ቀማኛ ዳኛ

Byaiga

Jul 20, 2023

ሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ

07/19/2023

ሰሞኑን መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ባካሄደው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ እና የጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ ያስተላለፉቸውን መግለጫና ውሳኔዎች በአንክሮ ተመልክቸዋለሁ፡፡ እንደዚሁም በትግራይ ላይ በተካሄደው ጦርነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደተቋምም ሆነ ተሿሚዎችዋና ሠራተኞቸቿ የነበራቸውን ተሳትፎ በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ የሃይማኖት አባቶችና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በጦርነት ወቅት እንደተቋምም ሆነ እንደማንኛውም አማኝ የደረሰባቸው ጉዳት በጥንቃቄ ተከታትያለሁ (ለደረሰው ጉዳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ይቅርታ መጠየቋን ያጤኑታል)፡፡   

ለዚህ ጽሁፍ ርእስ አድርጌ የመረጥኩት “ቀማኛ ዳኛ” በሁለቱም ወገን ላሉት የሃይማኖት አባቶች ስለ ግብዝ ሰው ታሪክ ለማስተማር በማሰብ ሳይሆን እየቀረቡ ካሉት የሁለት ወገን የሰሞነኛ መግለጫዎችና ውሳኔዎች በመነሳት ስለደረሰው ለከት የሌለው በደል የሰናፍጭ ታክል ስሜት ያላሳየው እንዳውም ሌላ ዙር እልቂትን የሚጋብዝ መግለጫዎችና ውሳኔዎች የማን እንደሆነ ወይም የትኛው አካል ራሱን ገርፎ እየጮሀ እንዳለ ለማየት ያስችለን ዘንድ ነው፡፡

በዚህ ሰለጠነ በተባለ ዘመን ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ በከፍተኛ ስሜትና በተግባር ተንሰላስሎ  በትግራይና በህዝቦችዋ ላይ የተካሄደው አረመኔያዊና ጄኖሳይዳል ጦርነት በረቀቀና በተጠና መንገድ ተከናውኖ በርካታ ሰብአዊ፤ ቁሳዊና የተፈጥሮ ሀብቶችን ያወደመና የበላ፤ ክልሉ ለዘበናት የገነባውን ሀብትና ልማት ወደ ኋላ የመለሰ፤  ከፕሪቶርያ ስምምነት በኋላም ቢሆን የሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ያልቆመ (በአንድ ወገን የሚካሄድ ዘርፈ ብዙ  ጦርነት እየተከነወነ እንደሆነ በርካታ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በማቅረብ መሞገት ይቻላል) በዘግናኝነቱም አለም በታሪክ ከትቦ ለማስቀመጥ ከድኖ እያበሰለው ያለ ሃቅ መሆኑን ለሚክዱ ሰዎች እርማችሁን አውጡ እላቸዋለሁ፡፡ በዚህ ምስቅልቅልና የተራዘመ ዘመቻ በርካታ ወጣቶች ተገድለዋል፤ ሴቶችና ህፃናት ተደፍረዋል፤ አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶች ወድመዋል፤ በርካታ ቅርሶች ተዘርፈዋል፤ የኢኮኖሚ ተቋሞች ወድመዋል ተዘርፈዋልም፡፡ ይህ ስሜት ወ ተግባር የተንሰላሰለበት ጦርነት ከመከሰቱ በፊት ረዘም ላሉ አመታት ሁሌም የህዝቦች ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር ራስ ምታት የሚሆንባቸው አእምሮ ስንኩላን ግለሰቦች (የፖለቲካ፤ የሃይማኖት፤ የአካዳሚክ፤ የሚዲያ፤ የንግድና፤ የኪነጥበብ ሰዎች) በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ብቅ ብቅ እያሉ የጦርነት አስቻይ ግብአቶች ሲደሰኩሩ ሲጽፉና ሲያቀጣጥሉ እንደነበር በተሰበረ ልብ ስናስታውስ አሁን ለምንገኝበት ጠባሳ የታሪክ ምእራፍ ብቸኛና ብቸኛው ምክንያት እንደሆነ መረዳት የሚያዳግት እንደማይሆን ግንዛቤ በመውሰድ ጭምር ነው፡፡  

