ሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ
01/09/2022
የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ የሚል ዜና አገሩን በሙሉ አዳርሶታል፡፡ ለወትሮው እንዲህ ሃይማኖታዊ በአል እለት አንዱ ሌላውን በአሉን አንተርሶ እንኳን ለዚህ በአል አደረሰህ/ሽ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡ በዘንድሮው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በአል እለት በስፋት ሲደመጥ የነበረው “ሰመተሃል/ሰምተሻል እነ እከሌ/እከሊት እኮ ሊፈቱ ነው”! ኧረ አንዳንዱ ጭራሽ “ተፈተዋል እኮ” ባይም አጋጥመውኛል፡፡ በእውነቱ ይህ ሲያደምጡት ለጀሮ በጣም የሚጥም ዜና ነው፡፡ በገዢዎቻችን እስርቤት በነበረን ቆይታ ለምን ታሰርን፣ እንዴትስ ተፈታን የሚሉትን የጥባጥቤ ጥያቄዎች በሚገባ ለምናውቅ ሰዎች፤ በእስር ወቅት ሲያሳዩን የነበረው እንስሳዊ ባህሪይ ምን እንደፈለጉ ለምንረዳ ሰዎች ይህ የመፈታት ዜና ብዙ የሚያስጨንቀን አይሆንም፡፡ የሚያስጨንቀው በርካታ ህዝብ ያለሀጢአቱ በብሄሩ ብቻ እየተለቀመ እንደ በግ ሲታሰርና ሲንገላታ፣ ስለመታሰሩና እየደርሰበት ስላለው በደል ሳያስጨንቀን የተወሰኑ የፖለቲካ ሰዎች (የስልጣን ተገዳዳሪዎች) ሲፈቱ የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በአል እለት እንኳን አድረሰህ/ሽ ማለቱን አስረስቶን እያሳየን ያለነው መላ ቅጥ የጠፋበት ቡረቃ በእጅጉ የሚያስተዛዝብ ሲሆን የችግሮቻችን መፍትሄ እሱና እሱ ብቻ አድርገን መውሰዳችን ስለነፃነት፤ ስለፍትህ፤ ስለእኩልነትና ስለሰላም ትግል ያለንን አተያይ የተወላገደ ፤ በጅጉ ፍቺና ማስተካከያ የሚያስፈልገው እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ በተረፈ ተፈችዎቹ ጉምቱ ሰዎች ለረዥም ወራት ከደረሰባቸው ግለሰባዊና ቤተሰባዊ ሰቆቃና ችግር አንጻር መለቀቃቸው በበኩሌ አድናቆት መስጠት ላይ ችግር የሌለብኝ መሆኑን በአክብሮት እገልጻለሁ፡፡ እንኳንም ከዚህ አስከፊ ቆይታ ተገላግላችሁ ከምትወዱት ቤተሰባችሁ ጋር በሰላም ቀላቀላችሁ እላለሁ፡፡
ሃቁ ግን ሰላማዊ ሰዎች በገፍ በእስር ላይ በማኖር የሚያምን መንግስት እነኚህ ሰዎች ከእስር በመፈታቱ ብቻ የምንፈልገው ሰላም፤ ነፃነትና እኩልነት በዘላቂነት ያጎናጽፍልናል ብዬ ራሴን ማሞኘት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ይህ መንግስት በሚከተለው “የመንታ ምላስ” ፖሊሲ ፍላጎታችን ለመደፍጠጥ የሚያስችለው ልዩ ልዩ ድራማዎች እየፈጠረና እያጨናገፈ ረዥም መንገድ መጓዙ በተጨባጭ አይተናልና፡፡ በአናቱ ላይም ይህ መንግስት አሁን አካሂደዋለሁ እያለ የሚናገረው ሁሉን አቀፍና አካታች ሀገራዊ ምክክር ዋናውን ቁስል ለማከም ቆርጦ የተነሳ ሳይሆን የዳርዳሩን እስክስታ ምልክቶች እያየን በመሆኑ ከጅምሩ የከሸፈ ያደርገዋል፡፡ ይህ የአሁናዊ ድራማ በጠልቀት ለመረዳት እንዲያስችለንም እስረኞች ስለመፈታት አመልክቶ በኢፌድሪ የመንግስት ኮሚኒኬሽን የተሰጠውን መግለጫ በውል መገንዘብ ይኖርብናል እላለሁ፡፡
