ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

ማሳሰቢያ፥ በጽሑፉ ርዕስ እንደተጠቀሰ “የትግራይ ዕድል ፈንታ የሚወስነው የትግራይ ህዝብ ነው” የሚለው የጻሓፊው እምነትና አባባል ትግራይ ከኢትዮጵያ ለወደፊቱ ጋር ሊኖራት ስለሚችል ግኙንነት እንደ ገዢ ፓርቲ እምነትህና አቋምህ የማሳወቅ ግዴታና ሃላፊነት አለብህና አቋምህ ለህዝብ በግልጽ አሳውቅ ሲባል “ህዝብ ነው የሚወስነው” ከሚለው የህወሓት መሪዎች ቅንነት የጎደለበትና በጥሩ ዕቃ የተዘጋጀ መርዛም አባል ጋር መንፈሱ ሆነ የመልዕክቱ ይዘት አንድ አንዳይደለ ሳሳስብ በአክብሮት ነው።

መንደርደሪያ፥ መንግስት፣ ፓርቲ፣ ሀገር፣ ህዝብ፣ አመራርና ፖለቲከኛ በተመለከተ የእያንዳንዳቸው ቃላትና ኦፊስ እንደ አፍሪካ (በአህጉር ደርጃ) ከመላ ጎደል ትርጓሜያቸውና ፍቺያቸው (በቃል ደረጃ) ባንስተውም ቃላቶቹ የተሸከሙት ኦፊስና አጠቃቀሙ ላይ ታድያ አንጻራዊ መንገድ የመከተል ክፉና አመጸኛ ባህል ያለን ህዝቦች ነን። በትግራይ ደረጃ፥ ስልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ የተጠቀመጠ አንድ ባለስልጣን ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ቃላቶች አንድ በአንድ እያነሳን ትርጉማቸው እንዲያብራራልን የጠየቅነው እንደሆነ በሚፈለገው ልክ ባይሆንም መንፈሱን ሳይለቅ በመረዳቱ ደረጃ አሳምሮ ሊነግረን እንደሚችል አያጠራጥርም። ቃላቶቹና ቃላቶቹ የተሸከሙት ኦፊስ በፍቺያቸውና በትርጉማቸው ልክ ነው የምንጠቀምባቸው? ለሚለው ጥያቄ ግን ትግራይም አፍሪካ ናትና በእውነቱ ነገር ቀና ምላሽ ይገኛል ብሎ የሚጠብቅ ባለ አእምሮ አይኖርም። በዚህ ጽሑፍ፥ እንደ ሉዓላዊ ህዝብ፥ ህልውናው፣ ደህንነቱ፣ ክብሩና ማንነቱ ለመጠበቅ ተደጋጋሚ የህይወት መስዋዕትነት የከፈለ ዳሩ ግን ዛሬም ከእጦት፣ ከችጋር፣ ከድህነትና ከፍትህ እጦት ያልተገላገለ የትግራይ ህዝብ ተደጋጋሚ የህይወት መስዋዕትነት ስለከፈለለት፣ ስለ የሚገባውና መሆን ስላለበት ፖለቲካዊ አስተዳደርና የስልጣን ባለቤትነት አንስተን እንመለከታለን።

