ከባለአገሩ
1-31-22
ከአብይ አሕመድ ሰፈር በየእለቱ ጉድ የሚያሰኝ ወሬ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከሁሉም በላይ ብዙ ጉድ የሚሰማበት ደግሞ በዲፕሎማሲው መስክ ነው ፡፡ አቶ ስዬ አብርሃ በጉዳይ ላይ ቢጠየቁ ኑሮ የኮማሪት ቤት ዲፕሎማሲ ብለው እጥር ምጥን ያለች መልስ በሰጡን ነበር፡፡ የአብይ አሕመድ ዲፕሎማሲ በነሲብ የሚካሄድ የጨበጣ ዲፕሎማሲ ነው ፡፡ ኢትዮጵያ ከወዳጆችዋ ክፍኛ የተነጠለችበት ዘመን ቢኖር አሁን ነው፡፡ይህ የሆነው አብይ አሕመድ ከእውነታ ጋር ታርቆ መኖር የማይችል ህልመኛ በመሆኑ ነው፡፡መዋቅራዊ ችግር ነው ፡፡ አብይ አሕመድ በብሄራዊ ጥቅምና በራሱ የግል ፍላጎት መካከል ያለውን ልዮነት የመረዳት አቅም የለውም፡፡ ዲፕሎማሲ የሰው አካላትን በመደባበስ የሚሰራ ይመስለዋል ፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወሬ የጠፋበትን ምክንያት ጥቅማችንን ተላልፎ ስለተሰጠ ነው፡፡ ኤርትራም የሰፈሩ ጎሮምሳ አድርጎታል፡፡
ሰሞኑን ከወደ ጄኔቭ የተሰማው ወሬ አለምን ጉድ በማሰኘት የሚስተካካለው የሚገኝ አይመስልም፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ በአለም አቀፍ የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ድጋሚ እንዲመረጡ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት በእጩነት ያቀረቧቸው ሲሆኑ ያለተወዳዳሪ በብቸኝነት አልፈዋል፡፡ የዶ/ር ቴድሮስ ዳግም መመረጥ በአብይ አሕመድ ሰፈር ትልቅ ንዴት ፈጥሯል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት ድርጅት በትግራይ እና በየመን ስለሚደርሱ ሰብዓዊ ቀውሶች በእኩል የሚያስተናግድ ሲሆን፤ በዘረኝነት ሕመም የሚሰቃየው የኢትዮጵያ መንግስት ዶ/ር ቴድሮስን በሚያይበት መነፅር ዓለም እንዲያይለት በመፈለጉ ለትልቅ ውርደትተዳርጓል፡፡በዚሁ የአብይ ተግባርም ያላፈረ አፍሪካዊ ዲፕሎማት የለም፡፡ ድርጊቱ የአፍሪካን ቅስም የሰበረ አንገት ያስደፋ ነበር፡ ፡ጨዋነትና ይታዘቡናል የሚል ነገር ጠፍቷል ፡፡
አብይ አህመድ ለዶ/ር ቴዎድሮስ ጥላቻ ያለው ቢሆንም እስከዚህ ድረስ ወርዶ አዋራጅ ተግባር መፈፀሙ አሳፋሪ ነው ፡፡ ቤተ መንግስቱ የበለውና የቁረጠው መንደር ከሆነ ሰነባብቷል ፡፡ለዚሁም ከውጭ ዘረኛችን መልምሎ ጥሮቶኞችም ደጋግፎ አሰማርተዋል፡፡ ዘረኝነት ዋንጫው ሞልቶ በፈሰሰበት አገር ይህ ሁኔታ የሚጠበቅ ነው ፡፡ በአገር ቤት በትግራይ ተወላጆች ላይ የፈለጉትን ሲያደርጉ የተጠየቃቸው ስለሌለ ድንበር ተሻግረው ህሱም