ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

አማራና ኦሮሞ የአንድ አባት ልጆች ነን፣ ደማችን አንድ ነው፣ አንድ ህዝብ ነን – “ኦሮ-ማራ”! እያሉ ተረታቸው ሲቀዱና ፕሮፓጋንዳቸው ሲነፉ የነበሩ የአማራ ልሒቃንና አጨብጫቢዎቻቸው ዛሬ 180 ዲግሪ ዞሮው ስለ ኦሮሞ ምን እያሉ እንዳሉ እየሰማን ነው። ከለንደን እስከ ዋሽንግተን የተሰለፈው ኩታራም ቢሆን በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት እንደ ቁራ እንዲሁ ሲጮሁ፣ እንደ እንቁራሪት ሲያጉረመርሙ፣ በሰው አገር ሰው ኢምበሲ በር እንደ ብቅል እንደ ተሰጡ ኖሩ፤ ሺህ አመት ንገስልን እያሉ የረገጠው አፈር እየላሱ ሲመርቁትና ሲያቆለጳጵሱት የኖሩት፣ አገሩን ሽጦ ጦርነታቸው ሲዋጋላቸው የከረመ ዐቢይ አህመድ ዓሊ በተመለከተም የተለመደ አልቃሻና ምዋርተኛ ምላሳቸው ወልውለው ምን እያሉት እንዳለ እየሰማን ነው። በርግጥ፥ ለአማራ ልሒቃንና ከበሮ መቺዎቻቸው ትግል ማለት በማህበራዊ ሚድያ ላይ ተጥደህ ምላስህ ከትናጋህ እስኪጣበቅ ድረስ ማልቀስና መጮህ ነውና ይኸው ሰዎቹ አለቅን፣ ገደለን፣ ፈለጠን፣ ቆረጠን፣ ጎመደን ኡ ኡ!  የምትለዋን በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የተጋገረች የአልቃሾች ነጠላ ዜማ አሁን ደግሞ ተምልሳ መጥታለች።

የአማራ ልሒቃን፥ በአንድም በሌላም መንገድ የመንግስትነት ስልጣን የያዙ እንደሆነ የሚያውቁትና የተካኑበት የበከተ የሴራ ፖለቲካ እየመነዘሩና እየሰለቀጡ ማለትም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጀርባ ላይ ታዝለው ጋላ ሻንቅላ እያሉ ታርጋ እየለጠፉ ህዝቡን በማሸማቀቅና በማሳጣት እንዲሁ ተዘለው በዘፈቀደ ለመኖር ካልሆነ በቀል ስልጣኑ ቢይዙትም ባይዙትም ምን እንደሚፈልጉ እንኳ ጭላንጭሉ የሌላቸውና ኮከቡ የጠፋባቸው ሰዎች ናቸው። ይህ የተገለጠ የአማራ ልሒቃን ሰልቃጭ ማንነት የተሰወረበትም ሌላው ህዝብ እንጅ ለእኛ ለተጋሩ አዲስና የማይታወቅ ባህሪያቸው አይደለም። የአማራ ልሒቃን መንግስተ ሰማያትም ቢገቡ ማጉረመረማቸውና ጎረበጠኝ ማለታቸውን የማይተዉ፣ ልበ ጠማሞችና ምዋርተኞች ስለ መሆናቸውም አንስተውም። ጥያቄው፥ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ቢፈጠር ነው ይህ ሁሉ ለቅሶና ጩኸት ያበዙ? የሚል ነው። የአማራ ልሒቃን የሚያስጮሃቸው ያለ እውነት አማራ ኢትዮጵያ ውስጥ በማንነቱ ስለተገፋ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለ? ሲል በዚህ ጽሑፍ የተነሳ ጥያቄና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችና ጉዳዮች እንመልሳለን አንስተንም እንወያያለን።     