በዚህ በአይነቱ ወደር የሌለው ጥፋት በርካታ ተዋንያን ተሳተፈውበታል፡፡ የተሳትፎው አይነት ፍላጎትና መጠን ወደፊት በሰነድ የሚታይ ሆኖ በጦርነት አስቻይነትና በቀጥታ ተሳታፊነት ከሚጠቀሱት ተቋሞች መካከል በግንባር ቀደም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትገኝበታለች፡፡ ለተሳትፎዋ የተከሰሰችበት ጉዳይ ቀጥሎ ባሉት ስድስት አበይት ጉዳዮች አጠቃልሎ ማየት ይቻላል፡፡

  1. በትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መእምን ላይ በተደረገው ወረራ ቀጥተኛና ተቋማዊ ተሳትፎ አድርጋለች የሚል ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? “እኔ ከመከላከያ ወገን ነኝ” የሚል የወቅቱ የካድሬዎች ቅስቀሳ ግራና ቀኙን ሳትመረምር በሃሳዌ ትርክት ተማርካ ለጦርነት ማስፈጽሚያ የሚውል ከቤተክርስቲያኒቱ ተቀማጭ ገንዘብ ወጪ አድርጋ ከመስጠትዋ በላይ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክልሎች የሚኖሩ ምእመናን በማስተባበር የገንዘብ መዋጮ በማሰባሰብ አስረክባለች፡፡
  2. የቤተክርስቲያኒቱ የሲኖዶስ አባላትና ሹመኞች ከሰው (ወያኔ) ይልቅ ሰይጣን ቢገዛን ይሻላል ምክንቱም ሰይጣን ፈሪሃ እግዚአብሄር አለው የሚል የተሳከረ ሀይማኖታዊ አስተምህሮት ለመእመናን ሲያስተምሩ ነበር፡፡ ይህ ዶግማዊ ስህተት ነው፤ ቤተክርስቲያኒቱም አስካሁን ድረስ አላወገዘችም፤
  3. በትግራይ አባቶች በኩል ለቤተክርስቲያኒቱ በየጊዜው ሲቀርብላት የነበረውን የሰላም ተማጽኖ ቁብ ሳይሰጣት እንዳውም ጦርነቱና እልቂቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት ያላት መሆኑ በሚያሳብቅ መልኩ የቤተክርስቲያኒቱ የሲኖዶስ አባላት እና ሹመኞች ጦር ሜዳ ድረስ በመሄድ ወራሪውን የጦር ሰራዊት ባርከዋል፤ አመስግነዋል፤ አበረታትተዋል፡፡
  4. ቤተእምነቶች ሲረክሱና ሲወድሙ፤ ልዩ ልዩ ቅዱሳተ ነዋያት ሲዘረፉና ሲቃጠሉ፤ ቤተክርስቲያኒቱን አናስደፍርም በማለት ከወራሪው ጋር የተናነቁ ካህናትና መእመናን በግፍ ሲገደሉ፤ መነኮሳት ወሲባዊ ጥቃት ሲፈፀምባቸው፤ የካህናት ሚስቶች በባሎቻቸው ፊት ሲደፈሩ  የቤተክርስቲያኒቱ የሲኖዶስ አባላት ”መረጃው የለንም“፤ “ምኑን እናውግዝ” እያሉ ጭፍን ጥላቻቸው መገለጫ የሆነ ሲደሰኩር በየሚዲያው  ያሰሙ ነበር፤
  5. በአዲስ አበባና በሌሎችም ሀገረ ሰብከቶች ሲያገልገሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ ካህናትና የቤተክርስቲያን ሊቃውንቶችና አባቶች ትግራዋይ በመሆናቸው ብቻ ከስራ በመገለል፤ እንግልትና ስቃይ አድርሳለች፤
  6. በተቀናጀ ከበባ ውስጥ ሆኖ በረሃብና በችግር ላይ ለሚገኘው መእመን ህዝብዋ አለመድረስዋ ብቻም ሳይሆን ለመድረስም ፍላጎት አለማሳየትዋ እንደዚሁም በመእመኑ ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ሰቆቃ የሀገሬው ህዝብና አለም እንዳያውቀው በሚዲያ እንዳይነገር በመከላከልና በተአምር ሾልኮ የወጣውንም ቢሆን እውቅና ለመንፈግ ረዥም ርቀት መጓዝዋ፤          

በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ የሃይማኖት አባቶች አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሚደመጠው ክስ ሲጠቃለል የሚከተለው ነው፡፡

  1. የትግራይ የሃይማኖት አባቶች መንበረ ሰላማ የተባለ መዋቅር በመፍጠር የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ አከናውነዋል፡፡ ይህ ድርጊትም “የቀኖና ጥሰት” “ህገወት አድራጎት” ነው፡፡

