ለ ቅዱስ ፓትሪያሪክ

አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ፤

ጽራሕ ኅበየ ወአወሥአከ ወእነግረከ ዓቢያተ ወኃይላት ዘኢተአምሩ (ኤርምያስ 33፥3)

“ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ”

ቅዱስ ፓትሪያሪክ ሆይ፥ ሌላ በደልና ኃጢአት ስለተገኘቦት ሳይሆን፥ ሰው ባያየኝም በምሕረቱ ብዛት የጠራኝ የቀባኝና ያከበረኝ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር ያየኛል፣ ዛሬም ሆነ ነገ ከጨለማ ስራ ጋር አልተባበርም፣ እውነትን እውነት ሐሰትን ሐሰት ከማለት ያለፈ ከአመፃ ጋር ምንም ክፍል የለኝም! በማለት ለእውነትና ለጽድቅ ለፍትህና ለፍርድ በመቆምዎ ማለትም ቀደም ሲል በወለጋ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በአማራ ከዚህ ሁሉ በከፋ መልኩ ደግሞ በዐቢይ አህመድ ዓሊ የሚመራ ዘራፊና ነፍሰ ገዳይ የባሪያ መንግስት (መጽሐፍ በምሳሌ 30፥22 ላይ ባሪያ በነገሠ ጊዜ እንዲል) እንዲሁም ግበረ አበሩ የክፋት አለቃና የሁከት አውራ ቂስ የኤርትራው ኢሳይያስ አፈወርቂ ግንባር በመፍጠር በትግራይ ህዝብ ላይ ወረራ በመፈጸም ይህን ተከትሎም በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም የጦርና የዘር ማጥፋት ወንጀል መቆም አለበት፣ ከመቃብር ለማያልፍ ምድራዊ ዓላማ ሲባል በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረውን ሰው ደሙን በከንቱ ማፍሰስና በዘፈቀደ ነፍሱን ማጥፋት ትክክል አይደለም፣ ልዩነቶቻችሁ በውይይት ፈትታችሁ ሰላም አውርዱ! በማለትዎ እና በማንነትዎም ትግራዋይ በመሆንዎ ብቻ ከቤተ መንግስት ብሎም የአጋንንት መናገሻ ከሆነው ከቤተ ክህነት በሚወረወር ሰይጣናዊ ፍላጻ ሰለባ ሆነው የአባትነት ክብርና መንፈሳዊ ስልጣንዎን ተገፍተውና ተገፈው ከቤተ ክርስትያኒቱና ከአገሪቱ የደህንነት ቢሮ በተውጣጡ ቅጥረኞችና አደጋጣዮች ዙሪያ ተከበው እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ የቁም እስረኛ ሆኖው በታላቅ መከራና እንግልት እንደሚገኙ ድፍን ዓለም የሚያውቀው ሐቀኛ ምስክርነት ነው።

ቅዱስነትዎ፥ የእግዚአብሔር ቃል 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥16-17 “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” እንዲል ቅዱስነትዎ በገዛ ቤተ ክርስትያንዎ እንደ ባዕድ ተቆጥረው አሁን ለሚገኙበት የግዞት ህይወት መፍትሔው ሌላ ምንም ሳይሆን ሓዋሪያው ያዕቆብ (5፥13) “ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ” እንዲል በምንም ነገር ሳይታወኩና ሳይጨነቁ በመንፈስ ቅዱስ መቃተት በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ፊት ምህጽንታዎን ማቅረብዎን እንዲቀጥሉ ስጽፍሎት በመንፈስ ቅዱስ ልጅነቴ ነው።

ቅዱስነትዎ፥ ሰው፥ ከፀሐይ በታች አለኝ የሚለው ስልጣንና ሀብት ሁሉ ተማምኖ፥ ያሰበውን፣ ያቀደውንና የወደደውን እንዲሁ የማድረግና የመፈፀም አቅም ቢኖሮው ኖሮ አንዳችንም ብንሆን እስከ ዛሬ ዕለት በህይወት ባልሰነበትን ነበር። ልዩ ልዩ ምክንያት ኖሯቸው ሊገድሉንና ሊያጠፉን በብርቱ የሚሹን ሰዎች ብዙ ናቸው። አንዳቸውም ግን (በመዳፋቸው ስር ገበተን ሳለንም) ምኞታቸውና ፍላጎታቸውን ማሳካት ሳይችሉ ዓመታት አለፉ እነሆ እኛም መጽሐፍ “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል። በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ፤ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬም የተረፈ ነው” እንዲል በጌታ ፈቃድ የድል ህይወት እየኖርን እንገኛለን። አራት ኪሎ ቤተ መንግስት የገባ የአክአብ አልጋ ወራሽ (በዐቢይ አህመድ ዓሊ የሚመራ ገዳይና ዘራፊ ቡድን) ቤተ እምነት ሲያስብ እስከ ዛሬ ድረስ በህይወት ያኖረኝ ስለ ራራልኝ ነው! ብለው እንደማያኑ አምናለሁ። ሐቁ፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ቅዱስነትዎንም እንደ ኢታማጆር ሹሙ ጄነራል ሰዓረ መኮነን በጠራራ ፀሐይ ገድሎ በምትክዎ ሌላ ሰው ለመሾም ሳያስበው ቀርቶ ሳይሆን ስላልቻለ አንድም የጌታ ፈቃድ ስላይደለ ብቻ ነው።