ለቅሶው ከፍየልዋ በላይ ነው

በእነ ዐቢይ አህመድ ዐሊ ቡድን ተመልምሎ በአዲስ አበባ የፌዴራል ስልጣን ተሰጥቶት ቀለብ እየተሰፈረለት የሚኖር ያለ የአማራ ልሒቅ ሆነ ሱሪው ፈትቶ (ሲጀምር ሲኖረው አይደል) ለአዳማ ፖለቲከኞች የሰገደ በአማራ ክልል ላይ ስልጣን የተሸነሸነ የአማራ ልሒቅ ሁሉ የኬኛ ፖለቲከኞች ተላላኪ በመሆኑ በይፋ የሚተነፍሳት የተቃውሞ ድምጽ የለችም ልትኖርም አትችልም። የተነፈሰ እንደሆነም እነ ሽመልስ በጠራራ ፀሓይ በጓዶቻቸው ላይ የፈፀሙት ቅትለት ጠንቅቀው ስለሚረዱ በውናቸው ቀርቶ በህማቸውም ቢሆን ዐቢይ አህመድ ዐሊን መቃወም አያስቡትም። ጩኸቱን እያቀለጠው ያለ የአማራ ልሒቅ ታድያ ማን ነው? ያልን እንደሆነ በዋናነት በማንኛውም የስልጣን ተዋረድ የሌለ፣ በደርግ ዘመን የደነቆረ ፖለቲከኛ ነኝ፣ ምሁር ነኝ ብሎ የሚያምን፣ በሌለው ባላለፈበትና ባልዋለበት እውቀት ነገር መቀላቀል የለመደ፥ አርቲስት ነኝ፣ አክቲቪስት ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ፣ ታዋቂ ነኝ፣ አዋቂ ነኝ – ለቅላቂ ነኝ የሚለውን ነው ዛሬ ሞትን አለቅን! እያለ የለመደው የለቅሶና የዋይታ ፋይሉን ከፍቶ በመጮህ ላይ የሚገኘው። ዛሬ ምን አዲስ ነገር ቢፈጠር ነው ሰዎቹ በዚህ ደረጃ የሚያስጩሃቸውና የሚያንጫጫው ያለ? ያልን እንደሆነ ደግሞ፥   

  • ትግራይ ለማውደምና የትግራይ ህዝብ ለማጥፋትና መሬቱን ለሱዳን አስረክቦ ከሱዳን ጋር የመከረ፣ ኢምሬትን ጋብዞ ከኤርትራና ከሶማሊያ ሰራዊት ጎን ተሰለልፎ በከፈተው ጦርነት በትግራይ ህዝብ ላይ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም የጦርና የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸመ፣ የትግራይ ህዝብ ሀብትና ንብረት የወረረና ያወደመ የአማራ ልሒቅ እንደ ተመኘው ትግራይና የትግራይ ህዝብ አጥፍቶ የትግራይ ታሪክ፣ ሃይማኖታዊና ማህበራዊና ሀብትና ቅርስ ባለቤት በመሆን ምንሊካዊት ኢትዮጵያ ፈጥሮ ለመኖር የነበረው ምኞትና ህልም የውሃ ሽታ ሆኖ በመቅረቱ፣ ሞተ አለቀ የተባለ ህዝብ ፅናቱና ታላቅነቱ፣ ታዋጊነቱና ጀግነቱ በዓለም መድረክ መታየቱና ትንግርት መፍጠሩ፣ ትግራዋይ ዳግም የጥላቶቹን ጉልበት አጥመልምሎና አሽመድምዶ ለዚህ መብቃቱ የአማራ ልሒቃን በአሁን ሰዓት የሚይዙትና የሚጨብጡት አሳጥቷቸዋል።
  • ይህ እንደ መዥገር በሌሎች ትክሻ ላይ ተንጠላጥሎና ታዝሎ ካልሆነ በቀር በታሪክ ራሱን ችሎ ቆሞ የማያውቅ የአማራ ልሒቅ ትግራይ ለመውረር ያሰማራው፣ የትግራይ መሬት የረገጠ፣ እንደ ፈርዖን ሰረገሎች በወጣበት ሰምጦ የቀረና በትግራይ መሬትና በሜዳው የተቀበረ ስፍር ቁጥር የሌለው የአማራ ኢንተርሃምዌ ሚኒሻና ታጣቂ ደሙ ደመ ከልብ ሆኖ በመቅረቱ ከዚህ የተነሳም በላዩላይ የተከመረ ዕዳ የቀን ዕረፍት የሌሊት እንቅልፍ ስለነሳቸው ነው። የሚያስጩሃቸው ያለ ሌላ ምንም ሳይሆን ተክነንበታል የሚሉት ቁማሩ መበላታቸውና ይህን ተክትሎም የተከናነቡት ኪሳራና ዕዳ ነው።
  • የትግራይ ሰራዊት፥ ሁሉንም በመረጡትና በሚገባቸው መንገድ ካስተናገደና የሚገባቸው ስፍራና ቦታ ካስያዘ በኋላ አሁን ደግሞ በሌላ ምዕራፍ ተገልጦ መቆሙን በዓይናቸው ማየታቸው ማለትም “ካብ ጉይይ ምውዓል ክሳድ ምሓዝ” ብሎ የሚያምን ትግራዋይ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል ለመጨረስ መስማማቱ አጨብጫቢዎቹ የአማራ ልሒቃንና ከበሮ መቺዎቻቸው ምክንያት እየፈጠሩ (ዐቢይ እንዲህ አደርገን፣ አዲስ አበባ እንዳትገቡ ተባልን፣ ወዘተ) ሞትን አለቅን እያሉ እናቱ እንደ ሞተችበት ህጻን ልጅ ሲያለቃቅሱና ሲጮሁ እየተመለከትን ነው።
  • ሰራዊት ትግራይ የአንዲት ጥይት ድምጽ ሳያሰማ ምዕራብ ትግራይ ነጻ የሚያወጣበት ስትራቴጂና (እዚህ ላይ መዘርዘሩ አስፈላጊ አይሆንም) አሁንም በቀጣይነት እየወሰደውና እየተከተለው ያለ እርምጃና አሰራር የአማራ ልሒቃን ክፉኛ በመረበሹና በማሸበሩ በዚህ መሃልም ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገው ይፋዊ ውይይት መደረኩ በባህሪይው አጨብጫቢዎቹ የአማራ ልሒቃን ስፍራቸውን የሚያሳውቅ በመሆኑ ነገሩ የሌሊት እንቅልፍ ስለነሳቸውም ዐቢይ አህመድ አዲስ አበባ እንዳትገቡ አለን እያሉ በምክንያት ለማልቀስና ለመጭህ ተገደዋል። ይህ ሁሉ የአማራ ልሒቃንና ከበሮ መቺዎቻቸው ብሶት ታድያ ዐቢይ አህመድ እንዲህ አደረገን፣ አዲስ አበባ እንዳትገቡ ተባልን፣ የኦሮሞ ፖለቲከኞች (የአባታቸው ልጆች) አስተዳደራዊ ሴራ እየፈጸሙብን ነው፣ በማንነታችን እየተገለልን ነው ወዘተ በሚል ሽፋን ደጉሰው እስኪ ወጣላቸው ድረስ ለመጮህ ተገደዋል። ለቅሶው ከፍየልዋ በላይ ነው! ያለ ማን ነበር?

