በ ሙሉቀን ወልዴ
አብይ አህመድ የመሰለ አፉን ከፍቶ የሚያላግጥ መሪ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምናልባትም የመጀመሪያው ሰው ሳይሆን አይቀርም፡፡ አብይ በየጊዜው የሚሰጣቸው ትንተናዎችና ንግግሮች ተከታትያለሁ፤ መሰረታቸው ግልብ ከመሆናቸው በላይ እራስ በራሱ የሚጋጭ፤ በውሸት ላይ የተደረቱ ናቸው፡፡ በተለያየ ወቅት ያደረጋቸው ንግግሮቹ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያው ለአንዳንድ ፍጆታ እዚህም እዛ በጥቂቱ እየተተቹ እየዋሉ መልሰውም ሲረሱ ይኸውና አሁን ላይ ደርሰናል፡፡ ታዲያ ሰሞኑን የሆነው ግን እንደዋዛ ሊታለፍ አልተቻለም፡፡ በሱ አስተሳሰብ እንደለመደው ንፍጡን ዘርግፎ ከሄደ በኋላ የተከተለው በአይነቱ በተለይም የኮሎኔል መንግስቱ የመንግስትነት የመጨረሻ ምእራፍ ላይ የሆነውን ጋር ሳስተያየው የገጠመ ይመስላል፡፡ ኮሎኔሉ ምናልባትም ከሀገር ሊኮበልሉ አእምሮአቸው በተወጠረበት ወቅት ላይ ያካሄዱት ብሄራዊ ሸንጎ ሰብሰባ ላይ አንድ የሸንጎ አባል “እርስዎ እዚቸው ወንበርዎ እንደቋንጣ ደርቀው ይቀራሉ እንጂ የትም አይሄድዋትም” ብሎ ያደረገው የድፍረት ንግግር በቀጥታ በቴሌቪዥን ለህዝብ በመተላለፉ መሪውን የተዳፈረ ካባ ደርበንለት እጃችን አፋችን ላይ ጭነን ጉድ ማለታችን አስታውሳለሁ፡፡ ተናጋሪው እንደቋንጣ ደርቀው ይቀራሉ ያለውን ምኞቱን ባይሰምርለትም መሪውን የተገዳደረ ንግግር በማድረጉ ምናልባትም በኢትዮጵያ በመሪና በተመሪ ግንኙነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ይኖረዋል፡፡ ኮሎኔሉ በዛች የተረገመች ቀን (በሳቸው አስተሳሰብ) የደረሰባቸውን ድፍረት ሲታሰብ መንበራቸውንና ክብራቸውን ያሰደነገጠና በድፍረቱም ወደር የማይገኝለት ክስተት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
አሁን አብይ የገጠመውም በይዘቱ ለየት ያለ ቢሆንም ተመሳሳይነት አለው፡፡ አብይ ጋዜጠኞችን ሰብስቦ በወቅታዊ ጉዳዮች መግለጫ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ይህ የሚያደርግበት በሁለት ምክንያት እንደሆነ ይገመታል፡፡ የመጀመሪያው በጋዜጠኖች ፊት ቆሞ ሙግት ለማድረግ ወኔ ስለሌለው ሲሆን ሁለተኛውና ዋነኛው ደግሞ በምእራባዊያን ዘንድ አምባገነን መስሎ ላለመታየት በመፈለጉ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ትንሽ ላፍታታው፡፡ ምንም እንኳን የዲሞክራሲ እንጥፍጣፊ ባይኖርበትም ጥቂት የተቃዋሚ አባላት በካቢኔው ውስጥ በመሰብሰቡ አብይ ራሱን እንደዲሞክራሲ አባት አድርጎ ይቆጥራል፡፡ በዲሞክራሲው አለም ሚዲያ ትልቅ ስፍራ የተሰጠው ስለሆነ መሪዎች በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም በየወቅቱ ሃሳባቸውን በሚዲያ ያቀርባሉ፤ በጋዜጠኞችም ፖሊሲያቸው ይሞገታል፤ ስነ ምግባራቸውም ይበጠለጠላል፡፡ ታዲያ የአብይ ፍራቻ ይህ ነው፡፡ አብይ ጋዜጠኖች የመጥራት ችግር ላይኖርበት ይችላል ከጠራ ደግሞ ሆድ አደሮቹ ኢቲቪ፤ ፋናና ዋልታ ብቻ አይሆኑም የግድ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሀገር በቀልና የውጭ ሚዲያ ተወካዮች ያለልዩነት መጥራት ሊኖርበት ነው፡፡ ታዲያ ምእራባዊያን ጥርስ ላለመግባት ሲል በደፈናው ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይሰጥ ከአመት ወደ አመት እየተቆጠሩ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ አብይ መልእክቱን