ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

ማሳሰቢያ፥ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “የትግራይ ህዝብ” የሚለው አገላለጽ አሁን በዚህ ሰዓት ትግራይ ውስጥ በጨለማ የሚገኝ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራትና መንግስታት ጋር ግንባር በመፍጠር በላዩ ላይ እልቂትና ጥፋት ያወጀችበት፣ በቀጥታ የመዓቱ ገፈት ቀማሽ የሆነውን  ህዝብ ብቻ ይመለከታል። 

የጽሑፉ ዓላማ፥ የትግራይ ሰራዊት ባለቤት ፈጣሪው የትግራይ ህዝብ እንደ መሆኑ መጠን ዓላማውና ተልዕኮው በተመለከተ ለህዝብ በግልጽ መገለጽ፣ መቀመጥና መታወቅ ስለሚገባው፤ በተመሳሳይ፥ ትግራዋይ “ይህን ያህል ገደልን ይህን ያህል ማረክን” በሚል ጊዜያዊ ዜና ሳይወሰድና ሳይደናገር፥ ገድለንና ማርከን ምን አመጣን? ትግራይ ዛሬም ድረስ ከበባ ውስጥ የምትገኝበት ምክንያት ምንድ ነው? የጠላቶቻችን ጥንካሬ ወይስ እኛ የማናውቀው፣ ለእኛ የማነገርና ያልተነገረን የተወሰወረን ምክንያት አለ? የሚል ሞጋች ጥያቄ አንስቶ ትግራዋይ ራሱን እንዲጠይቅና ምክንያታዊ በመሆንም ለመፍትሔ እንዲቆም አልሞ የተዘጋጀ አጭር ጽሑፍ ነው።

መደንደርደሪያ፥ ያለው ሰው ምን ጊዜም ቢሆን አለው! ባንኮች አይደለም ለአንድና ለሁለት ለአስርና ለሃያ ዓመታት በናስ ብረት ቢቆለፉ የውሃ ሮቶ መሬት ስር ቆፍሮ ቀብሮ ያከማቸውን ሀብት እያወጣ መብላትና መጠጣት የሚል ሰው በዚህ ሰዓትም ቢሆን ይኖራል። የወሃ ሮቶ መሬት ስር ቆፍሮ ገንዘብ ሊቀብር ቀርቶ የሚቆፈር መሬት የሌለው ድሃ ታድያ በዚህ ሰዓት በተቀመጠበት እንዲሁ እንደ ቅጠል እየወደቀ ይረግፋል እንጅ ይህን የርሃብና የእጦት ክፉ ጊዜ የመሻገር ዕድል አይኖሮውም። በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ከምግብና ከመድሃኒት እጦት የተነሳ በሽታና ርሃብ የገደለው ትግራዋይ ቁጥሩ ምን ያህል እንደሆነ ፈጣሪ ብቻ ነው ሊያወቀው የሚችል። ምናልባትም የዚህ ዓይነቱ ሪፖርት ከትግራይ የፖለቲካ አመራር ትክክለኛ ቁጥር ልንሰማና የምንችለው ድርጊቱ ለፖለቲካ ዓላማቸው ይጠቅመናል ብለው ያመኑ እንደሆነ ብቻ ይሆናል፤ በተረፈ ግን፥ ርሃብና በሽታ የገደለው ትግራዋይ ብዛት እንዲሁ ስጋው ብቻ ሳይሆን ስመ ዝክሩም አፈር አንደበላው ይቀራል። ጎብዝ፥ ደርሶ መለመስ ጀብድና ድል ሆኖ እንደ ሰበር ዜና ሲነግርህ እየሰማህ የምትጨፍርና ደስታህን የምትገልጽ ከሆነ እያደረገከው ያለኸው ባይገባህ ነው እንጅ በገዛ ራስህ ህዝብና አገር እየቆመርክ ነው። ቁማር ሲባልም የሚያበላ (የሚጠቅምህና የሚረባህ) ሳይሆን የሚያስበላ (እንደ ህዝብ የሚያከስምህና የሚያጠፋህ) ቁማር ነው እየተጫወትክ ያለኸው። 

ዘይት የሚባል ነገር ትግራይ ውስጥ ህልም ነው። ሽንኩርና ቲማቲምም ቢሆንም ቅንጦት ነው። ለአንድ ኪሎ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር እየገዛ ወጥ ሊያጣፍጥ ቀርቶ ድሃ ትግራዋይ በደረቁ የሚበላ እንጀራ ማጣቱን መረዳት የሚያቅተን ሰዎች ከሆን ሌላ ምን ልንረዳ እንደሚችል እርግጠኛ አይደለሁም። ሌላው ሁሉ ቢቀር፥ ለአንድ ኩንታል ጤፍ ሃያ ሺህ ብር፣ ታሞም ለመታከም በተመሳሳይ አስር ሺዎችን ከፍሎ መታከምና በኮንትሮባድ የሚገባ መድሃኒት ገዝቶ ማገገም የማይችለውን ድሃ ትግራዋይ ዕጣ ፈንታው ሞት እየሆነ እንዳለ ሊሰወረን አይገባም። ባይሆን ይህ ዓይነቱ የህጻናትና የድሃ ህዝብ በአጠቃላይ ህመምና ሰቆቃ የህወሃት መሪዎች ፖለቲካና አጀንዳ ከመደገፍና ከመቃወም ጋር መያያዝ ባልተገባ ነበር። በርሃብና በበሽታ እየተሰቃየ ያለ ህጻን፣ እየሞተች ያለች እናት፣ እየሞተ ያለ አባት የእኔ ወይም የእርስዎ የስጋ እባትና እናት ላይሆኑ ይችላሉ። ህጻናቱም ልጆቻችን አንድም ወንድምና እህቶቻችን ላይሆኑ ይችሉ ይሆናሉ።  የቆምኩት ለእውነት ነው፣ የምታገለውም ለዓላማ ነው! እያልን ስናበቃ እንደ ጥላ የሚያልፈው የፖለቲካ ፓርቲ ሃይማኖት ሆኖብን ምክንያታዊነት የሰማይ ከዋክብት በዚህ ደረጃ ከእኛ የሚርቅበት ምክንያት ምንድ ነው? ብናውቀውም ባናውቀውም፣ የቅርብም ይሁን የሩቅ፣ የድሃ የሁን የለማኝ ትግራዋይ ህመምና ስቃይ የማይሰማንና የማያንገበግበን ከሆነ ዐቢይ አህመድ ዓሊና ይውደም ኢሳያስ ይውደም እያሉ የሚያሰሙት ጩኸት ምን ሊፈይድ ነው? ይህ ማለት የትግራይ ነገር አይሰማዎትም አያንገበግቦትም እያልኩ አይደለም። በትግራይ ጉዳይ ላይ እኔ በተለየ መልኩ ጻድቅ የምሆንበት ምንም ምክንያት የለም፤ መልዕክቴም ቢሆን በተሳሳተ መልኩ እንዲተረጉም አልሻም። እኔ እያልኩ ያለኹተይ፥ ይህን ለማስቆም ማለትም፥ የትግራይ ህዝብ ከከበባ ለማናገፍና ነጻ ለማውጣት ምን እያደረጉ? ነው።  ችግሩ የኛው የራሳችን የፖለቲካ ውሳኔ ተከትሎ እያበበ ያለ ችግር እንደ መሆኑ መጠን በኢትዮጵያና በኤርትራ መሪዎች ላይ ብቻ መጮህ ሳይሆን የችግሩ አካል የሆኑ፣ አደራን መብላት የለመዱ፣ ጥቅምና ስልጣን ከማሳደድ ያለፈ ሌላ ዓላማና ራዕይ የሌላቸው፣ የእኛው የትግራይ ገዢዎች ህግና ስርዓት እንዲገዛቸው ምን አደረጉ? ወይስ “ጦርነት ላይ ያለነው” የሚል እውነት የሚመስል ዳሩ ግን አወናባጅና ተልካሻ ምክንያት እንደ ባንዴራ እያውለበለቡ ራስዎትን አሳምነው ሳያውቁት የትግራይ ህዝብ እንደ ቅጠል አርግፈህ በሚገነባ መቃብር ላይ ጥቅምዋን ለማሳደድ ተግተዋል የሚል ነው። 

ከከበባ የማይገላግል ሰበር ዜና፥ የእውነት ድል ወይስ የተለመደ ፖለቲካ? 