ሓቁ ይህ ከሆነ ዘንዳ፥ የአማራ ልሒቃን የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚከሱበት ያለ ምክንያት ምንድ ነው? ትናንት “ደማችን አንድ ነው፣ አንድ ህዝብ ነን፣ የአንድ አባት ልጆች ነን” ያሉን ሰዎች ዛሬ ምን ቢፈጠር ነው ኦሮሞ “በአማራ ማንነታችን” እየገፋን ነው እስከ ማለት የደረሱ? የአማራ ልሒቃን የተለመደ ለቅሶና ዋይታ ምን ቀርቶባቸው ነው? ምንስ ፍለጋ ይሆን? ማለታችን አይቀርም። በዚህ ዙሪያ ላይ እንደሚከተለው እንመለከታለን።

የኦሮሞ ፖለቲከኞችና የአማራ ልሒቃን ጸብ ምንጭ ምንድ ነው?

ከኦሮሞና ከኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር መክረን የህወሓት መሪዎችን አሸንፈናል፤ ቀጣይ አጀንዳችን ኦሮሞ ማታለልና ጠልፈን መጣል ነው በሚል እሳቤ፥ በቋንቋ፣ በባህል፣ በታሪክ፣ ወዘተ ምንም የሚያገናኝ ነገር የሌላቸው ሁለት ሕዝቦች “ኦሮ-ማራ” በሚል መደለያ ቋንቋ (የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለመደለል) ፍሬ ባያፈራም የተሰራ ስራ ቀላል አይደለም። በነገራችን ላይ፥ ቆይቶም ቢሆን የሃይለ ቃሉ አደገኝነት የተረዳ በወቅቱ በእነ ለማ መገርሳ ይመራ የነበረ የኦሮሞ ቡድን አባባሉ ከእውነት የራቀና ፍጹም ውሸት እንደሆነ ጠንቅቀው አውቀዋል። ዳሩ ግን፥ ሰዎቹ ካርታ ተቀባብለው የተቆናጠጡት ስልጣን እንግዶች ስለሆኑ (ለዙፋኑ አዲስ ስለሆኑ) እስኪጠናከሩ ድረስ ከማንም ጋር ፀብ አይፈልጉም፤ ይልቁንም፥ ሊያገኙት የሚችሉት እርዳታ ሁሉ የማግኘት ፍላጎት ስለ ነበራቸው አባባሉን ተቀብለው አስተጋብተወታል። ማናልባትም የአማራ ልሒቃን ለማዘናጋት አባባሉን በማመንጨት ረገድ እጅ ቢኖራቸውም ሃይለ ቃሉ ከሚገባው ማራገብ እንደሚያሳጣቸው ስለገባቸው ግን ስለ ኦሮሞ ይገደናል የሚሉ የሳይበር ተዋጊዎች በጎን በማሰማራት አባባሉ በእንጭጩ እንዲቀጭ ብርቱ ጥረት አድርጓል። ያም ሆነ ይህ ግን፥ አባባሉ የጫጉላው ወራት እንደ ተገባደደ ረጅም ርቀት ሳይጓዝ መክሰሙን ሁላችን እናስታውሳለን።