የሁለቱ ቤተክርስቲያኖች ክሶች ህሊናው ያልተዛባ ሰው ፍርድ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የማያዳግት ቢሆንም ጠቅለል ብሎ ሲታይ አንደኛው የሚያስጨንቀው ስለመሰረታዊ የክርስትና አስተምህሮት መዛነፍ፤ ስለሰብአዊነት፤ ስለፍትሃዊነትና ስለሰው ልጆች ክብር ሲሆን ሌላኛው አበክሮ የሚያስጨንቀው ጉዳይ የገዢና ተገዢ ስርአት ስለማንበር፤ ስለማንበርከክ፤ ስለግዛት ማስፋፋት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ አጠቃላይ ፍርዱ ለአንባቢው ልተወውና የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ምርጫ ተከትሎ የጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ ስሁት፤ ከፋፋይና ዘረኘነት የተንፀባረቀበት ባለ ስምንት ነጥብ መግለጫ ውስጥ በሁለት አበይት ግን ልብ ሊባሉ የሚያሻቸው ጉዳዮች ላንሳ፡፡

መግለጫው ወይም ውሳኔው ከሚያተከርባቸው ዋናውና መሰረታዊው የሆነው የትግራይ መንበረ ሰላማ ያከናወነው ተግባር “አገራዊ አንድነት የሚያናጋ” ነው ብሎ ይኮንናል፡፡ ይህ ግን ትክክል ነው ብዬ አልወስድም፡፡ በ2007 (እ.ኤ.አ) በኢትዮጵያ የህዝብና ቆጠራ ባለስልጣን ባካሄደው አጠቃላይ ቆጠራ ሪፖርት መሰረት ከኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል 44% ኦርቶዶክስ 32% ሙስሊም 19% ፐሮቴስታንትና ፔንቴኮሰታል ቀሪው 5% ደግሞ ሌሎች አማኞች እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እንግዲህ ይህ የዛሬ 16 አመት የተደረገ ቆጠራ በመሆኑ አሁን ምድር ላይ የሚኖረው የፐርሰንታይል ለውጥ ማወቅ አይቻልም፡፡ በቆጠራው ያገኘነውን ሪፖርት ተመስርተን አገሪቱ ባለ-በዝሃ ሃይማኖት አገር ሆና እያለች እንዴት ሆኖ ነው የትግራይ መንበረ ሰላማ አሁን የፈጠረውን መዋቅር አገር በታኝ ነው ብሎ መክሰስ የሚቻለው? በኦርቶዶክስ እምነት ግንባሩን የማያጥፈው የትግራይ ህዝብ ሌላ እምነት ይዞ የመጣ ይመስል የትግራይ መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመፍጠሩ እንዴት ሆኖ ነው በቀማኛ ዳኛው በተገጠመለት የተከሳሽ ሳጥን ውስጥ እንዲገባ የተፈረደበት? “ሃይማኖት የግል ሃገር የጋራ” የሚለውን የቀደምት አባበል ተውሰን 90-98% የትግራይ ህዝብ  የሆነው የኦርቶዶክስ አማኝ ሌላ እምነት ተከታይ መሆን እፈልጋለሁ የሚል ምክረ ሃሳብ ቢያቀርብ ኖሮ እነኚህ ጉደኛ የሃይማኖት አባቶች/ካድሬዎች ምን ይሉ ወይም ያደርጉ ነበር ብዬ ሳስብ ህሊናዬ መሸከም ከሚችለው በላይ ይሆንብኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ አሁን ይዘው ብቅ ያሉት “የሀገርና ልኡላዊነት አደጋ” የመጫወቻ ካርድ ከቤተክርስቲያኒቱ ቅጥረግቢ ውጭ ባሉ ሰዎችና ልብሰ ተክህኖ ደርበው በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ መሽገው በሚገኙ ኦርቶጳጳስ-ፖለቲከኞች ሰፊው አማኝ ለማወናበድ የተመዘዘ ካርድ በመሆኑ የአላጋጮች የቀቢፀ-ተሰፋ እርምጃነት ከመሆን በዘለለ የሚያዋጣ ስትራቴጂ ነው ብዬ አልወስድም፡፡ (እዚህ ላይ የስራ ባልደረባቸው የሆኑት አቡነ ሳዊሮስ ቤተክርስቲያንዋ የፖለቲካ ሸፍጥ መዶለቻ ስፍራ እንደሆነች አብይ አህመድ አሊ በተገኘበት ማጋለጣቸው ልብ ይሉታል)፡፡ ለምን ከዚህ አይነት የቁማር አዙሪት ወጥተው የወንጌልና ወንጌል ሰዎች ብቻ ሆነው የህዝቡን ልብ መማረክ እንደተሳናቸው ሳስብ ልቤ ድክም ይለዋል፡፡