የምንገነባት ትግራይና የምናገለግለው የትግራይ ህዝብ ሚዛናቸው ከባድ ዋጋቸውም እጅግ ታላቅ ነው

የትግራይ ህዝብ እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ ህዝብ የራሴ ነው የሚለው ባህልና ማንነት እንደጠበቀ እንደ ህዝብ ለመቆም ሆነ ለመኖር የበቃና የተቻለው በሌሎች መልካም ፈቅድና ይሁንታ ሳይሆን በትግሉና በቀጣይነት እየከፈለው በሚገኝ የህወይወት መስዋዕነቱ ለመሆኑ ጠላትም ወዳጅም የሚመመሰክረው ሐቅ ነው። በመሆኑም፥ ቀደም ሲል እንደተገለጸ የትግራይ ህዝብ ዛሬም፥ ከእጦት፣ ከችጋር፣ ከድህነትና ከፍትህ እጦት ያልተገላገለ፣ መልኩ የቀየረ ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ የሚገኝ፣ ከአብራኩ በወጡ ካርኒቨረስ (Carnivores) የሆነ ተፈጥሮ ያላቸው ግልሰቦችና ቡድን እየተበላ ያለ ቀን ያልወጣለት ህዝብ ቢሆንም ለህልውናውና ደህንነቱ ለክብሩና ማንነቱ ታድያ የትግራይ ህዝብ የተፈተነ ህዝብ ነው። ጥያቄው፥ ይህ የትግራይ ህዝብ “ከማታቀው መልዓክ የምታውቀው ሰይጣን ይሻላል” በሚል አባባል የታጀበ ክፉን የመቻልና ችሎ የመሸከም አጥፊና አደገኛ ባህል በሰለጠነ መንገድና በህግ አግባብ እንዴት እንለውጠው? የሚል ነው። በርግጥ፥ ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽና መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የትግራይ ህዝብ ማንቃትና የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ማደረግ ነው። ከዚህ ሁሉ እልቂትና ሞት በኋላ የምንገነባት ትግራይና የምናገለግለው የትግራይ ህዝብ ሚዛናቸው ከባድ ዋጋቸውም እጅግ ታላቅ ነው! ሲባልም መፈክር በማሰማት ሳይሆን በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ስልጣናቸውና ጥቅማቸው ለመጠበቅ በሌለ መንግስትነት፣ በትግራይ ሰማዕታት ስምና ሽፋን በዕቅድና በዓላማ እየፈጸሙት ያለ ወንጀል አሁኑኑ ነቅጠን ያስቆምናቸው እንደሆነና በጉዳያችን ላይ ሁላችን እኩል ድምጽና ተሳታፊነት ኖሮን የሚረባንን ማድረግ ስንችል ነው። ዕጣ ፈንታችን፥ ከዚህ ቀደም በትግራይ ህዝብና በትግራይ ሰማዕታት ስም የዘረፉትና ያግበሰበሱት የሀገርና የህዝብ ሀብትና ንብረት ለመጠበቅ፣ ይህን ማድረግ ያስችላቸው ዘንድም አንድ ጊዜ ፈጽመው የሰለጠኑበት የህዝብ ስልጣን ለማስቀጠል ሁሉንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ የበከቱ ግለሰቦችና ቡድን እንዲወስኑልን አሳልፈን በመስጠት ሳይሆን እንደ ህዝብ የስልጣን ባለቤቶች መሆናችን ገብቶንና ተረድተን ወራሪ ሃይሎች በተፋለምንበትና በገጠምንበት መንፈስ ገጥመን ልናራቁታቸውና ልንጥላቸው ይገባል። አንድም፥ በህጋዊነትና በመንግስትነት በስምህና በትግራይ ሰማዕታት ስምና ሽፋን ተደብቀው ያሹትን መፈጸም እንደሚችሉ የሚያምኑት ግልሰቦችና ቡድን በእጅህ ያለ የማደርግ አቅም ተጠቅመህ ለመብትህ የቆምክና ፊት የነሳሃቸው ዕለት ዕድሜያቸው አጭር ነው። የህልውናቸው ምስጢር አንተ እንጅ ተቃራኒው አይደለም።

የራሳችን ዕድል ፈንታ የሚወስነው እኛ ብቻ ነን

የትግራይ ዕድል ፈንታ የሚወስነው የትግራይ ህዝብ ነው ሲባል የትግራይ ህዝብ ማን ነው? ብሎ ጥያቄ የሚያነሳ ባይኖርም፤ እንዴት? የሚለው ግን ሁሉም ትግራዋይ መረዳቱ በሚገባ ሊያሰፋና ሊነቃ ይገባል። ትግራይ ማለት የትግራይ አመራር ማለት አይደለም፤ የትግራይ አመራር ማለትም የትግራይ ህዝብ ማለት አይደለም። ቀለል ባለ አማርኛ፥ ህዝብና በህዝብ ስም የሚደራጁ ማናቸውም አካላት በስልጣንና በባህሪይ አንድ አይደሉም፤ አንዳይደሉም ከእውቀት በዘለለ በተጨባጭ በተግባር የምንገልጸው መረዳት ሲሆን ነው ተጠቃሚዎች የሚያደርገንና፥ በትግራይ ስም የሚነገርና የሚራገብ አጀንዳ ሁሉ ከእኛ (ከህዝብ) ጥያቄ ጋር ሳንቀላቅል ነገሮች በተጠናጠል ለይተን ልናይ ይገባል። ይህ ማድረግ ስንችል ቀሪው የውሳኔ ጉዳይ ነው የሚሆነው ነው።

1. በድርድር የሚወሰን የትግራይ መጻኢ ዕድል የለም ማለት የፓለቲካ ፓርቲ የትግራይ ዕድል ፈንታ የመወሰን ስልጣን የለውም፤ አይችልምም ነው። ቀለል ባለ አማርኛ፥ የትግራይ ዕድል ፈንታ የሚወስነው የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው። መንግስት ነኝ፣ ፓርቲ ነኝ፣ አመራር ነኝ የሚል ሁሉ ለትግራይ ህዝብ የሚሰራ፣ የትግራይ ህዝብ አገልጋይ፣ የትግራይ ህዝብ ጥያቄና መሻት አስፈጻሚ እንጅ ከዚያ ያለፈ አስተዋጾዖ ሆነ ስልጣን የለውም። በሌላ አባባል፥ ትግራይ በተመለከተ ብቸኛ ባለ ስልጣን የትግራይ ህዝብ ነው። የትግራይ መንግስት ነኝ የሚል አካል ቢሆን እንደ ተቋም ስልጣኑ የሚመነጨው ህዝብ ፖሊሲውና ፕሮግራሙን አምኖበት ትሆነኛለህ ብሎ ድምጹና ይሁንታውን ሰጥቶ በኮንትራት ለስልጣን የሚያበቃው ህዝብ ነው። በመሆኑም፥ የትግራይ ዕድል ፈንታ በተመለከተ አገር ለመሆን ሆነ ሌላ ምርጫ ለመከትል ዕድል ፈንታውን የሚወስነው በትግሉና በመስዋዕትነቱ ህልውናውና ደህንነቱን ያረጋገጠ የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው።