የህወሓት መሪዎች ከስልጣን ለማስወገድ በመስማማታቸው ለጊዜው ቢሆን ተዳፍኖ የቆየ ዘመናት ያስቆጠረ ደምነታቸው እንደገና ያገረሸው በዚህ ሰዓት ነበር። አደጋው ያሳሰባቸው የኦሮሞ ፖሊከኞች ከዚህ ዓይነቱ እሳት ለመትረፍና ለማምለጥ የሰሩት ስራ ታድያ የአማራ ልሒቃን በህወሃት መሪዎች ላይ በማስነሳት ትግራይና አማራ ማያያዝ ነበር።  የህወሓት መሪዎች የ27 ዓመታት የስልጣን ቆይታ እንደ ገና በማፋፋም፣ የአማራ የሳበር ሰልቃጮች የህወሓት መሪዎች በቀጣይነት ርዕስ እድርገው እንዲጮሁ ማበረታታት፣ ከዚያም አልፎ በትግራይና በአማራ መካከል የለየለት ጸብ ለመፍጠር ታስቦ ወደ ትግራይ የሚወስድ መንገድ (የፌዴራል መንገድ) እንዲዘጋ ሁለቱን ህዝቦች የማያያዝ ነገር የኦሮሞ ፖለቲከኞ ከሰራቸው ስራዎች የሚጠቀስ ነው። የአማራ ልሒቃን በተመሳሳይ ከኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር መክረው በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ስም ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከስብሃት ነጋ ጋር የተደረገ ስምምነት አፍርሶ ትግራይ የማዳከምና የማንበርከስ ስራ እንዲሰራ በዚህም የአማራ ክልል ከጎኑ እንደሆነ በመወትወት የሰሩት ስራ (የፈጠሩት ጦርነት) ተጠቃሽ ነው። አሁንም፥ የሚያገናኝ የሌላቸው ሰዎች (የሚያገናኝ ነገር የለም እያሉን ስለሆነ) “የአንድ አባት ልጆች” ነን ያሉ ሰዎች እንዴት እንደ ገና መላላጥ ውስጥ ገቡ? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ ሚስጢሩ ወዲህ ነው።

በኦሮሞና በአማራ ልሒቃን መካከል ያለው ልዩነት፥ የኦሮሞ ልሒቃን መንቃትና የአማራ ልሒቃን የበከተ እምነትና እብሪተኛ አስተሳሰብ የፈጠረው ደምነት ነው። ከ“ኦሮ-ማራ” መክሰም በኋም ቢሆን ለጥቂት ጊዜያት ሊዘልቁ የቻሉ በትግራይ ላይ የተፈፀመ ወረራ አንድ ስላደረጋቸው ብቻ ነው። ጦርነቱ ሲረግብ ደግሞ ገደሉን፣ ሞትን፣ አለቅን እያሉ ያለ የአማራ ልሒቃን የሚያስጮሃቸው ያለ በድንገት ወይ አጋጣሚ ሳይሆን በነገር ሁሉ ከተላላኪነት ያለፈ ስልጣን ስለ ሌላቸውና ስለ ተፈነገሉ በዋናነት ደግሞ የትግራይ ትንሳኤ ነው። ኢትዮጵያ ከትግራይ ጋር ያላት ልዩነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ዕልባት ካላገኘችም ሁለቱም ህዝቦች በተጠረበ ድንጋይ ሊተራረዱና ሊገዳደሉ እንደሚችሉ አሁን ያለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሁነኛ አመላካች ነው። እዚህ ላይ የኦሮሞ ፖለቲከኞች መንቃት ምንድ ነው? ያልን እንደሆነ፥ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አሁን በበላይነት የተቆጣጠሩት የፌዴራል ስልጣን ይዘው ለመቀጠል እስከቻሉ ድረስ የአማራ ልሒቃን እርስበርሳቸው እያገዳደሉ ሰጥ ለጥ አድርገው ሊገዝዋቸው እንደሚችሉ፣ የምንሊክ ዘር ነኝ እያለ ቀረርቶ በማሰማት የተካነው ልሒቅ ከበሬ ወለደ ወሬና አሉባልታ ያለፈ እዚህ ግባ የሚባል አቅም እንደሌለው በሚገባ በርቶላቸዋል። የአማራ ክልል ተጠሪነቱ ለኦሮሚያ መንግስት ለመሆኑ ለማሳየትና ለማረጋገጥም አንድና ሁለቴ አይደለም ሦስትና አራት ጊዜያት ልሒቁን በማንሳፈፍ፣ እርስበርሱ በማጋጨትና በጠራራ ጸሐይ በጥይት ደብድበው በመግደል የወደዱት መሾምና መሻር እንደሚችሉ በይፋ አሳይተዋል። በመሆኑም፥ የኦሮሞ ልሒቃን በአማራ ልሒቃን ላይ ያዳበሩት አዲስ ዕይታና ዕድገት በንቀት ከሚመለከተው የአማራ ልሒቅ እምነትና አስተሳሰብ ሊስማማና ሊናበብ ባለመቻሉ በሁለቱም መካከል የሚታይ ያለ ፖለቲካዊ ልዩነትና አለመግባባት እውን እንዲሆን አድርጓል።  