አሁን ባለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ትግራይ መሬት ውስጥ የሚገኝ የትግራይ ህዝብ በታሪኩ አይቶት የማያውቅ፣ የለየለት ድቅድቅ ጨለማ ማለትም፥ የምግብና የመድሃኒት እጦት ተከትሎ የሚመጣና ሊገጥመው የሚችል ጊዜ የማይሰጥ ሞትና እልቂት ከፀሐይ በታች ሊተርፍፈው የሚችል ሃይል ሌላ ማንም ሳይሆን ኢትዮጵያ ምህረት ያደረገችለችና የራራችለት እንደሆነ ብቻ ነው (ለምን? እንዴት? የሚል ጥያቄ ካሎት ይታገሱኝ እንጅ በሚገባዎት አገላለጽ አብራራዋለሁ)። የትግራይ ሰራዊት፥ ጦርነቱን ተከትሎ ከግዛቱ አልፎ የደረሰባቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ለቆ ወደ ስፍራው ሲመለስ ይህ ለሁለተኛ ጊዜው ነው። ምክንያቱ ምንድ ነው? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ በእውነቱ ነገር ከአርባ ዓመታት በላይ የፖለቲካ ልምድ አለን የሚሉና ይህን ውሳኔ እያስተላለፉ ያሉ ሰዎች ብቻ ነው ሊያውቁት የሚችሉት። ይህ ማለት ግን የእነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ፖለቲካዊ ውሳኔ ዓላማና ግብ ከሰፊው ህዝብ የተሰወረ ነው ለማለት እንጅ የትግራይ የፖለቲካ አመራር በር ዘግቶም ቢሆን የሚመክረውና የሚወስነው ፖለቲካዊ ውሳኔ በአንድም በሌላም መንገድ የማወቅ አጋጣሚውና ዕድሉ ላላቸው ሰዎች የተሰወረ ነው ለማለት አይደለም። ልብ ይበሉ፥ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ጥያቄና ማጠንጠኛ ሰራዊቱ ዛሬስ ለምን ተመለሰ? የሚል አይደለም። ጥግ ድረስ የሚሄድበት ግልጽ የሆነ ስትራቴጅና ምክንያት ከሌለው፣ ዓላማውና ተልዕኮው የትግራይ ወጣት እየሞተበት ላለ ዓላማ ካልሆነ (ትግራይ ከከበባ ነጻ የማውጣት ተልዕኮ ከሌለው) መቀጠሉ ትርጉም ስለማኖረው መመለሱ ትክክለኛና ተገቢ ውሳኔ ነው። የሰራዊቱ መደራጀት የህወሓት መሪዎች የፖለቲካ አጀንዳና ፍላጎት መሳካት መጠቀሚያ ከሆነ  የሰራዊቱ መገስገስ ሆነ መመለስ የሚወስነው የፖለቲካ ጥቅም ያላቸው አካላት ስለሚሆን አሁንም መመለሱ ብቻ ሳይሆን ባስፈለገን ሰዓት ተመልሰን መምጣት እንችላለን እያለ መርገፍ የሚችለውን ያህል ትግራዋይ ወጣት ቢረግፍ የሚረግፈው እንጅ ማዶ ሆኖ በሬድዮ የሚያረግፈው ያለ ችግሩ ስላይደለ አሁንም መመለሱ በሰዎቹ እይታ ትክክል ነው። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የትግራይ ሰራዊት በየጊዜው ወደ ስፍራው ተመለሰ እየተባለ የሚሰራው ያለ ስራ አስመለክተን፥ ሰራዊቱ የህይወት መስዋእትነት ከፍሎ ከተቆጣጠረው ግዛት በተደጋጋሚ እንዲወጣና ወደ ስፍራው እንዲመለስ ድርጊቱም ለትግራይ ህዝብ ጥቅም ተብሎ እንደተደረገ በማስመስል በቀጣይነት እየተሰራ ያለው ደማዊ ድራማ፣ የህወሓት መሪዎች ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ውሳጣዊ ምክርና ዓላማ አስመልክተን በግርድፉ እንመለከታለን። 