2. ኢትዮጵያም ብትሆን በትግራይ ጉዳይ ድምጽ ሊኖራት ቀርቶ በስም ደረጃ ስሟ በዚህ ጉዳይ መነሳቱ ራሱ ለትግራይ ህዝብ ቀልድ ነው። ኢትዮጵያ ሆነች ኢትዮጵያውያን እንደ ማንኛውም ጎረቤት አገርህና ህዝብ ተጋሩ በውስጠ ጉዳያቸው ላይ ሲወያዩና ሲመካከሩ የመመልከት ፍላጎቱ ካላቸው የሩቅ ተመልካች ሆነው ከመታዘብ ያለፈ በትግራይ ጉዳይ ላይ እነሱን የሚመለከት (የሚመለከታቸው) ምንም ነገር የለም። የኢትዮጵያና የትግራይ ጉዳይ ምዕራፉ የተዘጋና ያከተመለት ጉዳይ ነው። በትግራዋይ ልብ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትባል ጎረቤት አገር እንጅ ከኢትዮጵያ ጋር ዝምድና አለኝ ብሎ የሚያምን ትግራዋይ የለም። ትግራይና ኢትዮጵያ የሚያገናኝ ነገርስ ምን ቢኖር ነው? ህገ መንግስቱ እንደሆነ ከማንም በላይ ቀደመው “ፈርሰዋል!” ሲሉ ሲጮሁ የምናውቃቸው ሌላ ማንም ሳይሆን በትግራይ ሰማዕታት ስምና ሽፋን እየሸቃቀጡ ላለፉት 30 ዓመታት የትግራይ የፖለቲካ ስልጣን በብቸኝነት የሰለጠኑበትና አሁንም ጥቅማቸውና ስልጣናቸው ለመጠበቅ በትግራይ ህዝብ ላይ እያሴሩ ያሉ ግለሰቦችና ቡድን ናቸው።

በርግጥ፥ ኢትዮጵያ የምታስቆመው ማለትም ይህ ለእኔ አይስማማኝም/አይመቸኝም የምትለው የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ሊኖር ቀርቶ የትግራይ ጥያቄ የምትጠይቅበት ሞራል እንደሌላት የትግራይ አመራር አቋሙን በግልጽ ሊያሳውቅ ይገባል። ድርድር ሆነ ውይይት ሲባል ሰዎች የሰጡህ መቀመበልና ሳታላምጥ መዋጥ ካልሆነ በቀርም “ስለምጣዱ ሲባል…” ተብሎ የሚተውና የሚታለፍ ነገር የለም አይኖርምም። በሌላ አባባል፥ ትግራይ ከውይይቱ ምን እንደምታትርፍ፣ የድርድሩ ዓላማና ግብ በቅጡ ሳትረዳ እንዲሁ በመድረኩ ለመገኘት አልተስማማችም። የሚረባውና የሚጠቅምው የሚያውቅ የትግራይ ህዝብ በተመሳሳይ ከህልውናውና ከደህንነቱ ከክብሩና ከማንነቱ በላይ የሚያየውና የሚበልጥበት ነገር አይኖርምና አሁን በዚህ ሰዓት የማያውቀው፣ ቀድሞ ገንዘቡ ያላደረገው መልካም ነገር በድርድሩ ማግስት ይፈጠራል ብሎ አያምንም። ይህ ማለት፥ ለኢትዮጵያውያን ሞራል መጠበቅ ሲባል በይፋ የማይነገሩ ዳሩ ግን በኢትዮጵያ በኩል ተፈጻሚነት የሚኖራቸው በርካታ ስምምነቶች ሊደረሱ ይችሉ ይሆናል በዚህ ሂደት መስማማት ማለት ግን የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ጥቅም በየሚገፋ መደራደሪያ ነጥብ ላይ መደራደር ማለት አይደለም። የትግራይ ህዝብ የሚፈልገውን ያውቃል፥ ህግና ስርዓት ተከትሎም በጊዜው እውን ይሆናል በማለት በተጠንቀቅ በመጠባበቅ የሚገኝ ህዝብ ነው። ዓይንህን ጨፍን ላሞኝህ! ግን በትግራይ ዕድል ፈንታ ላይ ቦታ የለውም። በነገራችን ላይ፥ ይህ ሲባል አካሄዳችን እናስተካክል፣ ከዚህ ቀደም (ላለፉት 30 ዓመታት) ይጠቅመናል ተብሎ የሄድንበትና የመጣንበት መንገድ (ውድብ ብቻ ናት አዋቂ የሚል ኋላቀር አስተሳሰብ) ፈጀን እንጅ አልበጀንም ለማለት ተፈልጎ እንጅ በትግራይ ደረጃ