ትግራይ የሌለችበት ኢትዮጵያ ለአማራ ልሒቃን መቃብራቸው ብቻ ነው ልትሆን የምትችለው

ስልጣን ላይ ሲወጣ መጨፍጨፍ ከስልጣን ሲገፈተር ምላሱ ከትናጋው እስኪጣበቅ ድረስ በመጮህ የሚታወቀው ለፌ ወለፌው የአማራ ልሒቅ በተመለከተ ሁለት ወሳኝ ባህሪያቱ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይኸውም፥ የአማራ ልሒቃን ችሎታ በዋናነት ወንዝ የማያሻግር ሐሰተኛ ወሬና አሉባልታ ማናፈስና ማመላለስ ሲሆን መድሃኒቱ ደግሞ ልሒቃኑ በሃይል የሚያምኑ ሰዎች እንደ መሆናቸው መጠን ልካቸውን አውቀው እንዲኖሩ የሚያደርግ ሌላ ምንም ሳይሆን ዱላ ብቻ መሆኑ ነው። ይህ ማለት ከትግራይ ውጭ (ትግራይ የአማራ ልሒቃን ስፍራቸው ለማስቀመጥ የፌዴራል ስልጣን መቀመጥ አይሻውም) ትናንት የተፈጠረ የሲዳማ ክልል ጨምሮ አፋርና ጋምቤላ የፌዴራል ስልጣን በበላይነት የመያዝ ዕድሉ የገጠማቸው ዕለት የአማራ ልሒቅ ሰጥ ለጥ አድርገው የመግዛት ዕድሉ ይኖራቸዋል። አሁን በዚህ ሰዓት የኢትዮጵያ ስልጣን በበላይነት የሚዘውረው ያለ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይህ ምስጢር በሚገባ ተረድቷል። ከነተረቱም፥ ከበሮ በሰው እጅ ሲያምር ሲይዙት ያደናግር! እንደሚባለው ኢትዮጵያን መምራትና ማስተዳደር በዚህ ደረጃ ግራ ያጋባቸው የአዳማ ፖለቲከኞች፥ የአማራ ልሒቃን በተመለከተ (ዘግይቶም ቢሆን) አንድ ነገር ግን በሚገባ ገብቷቸዋል፤ ይኸውም፥ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰ፥ አፉን ከፍቶ ሲቀደድና ዘራፍ እያለ ሲሸልል ለሚያየው፥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመዘወር አቅም ያለው የሚመስል የአማራ ልሒቅ ከኣፍኣ ወሬ የዘለለ ምንም ቁም-ነገር የሌለውና የማይገኝበት ቆርቆሮ (ባዶ በርሚል) እንደሆነ በሚገባ ገብቷቸዋል። መድሃኒቱም ቢሆን በትክክል ተረድተው ከሰኔ 2011 ዓ./ም ጀምሮም ለተግባራዊነቱ ተግተዋል። የአዳማ ፖለቲከኞች አራት ኪሎ ቤተ መንግስት የሙጥኝ ብለው ይዞው እስከቀጠሉ ድረስም፥ የአማራ ልሒቅ ከወሬ የዘለለ፤ አንድም፥ እዚህም እዚያም ተራ ሁከትና ግርግር ከመፍጠር ያለፈ የሚያመጣውና የሚፈጥረው ነገር እንዴሌለው ስለተረዱ የበላይነታቸው እንደያዙ ለመጠቀጠል ሁሉን ነገር ከማድረግ አይመለሱም። ዐቢይ አህመድ ዓሊ በባህርዳርና በጎንደር ከተሞች የተካሄዱ ሰልፎች አስመልክቶ “እንደዚህ ዓይነት ጩኸት አናውቀዋለን የትም አይደርስም!” ሲል የሰጠው መልስ ልብ ይሏል።      

ይህ ዓይነቱ (የኦሮሞና የአማራ ጸብ) ታድያ ሌላ ማንም የዘራው ጸብ ሳይሆን ይልቁንም የአማራ ልሒቃን ሁሉን የመግዛት ልሃጫም እምነትና አስተሳሰብ ከኦሮሞ ፖለቲከኞች መንቃት ጋር ሊስማማ አለመቻሉ የፈጠረው ግጭት ነው። የአማራ ልሒቃን ኢትዮጵያን የመግዛት መለኮታዊ ስጦታ ያለን እኛ ነን ብለው ያምናሉ የኦሮሞ ልሒቃን በተመሳሳይ መለኮታዊ ስልጣን ከመርካቶ ገበያ የሚገዛ ከሆነ ይሄው እኛም መለኮታዊ ስጦታ አለን ስለዚህ አርፋቹ ተቀመጡ ማለት መጀመራቸውን ግጭቱ በቀጣይነት ሊጋጋል ችሏል።  

