(Escalate to deescalate)
ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
ድርድርና ሂደቶቹን በተመለከተ ከዚህ ቀደም “መፍትሔው፥ ምስርታ ሀገረ ትግራይ እውን ማድረግ ነው” በሚል ርእስ ለንባብ በበቃ ሰፊ ጽሑፍ ላይ በግርድፉ ያነሳሁት ነጥብ ነበር። ይኸውም፥ ተስማሙ ሲባል ተታኮሱ ተታኮሱ ሲባል ተስማሙ የሚለው ዜና መስማት የድርድር ባህሪይ እንደሆነ፤ ይህን ዓይነቱ ክስተትም (ትንኮሳ) በድንገት የሚፈጠር ሳይሆን የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ አንድምንታ እንዳለው፤ በተለይ ጦርነት ተከትሎ የሚመጣ የድርድር መድረክ ሂደቱ እንዲሁ ቀላልና ፈጣን ሊሆን እንደማይችል፤ ተደራዳሪዎች ለይፋዊ ድርድር የሚቀመጡ (ከመቀመጣቸው በፊት) ድርድሩም ሆነ ውይይቱ ለማካሄድ በየደረጃው የሚጠይቀው መመዘኛ ሁሉ ያሟሉና በዚህም የተስማሙ እንደሆነ ብቻ ለይፋዊ ድርድር ሊቀመጡ እንደሚችሉ፤ ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ በስኬት ለማገባደድም ወራት የሚፈጅ ሂደት እንደሆነ ማንሳቴን ይታወሳል። ይህ ሂደት ቢያንስ ስድስት ወራት የፈጀ ሲሆን ማለትም ኢትዮጵያ “በየትኛውም ሰዓትና በማንኛውም ቦታ ለድርድር እቀመጣለሁ” ያለችው የትግራይ ሰራዊት እንዲመለስ ስምምነት ላይ ከተደረሰ ከስድስት ወራት በኋላ መሆኑ ነው።
ተፋላሚ ሃይሎች ለድርድርና ለውይይት እንቀመጣለን ብለው በተናጠል ሆነ በጋራ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ካደረጉና ከደረሱ በኋላ እንደ ገና የጦርነት ዜና መስማት ሆነ አንዱ አካል ስምምነቱን አፍርሶ ተኩስ የሚከፍትበትና የሚያጠቃበት ምክንያት ብዙ ነው። ወቅቱን በማገናዘብ ታድያ ሁለቱን አንጻራዊ ምክንያቶች ብቻ ላንሳ።
- ተፋላሚዎች በተናጠል ሆነ የጋራ የተኩስ ስምምነት በመድረስ ለድርድርና ለውይይት በሚዘጋጁበት ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈጻሚ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ የድርድሩ የመጨረሻ ምዕራፍ ተደርሶ ሰላም እስኪያወርዱ ድረስ ያለ ጊዜ በሁለቱም ተፈላሚዎች በኩል ሊነገር የሚችል የጦርነት ሆነ የሰላም ዜና ስለማይኖር ይህን ተከትሎ የሚፈጠር የመረጃ ክፍት ግድ ይሆናል። በመንግስታቱና በህዝቡ መካከል ክፍተት ሊፈጥሩ ከሚችሉ ሁኔታዎች መካከል አንዱም የውይይቱን ሂደትና ይዘት በተመለከተ ሆነ ተብለው የሚናፈሱ ሀሰተኛ መላምቶች (speculations) የሚጠቀስ ነው። ለምሳሌ፥ የኢሳያያስ አፈወርቂ መንግስት ዓይነቱ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፥ ማስኩን እየቀያየረ ህዝብን የሚያውክ የፈጠራ ዜናዎች ማሰራጨት ላይ መትጋቱ የማይቀር ነው። በተጨማሪም ከየ አቅጣጫው የሚናፈሱ ተመሳሳይ መላምቶች ይኖራሉ። ይህ ዓይነቱ ትንግርት ታድያ የነበረና ያለ ነው። በርግጥ የዚህ ዓይነቱ አሽክላ በአደራዳሪዎችና በተደራዳሪዎች ዘንድም የታወቀ ሲሆን ጋሬጣውን ለመግታትና ለማስቆም ታሳቢ አድርገው ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንዱም፥ ተፋላሚዎች በቅንጅት የሚሰሩት ድራማ ነው፤ ይኸውም፥ ተተኮሰብኝ! አልተኮስኩበትም! ዓይነቱ አርቴፊሻል ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት የሰፊውን ህዝብ ቀልብ የመስረቅና አሉባልታውን ጥሎ መስመር የማስያዝ ታክቲት ሲሆን ታክቲኩ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገራት ተግባራዊ ሲደረግ የመጣ የተለመደና የታወቀ ፍቱን የድርድር አካልና አሰራርም ነው። ሁለተኛ ነጥብ የዚህ አንጻራዊ ሲሆን የትንኮሳው ዓላማና መፍትሔው የሚጠቁም ነው።