የሚያደርስበት አንድ መላ ግን አለው፡፡ ገንዘብ በሚሰፍርላቸውና በሸምቆቆ በሚቆጣጠራቸው የካቢኔ አባላት፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፤ የብልጽግና ካድሬዎችና ወጣቶች፤ የሀገሪቱ ፓርላማ፤ የሀገሪቱ ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ መኮንኖች፤ በመናፈሻ ምርቃት ከይዘትም ሆነ ከጥራት ጋር የተፋታ ንግግር ያደርጋል፤ መልእክቱንም ያስተላልፋል፡፡ እነኚህ የህብረተሰብ አካላት ሲሰበስብ አእምሮውን የቻለውን ዘርግፎ መሄድ እንጂ ከተሰብሳቢ የሚቀርብ አስተያየት ባለመኖሩ ይህ ድርጊት ሰብከት ከመሆኑ ውጭ ሌላ ስም የሚሰጠው አይመስለኝም፡፡ በስብከቱም በርካታ ስብራት እያደረሰ፤ መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ እያደረገ መንግስትነቱም ሳይፀና አምስት አመታት ነጉደዋል፡፡
አብይ እንደበቀቀን እንዳሻው ብቅ እያለ ያለከልካይ ይናገር እንጂ በተናገረው ልክና አንዳንዴም ከጳጳሱ ቄሱ እንዲሉ ሦስት ክንደ አስበልጠው ሲቆማምሩ የነበሩ እዚህ ላይ ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተለይም ዛሬ ሞጋችና ክስ አቅራቢው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሽገው የሱን ልብ ለማሞቅ ብዙ ሲታትሩ የነበሩ ግለሰቦች መኖራቸው አይካድም፡፡ አሁንም ድረስ አቅላቸው እስኪስቱ ድረስ ስሙ መነሳት የለበትም ባዮች መኖራቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እንዳውም በእነዚህ ሃይሎች ባይደገፍ ኖሮ ዛሬ አብይ ታሪክ ሆኖ ሀገሪቱም ሰላም አግኝታ እፎይ ትል ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ የአርምሞ ጊዜው ማብቃቱን ማብሰሪያ የብርሃን ወጋገን ምልክት አሁን ተከስቷል፡፡ ይህ ግን ያለ መስዋእትነት አልተገኝም፡፡ ግንባር ቀደም ምስጋና የሚቸረው ለብጹእ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ ይሆናል፡፡ በዚያ የጨለማ ጊዜ በግለሰብ ደረጃ በድፍረት ወጥተው የአብይን እርቃን ያስቀረ ንግግር ያደረጉት እሳቸው ሲሆኑ፤ ተቀውሞአቸው ወደ ህዝብ እንዳይደረስ በማፈን በዙሪያቸው የከበቡ የአሁኑ አንበሶች በብጹእ አባታችን ያደረሱባቸው እንግልትና ማዋከብ መቼም ቢሆን ሳይረሳ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በተቀናጀና በድርጅት መልክ ይህ አብይ የመዝርጠጥ ሙከራ መደረጉ የተቃውሞ ምእራፉ አንድ ደረጃ ክፍታ መጨመሩ ያሳየናል፡፡
ታዲያ ምን ያደረጋል በቤተክርስቲያኒቱ ለተሰጠው ትችት እፍረት ሳይሰማው ጲላጦሳዊ መልስ ሰጠ “እኔ የፈጠርኩት አይደለም ለዘበናት የቆየ ችግር ነው” ብሎ አላክኮ አረፈው፡፡ ከአንድ ሚልዮን ህዝብ በላይ የረገፈበት የሰሜኑ ጦርነት፤ በከበባ ምክንያት፤ በምግብና በመድሃኒት እጦት በየእለቱ እየረገፈ ያለ በርካታ ህዝብ፤ ከአንዱ ስፈር ወደ ሌላኛው ለመንቀሳቀስ በፍርሃትና በስጋት ያለ ህዝብ፤ የውጭ ጠላት ሀገር ጦር በመጋበዝ፤ በመመሳጠርና በጋራ በማቀድ የራሴን ህዝብ በምትለው ህዝብ ላይ መአትና መከራ ማድረስ፤ በተዳከመው ኢኮኖሚ መብላት መጠጣት የተሳነው የት የሌለ ህዝብ ወዘተ…አብይ በሚያካሂደው እኩያዊ መንገድ የተፈጠረ ለመሆኑ አሁን ካለው ትውልድ በላይ ማን ሊናገርና ሊመሰክር ይችላል? መቸስ ”አቶ አይታክቱ“ ማቆም ካልተቻለ ወደፊት በርካታ ለማመን የሚከብድ የፈጠጤ ንግግር ሳያሰማን አይቀርም፡፡ ፈጣሪ ለዚች አገር አንድ መልካም ውለታ እንዲውልላት ሁላችንም አንድ ላይ የምንፀለይ ከሆነ የዚህ ክፉና አውሬ ሰው ገለል ማለት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