የአማራ ልሒቃን፥ “ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም” የሚል አምነታቸውን አይተዉም፤ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በተመሳሳይ፥ አገር መምራት እንደምችል ይሄው እያሉ በሃይልና በጉልበት ባላንጣቸውን ማድቀቅ ይቀጥሉበታል። የአማራ ልሒቃን መርዛማ የእባብ ምላሳቸው እየወለወሉ በፕሮፓጋንዳ ብዛት ያጠድፏቸውል የኦሮሞ ፖለቲከኞች በአንጻሩ በጥይት ይጠብሷቸዋል። ነገሩ በአጭሩ ያስቀመጥነው እንደሆነ “እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” በሚል አጭር ገላጭ ዐረፍተ ነገር በመጠቀም በእነዚህ ሁለት አካላት ያለ ነባራዊ ግኙንነት በአጭሩ ማስቀመጥ ይቻላል።  እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ መረዳት ያለብን ቁምነገር ቢኖር፥ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እውነተኛ ማንነት በተመለከተ ነው። ይኸውም፥ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በአማራ ልሒቃንና በትግራይ አመራር መካከል የተፈጠረ ግጭት የፈጠራቸው (ክፍተት የፈጠረው) ሃይል እንጂ ከዚያ ያለፈ ሌላ ምንም እንዳይደለ ልናሰምርበት ይገባል። በኢትዮጵያና በትግራይ መካከል የሚደረገው ስምምነት የአማራ ልሒቃን በተዘዋዋሪ ልክ የሚያስገባ በመሆኑ አንድም ዞሮ ዞሮው ከትግራይ ጋር ሰላም ማውረዳቸው ስለማይቀር አሁን ያለው የኦሮሞ ፖለቲከኞች አሰራር ባለበት የሚቀጥል አይሆንም። የኦሮሞ ፖለቲከኞችም ለምን ዕድሉን አንጠቀምበትም በማለት የገቡበት ፖለቲካ እንጅ የበላይ ሆነው አገሪቱን የመምራት ፍላጎት ኖራቸው አይደለም። ይህን እናድርግ ቢሉም እንደማያዋጣቸውና ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ከማንም በላይ ይረዳሉ።  

የኦሮሞ ፖለቲከኞች “ባለተራ ነን” በማለት አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ተቀምጠው አገር መምራት የሚችሉ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ሙሉ በሙሉ የከሰመች እንደሆነ ብቻ ነው። ይህ ኩልል ያለ ሐቅ ነው። የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሰጥ ለጥ አድርገው ሊገዙት የሚፈልጉትን ሰጥ ለጥ አድርጎው ኢትዮጵያን በሚፈልጉት መልክና ቅርጽ አበጀጃጅተው አገሪቱን መግዛት የሚችሉ ከትግራይ ጋር ሳይነካኩና ከትግራይ ጋር ያላቸው ርቀት ጠብቀው ብቻ ነው። ከትግራይ ጋር ሊኖራቸው የሚችል ግኙንነት እኩነት ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት የፈጠረ እንደሆነ ብቻ ነው። የአማራ ልሒቃን በተመሳሳይ፥ የምንሊክ፣ የጃንሆይና የደርግ ዘመነ መንግስት ዳግም መየት ቀርቶበባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም መኖር የሚችሉ ሰዎቹ ከትግራይ ጋር የተስማሙና ሰላም ያወረዱ እንደሆነ ብቻ ነው። አሁን ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ገብር ሲለው ሳያቅማማ የማይገብር ከሆነ የአማራ ልሒቅ እስከስታ እየመታ በቁሙ ያልቃል። ጥጉ፥ ትግራይ የሌለችበት ኢትዮጵያ ለአማራ ልሒቃን መቃብራቸው ብቻ ነው ልትሆን የምትችለው።  ለምን? በኢትዮጵያ ታሪክ ትግራይ የኢትዮጵያ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ማዕከል መሆንዋ ብቻ ሳይሆን የእነዚህ ሁለት ህዝቦች (የኦሮሞና የአማራ) ራዕይ፣ ዓላማና ተልዕኮ ለየቅል ስለሆነ ነው። አንድም፥ የኦሮሞ ልሒቅ የአማራ ልሒቃን የሚያይበት መነጽር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ መለወጡን ብቻ ሳይሆን ዓይኑም ጭምር በመክፈቱ የተቆናጠጠው የፌዴራል ስልጣን በአንድም በሌላም መንገድ አስካልጣለ ድረስ በጥይት እየጨፈጨፈና እየፈጀ ሰጥ ለጥ አድርጎ ሊገዛው እንደሚችል አምነዋል።  ችግሩ የኦሮሞ ልሒቃን የአማራ ልሒቃን በጉልበት ሊያንበርክካቸው እንደሚችሉ ቢያምኑም በዚህ መልኩ ሩቅ ሊጋዙ እንደማይችሉ፣ ዘመኑም እንደማይፈቅድላቸው፣ ይህን ሲያደርጉም “ልማት” የሚባለው ነገር ስመው በመለየት እንደሆነ በሚገባ ያውቃሉ። ከዚህ ለመትረፍ ታድያ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ውስጥ እኩል የሀብትና የስልጣን ተካፋዮች ሆነው ለመኖር ከትግራይ የፖለቲካ ዕርዳታ ይሻሉ። የምዕራቡም የምስራቁም ርዕሰ ሃያላን የትግራይ ህዝብ የሀገራዊነት ጥያቄ እውን እንዳይሆን የማጨናገፍ ስራ ላይ የተጠመዱም ያለ ምክንያት እንዲሁ ሳይሆን አንደኛውና ዋነኛው ምክንያታቸው ይህ ነው። ትግራይ የሌለችበት ኢትዮጵያ የእልቂት ቀጠና እንደሚሆን ስለሚያውቁ ነው። የትግራይ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ዕርዳታና ድጋፍ የሌላትና የተለያት ኢትዮጵያ አገር ሆና መቀጠል ትችላለች ብለው ስለማያምኑ ነው። ይህ ለም የእርሻ መሬት በመቀራመት ህልውናው ለማስቀጠል የሚቃምጠው የዐረቡ ዓለም እምነት ጭምር ነው። ያለ ትግራይ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ማየት ይሳናቸዋል።