የፖለቲካ ባለስልጣናት አቅምና ጉልበት (ለጥፋት፣ ለድህነትና ለውድቀት) በመጠራጠሬ፤ አንድም፥ የትግራይ ህዝብ ደንቆሮ ነው ብሎ የሚያምን የትግራይ አመራር ዛሬም እንደለመደው በትግራይ ሰማዕታት ስም ሲያለቃቅስበት ይለፍ የሰጠው እንደሆነ መሻቱን አያገኝም ማለት ሲበዛ የዋህነት ነው። ውሎ አድሮ የሚከፋውና የሚበደለው ታድያ ሌላ ማንም ሳይሆን ህዝቡ ራሱ ነው።

እውነት ነው፥ የትግራይ ህዝብ ምርጫ በተመለከተ በደረቅ ማስረጃ የታጀበ ይሄው ለማለት የሚያስችል እስከ አሁን በይፋ የተሰራ ምንም ዓይነት ህጋዊ ቆጠራ የለም። ትግራዋይ ባለፈበት መንገድ ያለፉ እንደሆነ ግን (Public opinion) የትግራይ ዕድል ፈንታ በተመለከተ የትግራዋይ ምርጫ ነጻ ሀገረ ትግራይ! የሚል ነው። ለምን? አይደለም አዲስ አበባ ቀርቶ ትግራይ ውስጥም ቢሆን ምንም ነገር የሌለን ሰዎች ሰርተን ራሳችንና ሀገራችን መለወጥ እንደምንችል፣ ተግባብተንና ተከባብረን ለአንድ ዓላማ አብረን ከተሰለፍን፣ እርስበርሳችን ከተቀባበልንና እየተመካከርንም መስራት ከቻልን የትግራይ መጪ ዕድል ብሩህ እንደሆነ ስለምናውቅና በጽኑ ስለምናምን ነው። ይህን የምናምን ሰዎች ደግሞ እምነታችንና አቋማችን የምንገልጸው በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ በልበ ሙልነት ነው። በአንጻሩ፥ በግልጽ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና መቀጠል አለባት በማለት ሳይሆን “የትግራይ ህዝብ ይወስናል” የሚል ፈሊጥ ተጨምሮበት በገደምዳሜ ትግራይ ሰዋችንና ንብረታችን በግፍ ካጠፋችና ካወደመች ከኢትዮጵያ ጋር መቀጠል የሚፈልጉ ከመቶ ሺህ አስር የማይሞሉ ሰዎች ባይታጡም የእነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህቡእ ፍላጎታትና ምርጫ መሰረትና ምንጭም በጥንቃቄ የመረመርንና ያጠናን እንደሆነ እነዚህ ሰዎች በዋናነት፥ ጥቅማቸውና ስልጣናቸው ለመጠብቅ የሚሹ፤ ቀድሞ በነበረ የኢህአዴግ ስርዓት የስርዓቱ ዘዋሪዎችና ተጠቃሚዎች የነበሩና በዚህም ሀብትና ንብረት ያፈሩ፣ ሀብታቸውና ንብረታቸው በአዲስ አበባና አከባቢዋ የተያዘባቸው ሰዎች ሆነው እናገኛቸዋለን። የተረፉ ደግሞ ፥ በስተርጅናቸው የትግራይ ፊተውራሪዎች የመሆን ፍላጎትና ምኞት ያላቸው ስማቸው ቄስ ይጥራው ተብለው የሚተዉ እንደ አረጋዊ በርሀ ያሉ የቀድሞ የህወሓት መሪዎች ናቸው።