ምግባራቸውን መደበቅ አልቻሉም ፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ ዘረኝነትን የሚዋጋ አፍሪካዊ ነው ፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ በአለም ዙሪያ በየቤቱ ስሙ የሚጠራ የአፍሪካ ኩራት ነው ፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ ትጉህ የአለም ዜጋ ነው ፡፡ አብይ ይህን ሊገነዘብ የሚችል እውቀት የለውም፡፡ በዶ/ር ቴድሮስ ደረጃ ቅቡልነት ያለውን ሰው ባትወደውም እንዳላየህ ሆነህ ማለፍ ይቻል ነበር ፡፡ በዚህ ተግባር የተዘፈነለት ፓን አፍሪካኒዝምም ቢሆን ውሃ በልቶታል ፡፡
የጥሞና ግዜ ለራሳችን
አሁን ሁሉም ዜጋ የራሱ የጥሞና ግዜ ያስፈልገዋል፡፡ አብይ የሚለፍፈው የጥሞና ግዜ ማጭበርበሪያ ስለሆነ የሚፈለግ አይደለም፡፡ ሰውን በረሃብ እየቀጣ፤ በቦንብ እየደበደበ የጥሞና ግዜ ሰጥቻለሁ ማለቱ ሃሳዊ መሲህ መሆኑን የሚያመለክት ነው ፡፡ ሁላችንም ቆም ብለን የምናስብበት የጥሞና ግዜ አስፈልጎናል ፡፡ ያለንበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ስለሆነ ቆም ብለን መመርመር ያለብን ይመስለኛል ፡፡ ጉድ ሳይሰራን፡፡
ማሰብ ስንጀምር ከጦርነቱ መጀመር አለብን፡፡ አገራችን እቶን ላይ የተጣደች አገር ሆናለች ፡፡ አንዳንዶቻችን ትግራይ ስትወረርና ስትፈርስ እንዳሻቸው ያድርጓቸው ብለን ሊሆን ይችላል ፡፡ የተረሳው ትልቁ ጉዳይ ግን የኢትዮጵያ ሰላም አንድና ውሁድ መሆኑን ነው ፡፡ ትግራይ ላይ ጦርነት ሲካሄድ አማራ ክልል አፋር ኦሮምያ የሰላም ደሴት ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ ገራገርነት ነው ፡፡ የአንዱ ሰላም ለሌላው ዋስትና ሲሆን የአንዱ መደፍረስ ደግሞ ለሌላው ጠንቅ ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ሰላም የሚነጣጠል አይደለም፡፡ ሰላምና ጦርነትን በከፊል ማየት አይቻልም፡፡ ቀድሞ ነገር በሰላም ማለቅ የነበረበት ችግር በቀላሉ በዋዛ ወደ ጦርነት መገባቱ አሳዛኝ ነው ፡፡ የባእድን ጦር በመጋበዝ ክህደት መፈፀሙ ሌላው አሳሳቢና የማይሽር ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ትግራይን እንደ ባእድ በመቁጠር የተፈፀመው ወንጀል ሁሉንም ወገን አንገት የሚያስደፋ የማይሽር ቁስል ነው፡፡ ስለዚህ እኛም የጥሞና ግዜ ያስፈልገናል ፡፡