- በተናጠል ሆነ በጋራ ከሚደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ የሚደረገው ማንኛውም ዓይነት ትንኮሳ (aggression) በተለይ ወዶ ሳይሆን ተገድዶ ለድርድር የሚቀመጠው አካል እንደዚህ ዓይነት ትንኮሳዎች በመፈጸም ይታወቃል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ፣ ዓላማውና መፍትሔው ምን እንደሆነና ሊሆን እንደሚችል እንደሚከተለው በአጭሩ እንመለከታለን። ለድርድር ከመቀመጥ ውጭም ሌላ አማራጭ የሌለው ሃይል ለድርድር እቀመጣለሁ የሚልበት ምክንያት ብዙ ቢሆንም ኢትዮጵያ ለድርድር እቀመጣለሁ ያለችበት ዋነኛው ምክንያት ግን አገሪቱ የጎረቤት አገራትና መንግስታት አስከትላ በትግራይ የፈጸመችው ወረራ የተነሳ ከገባችበት መቀመቅና አሁን ከምትገኝበት የእልቂትና የመበታተን አደጋ ለመትረፍ ከትግራይ ጋር ያላት ችግር በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጭ ሌላ አማራጭ ስለሌላት ብቻ ነው። እውነቱ ይህ ከሆነ ዘንዳ ኢትዮጵያ በትግራይ ሰራዊት ላይ ትንኮሳ የምትፈጽምበት ምክንያት ታድያ ምንድ ነው? ማለታችን የማይቀር ነው። ከትግራይ ጋር ከመደራደርና ከመወያየት ውጭ ሌላ ማምለጫ መንገድ የሌላት ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን በመጣስ በትግራይ ሰራዊት ላይ የሚታደርጋቸው ትንኮሳዎች ምክንያት አንዱ የትግራይ ሰራዊትና የፖለቲካ አመራር የሙቀት ልክ ለመለካት ያለመ ሲሆን ይህ የምታደርግበትም የስምምነቱ ተርም በበላይነት ለመዘወር ካላት ፍላጎት የሚመነጭ ነው። የዚህ ዓይነቱ ትንኮሳ አደገኛ የሚደርገው ታድያ ኢትዮጵያ ይህን ዓይነቱ ትንኮሳ ስትፈጽም አጸፌታው ምላሽ ካላገኘት ሁኔታዎች የምትገመግመውና የምትተረጉመው የትግራይ ሰራዊትና የፖለቲካ አመራር እንቁላሉን አንድ ባስኬት ላይ አስቀምጧል በሚል ነው። አጸፌታው ምላሽ አለማግኘትዋ የድካም ምልክት አድርጋ ስለ ምትወስደው ሌላ ድንገተኛ የሆነ ትልቅና የከፋ ጥቃት በመፈፀም የድርድሩን አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ዕድሉ ይሰጠኛል ብላ ታምናለች። መፍትሔው፥ የተኩስ ስምምነቱን ተላልፎ ለተኮሰብህ አጸፌታው ምላሽ በመስጠት በሙሉ ልቡ ለድርድር እንዲቀመጥ ማስገደድ ነው። ይህ በወታደራዊ ስትራቴጂ እይታ አንጻር ትክክለኛ ተገቢ እርምጃ ሲሆን ሁኔታዎች ለማርገብና ለማረጋጋት አንድ እርምጃ እልፍ ያለ፣ ከፍተኛ ጉዳት ልታደርስበት በምችልበት ወታደራዊ ዒላማ ላይ ለይተይ በማጥቃትና ከበድ ያለ እርምጃ በመውሰድ ግልጽና አጭር መልዕክት መላክ መቻል፤ ስልቱም፥ escalate to deescalate ተብሎ ይታወቃል።
ጥጉ፥ የትግራይ ህዝብ ሆነ ቀጠናው በአጠቃላይ ሰላም ሊያገኝ የሚችለው ኢትዮጵያ የምትፈልገው በመስጠት ብቻ እንደሆነ መታወቅ አለበት። ይህ ማለት፥ አሁን በቀጠናው ያለ አለመረጋጋትና ሁከት ፈጽሞ ሊሰክን የሚችለው ኢትዮጵያ በመረጠችውና በምትፈልገው መንገድ በማስተናገድ እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያ የምትፈልገው ሰላም ከሆነ ሰላም ሊወርድበት የሚችል አሰራር (ውይይትና ድርድር) በሙሉ ልብ ተሳታፊ በመሆን ሰላም ማውረድ። ኢትዮጵያ በአንጻሩ የምትፈልገው ጦርነት ከሆነ ደግሞ አገሪቱ አሁን ከምትገኝበት የእልቂትና የመበታተን አፋፍ ጫፍ ዶርሶ የዘራቸውን እስካታጭድ ድረስ የምትፈልገውን መስጠት ነው። ለኢትዮጵያ ችግር ሌላ መፍትሔ የለውም። አንድም፥ የኢትዮጵያ ችግር የትግራይ ችግር የሚሆንበት ጉዳይ እዚህ ሊያበቃ ይገባል። ኢትዮጵያ፥ እንደ አገር የመቀጠል ሃሳቡና ፍላጎቱ ካላት ከዚህ ቀደም፥ “በማንኛውም ሰዓትና በየትኛውም ስፍራ ከትግራይ ጋር እደራደራለሁ” ብላ ያወጀችው የሰላም አዋጅ በማክበር ለውይይትና ለድርድር ከመቀመጥ ውጭ ሌላ ምንም ማውጫ/ማምለጫ አማራጭ የላትም። የኢትዮጵያ ባለ ስልጣት፥ የኢትዮጵያ ህዝብ በጦርነት ወሬ ወጥረን በመያዝ ዕድሜያችን እናራዝማለን የሚል ተስፋና እምነት ካላቸው ደግሞ ቀደም ሲል እንዳለሳሁት የኢትዮጵያ ችግር የትግራይ ችግር አይደለም ሊሆንም ስለማይችል ነገሩ በአጭሩ ዕልባት ያገኝ ዘንድ የትግራይ አመራር ጉዳዩን በጥልቀት ያስብበትና ይመክርበት ዘንድ ይመከራል።