ዓይንህን ጨፍን ላሞኝህ በትግራይ ዕድል ፈንታ ላይ ቦታ የለውም

የፖለቲካ ፓርቲዎች ግዴታና ሃላፊነት፥ የትግራይ ብሔራዊ ጥቅም (ህልውናና ደህንነት) ያስጠብቃል፣ የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል፣ የትግራይ ህዝብ ጥያቄና መሻት ይመልሳል፣ የለውጥና የዕድገት መንገድ ይህ ነው ወዘተ ብለው የሚያምኑት እምነትና ሃሳብ በፕሮግራምና በፖሊሲ ደረጃ ቀርጸውና በሚገባ ሰንደው መቅረብና በጽሑፍም በቃልም በይፋ ሃሳባቸው ለሰፊው ህዝብ ማስተዋወቅ፣ ማሳመንና መሸጥ ብቻ ነው። የሚረባው የመምረጥና ይበጀኛል የሚለው እምነትና ሃሳብ የመያዝ ሆነ የማራመድ ጉዳይ በተመሳሳይ የእያንዳንዱ ትግራዋይ ምርጫ ይሆናል። ሲጀመር ይህ ማድረግ የማይችል ፓርቲ ለምርጫ የሚያበቃ (ይዞት የሚቀርብ) መወዳደሪያ ሃሳብ ከሌለው የሂደቱ ተሳታፊ ሊሆን አይችልም። ሰለዚህ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለስልጣን ሊያበቃቸው የሚችል (የፖለቲካ ፓርቲ መደራጀት በዋናነት ለስልጣን ነውና) ሃሳብና እምነት ማቅረብ ይጠበባቸዋል። ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣንና ውሱኑነት ሲሆን በተመሳሳይ አንድ ፓርቲ አርባ ዓመት ዕድሜ ይኑሮው አራት ዓመት ማንናቸውም ቢሆኑ የትግራይ ዕድል ፈንታ የመወሰን ስልጣን እንደሌላቸው ነው። ጥጉ፥ የመንግስት ሆነ የፓርቲ አመራር አባላትና ባለ ስልጣት የህዝቡ አካላት እንጅ የህዝቡ ፈጣሪዎች አይደሉም ሊሆኑም አይችሉም።

አሁንም፥ የህወሓት መሪዎች ጨመሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፓርቲ አመራር አባላት በር ዘግተው የፓርቲያቸው ውስጠ ጉዳይ በተመለከተ እንደ ፓርቲ ተጠቃሚዎች የሚያደርጋቸው መንገድና አሰራር ለማመቻቸትና ለማበጃጀት የሚረባቸው ውሳኔ ያስተላልፉና በውሳኔያቸው መሰረትም ወደ ስራ ይገቡ እንደሆነ ነው እንጅ የትግራይ ዕድል ፈንታ በተመለከተ የፓርቲ አመራር አባላት በር ዘግተው የሚውስኑት ሆነ የሚያጸኑት ውሳኔ የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ያስብበት ዘንድ ፈጣሪ የሰጠጣቸው አእምሮ መጠቀምን ትተው ሁሉም ነገር በሃይልና በጉልበት የማከናወን የላቀ ልማድና ባህል ያላቸው፣ በውሳኔዎቹ ሁሉ የተሸከመው ህዝብ ያገለለና የጣለ፣ ከተሰመረለት መስመር አልፎ ያለ ከልካይ ዥዋዥዌ ሲጫወት መስመር አልባ የሆነ አሰራር የፈጠረ የትግራይ አመራር፥ ትግራይ ዛሬ ለገባችበት ወጥመድ የዚህ ዓይነቱ አሰራና አመራር ውጤት ነው ብሎ ለማመንና ለመቀበል የሚዳግተው የለም ባይባልም እንደ ህዝብ ከደረሰብን ጥፋትና እልቂት ማምለጥ አለመቻላችን ግን ተጨባጭ ሐቅ ነው። አንድም፥ የትግራይ ህዝብ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል ታግሎና የልጆቹን ደም ገብሮ ያገኘው ዕድልና አጋጣሚ ተጠቅሞ ሰው የደረሰበት ዕድገትና ለውጥ መድረስ ሲገባው ለታገለለት ዓላማ ሳይሆን ለራሱና ለቤተሰቡ

ጥቅም መጠበቅ ያመቸው ዘንድ የፈጠረው መስመር አልባ አሰራርና አመራር እንዴት ወደኋላ እንዳስቀረንና ዛሬም ከሣላሳ ዓመታት በኋላ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ከማጣት የተነሳ የሚሰቃይ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆን ህዝባችንም መብራት ብርቅ የሆኖነት በኩራዝ የሚኖር ከመሆኑ በላይ የዛሬ አርባና ሰላሳ ዓመት የተፈጸመ ታሪክ ስናወራ ከድህነትና ከእጦት ያልተገላገለ ማህበረሰብ ተሸካሚዎች መሆናችን ተሰምቶን ለእውነት እንድንቆምና ዛሬ አንድ ነገር እንድናደርግ ህሊናችን የማይወቅሰን ሰዎች ከሆን ነፍስ ይማር ማለት ብቻ ነው የምችለው።