በዚህ መግለጫ ላይ ሁለት ዋና ዋና የምንላቸው ጉዳዮች ተጠቅሰዋል የመጀመሪያው “ኢትዮጵያ ለዘላቂ ህብረ ብሄራዊነት አንድነት የትኛውንም መስዋእትነት ትከፍላለች” ይላል ሲቀጥልም “መንግስት አካታች አገራዊ ምክክር እንዲሳካ ከሚጠበቅበት ሞራላዊ ግዴታዎች አንዱ ምህረት መስጠት መሆኑን” ይገልጽና፤ በነኚህ ሁለት አንካር ጉዳዮች መካከልም ከአባልነት መዝገብ ከተፋቁ ረዥም ጊዜ የሆናቸው ታሳሪዎች “በጤናና በእድሜ” ምክንያት የይፈታሉ ዜና ለመግለጫው ማጣፈጫነት ነካ አድርጎ ያልፋል፡፡ በዚች ሀገር በጽሁፍም ሆነ በንግግር የሚደረጉ የመንግስት የአቋም መግለጫዎች እንከን አይወጣላቸውም የሚያሰኙ ቢሆንም በመሬት ላይ ካለው ሃቅ ወይም ከተግባር ጋር ያላቸው ተቃርኖ ሁሌም ቢሆን አሳዛኝ ፍጻሜዎች፤ መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በትውልድ መካከል እምነትን የሚሸረሽሩ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለዚህ አስረጅ የሚሆኑ በርካታ ምክንያቶች መዘርዘር የሚቻል ቢሆንም ለጊዜው የዘላቂ ሰላም፤ እኩልነትና ነፃነት ፍላጎታችን በዚህ መግለጫ ሳቢያ እንዴት ችግር ላይ እንደወደቀ ለመረዳት አውዱን በማስታወስ እንመልከት፡፡
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተከብረው ለማየት የተደረገው እልህ አስጨራስ የዘመናት ትግል በ1983 ወደ ማጠቃለል በደረሱበት ዘመን ሀገሪቱ አዲስ ተስፋ ሰንቃ ሁሉም ዜጎች የኔ የሚሉትን ህገ መንግስት በማርቀቅ ለዚያው የሚመጥን መንግስት አቁመው የሰላም፤ የልማትና የዲሞክራሲ ጎዳና ላይ ለመጓዝ በጋራ ቃል ኪዳን ገብተው ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል፡፡ ይህ በጎ ጅምር በተለይም በሰላምና በልማት ላይ እንደሀገር የተገኘውን ድል አበረታች እንደሆነ በርካታ መረጃዎችን እየጠቀሱ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የዲሞክራሲ ግንባታው የሀገሪቱ ተጨባጭ ባህል፤ እምነትና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በሚፈቅደው መሰረት መገንባት አጠያያቂ ባይሆንም በብሄርና፤ ውሉ በማይታወቅ የዜጋ ፖለቲካ አስተሳሰብ ተሳክሮ አሁን ላይ ቆመን ላለንበት የዘመናት ሁሉ የበላይ የሆነው እልቂት ላይ አድርሶናል፡፡ በሌላ አነጋገር ህብረ ብሄራዊነት አንድነቱ ያጋጠመው የአሁናዊ ፈተና ህገመንግስት መሰረት አድርገው የተቋቋሙትን ብሄር ብሄረሰቦች ያጣጣሙትን የሰላምና የልማት ድል ለመንጠቅ በፈለጉ የተወሰኑ ግለሰቦችና መስዋእትነት ከፍለው ሰላምና ልማት እንዲመዘገብ ዘብ በቆሙና በግንባር ቀደምትነት በተሰለፉ ሃይሎች መካከል እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እንግዲህ ይህ መሰሉ የነፃነት፤ የሰላም፤ የፍትህ ትግል የጠየቀ ወገን ነው ወደ ወንጀልነት አውረደው ሌላውንም በማስተባበር ከምድረገጽ ለማጥፋት ሲሰሩና ሲያሰሩ የምናየው፡፡ እንግዲህ ይህ መሰሉ የእኩልነት ጥያቄ በሚያቀርብ ማህበረሰብ ላይ ነው ዝርፊያ፤ ጾታዊ ጥቃት፤ ግድያና መራብ የተፈረደበት፡፡ ይህ የወንጀለኛ ስነምግባር ተሸክመው ነው ኢትዮጵያ ለዘላቂ ህብረ-ብሄራዊ አንድነት የማትከፍለው “መስዋእትነት” የለም እያሉ የሚያስነግሩ ያሉት፡፡ በአሁኑ ደግሞ በሰላም የዘንባባ ካባቸው ውስጥ ተወሽቀው በመምጣት ስለ “መስዋእትነት” በማውራት ተቃርኖአዊ ስብእና መገለጫቸው የሆነውን ድራማ እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ አንዳንድ የዋሀን በትግራይ በተከፈተው አውዳሚ ጦርነት ኣስመልክቶ ሞኝ መሰል ጥያቄና ምክር ጣል ሲያደርጉ ይደመጣሉ “ህዝቡ ለምን ተፈላጊዎቹ ጥቂት ሰዎች አሳልፎ አይሰጥም”፤ አዛኝ መስለውም “ይህ ህዝብ በነኚህ ወንጀለኛ ሰዎች አመካኝነት መሰቃየት የለበትም” ይላሉ፡፡ ይህ የሚገርምና በጣም አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ አደገኛ የሚያደርገው ይህ የሰላም፤ የነፃነትና የእኩልነት ትግል በሌላ መርዝ ቀባብተው የሌሎችን ድጋፍ ለማግኘት የሚያቀርቡበት ስልት መሆኑ ነው፡፡ ወንጀለኛ ከተባሉም በየትኛው ስነ አመክንዮ ነው ለወንጀለኛ ተላልፈው የሚሰጡት? ይህ ጉዳይ በትክክል መረዳት ወይንም ለመረዳት አለመፈለግና ሌላ የዳቦ ስም በመስጠት ወዲያና ወዲህ መቅበዝበዝ ለችግሩ ማወሰብሰቢያ መንገድ ከመፈለግ በስተቀር ለህብረ ብሄራዊ አንድነቱ አስተዋጽኦ እንደሌለው መረዳት ይገባል፡፡
ሌላኛው የመግለጫው ይዘት ያነጣጠረው ደግሞ ህዝብ በፈለጉት ሰአት እንደበግ እያሰሩና እየፈቱ በሚኖርበት ሀገር የጉምቱዎች መፈታት ብቻውን የዘላቂ ፍትህ፤ ሰላም፤ ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጫ መንገድ አይሆንም፡፡ ከተፈቱት አንደበት “ስንታሰርም በትእዛዝ ነው የታሰርነው፤ ስንወጣም በትእዛዝ ነው፤ ውጡ ነው የተባልነው ወጣን” “ድንገት አመሻሽ ላይ መጥተው እቃችሁን ይዛችሁ ውጡ አሉን፡፡ ያው እቃችንን ይዘን ወጣን፤ ምንም የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉን እንዳዳመጥነው ቀድሞውንም ቢሆን አሳሪዎቹ ተጨባጭ ምክንያት አልነበራቸውም እንድንል ግድ ይለናል፡፡ አሁን ደግሞ ለሌላ ሊቀቅሉት ለፈለጉት እቅድ ማጣፈጫ ይሆን ዘንድ ከእስር ፈቷቸው፡፡ ምክንያት ፈጥረው አሰሩ፤ ምክንያት ፈጥረው ደግሞ ፈቱ፡፡ ይህ በማድረጋቸው ደግሞ ለአካታችነት ስንል “ሞራላዊ” ግዴታችንን ተወጣን አሉ፡፡ በምን መስፈርት ነው ምክንያት ፈጥረህ ላሰርከውና ምክንያት ፈጥረህ ለፈታኸው ንጹህ ሰው ሞራላዊ ግዴታዬን ተወጥቻለሁ ብለህ እያቅራራህ የምትናገረው? በፍርድ እንዲዳኝ ለከሰስከው ሰው በፍርድቤት ማቅረብ የሚገባህ ማስረጃ ልታቀርብ ባለመቻልህ አጋጣሚዎችን (ድራማ) እየፈጠርክ መፍታት ምን የሚሉት የሞራልና የህግ ልእልና ሊሆን ነው? አንድ መንግስት በዚህ በተዋረደና በረከሰ የሞራል ደረጃና ተግባር ላይ ሲገኝ እንዲህ አይነት ነገር በትውልድ አይድረስ ይባላል ምክንያቱም ቀጣዩ ትውልድ የሚወርሰውን “ክፉ መንፈስ” በማሰብ፡፡ እነኚህ ለትውልድ ምንም አይነት ደንታ የሌላቸው ግን በውሸት ላይ ውሸት እየደራረቡ ስለ ሞራል ልእልና ሊነግሩን፤ ለሰብኩን ይቃጣቸዋል፡፡