በመቀጠል፥ የአማራ ልሒቃን እንደ ማንኛውም ዜጋ በሰላም ለመኖር ያላቸው አማራጭ ሰላም መፍጠርና ከሌሎች ጋር መስማማት ከሆነ ከዚህ ውጭ ሊከተሉት የሚችሉት ማንኛውም መንገድ በአንጻሩ መጥፊያቸው ከሆነ ለምን ያላቸው አማራጭ ተጠቅመው ተጠቃሚዎች አይሆንም? ከኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር መዝለል የት ያደርሰናል ብለው ነው የሚያስቡ? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ አጠር ባለ መልኩ እንደሚከተለው እንመለከታለን።

የቀቢጸ ተስፋዎቹ መወዳጅነትና አንድምታው  

ኦሮሞ አሁን ያለው ጦርነት እንዲቀጥል አይፈልግም፤ አንድም፥ ከጦርነቱ የሚያተርፈው ነገር ስለሌለው ብቻ ሳይሆን አስከፊው አደጋ ስለቀመሰውና ቀጣዩም ምን ሊሆን እንደሚችል በደንብ በሚገባ ስለገባቸው ነው። ልሃጫሞቹ የአማራ ልሒቃን በአንፃሩ መሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን ዕዳው ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው አሁን በዚህ ሰዓት አጥፍቶ የማጥፋት ተልዕኮ ላይ ናቸው። የኢትዮጵያ ዕድገትና መልካምነት ማየት ከማይሻ የኤርትራ ዕድሜ ልክ ገዢ ከኢሳይያስ አፈወርቂ የሚተሻሹበት ያለ ምክንያትም ይህ ነው። ሰዎቹ (የአማራ ልሒቃን) ተስፋ ስለሌላቸውና ስለቆረጡ ነው። የአማራ ልሒቃን፥ “ኣምሓራይ ኣድጊ ወዲ ሰበይቲ…” እያለ ከሚዘፍንበት፣ አህያ አያለ ከሚጠራቸው፣ አንደ አሳማ ስጋ ከሚጸየፋቸው አምባገነን ቡድን ያላቸው ግኙንነት፤ ከነተረቱም፥ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው በዋናነት የአማራ ልሒቃን መረኑ የለቀቀ ፍርሃት እንዲሁም የኢሳይያስ አፈወርቂ ነገሮች ባቀደው መልኩ አለመሄዳቸው መረበሽ የፈጠረው ሩቅ የማይሄድ ጊዚያዊ መተሻሸት ነው። ዓላማው? የትግራይ ህዝብ አሁን ያለበትና የሚገኝበት ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንዲራዘም ማድረግ ያለመ ነው።