በተረፈ፥ የትግራይ ህዝብ በህግና በስርዓት የሚያምን ህዝብ ቢሆንም ህግና ስርዓት ከማይገዛት ኢትዮጵያ የሚጠብቀው አንዳች መልካም ነገር የለውም። ኢትዮጵያ ወዳና ፈቅዳ ለትግራይ የምታደርገውና የምትሰጠው ምንም ዓይነት መልካም ነገር የለም። ትግራዋይም ቢሆን ኢትዮጵያ ወዳና ፈቅዳ ይህን ነገር ትሰጠኛለች ያንን ታደርግልኛለች ብሎ በህልሙም በውኑም አያስበውም፤ አይጠብቅምም። ለመሆኑ ኢትዮጵያና ትግራይ ምን የሚያገናኝ ነገር ቢኖራቸው ነው ኢትዮጵያ በትግራይ ጉዳይ ላይ ድምጽ ሊኖራት የሚችለው? እነዚህ ሁለት ህዝቦች ከተፋቱና የየራሳቸው መንገድ መጠብጠብ ክጀመሩ ዓመታት አልፏል። ኢትዮጵያ ትግራይ የግዛትዋ አካል እንዳልሆነች ስለማታምምንና ለብሔራዊ ጥቅምዋም ስጋትና አደጋ ነች ብላ ስለደመደመች አይደለም ወይ ከጉረቤት አገራትና መንግስታት ግንባር በመፍጠር የወረረቻትና በትግራይ ህዝብም በሰብአዊነት የሚፈጸም የጦር የዘር ጭፍጨፋ የፈጸመችው? በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ውስጥ በልዩ ለዩ ምክንያት የእርስበርስ ጦርነት መቀስቀስና ማካሄድ ያለነ የነበረ በዚህ ሂደት ያላላፈ አገርና መንግስትም ይኖራል ተብሎም አይታመንም። ኢትዮጵያ በትግራይ ላይ የፈጸመችው ወረራና ያካሄደችው ጦርነት ግን በዓለማችን ታሪክ ከዚህ ቀደም የተከሰተ እንደሆነ ለማወቅና ለመማር ዝግጁ ነኝ። ኢትዮጵያ በትግራይ ላይ የከፈተችው ጦርነት በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች የሚደረግ የእርስበርስ ጦርነት ሳይሆን ኢትዮጵያ በትግራይ ላይ የፈጽመችው ጦርነት የጎረቤት አገራትና መንግስታት ጋብዛ የፈጸመችው በመሆኑ በዓይነቱ በታሪክ የተለየ ያደርገዋል። ቢገባንም ባይገባንም ትግራይ ሆነች የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ልብ የጠፋ ግዛትና የከሰመ ህዝብ ነው። ያልነጠፋነው ከትግላችን የተነሳ ነው። ይህ ኩልል ቅልብጭ ያለ ሐቅ መረዳት የሚያቅተው ትግራዋይ ይኖራል ተብሎም አይታመንም።

ባለቀ ጉዳይ ላይ ሐተታ?

መውደቅህ አይቀር አወዳደቅህ አሳምርህ እንድትወድቅ እንጅ ባለቀ ጉዳይ ላይ ማተት ትርጉም አለው/ይኖሮዋል ባይ ስለሆንኩ አይደለም። በዕድሜም በአስተሳሰብም ያረጀ ግለሰብና ቡድን በህይወቱ መጨረሻ የሚፈልገው ነገር ቢኖር ማንኛውም ነገር ከፍሎ (ሀገርና ህዝብ መስዋዕት ማድረግ ካለበትም ይህን በማደርግ) ፍርሃቱ እንዳይውጠው መከላከልና ሞቱን ማሳመር ነው። በትግራይ አመራር ውስጥ አሁን በዚህ ሰዓት በተጨባጭ እየሆነ ያለና የሆነም ነገር ቢኖር ይህ ነው። ላለፉት 30 ዓመታት የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሳዊ መብት አሳጥቶ፣ በህዝቡና በሰማዕታቱ ስምና ሽፋን ህዝብና አገር እያጭበረበረና እያደናገረ ሀብትና ንብረት ያፈራ የህወሓት መሪዎች የፊውዳል-ኦሊጋርክ ቡድን የመጨረሻ ፍላጎት የትግራይ ህዝብ የልጆቹን ህይወት የገበረለት ዓላማ መሳካትና ከግቡ ማድረስ ሳይሆን ፓርቲው በግለሰብና በቡድን ደረጃ ለዘመናት ከዘራው ሃጢአት የሚተርፍበትና በህይወት የሚኖርበት መንገድ ነው የሚፈልገው። ይህ የበሰበሰ አመራር በየትኛውም መድረክ አንገቱ ቀና አድርጎ የሚሄድበት ስብእናና ታሪክ ስለሌለውም በዚህ ሰዓት በትግራይ ህዝብ ስምና ሽፋን ዘመኑን ለማራዘም እያደረገውና እየሰራው ያለ ቆሻሻ ስራ ይህ ነው። በስተርጅናቸው የሚወስዱት ሃላፊነት አይኖርምና የሚኖራቸው አማራጭ የታዘዙትን ማለትም የትግራይ ህዝብ ድምጽ በማፈን አዲስ ሜክአፕ ቀባብተው ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆኖ እንድትቀጥል በመስማማት ቀሪ ዘመናቸው በተሰጣቸውና በሚሰጣቸው ዋስትና ተጠለው መኖርን መርጠዋል። የትግራይ ህዝብ፥ ለህልውናውና ለደህንነቱ ለክብሩና ለማንነቱ ያፈሰሰው ደም – ደመ ከልብ በማድረግ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የስልጣን ባለቤት ሆኖ መቀጠል። ኢትዮጵያም ሆነች ከዚህ ሁሉ አመጽና ሴራ ጀርባ ያሉ አካላት ደግሞ በዚህ ዓይነቱ አረንጅመን ደስተኞች ናቸው። ይህ ዓይነቱ ሽር-ብትን ታድያ የትግራይ መጨረሻ ነው የሚል እምነት የለኝም። በሌላ አባባል፥ የትግራይ ህዝብ ጥያቄና መሻት አገር መሆን ከሆነ፥ አሁንም በሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል የሚል እምነት የለኝም። አድርጉ የተባሉት ሁሉ ያለ አንዳች መቅማማትና ጥያቄ ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ የሌላቸውና ሊኖራቸውም የማይችሉ አቅመ ቢስ ግለሰቦችና ቡዱኖች ዘንድ ነገሩ የተቆረጠ ቢሆንም፥ ትግራዋይ፥ ለእኔ የሚረባኝን የማውቀው እኔ ራሴ ነኝ በማለት ለመብቱ በመቆም መሻቴ ሀገረ ትግራይ ነው! ከዚህ ያነሰ እሺ በጀ ብዬ የምቀበለው ሌላ ምንም ዓይነት የስምምነት ነጥብ