ሌላው በዚህ መግለጫ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ፍቅር አንድነት ከሚሰብክበት ቤተክርስቲያን የወጣ መግለጫ አይመስልም፡፡ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ በተጻራሪ በአንድ ማህበረሰብ ተወላጆች መካከል አንድነትን በመሸርሸር በመካከሉም አለመተማመን ተፈጥሮ እርስ በርሱ እንዲባለ የጋበዙበት ጥሪ ነው፡፡ ይህ ጥሪ በትግራይ ውስጥ የሚገኙ ሊቃውንቶች፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት ተመድበው አገልግሎት ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የሃይማኖት ሊቃውንቶችና ካህናት ብቻም ሳይሆን በአተቃላይ በሃገሪቱ ያሉ መእመናንና መእመናትም ያጠቃልላል፡፡ ይህ ውሳኔ በጦርነቱ ወቅት ቤተክርስቲያኒቱ ስትከተለው የነበረው የአስቻይነት የውድመት ፖሊሲ ቀጣይነት ማረጋገጫ የሰጠችበት ነው ብሎ እንደ አንድ ማስረጃ በመቁጠር መከራከር የሚቻል እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ጥሪ ሁልጊዜም ቢሆን ከአመፀኞችና ሸፍጠኞች ቤት የሚመነጭ ነው፡፡ አሁን የትግራይ ህዝብ ሰላም ያስፈልገዋል፤ ይገባዋልም፡፡ ሌሎች በሚፈጥሩለት አጀንዳ ተነሳስቶ ራሱን የሚጫረስበት ጊዜ አይደለም ያለው፡፡ እንደ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመሳሰሉ በሚፈበርኩት ከፋፋይና ግዴለሽ ትርክቶች የትግራይ መእመን ሌላ ዙር እልቂት የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ይህ ሊረዱለት ይገባቸዋል፤ ይኖርባቸዋልም፡፡       

በመጨረሻም ለንጽጽር ይረዳ ዘንድ የተጠቀምኩት የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ያወጣው የ2007ቱ የህዝብ ቆጠራ እንደሀይማኖት ተቋምነትዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሰፊ ስራ እንደሚጠብቃት ግልጽ አድርጌ ማለፍ እፈልጋለሁ፡፡ በኔ እምነት ይህ ጊዜ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መልካም፤ ታሪካዊ አጋጣሚና እድል አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ በዚህ ሦስት ነገሮችን ጠቁሜ ልለፍ፡፡ (1) ይህ አሁን የምትከተለውን አሳሳች “ራስን ከፖለቲካና ከሃገር አዳኝ” የመሲህነት መነጽር ወጥታ ወንጌልና ወንጌል ብቻ በማስተማር ላይ ማተኮር፤ (2) በሃይማኖት መሪዎች “ስበከት” መእመኑ ተነሳስቶ “በተግባር የሚከውነው” መረን የለቀቀ የእርኩሰት መንፈስ በአርአያነት መንገድ ማውገዝ፤ ዳግም እንዳይከሰትም ተቋማዊ ዝግጅት ማድረግ፤ (3) በአታካራና ተረት ተረት ጨዋታ የምታሳልፈው ጊዜ በቃ ብላ ሰፊው አማኝዋ ሰላሙንና መንፈሳዊ ምቾቱን የሚያረጋግጥበትን ስራ መስራት አማኝ ለማብዛት ይረዳታል (4) ችግሮችን ወደውጪ ከማማተርና ከማላከክ ይልቅ ዳግም ራስዋን ከውስጥ መፈተሸና ማስተካከል ይጠበቅባታል፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዳንኤል ክብረት አጋፋሪነት የተሰባሰቡ እንጭጭ የታሪክ አተላዎች በሚያመነጩት ያላዋቂ ሳሚ ትርክት በሚያስከትለው ዳፋ ታሪክ ሆኖ መቅረትንም ስለሚያመጣ የዛሬው መጣጥፌ የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅስ በመጥቀስ ላሳርግ፡፡ በምድር ላይ እስካሉ ሲያደርጉት እንደተመለከትነው እውነታዎች በማድበስበስ፤ መእመናን በማወናበድ ሃቅና ርትእ በመደባበቅ እዚህ ደርሰዋል ወደ እውነተኛው ፍርድና ፍትህ ሰጪው አምላክ ሲቀርቡ ግን ”ማሰማሪያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወየላቸው“ በሚል የተገለፀውን የፈጣሪ ቃል መጠየቅ አይቀርምና ምን መልስ እንዳዘጋጁ አላውቅም፡፡