ዐቢይ አህመድ ዓሊ ሆነ ኢሳያያስ አፈወርቂ መቐለ ከተማን መግባትና መቆጣጥር የፈለጉበት/የሚፈልጉበት ምክንያት ለእኔ ግልጽ ባይሆንም (ከዓላማቸው አንጻር)፤ አንድም፥ ዓላማቸው ትግራይ ከተቀረው ዓለም/ከስልጣኔ በመቁረጥ ማኮላሸትና ከጥቅም ውጭ ማድረግ ከሆነ ይሄው የጥይት ድምጽ ሳያሰሙ ትግራይ በቀላሉ ማዳከም የሚችሉበት ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ዛሬም ድረስ አንቀው ይዘውና ተቆጣጥረው ይዘዋል። ማኸል ትግራይ ገብተው የሚያልቁበት ነገር ግን ለእኔ እንቆቅልሽ ነው። የእነዚህ ሁለት አገራትና መንግስታት ዓላማና ግብ ትግራይን ማዳከምና ማኮላሸት፤ ትግራይና ትግራዋይ ደም ያለው ፍጥረት ሁሉ በታሪክ ህልውና ላይኖራቸው ከካርታ መፋቅ ለመሆኑ ከአንደበታቸው የሰማነው ሐቅ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሁለት ዓመት ሙሉ ጦርነት ማዋጋት ሳያስፈልጋቸው ማድረግ የሚችሉት እንደሆነ ከፍ ሲል ተመልክተናል። እዚህ ላይ አንድ እውነት አለ ይኸውም፥ አሁን በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ሆነች ኤርትራ የፈለጉት የመሳሪያ ዓይነትና የሰው ሃይል ብዛት አሰልፈውና ተሸክመው ቢመጡም ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ቀንቷቸው ትግራይ መሬት ላይ ዘው ብለው መግባት አልተቻላቸውም (የምዕራብ ትግራይ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ)። ይመጣሉ ይረግፋሉ፤ ይሞክራሉ ያልቃሉ። ይህ ዓይነቱ ትእይንት በአሁን ሰዓት በተለይ ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ ባለቤት ለሆነችው ለኢትዮጵያ ቆሻሻ የመጣልና የመድፋት ያህል ሰራዊትዋን እያመጣች በትግራይ አዋሳኝ ቦታዎች (በአፋርና በአማራ ግዛቶች) ለሞትና ለእልቂት የቀናው ደግሞ ለምርኮ ማስረክብና መማገድ ባህል ሆኖባታል፤ ጭንቀትዋም አይደለም። ጥያቄው፥ ትግራይ ዛሬም ድረስ ከበባ ውስጥ የምትገኝበት ምክንያት ምንድ ነው? የጠላቶቻችን ጥንካሬ ወይስ የህወሓት መሪዎች ጥቅም ላይ መሰረት ያደረገ የተለመደ የቁማር ፖለቲካ? የሚል ነው። 

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ግንባር በመፍጠር በትግራይ ህዝብ ላይ እየተከተለችው ያለ ወታደራዊ ከበባ አጠናክራ የቀጠለች እንደሆነ የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ በምግብና በመድሃኒት እጦት እንደ ቅጠል መርገፉ የታመነ ነው። የጦርነቱ መጓተት በተመሳሳይ ኢትዮጵያን እንደ አገር በልዩ ልዩ መንገድ ማለትም በማህበራዊውና ኢኮኖሚያዊው ዘርፍ ጨምሮ በሁሉም አቅጣጫ አገሪቱ አሁን ከምትገኝበት አስከፊ ሁኔታ በባሰ መቀመቅ ውስጥ የሚጨምር ከመሆኑም በላይ ህልውናዋን የማክሰምና የመበታተን አቅም እንዳለው ከወዲሁ ለመናገር ልዩ መንፈሳዊ ፀጋና ተሰጥኦ አይጠይቅም። ጦርነት ሰዎች በህግ የሚገዳደሉበት ብቻ ሳይሆን ጦርነት ኢኮኖሚ ነው። ከሰማይ በሚወርድ ዝናብ የሚካሄድ ጦርነት የለም፤ ጦርነት የሚካሄደው በህዝብና በሀገር ሀብት ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ የተራዘመ ጦርነት ለማካሄድ (ጥይት ለመሸመት) የሚውል ገንዘብ የምታገኛው ከሌላ ከየትም ሳይሆን ከህዝቡ ኪስ ነው ሊሆን የሚችለው። አሁን ባለው ተጨባጭ የአገሪቱ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያ ይህን በማድረግ ልትቀጥልና በዚህ መልኩ ረጅም ርቀት ልትጓት የምትችል አገር አይደለችም። አንድም፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የአገሪቱ ሀብትና ንብረት ሽጦና ለውጦ የሚያገኘው ያለ የጦር መሳሪያ ብዛትና ዓይነት ተማምኖ ጦርነት የከፈተ ቁጥር በውጭ ምናዛሬ የሸመተው የጦር መሳሪያ ለትግራይ ሰራዊት እያስረከበና የትግራይ ሰራዊት እያስታጠቀ ይቀጥላል። ይህ ሲይደርግ ታድያ ኢትዮጵያ አንገት ላይ የገባውን ገመድ እያጠበበ የአገሪቱን ህልውና ወደ ማክሰም መምጣቱ የማያከራክር እውነት ይሆናል። ስለ ኢትዮጵያ እዚህ ላብቃና ስለ ራሳችን ችግርና መፍትሔው እንወያይ።  

እስከ ዛሬ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንነጋገር ከተባለ፥ ትግራይ በምዕራብ በኩል ሆነ በአፋር አቅጣጫ ከበባውን መስበርና መውጫ በር በመክፈት፣ በምግብና በመድሃኒት እጦት እየተሰቃየ የሚገኝ ህዝብ ነጻ ማውጣትና ማትረፍ አልተቻላትም። አልቻልንም (ያልቻልንበት ምክንያትም አብራራለሁ)። አለመቻላችን ደግሞ እንዲሁ የምናስተባብለው ዲስኩር ሳይሆን አሌ የማይባል ሐቅ ነው። አንድም፥ ከበባውን መስበርና ጥሰን መውጣት ቢቻለን ኖሮ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰራዊት አሸንፈን ህዝባችን ከከበባ መገላገል ብቻለን ነበር። ከበባውን መስበር ብንችል ኖሮ ሁለት ዓመት ሙሉ ህዝባችን በምግብና በመድሃኒት እጦት እንዲሰቃይና ክፉ ሞት እንዲሞት ባይልፈቀድን ነበር። ብንችል ኖሮ፥ ይህን የማናደርገበት ምክንያት ለማን አዝነን ይመስሎታል? ኢትዮጵያ ጦርነት ስትፈልግ ጦርነት እንድንዋጋ፤ ለድርድር ዝግጁ ነኝ ባለች ቁጥር የያዝነውን ጥለን በጠራችን ስፍራና ሰዓት “ለመደራደር” እየደረግነው ያለ መሯሯጥ ትግራይን በብቸኝነትና በበላይነት እየገዛ የሚገኝ የህወሓት አመራር ሰላም ወዳድ ቡድን ስለሆነ ይመስሎታል? የሚፈገው ቢያመንም እውነት እውነቱ ተነጋግረን መፈወስ ከሆነ እውነቱ ይህ ነው። ትግራይ ዛሬም ድረስ ከበባ ውስጥ የምትገኝበት ምክንያት የጠላቶቻችን ጥንካሬ ሳይሆን ይልቁንም የህወሃት መሪዎች የበከተ ፖለቲካዊ አመራርና በቀጣይነት በሰራዊቱ ላይ እያደረገው ያለ ጣልቃ ገብነትና ውሳኔዎቹ ነጸብራቅ ነው። ይህ ስም ብቻ ይዞ የቀረ አመራር (የህወሓት መሪዎች) ከተማ ገብቶ መዝረፍ የለመደ ዕለት የተሰለባ ቡድን ለመሆኑ ድጋሜ የዘነጋነው ይመስላል። አሁን ደግሞ ከቀድሞ መገለጫው በከፋ መልኩ አመራሩ (የህወሓት መሪዎች) ነባራዊ ሁኔታው  ከብዙሐኑ የተሰወረ ቢሆንም ራሱን ችሎ መቆም የማይችል፣ ህዝባዊ አጀንዳ የሌለው፣ ወዶ ገብ ተላላኪ መሆኑ ማወቁ ይበጀን እንደሆነ እንጅ አይፈጀንም። አድርግ የተባለውን ነገር ሁሉ (ይህን ጻፍ/ይህን ተናገር/አሁን ተዋጋ/አሁን ደግሞ ተመለስ) ለማድረግ እንቅልፍ አጥቶ የሚያድር፣ የጌቶቹን ትዕዛዝ እየተቀበለ የትግራይ ህዝብ በቀጣይነት የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለበት የሚገኝ ዓላማ ውሃ ለመቸለስ የሚጓጓ አሳፋሪ ቡድን ነው። አሁን የብዙሐኑ ጥያቄ ሊሆን የሚችልና ማወቅ የሚሹት ነገር ቢኖር፥ የህወሓት መሪዎች ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል ነው ብዬ እገምታለሁ። በርግጥ፥ ምላሹ “የትግራይ ችግርና መፍትሔው” በሚል መጽሐፌ ላይ በስፋት ያስቅመጥኩት ቢሆንም በአጭሩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።   