ባለፈው እትም ስለሰላም ጽፌ ነበር፡፡ ስለሰላም ለመጻፍ የተነሳሳሁት ዋናው ምክንያት የትግራይ መንግስት ለበርካታ አመታት ሲያቀርብ የነበረውን ተከታታይ
የሰላም ጥሪ መሰረት በማድረግ ለተግባራዊነቱ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን በመመልከቴ ነበር፡፡ በዛው ጽሁፌ ላይ የቀረበው የሰላም ሃሳብ ከግብ እንዲደርስ ሌሎቹ ከልብ እንዲቀበሉት ተማጽኖ በማቅረብ ጭምርም ነበር፡፡ ሆኖም በሌላ ክበብ ያሉት ጭንቅላተ-ድኩማን ለሰላም ጥያቄው ምን አይነት ምላሽ ሲሰጡ እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ከእስር ተፈቱ ወይም ሊፈቱ ነው የሚል ዜና ስሰማ በተንሸዋረረና አውዳሚ ሃሳባቸውና ድርጊታቸው በሀገር ላይ ያስከተለውን ውድመት ለተመለከተ ዜጋ አሁንስ በውስጣቸው ያለው የሚያቀረሽ የጥላቻ ሰንኮፍ አውጥተው አለመጣላቸው ምን ማረጋገጫ ሊኖር ይችላል የሚል አስተሳሰብ ገዢ ሃሳብ ሊሆን እንደሚችል በማመንም ጭምር ነው፡፡ ስለሰላም አለም በሞላ ሲሰብክና ተማጽኖ ሲያደርግ ቁብ ያልሰጣቸው ሰዎች ያ ትእቢታቸው የት አድርገውት ነው አሁን ደርሰው ስለ አካታች ሀገራዊ ምክክር ልብ አድርቅ ንግግራቸው የጀመሩት ያሰኛል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሀገሪቱ የረጋ መንፈስና እውቀት የሌላቸው እነኚህ ፖለቲከኞች፤ ጨለምተኛና ህዝብ በጥላቻ የማየት አባዜ ያልለቀቃቸው አማካሪዎች፤ በጥላቻ እውርነት የተጋረዱ አሳቢ መሳይ ቃልቻዎች በአጠቃላይ ከአእምሮአቸውና ከስብእናቸው የተጣሉ ተልካሻ ፍጡሮች በደረሰባቸው ከባድ ምትና ውርደት (ወታደራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ) ወደፊት መራመድ ባለመቻላቸው፤ ኪዚህ ለጥቂትም ቢሆን ቢንከላወሱ ተጨባጭ የሆነ ውጤት ሊያመጡ፤ ይልቁንስ ማእበሉ ጠራርጎ እንደሚወስዳቸው በዛችው ድንክዬ ጭንቅላታቸው ስለተገነዘቡ ብቻ ነው፡፡
ለማጠቃለል ያህልም ይህንን የ“መስዋእትነት” የማያባራ ፍላጎትና “ኢ-ሞራላዊ” ግዴታ ተከትሎ የወጣውን የደንባራው መንግስት መግለጫ ወደፊት ዋስትና ሊሰጥና ሊታመን የማይችል ከመሆኑም በላይ ይህ ጥሪ የምናስተናግድበት አቅጣጫና ሚዛን በሰፈረው ልክ በማስቀመጥ መሆን እንዳለበት ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ የሰላም የዘንባባ ንጣፍ ያዘጋጀ በማስመሰል በሌላ መልኩ ስለ መስዋእትነት ማውራት ተቃርኖአዊ መገለጫው እንደሆነ መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይህ የፍትህ፤ የነፃነት፤ የሰላምና የእኩልነት እጦት የሚመነጨው አሁን ሀገሪቱ በመምራት ላይ ያለው አመራርና በዙሪያው የሚገኙ ልበ ስንኩላን ጭንጋፎች ፈቅደውና አቅደው እየፈጸሙ ያሉት መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን እንደ “ለህዝብ በጎ አሳቢዎች” አድርገው በመቁጠር ብዙሃኑን ለእልቂትና ለስቃይ የዳረጉ ግብዝ ፍጡራን በመሆናቸው በጥላቻ አስተሳሰባቸው በታሪክ ለዘላአለም ሲወገዙ ይኖራሉ፡፡