የአማራ ልሒቃን፥ የትግራይ ሰራዊት የተፈጠረ ዕለት እጅ የሰጡ ሰዎች ናቸው። ከስረናል፣ ተሸንፈናል፣ አልተሳካልንም! ብለውም ስለሚያምኑ የሚሰሩት ያለ ስራ ሁሉ ጭንቀት የወለደው በዘፈቀደ/በግምት የሚሰሩት ያለ ስራ ነው። የአማራ ልሒቃን ህልም (ትግራይን በማንበርከክ የትግራይ ህዝብ ሀብትና ንብረት ባለቤት የመሆን) የቀን ቅጀት ሆኖ በመቅረቱ ልሒቃኑ የተካኑበት በሬ ወለደ ወሬና አሉባልታ እያናፈሱ የዜጎችዋን ሰላም ለመንሳት ከሻዕቢያ ጋር ግንባር ይፈጥሩ ዘንድ አስገድዳቸዋል። የአማራ ልሒቃን አሁን በዚህ ሰዓት ከሻዕቢያ ጋር ያላቸው ምስጢራዊ ግኙንነት ልሒቃኖቹ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለው ጨርቅ አንደ ልብስ አሰፍተው የአዞ አንባ እያፈሰሱ አገሬ! መቃብሬ! የሚላዋትን አገር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ለማተረማመስ ካልሆነ በቀር ኢሳይያስ አፈወርቂ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ያስገባናል ብለው አይደለም። ኢሳይያስ አፈወርቂ ይህን ማድረግ እንደማይችል ያውቃሉ፤ የኢሳይያስ አፈወርቂ ዓላማም፥ “ሃሊሉያ ዝመፀካ ኣድግስ ኣጥቢቕካ ፀዓኖ” እንደሚባለው የአማራ ልሒቃን በመጠቀም የትግራይ ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል ጊዜ ለመሸመት ካልሆነ በቀር የአማራ ልሒቃን መሻት ሊፈጽምላቸው እንደማይችል አቅሙም እንደማይፈቅድለትና እንዳበቃለት ያውቃል። ኢሳይያስ አፈወርቂ አሁን በዚህ ሰዓት አይደለም የትግራይ ሰራዊት ሊገዳደር ቀርቶ የዓይን ቅንድብ ማንቀሳቀስ የማይችል የከሰረ ሰው ነው። ይህ ማለት ግን ጦርነት አይከፍትም፣ ዕድሉን አይሞክርም ማለት አይደለም፤ የሞከራት እንደሆነ የመንግስትነቱ ፍጻሜ ይሆናል ለማለት እንጅ።  

ትግራይና ኢትዮጵያ በሚያደጉት ስምምነት ላይ ለመገኘት (የውይይቱ አካል ለመሆን) ያደረገው ከፍተኛ ጥረት እስከ አሁን ባለው መረጃ አልተሳካለትም። የኤርትራ ሰራዊት ትግራይን ለቆ የወጣ ወዶ በፈቃዱ ሳይሆን ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሰራዊትና የአማራ ኢንተርምሃዌ ሚኒሻና ታጣቂ ተሰብሮ ነው። የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ የወጣ ከደረሰበት ወታደራዊ ሽንፈትና ኪሳራ የተነሳ ነው። አሁንም ቢሆን (ትግራይና ኢትዮጵያ ይፋዊ ውይይት ያካሂዳሉ ሲባል) የሚፍጨረጨረው ያለ የዓለም ማህበረሰብ ቀልብ ለመሳብ እንጅ ከትግራይ ጋር ብገጥም የትግራይ ሰራዊት አሸንፋለሁ ብሎ አይደለም። እንዲህ ያለ ሃሳብ ኢሳይያስ አፈወርቂ በህልሙም አያስበውም። ማሸነፍ ቢችል ኖሮ የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ሰራዊትና ከአማራ ኢንተርሃምዌ ሚኒሻና ታጣቂ ጎን ተሰልፎ ደቡብ ትግራይ ድረስ ዘልቆ በመግባት ሲገድልና ሲዘርፍ የነበረ ቅጥረኛ ሰራዊት ነው። ኢሳይያስ አፈወርቂ አሁን እያደረገው ያለ በማድረግ ለማሳካት የሚያስበው ታድያ ከዚህ ቀደም እንደ መከረው የትግራይ ህዝብ ለማንበርከክ ሳይሆን ይልቁንም ሊያደርገው በሚፈልገው ትንኮሳዎች ትግራይ የጦርነት ቀጠና ሆና እንድትቆይ በማድረግ የትግራይ ህዝብ ትግል ለማዳከም ታስቦ ተግባራዊ የተደረገ የምግብና የመድሃኒት አቅርቦት ክልከላ/ከበባው ለማስቀጠልና የትግራይ ሰለም በቀጣይነት ለማወክ ነው። የትግራይ ሰራዊትም ለዚህ ዓይነቱ ትንኮሳ ፍቱን መድሃኒት እንዳለው አምናለሁ። የአማራ ልሒቃን እንደሆኑ፥ አበው ሲተርቱ፥ ጥንቸል ዘላ ዘላ ተመልሳ ከመሬት! እንዲሉ ሰዎቹ አንገራግረው አንገራግረው ሲደክማቸው አይደለም ኢሳይያስ አፈወርቂን እርስ በርሳቸውም ተረሳስተውና ተፋተው ልካቸውን አውቀው አርፈው የሚቀመጡበት ጊዜ ሩቅ አይደለም በደጅም ነው።

By aiga