓት የማን ነው? ማን ሲመራው ነው ታድያ ህወሓት በህይወት የሚኖረው? ስትራቴጂክ አመራሩ እንዴት እና ከወዴት ነው የሚገኘው? ስለሆነም ህወሓት የስትራቴጂክ አመራር እጦት ሳይሆን የገጠመዉ ለህዝቡ የውሰጠ ችግሩ ግልፅ አድርጎ ማቅረብ ባለመቻሉ ነው፡፡
4. ህወሓት እና የፕሪቶሪያ ስምምነት
ትግራይ እንደ ትግራይ ዓለም-አቀፍ ስምምነት ስትፈርም የመጀመሪያዋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረምን ምክንያት በትግራይ በተካሄደው ጦርነት በሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች ብቻ ሳይሆን ሌላ የውጭ ሃይሎች የተሳተፉበት በመሆኑ ጉዳዩ ውስብስብ አድርጎት ስለነበር የጦርነቱ መነሻ ምክንያት (cause of the war) በማወቅ መፍትሄ ለማበጀት ከጦርነት ይልቅ በድርድር እንዲሆን ነው፡፡ በሁሉም ተፋላሚ ሃይሎች የታየው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ባህሪ እንጂ ዘመኑ የሚዋጅ win-win approach የሚከተሉ ወይም ከግጭት በኋላም ቢሆን ድርድር እንዳለ በቅጡ የተረዱ አይደሉም፡፡ ካልሆነም ‘’አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት ኣይሰማም’’ ነው የሚሆነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የፕሪቶሪያ የተፈረመ የስምምነት ወረቀት ቀጥሎም በኬንያ በጦር መሪዎች መካከል ተፈረመውን እየተመለከቱ በፖለቲካ መሪዎች የተፈረመው አደገኛ ነበር ይሁን እንጂ በኬንያ የጦር አመራሮቹ ጉዳዩ ቀጥታ ስለሚረዱት አሻሽለውታል የሚል ሃሳብም ይነሳ ነበር፡፡ ይህን ስምምነት መነሻው ከድህረ ግጭት ስነ- ሃሳቦች በመሆኑ ዋናው ማጠንጠኛው ደግሞ የጦርነቱ መነሻ ምክንያት(cause of the war) ተለይቶ ተፋላሚ ሃይሎች በሰለማዊ መንገድ ጉዳዩ የሚፈቱበት ሂደት ነው፡፡ በጦርነቱ ወቅት በሁሉም ተፋላሚሃይሎች የመሳሪያ ድምፅ የማይሰማበት ሁኔታ በመፍጠር በሰለጠነ አገባብ ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችል መደላድል መፍጠሩ ነው፡፡
ይህ ሂደት በተፈረመበት ወቅት ህወሓት ስምምነቱን እንዲፈርም ፕሪቶሪያ የተላከ አመራር የለኝም በማለት ማእከላይ ኮሚቴው አማካኝነት መግለጫ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ ማእከላይ ኮሚቴው ስምምነቱን ባይቀበለውም ተወደደም ተጠላም ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ የሌለው መሆኑና ይረዳው አይረዳው ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ጀመረ፡፡ ይህ ሂደት ሊመራ የሚችል ጊዚያዊ አስተዳደር አቋቋመ፡፡ አስተዳደሩም በዋናነት በህወሓት አብላጫ ወንበር የሚመራ ቢሆነም ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከምሁራን የተዋቀረ ነው፡፡ አስተዳደሩ ሲቋቋም ህወሓት ያሰበው ከሱ ስር የሚታዘዝ አካል እንጂ ራሱ የቻለ መንግስት መሆኑ ባለመረዳት ከህወሓት ፅ/ቤት ሆኖ አስተዳደሩን የሚቆጣጠር መስሎት ነበር፡፡ በሌላ አባባል ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ስልጣኑም ታንኩም ባንኩም በሱ ስር ሆነው ነበሩትን ተቋማት ወደ ጊዚያዊ አስተዳደር መግባታቸውን እውን መሆን ጀመረ፡፡ ከዛም አልፎ ፓርቲና መንግስት መለየት እንዳለባቸው የሚያሳዩ ድርጊቶች ተግባረዊ መደረግ መጀመሩ ስልጣን መክበሪያቸው ላደረጉ ግለሰቦች ጥቅማቸው መነካቱ መጀመሩ እና ተጠያቂነት ሊመጣ መሆኑን የተረዱ ይመስላል፡፡
የፕሪቶሪያ ውል ወደ አፈፃፀም ሲገባ የጦርነቱ መነሻ ምክንያት (cause of the war) በውስጥም በውጭም መመልከቱ ስለማይቀር በዚህ ሂደት የሚኖሩ የተጠያቂነት ዞሮ ዞሮ ስልጣን ባንክ እና ታንክ የያዘው ጋር እንደሚወድቅ ግልፅ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብም ለሓርነት ብሎ ለከፈለው እና እየከፈለው ያለውን ዋጋ ህወሓት ውስጥ ስልጣን የሙጠኝ የሉት ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉት መረዳቱ አይቀርም፡፡ በመሆኑም የሚከተሉት ጥያቄዎች ማንሳቱ ይቀጥላል፡
- ህወሓት ስትራቴጂክ አመራር መፍጠር ለምን አልቻለም?
