ይህ አባባል የደደቢት ሚዲያው ዶ/ር ሃይለ ወይም የትግራይ ሚዲያ ሃውሱ ስታሊን ገ/ስላሴ ወይም የርእዮቱ ቴዎድሮስ ፀጋይ ከዚህ በፊት ሲጠቀሙበት ሰምቻሎሁ፡፡ እርግጠኛ ስላልሆንኩኝ ከሶስቱ አንዱ ሳይሆን ቀርቶ እና ሌላ ሰው ይጠቀምበት ከነበረ በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃሎሁ!! አባባሉ እጅግ ስለተስማማኝ፣ በውሰትም ቢሆን መጠቀሙ አይከፋምና እውቅናውን ለሚገባችሁ ሰጥቼ ትንሽ እናውጋ!! ትንሽ ጊዜ ሲኖረኝ ዘርዘር ያለ ትዝብቴን አጋራሎሁኝ!!
ከ14/06/2022 ጀምሬ ለተወሰኑ ቀናት ኑሮ ከተወደደበት ህዝብ መሀል ሁኜ፣ አዲስ አበባን የቻልኩትን ለመቃኘትና ለመታዘብ ሞክሬ ነበር! ከአዲስ አበባ ስበባና ኑሮ ከተወደደበት ህዝቧ ስገናኝ አንድ ዓመት ከሦስት ወራት አከባቢ ሁኖኛል፡፡ የከተማዋን መሬት እንደረገጥኩኝ፣ ኮንትራት ታክሲ ያዝኩኝና፣ ግራ ቀኙን እያማተርኩኝ ጉዞየን ቀጠልኩኝ፡፡ መጀመሪያ ተጋሩ በብዛት አገኝበታሎህ ብየ ወዳሰብኩት 22 አከባቢ ተጓዝኩኝ፡፡ ቦታው ላይ ደርሼ ከታክሲው ስወርድና ሂሳብ ለመክፈል እጄን ወደ ኪሴ እየከተትኩኝ “ሒሳብ ስንት ነው?” ስል አሽከርካሪውን ጠየኩት፡፡ እሱም ወዲያው ተቀብሎ 350ብር አለኝ፡፡ ትንሽ ግራ ተጋብቼ እና ጆሮየን ተጠራጥሬ “ስንት አልከኝ?” የሚል ጥያቄ ደግሜ ወረወርኩኝ፡፡ 350 ሲል እሱም ደግሞ ስለመለሰልኝ፣ ሳላመነታ የተባልኳትን ብር ቆጥሬ ሰጠሁት፡፡
ከዚህችው ተመሳሳይ መነሻ እና መድረሻ ከ120 – 150 ብር ነበር ከዚህ በፊት እከፍል የነበረው፡፡ እንግዲህ በቅፅበትና ሳይታወቀኝ ኑሮ ከተወደደደበት ህዝብ መካከል አንዱ ሁኜ ለጥቂት ቀናት የምቆይባትን ጀልባ ላይ መሳፈሬን ገባኝ!! 22 አከባቢ ሁሌም ደመቅ ያለና በብዛት ተጋሩ የሚገናኙበት ሰፈር ነው፡፡ አሁንም እንደ ከዚህ ቀደሙ በብዛት ባይሆንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተጋሩ አሉ፡፡ ወዲያው ከታክሲ ወርጄ፣ የወንድሜ ልጅ የሆነችው ቆንጆ በምታንቀሳቅሰው ምግብ ቤት እንደገባሁኝ፣ ታላቁ ጓደኛና ወንድም ሙ. ተን ጨምሮ በርካታ ተጋሩ አገኘሁኝ፡፡ እነሱ መኖር ስለተወደደበት የትግራይ ህዝብ ሁኔታ፣ እኔም ኑሮ ስለተወደደበት የአዲስ አበባ ህዝብ ሁኔታ ለማወቅ እየተጠያየቅን ሰፊ ጊዜ ወሰድን፡፡ በየደቂቃው መብሉም መጠጡም በየዓይነቱ ይቀርብ ነበር፡፡

በዚህ መሃከል ታላቁ ወንድሜ፣ ታናሽዋ እህቴ እና ባለቤትዋ ስለተቀላቀሉን፣ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቃቅፈን ናፍቆታችንን ተዋጣን፡፡ ገና ታናሽ እህቴን ሳይ ውስጤ የመረበሽ ስሜት ቢሰማኝም፣ ስሜቴን ዋጥ አድርጌ ከሷና ባለቤቷ ጭዋታችንን ቀጠልን!! ለጊዜው ስለአጠቃላዩ ህዝብ ማውራት አቁመን፣ እነሱ ትግራይ ስላለው እኔም አዲስ አበባ ስላለው ቤተሰብ አንድ በአንድ እያነሳን አወራን፡፡ እስርቤት ገብተውና ተጋሩ በመሆናቸው ስለታጎሩ ወንድሜን ጨምሮ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት አወጋን፡፡ ታናሽዋ እህታችንና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት፣ የታሰሩትን ለማስፈታትና ለመጠየቅ ያሳለፉት ውጣ ውረድ በዝርዝር አዋሩኝ፡፡ ፊታቸው ላይ ሁሉም ዓይነት ስሜት አነበብኩኝ!! የስኳር በሽታ ታማሚ የሆነው ወንድሜ፣ የት እንደታሰረ ሳይታወቅ ቆይቶ ከሳምንት በኃላ ቦታው ቢታወቅም ምግብና መድሃኒት ተከልክሎ እግሩ ቆስሎ አደገኛ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ያሳለፈበት የእስርቤት ቆይታው እንዲሁም ህመሙ ከፊቱ ይታይ ነበር፡፡