የለኝም ብሎ ወጥሮ ከያዘና ለዚህም መክፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ከተዘጋጀ መሻቱ እንደሚያገኝ ምንም ጥርጥር የለኝም።

ትግራዋይ ሁሉ ከእንቅልፉ ነቅቶ ለሞተለት ዓላማ እስከ መጨረሻ የቆመ እንደሆነ፥ በስሙና በሰማዕታት ስም እየተማማሉ ለጥፋቱ እየተባበሩ የሚገኙ፥ ከሞትና ከእስር ያመለጡ መሪዎች ያሸንፋቸዋል እንጅ አይሸነፉትም። ሰዎቹ ይህን ስለሚያውቁ ታድያ የትግራይ ህዝብ ለማንበርከክ፣ በመንግስትነት ስምና ሽፋን ከሚሸቃቅጡት አጀንዳ ጋር እንዲስማማ፣ ሃሳባቸው ደግፎ እንዲቆም፣ ተቃውሞ እንዳያሰማ ሴራቸው በቀጣይነት በህዝቡ ላይ ተፈጻሚ ከማድረግ ወደሃላ አላሉም። ይኸውም፥ ኢትዮጵያን በቀጣይነት ተጠያቂ በማድረግ የትግራይ ህዝብ በቀጣይነት ማስራብ ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ከወንጀል ንጹሕ ናት ማለት ሳይሆን ይልቁንም ይህን እያደረገ ያለ ወንጀለኛ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ውክልና አለኝ የሚል አመራር ጭምር መሆኑ ለመግለጽ ነው። ኢትዮጵያና ኤርትራ የትግራይ ህዝብ እህልና መድሃኒት እንዳያገኝ 360 ዲግሪ ቆልፈው የያዙትበት አንዱ ምክንያት ትግሉን ለማዳከም፣ ከዚህ የተነሳም እጁ እንዲሰጥ፣ ለጥቆም የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ በረሀብ በበሽታና በችጋር እንዲያልቅ ነው። የህወሓት መሪዎች የትግራይ ህዝብ ለመብቱ እንዳይቆም ማዳከም የሚችሉበት አንዱና የተፈተነ መንገድ ይህ ነውና በህዝቡ ላይ እየፈጸሙት ያለ ወንጀል ያለ ይህ ነው። ነገሩ፥ ሄኔሪ ኪሲንጀር ከዘመናት በፊት፥ “ዓለምን ለመቆጣጠር ነዳጅ፤ ህዝብ ለመቆጣጠር ምግብን መቆጣጠር ነው” እንዳለው ነው።