በቸር እንሰንብት

By aiga

2 thoughts on “ቀማኛ ዳኛ”
  1. FANNOS CRIMINALS MUST BE DISMANTLED AND LOCKED UP :FREE TIGRAY FROM FANNO AND ERITREAN MERCENARIES says:

    ሰባተኛው ንጉስ አቢይ አህመድ የከዳቸውን የቀድሞ ሎሌያቸውን የአሁኑ የሻዕቢያ ደንገጡር ስለሆነው ፋኖ ዘራፊ ልክስክስ ሌባ ተብከንክነው፥በክነው፥ቆሽታቸው አሮ ቢቀረና ይህን ያልተለመደ የንጉሡን ጠባይ ያየ አሽከራቸው ደመቀ መኮንን እየተነፋረቀ አረቄውን ጠጥቶ ሲያበቃ ጥሙን እንኳ ሳይቆርጥ እንዲህ እያለ ሙሾ አወጣላቸው

    ይገመጣል እንጂ ዳቦ አይጠጣም
    ፋኖ ጠላት ሲሆን ምነው አይቀጣም ብሏቸዋል፤፤

    እንዴት ሳይቀጣ ይቀራል ይቀጣል እንጂ ማለቸው ነበር፤በዙያው የተሰበሰቡተኝ ለጊዜው አልተገንዝበውትም ነበር…
    ሰባተኛው ንጉስም ዝቅሎ ባቱን ከፍሎ ታንገቱ ይቀጣ ሲሉ ለብርሃኑ ጁላ መልእክት ላኩ፤፤ፋኖ ሌባ መተተኛ ዘራፊ ህፃን ደፋሪ ይደምሰስ ይፍረስ ይፍለስ፤፤የንጉሡን ፍርዱ የሰሙ ሁሉ ድል ለመከላከያ ይሁን ጀምበር ሳይጠልቅ ፋኖ ይቀጥቀጥ ሲሉ ድምጣቸውን አሠሙ!!!!!!!

  2. FANNOS CRIMINALS MUST BE DISMANTLED AND LOCKED UP :FREE TIGRAY FROM FANNO AND ERITREAN MERCENARIES says:

    FANNOS CRIMINALS MUST BE DISMANTLED AND LOCKED UP :FREE TIGRAY FROM FANNO AND ERITREAN MERCENARIES

    ሰባተኛው ንጉስ አቢይ አህመድ የከዳቸውን የቀድሞ ሎሌያቸውን የአሁኑ የሻዕቢያ ደንገጡር ስለሆነው ፋኖ ዘራፊ ልክስክስ ሌባ ተብከንክነው፥በክነው፥ቆሽታቸው አሮ ቢቀረና ይህን ያልተለመደ የንጉሡን ጠባይ ያየ አሽከራቸው ደመቀ መኮንን እየተነፋረቀ አረቄውን ጠጥቶ ሲያበቃ ጥሙን እንኳ ሳይቆርጥ እንዲህ እያለ ሙሾ አወጣላቸው :
    ይገመጣል እንጂ ዳቦ አይጠጣም
    ፋኖ ጠላት ሲሆን ምነው አይቀጣም ብሏቸዋል፤፤

    እንዴት ሳይቀጣ ይቀራል ይቀጣል እንጂ ማለቸው ነበር፤በዙያው የተሰበሰቡተኝ ለጊዜው አልተገንዝበውትም ነበር… ሰባተኛው ንጉስም ዝቅሎ ባቱን ከፍሎ ታንገቱ ይቀጣ ሲሉ ለብርሃኑ ጁላ መልእክት ላኩ፤፤ፋኖ ሌባ መተተኛ ዘራፊ ህፃን ደፋሪ ይደምሰስ ይፍረስ ይፍለስ፤፤የንጉሡን ፍርዱ የሰሙ ሁሉ ድል ለመከላከያ ይሁን ጀምበር ሳይጠልቅ ፋኖ ይቀጥቀጥ ሲሉ ድምጣቸውን አሠሙ!!!!!!!

Comments are closed.