- ስትራቴጂክ አመራር በሌለበት እና በቂ ዝግጀት ሳይደረግ ለምን ወደ ጦርነት ገባን?
- የትግራይ ህዝብ ከአጎራባች ወንድም ህዝቦች በግጭት አዙሪት እንዲኖር ምክንያቱ ምንድ ነው?
- ህወሓት ከማእከላይ መንግስት ጋር ወደ ጦርነት የገባው እውነት ብልፅግናን ላለመቀላቀል ነውን?
- ከግጭት ብኋላ እርቅ እንደሚኖር ሁሉ ቀድሞ መፈራረም ያልተቻለበት ለምንድ ነው?
- ህወሓት ዲሞክራሲ እንዳይኖር እና ብቸኛ ፓርቲ ሆኖ እንዲቀጥል ለምን ተፈለገ? ይህ ከታገልበት ዓላማ አይጋጭው ወይ?
የትግራይ ህዝብ አንድነት ቢኖረው ኖሮ የውስጥ ችግሩ በራሱ ዓቅም የሚፈታበት እድል ነበረው፡፡ ብሄራዊ ጥቅም ወደ ስልጣን ጥቅም፤ ብሄራዊ ምግባባት ወደ ፓርቲ ታማኝነት ፤ የህዝብ አገልጋይነት ወደ ፓርቲ አገልጋይነት አሰራርና አደረጃጀት በመቀየር አንድነትን በመደብዘዙ ለጠላት ጥሩ እድል ፈጥሮ ነበር፡፡ ትግራይ ማለት እኮ ለሁሉም ስልጣን ለሚወድ ተወዳድሮ ስልጣን ላይ የሚወጣበት፤ ሃብት ማካበት ለሚፈልግ ስርዓቱ ጠብቆ ሃብት የሚፈጥርባት፤ በአካዳሚክ እውቀቱ ለህዝቡን ችግር በመፍታት አንቱ መባል የሚፈልግ የሚያገኝበት፤ ሌላ ሙያ ያለው በሚችለው የሙያ መሰላል ህዝቡ የሚገለግልበት የሚመራበት እድል ቢኖር፤ ትግራዋይ ሆኖ የተወለደ በዚች መሬት እስከተፈጠረ ድርስ እና እስከ እረፍቱ ጊዜ በትግራይ ሃብት በየደረጃው ባለቤት የመሆን አደረጃጀት እና አሰራር መዘርጋት ነበረበት፡፡
ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሱት ትግራዋይ ሰው በመሆኑ የሚያገኛቸው መብቶች ሲሆኑ ስልጣን በሸፍጥ፣ ሃብትም በማጭበርበርና በወንጀል፣ በእውቀትህ ሳይሆን በፖለቲካ አመለካከትህ የምታገልግልበት እንዲሁም ትግራዋይ በመሆንህ አቅምህ በፈቀደ በትግራይ ሃብት ተጠቃሚ የማትሆንበት፡፡ በአጠቃላይ ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራርና አደረጃጀት ያላት በመሆንዋ በልጆችዋ ልዩነት በመፈጠሩ የውስጥ ችግር ከውጭ የሚመጣ በማስመሰል አንዱ ለአንዱ በመወነጃጀል ባንዳ ተለላኪ የሚባባልበት ሲሆን እነሱ ባይረዱትም ለትግራይ ህዝብ ጥቅሙ አሳልፈው የሰጡ ቀማኞች መሆናቸው ነው፡፡ ትግራዋይ ማለት ከጫፍ fhመራ እስከ ጫፍ አላማጣ ወዘተ ተብለህ ለመስዋአእትነት ጥሪ የሚቀርብልህ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለመስዋእትነት ጥሪ እንደቀረበልህ ለፖለቲካ ስልጣን እና ሃብት መፍጠር ሲሆን የእንጀራ ልጅ የሚያደርግ ተለምዳዊ አሰራር ያለ መስሏል፡፡
ስለሆነው እነዚህ ጥያቄዎች በሚመለሱበት ሂደት ሁሉ ትግራወይ ባለው ሙያ፣ እውቀቱ እና ክህሎቱ ካለው እና ከሚፈጠረው ሃብት በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት፤ በሚያጋጥሙ አደጋዎች ደግሞ ግዴታዉን የሚወጣ ዜጋ የሚፈጠርበት እንጂ አንዱ በአንዱ በብልጣብልጥነት የሚጠቀምበት ሳይሆን በውድድር የሚሆንበት አሰራርና አደረጃጀት እንዲኖር ማድረጉ አይቀርም፡፡ በተጨማሪም የትግራይ ህዝብ የዘር ፍጅት እንዲደርስበት ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች ተጠያቂ በማድረግ እንዲሁም የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንቅፋት በመፍታት ህወሓት ሆነ ሌላ በትግራይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስልጣን በዲሞክራሲያዊ ሂደት የሚያገኙ እንጂ ታንኩንና ባንኩን በመያዝ በዝባዥ አገዛዝ የሚገነባበት ስርዓት የሚያከትምበት አሰራር ለማበጀት እድል የሚሰጥ ይሆናል፡፡
