የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድርጅታችን ህ.ወ.ሓ.ት ህጋዊ ሰውነት የመመለስ ጥያቄ ኣስመልክቶ በሰጠው ውሳኔ ላይ ከህ.ወ.ሓ.ት የተሰጠ መግለጫ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጥር-10-2013 ዓ/ም ያስተላለፈውን ውሳኔ ዳግም በማጤን የህወሓት ህጋዊ ሰውነት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ፣ የድርጅታችን ሓላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንዲችሉ እና የድርጅቱ የተወረሱ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንዲመለሱ ጥያቄ ማቅረባችን ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 04-2015ዓ/ም ከህወሓት የቀረበለትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ውሳኔ ማስተላለፉ በኤለክትሮኒክስ ሚድያ የተገለፀ ቢሆንም የተወሰነው ውሳኔ ለድርጅታችን የተሰጠበት ቀን ግን ግንቦት 07-2015 ዓ/ም ነው፡፡ በዚህ መሰረት በቦርዱ የተሰጠው ውሳኔ ቅቡልነት የሌለው፣ በፕሪቶርያ የተደረሰው ስምምነትና ህግን መሰረት ያላደረገ መሆኑ ተገንዝበናል።

ድርጅታችን ህ.ወ.ሓ.ት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የቆየውን አፋኝ ስርዓት በመገርሰስ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣ በማንነታቸው እንዲኮሩና ታሪካቸው እንዲያሳድጉ የሚያስችል ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና እንዲረጋገጥ በማድረግ በኩል ደማቅ ኣሻራ ያለው ኣንጋፋ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ ፣ዲሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ መንገድ መፈታት ባለመቻሉ በ2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ደም አፋሳሽ ግጭት ተፈጥሮ እስከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ወራቶች ድረስ ዘልቋል። ይህን ደም አፋሳሽ እልቂት በተቻለ መልኩ ለማስቆም የተለያዩ ጥረቶችን ሲደረግ ቆይቶ በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድ እና በአሜሪካን መንግስት አሸማጋይነት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካና በኬንያ መንግስታት አመቻችነት ከፌደራል መንግስቱ ጋር ድርድር ተደርጎ በሕዳር 23-2022 በፕሪቶሪያ ከተማ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊፈረም ችሏል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት በመሰረታዊነት ማዕከል ያደረገው ሰላም፣ ሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ ተጠያቂነት እና ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት መመለስ ነው። ከስምምነቱ መፈረም ጀምሮም ህ.ወ.ሓ.ትና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት በጋራና በተናጠል የገቡትን ግዴታና የስምምነቱን ዓላማዎች እየፈፀሙ ይገኛሉ። ለዚህም አበረታች የሚባል ውጤትና ለቀጣይ ስራዎች ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ እየተፈጠረ በመምጣቱ ስምምነቱ ዓለም አቀፍዊ እና አገራዊ እውቅና ተሰጥቶታል። የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ፣ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተለያዩ አገራት መንግስታት እውቅና እና ድጋፋቸውን ሰጥተውታል። በሌላ በኩል የፌደራሉ መንግስት ህግ አውጪ አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር-ቤት፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ኣቃቢ ሕግ፣ የክልል መንግስታት እና የከተማ አስተዳደሮች ለስምምነቱ እውቅናና ድጋፍ የሰጡ ህገ-መንግስታዊ አካላት ናቸው።

በዚህ መሰረትም የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ድርጅታችን ከአሸባሪነት ስያሜ የመሰረዝ ውሳኔ አስተላልፏል። ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ ኣስተዳደር እንዲመሰረት በፕሪቶርያው ስምምነቱ አንቀፅ 10(1) በተገደነገገው መሰረት የትግራይ ኣካታች ጊዜያዊ ኣስተዳደር በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ተመስርቷል። የፕሪቶሪያው ስምምነት ዓላማ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ክልሉን እና የክልሉን ህዝብ ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ መመለስ ነው።

በዚህም መሰረት የስምምነቱ ይዘት ተፈፃሚ እንዲሆን የትግራይ ህዝብና ድርጅታችን ህወሓት እንዲሁም ሃላፊነት ያላቸው የፌደራል መንግስት አካላት ግዴታቸውን ሊወጡ የሚገባ ቢሆንም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን የድርጅታችን ህጋዊ ሰውነት የመሰረዝ ውሳኔ እንዲነሳ ያቀረብንለትን ጥያቄ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የተሰረዘ የፖለቲካ ፓርቲ ተመልሶ ህጋዊ ሰውነት የሚያገኝበት ድንጋጌ ስለሌለ የድርጅታችን ህጋዊ ሰውነት ሊመለስ እንደማይቻል ከፕሪቶርያ ስምምነት ውጪ በሆነ መንገድ ውሳኔው አሳውቆናል።

ከዚህ በመነሳት በቦርዱ የተላለለፈውን ውሳኔ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የማይቀበል፣ እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ያለውን የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ ከጦርነቱ ወደ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ለሚገቡ ሃይሎች መደገፍ እና ማበረታታት ሲገባ ድርጅቶችን በማፍረስ ቀጣይ ሰላም እንዳይረጋገጥ የሚያደርግ መሆኑ፣ ለህዝቦቻችን የማይመች እና ለሌሎች ሃይሎችም ተስፋ የማይሰጥ ነው ብሎ ድርጅታችን ህወሓት ያምናል።

በአጠቃላይ ድርጅታችን ህወሓት ውሳኔው እንደማይቀበለው እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይበት እያሳወቀ የምርጫ ቦርድ ውሳኔውን እንደገና በማጤን የፕሪቶርያ ስምምነትና ሌሎች የፌደራል ተቋማት ያስተላለፉትን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ እንዲያስተካክል ይጠይቃል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ባለቤት የሆናችሁ መላው የድርጅታችን ኣባላት፣ የትግራይ ህዝብና ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህንን ውሳኔ የሰላም ሂደቱ ኣደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑ በመገንዘብ የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ድርጅታችን ህ.ወ.ሓ.ት ጥሪውን ያቀርብላችኋል። የፌደራል መንግስትም ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ በተጀመሩት አወንታዊ የሰላም እና የመደጋገፍ ጥረቶች ላይ ሊያሳድረው የሚችል አላስፈላጊ ጫና እንዲሁም የፌደራል መንግስቱ ህጋዊ ውሳኔዎችንና ስምምነቶች በሁሉም የመንግስት ተቋማት እና አካላት እንዲከበሩ የማድረግ ሀላፊቱን ግምት ውስጥ በማስገባት የቦርዱን ውሳኔ እንደገና ታይቶ ከህ.ወ.ሓ.ት ህጋዊ ሰውነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ያሉትን ህጋዊና ፖለቲካዊ አማራጮች ተጠቅሞ በቅድመ-ጦርነት ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ በሚያደርግ ቀና አካሄድ እንዲፈቱ፣ የፕሪቶርያ ስምምነት በተሟላ መንገድ ተግባራዊ እንዲደረግ እና የተጀመረውን የሰላም ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በተጨማሪም የፕሪቶርያ ስምምነት እንዲሳካ ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ የነበራችሁ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በአጠቃላይ የአፍሪካ ህብረት ደግሞ በተለይ ሂደቱ የሚያደናቅፍ እና አደጋ ውስጥ የሚከት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ተቃኝቶ እንዲስተካከል የድርሻችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን።

ዘልኣለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማእታት!

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ

ግንቦት 08፣ 2015ዓ/ም

መቐለ

By aiga