ቅዱስነትዎ ሆይ፥ የዐቢይ አህመድ ዓሊ እና በፌርማውና በይሁንታው የንጹህ ሰው ነፍስ በመጣል የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰይጣናዊ ሲኖዶስ ምክር በህይወትዎ ላይ ያልፀናበት ምስጢር፥ ለሚወድዱትና ትእዛዙን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን የሚጠብቅ ታላቅና የተፈራ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር በላባዎቹ ስለ ጋረድዎትና የእግዚብሔር እውነትና ምሕረት እንደ ጋሻ ስለ ከበብዎት ብቻ ነው። የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳና እንደ ተራበ ድብ የሚያቁነጠንጣቸው ያለ በቅዱስነትዎ ዙሪያዎ የሚገኙ ቁም ነገር የማገኝባቸው ምናምንቴዎች፣ የተናቁ ፍሬ አልባ ቅሌታሞች፣ ለመልካም ነገር የማይበቁ ሸማቂዎች፣ ካባ ለባሽ የጎንደር ሽፍቶችና ጆቢራዎች እንደሆኑም፥ መጽሐፍ “እግዚአብሔር ታማኞቹ ይጠብቃል ትዕቢተኞች ግን ፈጽሞ ይበቀላቸዋል” እንዲል (መዝ 31፥23) በቀኑ መጨረሻ ቁማርተኞቹ በስራቸው ያፍራሉ እንጅ ጫፍዎን የሚነካ አንድም ስጋ ለባሽ አይኖርምና ሰማይንና ምድር በቃሉ ያፀና፣ ለዮሴፍ በግብጽ ምድር ጥብቅና የቆመለት፣ የሌለውን እንዳለው የሚጠራ ልዑል እግዚብሔርን ታምነው እስከ መጨረሻ ድረስ ከእውነት ጋር ተጣብቀው እንዲጸኑ ጸሎቴ ነው።   

ቅዱስነትዎ፥ የትግራይ ቅዱስት ቤተ ክርስትያን ማህበረ ምእመናን እና መንፈሳዊ አስተዳደርዋ መንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ በሚመለከት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኘው የትግራይ ማህበረ ምእመናንና መንፈሳዊ አስተዳደሩ “ሰይጣን ይሻለናል” ብሎ ከሚል ሰይጣናዊ ሲኖዶስ ጋር ህብረት ሆነ ክፍል የለንም! ሲል የገለፀው አቋምና የወሰደው መንፈሳዊ እርምጃ ተገቢ፣ ትክክለኛና መጽሐፍ ቅዱሳዊም ነው። አንድም፥ “ሰይጣን ይሻለናል!” ብሎ ማለት ይቅር የማይባል በመንፈስ ቅዱስ ላይ የተነገረ ሰድብ ነውና (ማቴ 12፥31-32)። ኢትዮጵያ፥ የቅርቡም የርቁም የጎረቤት አገራትና መንግስታት አስተባብራ በሀሰተኛ ክስና በተፈበረከ ትርክት በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀመችው ወረራና የከፈተችው ጦርነት ማግስት ቅዱስነትዎ የሚገኙበት ሁኔታ አይደለም ልብና ኩላሊት ለሚመረምር ለፈጣሪ ለሰውም ግልጽና የተገለጠ ነው። አሁንም፥ መንበረ ሰላማ የት/ኦ/ተ/ቤ/ያን በተመለከተ በዋናነት በሲኖዶሱ ፀሓፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስራ አስካያጅ በኩል የሚቀርብሎት ያለና የከረመ ሪፖርት ሁሉ ሐሰተኛና የፈጠራ አሉባልታ ነው። ምናልባትም፥ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ አባል የሆነ ሊቀ ጳጳስ አንዱ ዓውደ ምህረት ላይ ቆሞ የአማራ ህዝብና ወጣቶችን በሰይጣናዊ ትምህርትና መንፈስ አጥምቆ ለጦርነትና ለእልቂት ሲቀሰቅስ “ሰይጣን ይሻለናል!” ብሎ ለመስበኩ ላይሰሙ እንደሚችሉ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ቤተ ክርስቲያን ይህን እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በማስመልከት በጦርነቱ ወቅት ሳይቀር በተደጋጋሚ የፃፈችው ደብዳቤ ቅዱስነትዎ ጠረጴዛ ላይ እንዳይደርስ የደረሰ ካለም ቅዱስነትዎ ሆነ ተብሎ ለማሳሳት በትግራይ ስም የተፃፈ ሐሰተኛ ደብዳቤ እያዘጋጁ በተሳሳተ መረጃ የተሳሳተ ነገር እንዲናገሩና ያለ ፈቃድዎ በስምዎና በፌርማዎ የተሳሳተ ነገር ይፋ እየተደረገ እንዳለ ይታመናል።   

ቅዱስ ፓትሪያሪክ ሆይ፥ ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ (ቆሮ 6፥14-18) ሰዎች በጻፈው መልክዕክት ላይ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፥ በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ስለዚህም ጌታ፥ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ፥ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል” እንዲል የትግራይ ቅድስት ቤተ ክርስትያን ማህበረ ምእመናን እና መንፈሳዊ አስተዳደርዋ መንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ መንፈሳዊ ውሳኔ ከእግዚአብሔር እውነት ጋር የወገነ ሐቅ መሆኑን አውቀውና ተረድተው በቅዱስነትዎ ዙሪያ በሚገኙ አፅራረ ጽድቅና ስምዐ ሐሰቶች ምክርና ማስፈራራት የተነሳ በትግራይ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ በቃልም ሆነ በጽሑፍ ስህተት ውስጥ እንዳይገኙ ስጽፍሎት አሁንም በታላቅ መንፈሳዊ አክብሮትና ልጅነት ነው።

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

By aiga