ከሁሉም ያገኛሁዋቸው ተጋሩ እና ወንድም እህቴ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ አሁንም ከፍተኛ የደህነነት ሥጋት ውስጥ ስለመሆናቸው ነው፡፡ የከተማዋ የመንግስት ፀጥታ አካላት እንዴት እንደ ኤቲኤም ማሽን እንደተጠቀሙባቸው፣ ምን ያክል ጉዳት እንዳደረሱባቸው፣ አሁንም እንደፈለጉ ሰውን እያሰሩና እያሰቃዩ እንዳሉ በዝርዝር ነገረዉኛል፡፡ በተለይ ተጋሩ ይበዙባቸዋል የተባሉ እንደ 22 ዓይነቱ ሰፈሮች፣ የመንግስት ሀይሎች የሌሊት ዳሰሳ በማካሄድ እንደሚያስሩ፣ እንደሚያንገላቱና ንብረት እንደሚዘርፉ ገልጸውልኛል፡፡ ብዙዎቹ እንደ ምክር ቢጤ ጣል ያደረጉልኝ ነገሮች፣ እዛው አከባቢ አልጋ እንዳልይዝ፣ ለማንም ከትግራይ መምጣቴ እንዳልናገር፣ በርካታ የድህንነት ሰዎች (ኤርትራውያንጨምሮ) በአከባቢው እንዳሉና አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ መግባት እንደሌለብኝ ነበሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእህቴ ባለቤትን ጨምሮ በርካታ ያገኘሁዋቸው ተጋሩ በማንነታቸው ብቻ ከሥራቸው ተሰናብተው እንዳሉ እና ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንዳሉ ተረዳሁኝ፡፡ እነዚህ ስጋቶችና የነሱ ልምዶች ከግምት ውስጥ አስገብቼ ሳስበው፣ መሃል አገር ያሉ
ተጋሩ እንደ ትግራይ ያለው ህዝብ “መኖር እንደተወደደባቸው” ተረዳሁኝ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ተጋሩ እንደ ከተማዋ ነዋሪዎች “ኑሮም ተወዶባቸዋል”!! ኑሮና መኖር የተወደደበት ሁለት ዓይነት ህዝብ በአገሪቷ እንዳለ ባውቅም፣ የከፋው ሆኖ ያገኘሁት ግን ሁለቱም የተወደደባቸው ተጋሩ መኖራቸው ማየቴ ነው!!!!
ጊዜው በመመሸቱና ድካም ቢጤ ስለተሰማኝ ሂሳብ ከፍለን አረፍ ወደ ምልበት ሰፈር ከወንድሜ፣ እህቴ እና ባለቤቷ ጉዞ ጀመርን፡፡ የተከፈለው ሂሳብ ከምታስቡት በላይ እጅግ ብዙ ነበረ!! የዛሬ ዓመት 20 – 50 ብር የነበረው ቢራ እጥፍ መጨመሩ፣ ሽሮና ጥብስም እንዲሁ በእጥፍ ዋጋቸው አድጎ አየሁኝ!! እውነቱም የአዲስ አበባ ህዝብ ኑሮ እንደተወደደበት በተግባር አየሁኝ!!
ወደ እማድርበት ሆቴል ስጓዝ ዓይኔ ቀኝና ግራ እያማተርኩኝ ትዝብቴን ቀጠልኩኝ፡፡ አዲስ አበባ የንግድ እንቅስቃሴዋ እንደተዳከመ የሚያሳዩ ምልክቶች አየሁኝ! እኔ የማውቃት አዲስ አበባ የሰው ትርምስ የበዛባት፣ በየመንገዱ የእለት ጉርሳቸው ለማግኘት ከዚህም ከዚህም የሚሯሯጡባት እና ህይወት ያለባት ከተማ ነበረች፡፡ አሁን ያለችው አዲስ አበባ እጅግ የቀዘቀዘች እና ሂይወት አልባ ነች! ይህ መቀዛቀዝ የገንዘብ ዝውውር እና በልቶ ለማደር የሚደረገው ሩጫ መቀነስ የሚያሳየው ከተማ ውስጥ ከባድ እንደሚያደርገው ግልፅ ነው!! ይህን ከግምት ውስጥ አስገብተህ ስታየው እውነትም በከተማዋ ኑሮ የተወደደበት ህዝብ አለ ያስብላል!!
ሌላው ስጓዝ ያየሁትና ኑሮ የተወደደበት ህዝብ እንዳለ የተገነዘብኩበት አጋጣሚ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት
በየፌርማታው ያየሁት የሰው ሰልፍ ነው!!

By aiga