ከእንግዲህ ወዲህ የህወሓት መሪዎች ጥቅማቸውና ስልጣናቸው አስጠብቀው ትግራይን መግዛትና ትግራይ ውስጥ መኖር የሚችሉ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና እንድትቀጥል በማድረግ የኢትዮጵያ ድጋፍ ያገኙ እንደሆነ ብቻ ነው። የህወሓት መሪዎች ትግራይ ውስጥ መኖርና መቀጠል የሚችሉ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የቀጠለች እንደሆነ ብቻ ነው። የህወሓት መሪዎች ኢትዮጵያ ከምትባለው አገር ተለይተው መኖር የሚችሉ ሰዎች አይደሉም። የህወሓት መሪዎች ላለፉት 30 ዓመታት በመጡበት መንገድ ትግራይ ውስጥ ገዢ የመቀጥልና ያለ መቀጠል ጉዳይ ከትግራይ መጪ ዕጣ ፈንታ ጋር የተያያዘ ነው። የትግራይ ህዝብ በድምጹ አሸንፎ መሻቱ ያገኘና ትግራይ ራስዋን ችላ የቆመች ዕለት የህወሓት መሪዎች የሚኖራቸው ምርጫ ሁለት ምርጫ ብቻ ይሆናል። ይኸውም፥ ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ ያለፈውን ዘመን እርግፍ አድረው ትተው እንደ ማንኛውም ትግራዋይ መመላለስ ካልሆነ ደግሞ ልክ ከጦርነቱ በፊት የጀመሩት የቻይና ሞዴል በመከተል ለዘብተኛ ፖለቲካ አራማጆች በመሆን አምባገነናዊ መንግስት አቋቁመው ሀብትና ንብረታቸው ለማስጠበቅ በሚያደጉት የሴራ ፖለቲካ በገዛ እጃቸው መቃብራቸው ቆፍረው መክሰም ይሆናል። የህወሓት መሪዎች ግን ሦስተኛ መንገድ መርጠው በመታገል ይገኛሉ፤ ይኸውም፥ ልክ የዕርቅና የሰላም ሰዎች በመምሰል በዕርቅና በሰላም ስምና ሽፋን ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና እንድትቀጥል በማድረግ ሃይላቸውና ጉልበታቸው እንደገና አጠናክረው ገዢ ሆነው የመቀጠል ዓላማ ነው ያላቸው። ከዚህ የተነሳም የትግራይ ሰራዊት ጉልበት በተደጋጋሚ እያጠፉና እያመከኑ ትግራይም በቀጥይነት ከበባ ውስጥ እንድትኖርና የትግራይ ህዝብም በርሃብና በበሽታ እንዲያል ፈርደውበታል። ለምን ሲባል? ለኢትዮጵያ ሲባል። ኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትዋ እንደያዘች መቀጠል አለባት ብሎ የሚያምነው ብሄራዊ ጥቅሙ የሚሳስበው የምዕራቡ ዓለም ብቻ ሳይሆን ጥቅምና ስልጣን ላይ የተንጠለጠለ የህወሓት መሪዎችም ጭምር ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የፈለገውን ቁጥር ያለው ትግራዋይ ቢያልቅ ጉዳያቸው አይሆንም። 