ለራሳችን በምንሰጠው የጥሞና ግዜ የአብይን ጥሪ ተቀብለው አገር ቤት የገቡት ዳያስፖራዎች ስለጦርነቱ ስላላቸው አመለካከት መገንዘብ ያስፈልጋል ፡፡ እነዚህ ወገኖች የተሻለ ህይወት ፍለጋ የተሰደዱ ሲሆኑ በአገር ቤት የሚኖረው ወገናቸው በጦርነት እሳት መንደዱ የሚያሳስባቸው አልሆነም፡፡ ጦርነቱ ለእነሱ እንደ እግር ዃስ ዜና ነው ፡፡ የሚያዝና ዜና፡፡ የእነሱ ጦርነት ናፋቂነት በሚድያ ያገኘው ሽፋንም ሌላው ገራሚ ነገር ነው፡፡ ጦርነት ይቀጥልልን ማለታቸው አስገራሚ ነው ፡፡ ለዚህ ነው ለራሳችን በሰጠነው የጥሞና ግዜ ስለነሱም ማሰብ ያለብን፡፡ ዳያስፖራዎቹ ማህበረሰቡን የሚወክሉ አይደሉም ፡፡
በራሳችን ውሳኔ ለራሳችን በሰጠነው የጥሞና ግዜ ስለ ዳንኤል ክብረት፤ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ፤እና ስለ ሌሎች የዘረኝነት መልእክቶች እንድናስብ እንገደዳለን፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ካለበት ስደት ሆኖ ሰብአዊ እርዳታ ትግራይ እንዳይገባ ሲከለከል የትግራይ ህዝብ እጅ ነስቶ እንደ ነጻ አውጪ መንግስትን ይቀበላል ብሎ የፃፈውን ሳነብ ይህ ሰውየ ማን ነው? ለምን እንዲህ አለ? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድዳል፡፡ የመኢሶን አባል ፤የደርግ የመምህራን ማህበር ሊቀመንበር፤ የኢሰፓ አባል የነበረ ሰው ነው ፡፡ ኢሰፓ የነበረ ሰው ስለ ትግራይ ምን ሊያስብ ይችላል? ቀይ ሽብርን ታሪካዊ ግዳጅ ብሎ ተቀብሎ የሚያምን ሰው በስተእርጅና ይህን ቢል አይገርምም፡፡
ዳንኤል ክብረትን የመሰለ ዘረኛ መግለፅ የሚዳግት ባይሆንም በዓሉ ግርማ በሕይወት ቢኖር ኖሮ እንዴት ይገልፅልን ነበር ብዬ ራሴን ስጠይቅ ሁለተኛ ኦሮማይ ይፅፍልን ነበር ብየ ዘወትር እጠይቃለሁ፡፡ ፡ በዓሉ ግርማ ኦሮማይ በተባለው መፅሓፉ የደርግ ሰዎችን ባህርይ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ፀጋዬ ሃይለማሪያምን ፤ፊያሜታ ጊላይ፤ ስሱሎቭ ፤ ወዘተ እያለ የባለ ስልጣንነትን ገፀ ባህርይት ይተርክልናል ፡፡ በዓሉ እንዴት ሊገልፅ ይችላል ብዬ ሳስብ ዳንኤልን የሰይጣን ቁራጭ የሚመስል ፤ሲናገር እንደ ተናካሽ እባብ ጭንቅላቱን የሚነቀንቅ፤ የቁመቱን ማጠር አይቶ ወፍራም ድምፅ የሰጠው የሚጮሁ ቃላት በመልቀቅ የሚዘብት ፤ የቋንቋው ፍላፃ የሰው ህሊና ለመስበር የሚተኮስ ፤ እውቀቱ ተረት ተረት ፤ መርዝ ረጪ አንደበቱ ለመሸፈን ሙሓዘ ጥበባት የሚል ሽፋን የተሰጠው መኆኑን ፤ አርቆ እንዳያይ ቁመቱ የበደለው ከጥፋት ዘመን በፊት የነበረ ደብተራ መሳይ በማለት ሰይጣን ያዳቆነው ብሎ በገለፀልን ነበር ፡፡ በዓሉ በሕይወት የለምና ብዕሩን ተከትለን በዚህ ደረጃ ከሞከርን ገላጭ ነው ፡፡ ዳንኤል ለወያኔ ያለው ጥላቻ ዘርዓ ያዕቆብ ለደቂቀ እስጢፋኖስ ከነበረው