ትናንት፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊን የሾመችው አሜሪካ ናት፣ በውስጠ ጉዳያችን ገብታ ኢህአዴግን ያፈራረሰችና እኛን ያባረረችን አሜሪካ ናት፣ ለቻይና በር ስለ ከፈትንና ከቻይና ጋር ወዳጅነት በመፍጠራችን ቂም ቋጥራ አመጽ ያስነሳችብን አሜሪካ ናት! ወዘተ እያሉ አሜሪካን በይፋ በአደባባይ ሲከሱና ተጠያቂ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ተገልብጠው፥ አሜሪካ ያልባረከችው ጉባኤ የለንበትም፣ አሜሪካ የሌለችበትና የማትገኝበት መድረክ አንገኝም፣ ያለ አሜሪካ መገኘትና ዳኝነት አንዳኝም፣ ዳኛችን አሜሪካ ናት! ለማለት የበቁበት ምክንያት ምንድ ነው? ብለህ መጠየቅ ካልቻልክ፥ ስስታም የትግራይ አመራር ቻውን ሲሮጥ በሚፈጽመው ተደጋጋሚ ስህተት ዘልአለም ልጆችህ እየገበርክ ሞቱን ስትሞትለት በመጨረሻም ፖለቲካዊ ሽንፈት መከናነብ መታወቂያህ እንደሆነ ትኖራለህ። ከነቃህ መንቃት አሁን ነው። በነገራችን ላይ፥ የእነዚህ ሰዎች በዚህ ደረጃ መገለባበጥ የፖለቲካ እውቀት ወይም ችሎታ ሳይሆን ዝቅጠት፣ ራስ ወዳድነትና ራዕይ አልባነት የሚፈጥረው መንቀዥቀዥ ለመሆኑ ለሁሉም ግልጽ ሊሆን ይገባል። በፖለቲካው ዓለም/መድረክ አቅም ማጣት ከሚገለጥባቸው ባህሪያት አንዱ የዚህ ዓይነቱ መብረክረክና ቀላዋጭ ጸባይ ነው። ሃያላኑ እንደሆነ የሚፈልጉት ነገር እስካገኙ ድረስ ሚድያ ላይ እየወጣህ ዘራፍ፣ ዘራፍ አካኪ ዘራፍ! እያልክ ብትፎክርና ብትቀደድ ጉዳያቸው አይደለም። እንደውም ይህን ታደርግ ዘንድ ያበረታቱሃል። የሚፈልገውን የሚያውቅ ህዝብ ታድያ በዚህ ሁሉ ወከባና ሴራ አይደናገርም።

በመጨረሻ፥ ኢትዮጵያን በመቀራመት ረገድ ከዕለት ወደ ዕለት ተጽዕኖአቸው እየጨመረና እየበረታ የመጣ የቻይናና የራሽያ መንግስታት ለሌላው ሃይል ከፍተኛ የሆነ ስጋት በመፍጠራቸው ይህ ሃይል የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አደብ ለማስያዝና አማራጭ ለማሳጣት ልክ እንደ ዩክሬይንና ታይዋን ትግራይ እንደ ልጓም የመጠቀም አሰራር ከሞትና ከእስር ያመለጠ የህወሓት አመራር ከመታደጉ በላይ (ስለሚቀበልዋቸውና ስለሚደግፏቸው አይደለም ዳሩ ግን የሰው አገር አጀንዳ ለማስፈጸም ጠቃሚዎች በመሆናቸው እንጅ) ይሄው የፓርቲው የበላይነት በመገንባት ትግራዋይ ለሞተለት ዓላማ ሳይሆን የምዕራቡ ዓለም የሚረባቸውና የሚፈልጉትን ለማድረግና ለማግኘት በጥድፊያ ላይ ይገኛሉ። በነገራችን ላይ፥ የምስራቅ አገራት ተጽዕኖ በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ በሙሉ የበላይ እጅ ካገኘ የምዕራቡ ዓለም የትግራይ አገር የመሆን ጥያቄ በመደገፍ ከትግራይ ህዝብ በላይ ነገሩን ማቀንቀናቸው የማይቀር ነው። በዚህም ልንደነቅ አይገባም። የህወሓት መሪዎች የትግራይ አገር መሆን ሲሰሙ የሞት ያህል የሚከብዳቸው ያለም አጀንዳው ለጌቶቻቸው ስለማይጥም ሲሆን እነዚህ አካላት የትግራይ የሀገራዊነት ጥያቄ በማራገብ የሚጠቀሙ ከሆነ ደግሞ የህወሓት መሪዎች 45 ዓመታት የታገልነት ነው የሚል አቧራ የበላይ ፋይሎቻቸው እያገለባበጡ ትግራይ ወይ ሞት ማለታቸው የማይቀር ይሆናል። ለጊዜው ግን የተሰጣቸው ትዕዛዝ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና እንድትቀጥል የትግራይ ህዝብ ድምጽ ማፈን ነውና ይህን በማድረግ ላይ መጠመዳቸውን አውቀን አወዳደቃችን ልናሳምር ይገባል ለማለት እወዳለሁ።

By aiga