አሁንም ደገሜ እላለሁ፥ በትግራይ ህዝብና በትግራይ ሰማዕታት ቀሚስ ተደብቀውና ትግራይ የወላድ መሃን አድርገው ላለፉ 30 ዓመታት በሃይልና በጉልበት የገዙ የህወሓት መሪዎች ትናንት፣ ዛሬም ቢሆን ነገ በመውስቦ፣ በጥቅምና በጋብቻ የተጋመደ የግልና የቡድን ጥቅማቸውና ፖለቲካዊ ስልጣናቸው ጠብቀው ከማስጠበቅ ያለፈ የትግራይ ህዝብ መሻትና ጥያቄ የመመለስ ፍላጎት ሆነ ዓላማ የላቸውም ኑሮአቸውም አያውቅም። ጎበዝ፥ የህወሓት መሪዎች በማንነታቸው ተጋሩ መሆናቸው ሳይሆን የሰዎቹ ፖለቲካዊ ዓላማና ተልዕኮ ማወቅና በቅጡ መረዳት አስፈላጊ ነው። የህወሓት መሪዎች የትግራይ ህዝብ የሀገራዊት ጥያቄ ተቀብለው ማስፈጸም የሚገደዱበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው ታድያ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ፈጽሞ ፊት የነሳቸውና ተስፋ ያስቆረጣቸው እንደሆነ ብቻ ይሆናል። ይህ የሚሆንበት ምክንያትም ሰዎቹ ሌላ መሄጃና አማራጭ ስለሌላቸውና ስለማይኖራቸው ብቻ ነው። ሁላችን እንደምናውቀውና እንደምናስታውሰው የህወሓት መሪዎች ከአዲስ አበባ ሲባረሩ የሄዱት ወደ ሌላ ሳይሆን ለሃያ ሰባት ዓመታት ወደ ተፀየፍዋት ትግራይ ነው መደበቂያቸው ያደረጉ። አሁንም ተመሳሳይ ነው፤ ዐቢይ አህመድ ዓሊ፥ እኔ በምለው ሃሳብ የሚስማሙ ከሆነ እሺ እሰማችሃለሁ ካልሆነ ግን ፍላጎታቸው ትግራይ መገንጠል ከሆነ ጥርግ ይበሉ፣ እባካችሁ በፈጠራችሁ እኔን አታድኩሙኝ! የሚለው አቋሙ እንደያዘ የፀና እንደሆነ ብቻ ነው የህወሓት መሪዎች የትግራይ ሀገራዊነት አቀንቃኞች ሊሆኑ የሚችሉ። 

የትግራይ ህዝብ ጠንካራ ሰራዊት ፈጥሮ በጠላቶቹ ላይ ተደጋጋሚ ድል ቢቀዳጅም “ምን ያለበት ምን አይችልም” እንደሚባለው ዛሬም ዛሬም የትግራይ ህዝብ መደበቂያቸው ያደረጉ የህወሓት መሪዎች በፖለቲካው መድረክ ትግራዋይ አጀንዳ ማራመድ ባለመቻላቸው ይሄው ዐቢይ አህመድ ዓሊ በሚለውና በሚያቀርበው ሃሳብ የማይስማሙ ከሆነ በመጡበት እንዲሄዱ በተደጋጋሚ ሸኝቷቸዋል። ተወደደም ተጠላም፥ የትግራይ ፖለቲካ ከህወሓት መሪዎች እጅ እስካልወጣና ኢትዮጵያውያን ዐቢይ አህመድ ዓሊን አውጥተው እስካልጣሉት ድረስ በሌላ አባባል ዐቢይ አህመድ ዓሊ ስልጣኑ ላይ እስካለ ድረስ የትግራይ ጉዳይና አጀንዳ በዐቢይ አህመድ ዓሊ እጅ ውስጥ እንደሆነ ይቀጥላል። ጦርነቱ ቢሸነፍም ፖለቲካው በእጁ ነው በእጅ እንደሆነም ይቀጥላል። ዐቢይ አህመድ ዓሊ አቋሙ ግልጽ አድርጓል (እስከ ዛሬ ያለውን)፤ ይኸውም፥ የትግራይ መሻትና ፍላጎት መገንጠል ከሆነ በእኛ በኩል ችግር የለብንም። ጥያቄአቸው በይፋ ያቀረቡ ዕለት እናስፈጽማቸዋልን! በማለት ከትግራይ ጋር መሳሳብ እንደሰለቸውና በማይረባ ነገር መጠመዱን ጭምር ሲግልጽ እንድ ጊዜ ሳይሆን በተደጋጋሚ ነው። በተረፈ መመለሳችን ፊታችን ወደ አስመራ ለማድረግ ከሆነ ደግሞ አብረን የምናየው ይሆናል። 

By aiga