አብይ በስልጣን ዘመኑ ስንቱን ከስንቱ እያተራመሰ ይኸውና ቅንደቡንና ቀንዱን የሚነካካ ምእራፍ ላይ ደርሷል፡፡ አብይ እንደለመደው ካቢኔውን ሰብስቦ አፉ በማላቀቁ ልዩ የሆነ መዘዝ ብቅ ብሎበታል፡፡ ከዚህ በፊት በቀበጣጠረው ልክ የሚመጥን የመልስ ምት ባለመኖሩ የለመደች ጦጣ ሸምጥጣ ሸምጥጣ …… እንዲሉ አሁንም ቀበጣጥሮ ለማለፍ ነበር እሳቤው፡፡ የአሁኑ ግን ሌላ ነው፡፡ በቅብጠራው አብይ በቤተክርስቲያን ላይ ስላጋጠመ ሁኔታ ብዙ አብራርቷል፤ የሱ ግምትና ውሳኔም አስቀምጧል፡፡ እኔ እሱ ስለተናገረውም ሆነ ስለተከሰተው ጉዳይ እዚሁ በዝርዝር ማስቀመጥ አልፈልግም፡፡ ማተኮር የምፈልገው ይህ አይነቱ ድፍረት የተሞላበት ንቅናቄ በስርአትና በጥንቃቄ ከተመራ ለሀገር ፍይዳው ከፍተኛ መሆኑን በሌላ አከባቢ ከተደረጉ መሰል ንቅናቄዎች የምንማረውን ለማመላከት ነው፡፡ በመሆኑም ወደፊት የሚደረጉ ንቅናቄዎች በውጤማነት እንዲታጀቡ ቀጥሎ የተመለከቱትን ነጥቦች ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡
- የንቅናቄው ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት፦ የንቅናቄው ዝርዝር አላማ፤ መድረስ የሚፈለገው አጠቃላይ ግብና ማስፈጸሚያ ስልት በሚገባ መንደፍ፡፡ ፍኖተ ካርታውንም በንቅናቄው ተሳታፊዎች ዘንድ እንዲታወቁ ብርቱ ጥረት ማድረግ፡፡
- ነቃ ያሉ አስተባባሪዎች መፍጠር፦ አጠቃላይ ንቅናቄውን የሚመሩ ጠንካራ አስተባባሪዎች መመደብ፤ ተተኪ ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶች በብዛት መመልመል ማሰልጠንና ማሰማራት፡፡
- መረጃን በአግባቡ ማደራጀት፦ በየጊዜው የሚከናወኑትን እንቅስቃሴዎች ከግቡና አላማው ጋር እየተገናዘበና እየተናበበ መሄዱን ለመገምገም የሚያስችል ወቅታዊ መረጃ መሰብሰብ፤ ማደራጀትና መተንተን፡፡
- ወቅታዊ መረጃ ፈጣን በሆነ መንገድ ማድረስ፦ ስለንቅናቄው ያልተቋረጠ ትክክለኛ መረጃ በፍጥነት ማስተላለፍ፡፡ አፍራሽ የሆኑ መልእክቶች ተከታትሎ ማክሸፍ፡፡
- በዋና ዋናዎቹ አስተባባሪዎች ሊደርስ የሚችል ጥቃት እንዳይኖር ነቅቶ መጠበቅ፦ ተቃዋሚህ ባለብዙ እጅ መሆኑን መገንዘብና በብዙ መልኩ ጥቃት ሊያደርስ የሚችል መሆኑን ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ባልታሰበና በተቀናጀ መልክ ሊደርስ የሚችል አጋጣሚን ነቅቶ በመጠበቅ ማክሸፍ፡፡
- በጊዜያዊ ድል አለመኩራራት፦ በየደረጃው የሚመዘገቡ ውጤቶች በጥንቃቄ በመያዝ ለወሳኝ ድል የሚኖራቸውን እስተዋጽኦ በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በጥቃቃን ጊዜያዊ ድሎች በመዘናጋት አጠቃላይ ግቡን የሚያውኩ ክስተቶች ሊፈጠሩና ቀሪ ጉዞውን ሊያሰናከሉ ስለሚችሉ አስተባባሪዎች በሚመዘገቡት ጊዜያዊ ድል የሚያስተላልፉአቸው መልእክቶች ይዘት ላይ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡
- የፍትህ ስርአትን መጠቀም፦ የፍትህ ጉዳይ የንቅናቄው አንድ አካል አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም በአብይ ያልታረመ ንግግር ምክንያት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እስካሁን የደረሰው ሰብራትና ወደፊትም ሊደርስ የሚችል ጥፋት በመሰነድ በአብይ ላይ ክስ መመስረት ወደፊትም መሪዎች ከህግ በላይ አለመሆናቸውን ለማስተማር ይጠቅማል፡፡