ጥላቻ ጋር ይመጣጠናል፡፡ ዘርዓ ያዕቆብ ጨካኝ ነበር ፡፡አንተ ሰው ነህ እጅ የምንነሳው ለአምላካችን ብቻ ነው ስላሉ ደቂቀ እስጢፋኖሶችን በሰው ልጅ ላይ ሊፈፀም የማይችል በደል በእነሱ ላይ ፈፀመ፡፡ ለነገሩ አብይ ጭካኔን ለመማር ጀርመን ወይም ከጃፓን መሄድ ሳያስፈልግ ራሱ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፈፀመው ግፍ መማር እንደማይቻል በመጥቀስ ሌሎች ተቃዋሚዎችንም በተመሳሳይ ጭካኔ ለመድገም ያለው ዝግጁነት ሲገልፅ ተሰምቷል፡፡ ዳንኤል ትግራይን ሲያነሳ ይደንግጣል ፡፡ይፈራል፡፡ ይንቀጠቀጣል ፡፡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ ያማትባል ፡፡ ትግራይን ለመጨረስ በየከተማው አንድ አንድ ቦንብ መወርወር ይበቃል ብሎ የተናገረው ከድፍረት አይደለም ፡፡ ትግራይን እንዳናስታውስ እንፍጃቸው ሲልም ተደምጧዋል ፡፡ ይህ ሰውዬ ታማሚ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ችግሩ ያለው ግን ይህን እድል ከፈጠረለት ሰው ነው ፡፡ ስለዚህ እነዚህንና ጅብ በልተህ ተቀደስ ከሚሉት ጋር አንድ ነን እንዴት ይባላል? የጥሞና ግዜ የሚያስፍልገው ይህን እንድናስብ ነው ፡፡
በሬ ካራጁ ይውላል ፤
የትግራይ ህዝብ ከአብይ ጋር ያለው ግንኙነት በሬ ካራጁ ይውላል በሚል ሊገለፅ ይችላል፡፡ ሲጀመር ጦርነቱ ትግራይን ማደህየት ነው፡፡ ጄኔራል ማእርግ የተሰጠው አበባው ትግራይ ሙሉ በሙሉ ማውደሙን በድፍረት ሳያፍር በሚድያ ሲናገር ተደምጧል፡፡ ትግራይን የወረሩ ጠላቶች የገበሬውን እህል፤ እንስሳት ዘርፈዋል፤ አፍርሰዋል ፡፡ ከተሜውን ባንክ ዘግተውበታል ፡፡ትግራይን ማንበርከክ የሚቻለው በማስራብ ነው ብለው መክረዋል ፡፡ የማስራብ ፖለቲካ ለትግራይ ህዝብ የጥሞና ግዜ ሲሉት ተሰምቷል ፡፡ የትግራይ ህዝብ በዚህ አጋጣሚ የራሱ የጥሞና ግዜ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር እንዴት አብሮ መኖር ይቻላል ብሎ ማጤን ግድ ይላል፡፡ ስለነፃነትም ማሰብ በዚህ ዘመን መብት ነው ፡፡ መብት የበላይነት ያገኘበት ዘመን ነው ፡፡ የትግራይ ህዝብ አብይ አህመድን የመውደድ ግዴታ የለበትም ፡፡ የራሱን ነፃ ውሳኔ ማድረግ አለበት ፡፡ ዲሞክራሲ ነው ፡፡ ሌሎች ስለትግራይ ህዝብ ነፃ አስተሳሰብ ከመቅናት ይልቅ ነፃነትን መምረጥ አለባቸው ፡፡ ረፍዷል ፡፡
ጦሩነቱ ተጀምረዋል ፡፡አብይ በስልጣን እስከቆየ ድረስ ይቀጥላል፡፡ይህን ስናውቅ ለመፍትሄም በጋራ እንድንሰራ ግድ ይለናል፡፡ አንድ ንቅል በርበሬ መንቀል አቅቶን በዚህ ደረጃ ራሳችን ለማዋረድ መፍቀድ የለብንም፡፡ ሁሉም ወገን ማሰብ አለበት ፡፡