ሰው ሶስቴ እንዲበላ

ለ17 አመት እንዳልታገለ

በቀን አንዴ እህል እንዳይቀምስ ታገደ ተከለከለ

ያረሰው ማሳ ያጨደው እህል በክምሩ ተቃጠለ

አይ ያልታደለ

ነፃ አውጭው ነፃነት ተነፈገ

ትናንት ማርኮ በፈታው

ለባርነት ተዳረገ

ለብሄር መብት ዘብ የነበረው አርበኛ 

ቆመው አዩት ሲገደል ሲሳደድ ሲዘረፍ በቀማኛ

ወንድሜ ባዩ ወንድም ኣጣ

መሬቱን ቆርሶ የለገሰው ወጋው እንደባላንጣ

ጥላ እንዳልነበር ዛሬ መጠለያ አጣ

መኖሪያው ተዘረፈ ተፈናቅሎ ጥሎ ወጣ

እምቢ ኣልገዛም ባለ

ከጠብመንጃ የተረፈው በጠኔ ይለቅ ተባለ

አይ ያልታደለ

የአብርሃምን ሃይማኖቶች የጠበቀ የከለለ

መስጊዱና መቅደሱ

ሓጂውና ቄሱ በሰቆቃ ተገደለ

ሰማይ የእግዚኣብሄርና የከዋክብት የመሰለው

በድሮን መድፍ ተወርውሮ

ምድሩ ደባየ ግማሹ ሞተ ቀሪው ቆሰለ

አይ ያልታደለ

ሰላም አፍቃሪው ምስኪን ሰላም ተከለከለ

ነጭ ወርቅ የሚያመርተው መሬቱ ለቀማኞች ታደለ

አይ ያልታደለ

አገር የቤት ክራይ አይደለ

ለቆ እንዳይሄድ በምን ፍርጃ

እዚህ መሬት ላይ ተተከለ?

አይ ያልታደለ

ገንዘብ እያለው ተነፈገ ለማያውቀው ሰቆቃ ተዳረገ

ዙሪያውን በእሾህ ታጥሮ መውጫ ተከለከለ

አይ ያልታደለ

አንጐሉ ተናወጠ ሃኪም እያለ መዳኒት አጣ

በበሽታና በራብ ከሰውነት አቅም ወጣ

ምን አረገ ለምንስ ከዚህ መሬት መጣ?

ነፃ አውጪው ነፃነት ተከለከለ

ምን አረገ ምን በደለ

አይ ያልታደለ

ወነጀለኛው ዳኛ ሆነ

ፍርድና ፍትህ ተጓደለ

መሬት ሲኦል ሆነችበት

ከሰው ሁሉ ተገለለ

ይህንን ሳያይ የሞተው ተገላገለ

መቃብሩ ውስጥ በጸጥታ ተንጋለለ

ህያው በቁሙ አበሳ አየ

አይ ያልታደለ

ማለቂያ ያጣውን የትግራይ መከራ በማሰብ

የሩሳሌም

Nov 14/2022

By aiga