5. የፕሪቶሪያ ስምምነት እና መልካም ዕደሎች
የፕሪቶሪያ ስምምነት በበቂ ትንታኔ እና ኣፈፃፀም ተግባራዊ በምናደርግበት ሂደት ውሰጥ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በትግራይ ህዝብ የትግል ፍላጎት ዕንቅፋት ሆነው የቆዩ ምሶሶዎች የሚናዱበት እና በጠንካራ አደረጃጀት ሰላም፣ ልማት እና የዲሞክራሲ ሂደት ላይ መሰረት ይጥላል፡፡ በመሆኑ የሚከተሉ መልካም እድል ይፈጥራሉ የሚል እይታ አለኝ፡፡
- የፕሪቶሪያ ሰምምነት የተገኘው በአሜሪካ አደራዳሪነት ነው፡፡ ስምምነቱ እንዲፈርሙ በፕሪቶሪያ የተገኙ ሃይል ብልፅግና እና ህወሓት ሁለቱም የዜሮ ድምር ፖለቲካ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የነዚህ ሁለት ሃይሎች መጫወቻ ሜዳ ሆኖ ያለው ደግሞ ንቡር እና ነውር የሚያቅ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሓርነት የሚፈልግ የትግራይ ህዝብ ነው፡፡ ብልፅግና ህወሓት መንግስት ኣይደለም በማለት ህወሓት በበኩሉ የተመረጥኩኝ ህጋዊ መንግስት እኔ ነኝ በማለት በዜሮ ድምር አስተሳሰባቸው ውግያዊ እንዲቀጥል በሁለቱም ሓይል ተፈልጎ ነበር፡፡ ስለሆነም አሜሪካ የትግራይ ህዝብ ከነዚህ ዝሆኖች ማላቀቅ የተከተለችው ከሁለቱም ሃይሎች ፈልቅቆ ማውጣት ነው፡፡ በተጨማሪም በሁለቱም ሃይሎች የማይታዘዝ አሰተዳደር እንዲቋቋም ነው በብልፅግና እና ‘’ህወሓት’’ ይህን ለማሰናከል ከሁለቱም ሃይሎች ሌላ ዕንቅፋት ለመስራት ቢሞኩሩም፡፡ የትግራይ ህዝብ ለማጥፋት እና ለማዋረድ በውጭ ጠላት የተለመደ ድርጊት ነው አዲስ ጉዳይም አይደለም አዲስ ሚሆነው በአብራኩ ክፋይ አመራር ይህ መከራ አሳልፋለሁ ብሎም አያውቅም፡፡ ስለሆነም ስምምነቱ የትግራይ ህዝብ የሓርነት ጥያቄውን እውን ለማድረግ የሚያስችለውን መደላድል የሚፈጥርለት ይሆናል፡፡
- የትግራይ ህዝብ ብሄራዊ ጥቅሙ ለይቶ ለማስፈፀም ትግል ከጀመረው ግማሽ ክፍለ ዘመን
አልፎበታል፡፡ ለዚህ ብሄራዊ ጥቅም ማስፈፀሚያ የሚሆን በቂ አደረጃጀት እና አሰራር ሳይበጅለት ትግሉ በስልጣን ጥመኞች እጅ በመውደቁ ህዝቡ የዚህ ችግር ሁሉ ገፈት ቀማሽ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም በስምምነቱን ኣፈፃፀም ሂድት ላይ የትግራይ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሓርነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሪፎርም ማድረጉ አይቀርም፡፡ብሄራዊ ጥቅሙን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ትግል ሌሎች ህዝቦች በገንዘብ፣ ክህሎትና ሙያ ድጋፍ ሊያደርጉልን እና ወዳጅ በማድረግ አብሮ መስራት የሚያስችል ዕድል ሊፈጥር ይችላሉ ካልሆነ ግን በየሃያ ሰላሳ ዓመት የገነባውን የሚያፈርስ ህዝብ ለመደገፍም ሆነ አጋር ለማድረግ የታክስ ከፋይ ዜጎቻቸው መዋእለ ነዋይ እኛ ላይ የሚያፈሱበት ጉዳይ መቀነሱ አይቀርም፡፡ ከግጭት አዙሪት ውስጥ ለመውጣት በሚገነቡ ተቋማት በሚፈጠረው ሰላም በሚገኝ የልማትና የዲሞከራሲ ግንባታ ሂደት ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፍላጎት ማሳደሩ ስለማይቀር ትግራይ ዲፕሎማሲ ማእከል ማድረጉ አይቀርም፡፡
- ብሄራዊ ጥቅምን ለማሳካት የሚፈጠሩ ተቋማት ለሁሉም ትግራዋይ ተሳታፊ የሚያደርጉ
አሰራርና አደረጃጀት የሚከተሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ፡፡ ምክንያቱም ትግራዋይ ለመሆን በራሱ ፈቃድ የተፈጠረ እስከሌለ ድረስ ለመኖር ደግሞ የሚከለክለው ተፎጥሮአዊ ሆነ ሰው ሰራሽ ስጋት ሊኖር አይችልም፡፡ አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ የሚሆንበት አመለካከትና ተግባርም አይኖርም፡፡
- ብሄራዊ ጥቅም እና ይህን ለማሰፈፀም የሚስችል አሰራርና አደረጃጀት ያላት እና ዜጎችዋን በተፈጠሩ ተቋማት እኩል ተሳታፊነት ያላቸው ከሆኑ ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ደግሞ በውድድር ይሆናል፡፡ ማለትም ለፖለቲካ ስልጣን፣ ለሙያ ብቃት፣ ሃብት ለማካበት እና አንቱ ለመባልም የሚኖረው ብቸኛ አማራጭ ውድድርና ውድድር ብቻ የሚሆንበትን እድል ይከፍታል፡፡
- ዜጎች በእኩልነት የሚኖርበት ሃገር ለመገንበት የሃሳብ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የዲሞክራሲ ግንባታ ሲታሰብ መነሻ መሆን ያለበት “አንድም ድምፁ ሳይሰማ መቅረት የለም’’ የሚል እና ድምፃቸውን የሚያሰሙበትን ህጋዊ ተቋም እና አሰራር ሲበጅ ነው፡፡ በዚህ የአሰራር ሂደት ደግሞ የሚጣል ሃሳብ ሆነ አመለካከት አይኖርም ማለት ነው፡፡
- የሃብት ክፍፍልን ለማስፈን እና ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ ሃብታም በሃብቱ፣ ምሁር በእውቀቱ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ አርበኛ በአርበኛነቱ ሌላውም ግዴታውን የሚወጣበትን መብቱን የሚከብርለት እና የሚያስከብርበት አሰራር በመዘርጋት ማለት ግጭትን እና ሌብነትን መቆጣጠር ይቻላል፡፡
- ሌላው እድል ችግር የሚፈታው በምርምር ነው፡፡ ምርምር ደግሞ ሳይንስ ነው፡፡ ሳይንስ ደግሞ እውቀት ነው፡፡ የሚመራመረው ደግሞ ምሁር ነው፡፡ ሰለሆነም ከውስጥም ከውጭም የሚደቀኑ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች የሚፈቱት በምርምር ነው፡፡ ምሁር በምርምር ዓቅሙ የሚሳተፍበትን ተቋማት እና አሰራር በማስፈን በእውቀቱ ህዝቡን የሚገለግልበት አሰራር ማስፈን የህዝቡ ህልውና ማረጋገጥ ይሆናል፡፡
- ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራዊ ለማድረግ የህዝቡ ብሄራዊ ጥቅም ከውጪ ከውስጥም ኣደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል ጠንካራ የፀጥታ ተቋማት ግንባታ እድል ሊፈጥርለት ይችላል፡፡