ሙሉጌታ ወልደገብርኤል (ክፍል አንድ)
የጽሑፉ ዓላማ፥ ትግራይ እንደ ማህበረሰብ ድህነትና ጦርነት ያደከመን ህዝብ ነን። ለዘመናት በላያችን ላይ ከሰለጠነብን የሰቆቋ ህይወት መውጣትና ሰው የደረሰበት መድረስ የምችለው ታድያ እንዲሁ እየተሸናገልን ሳይሆን ድካማችንና ችግራችን በሚገባ አውቀን ችግራችን ስንተረጉመው፣ ለመፍትሔውም ምን እናድርግ? ተብሎ እርስበርሳችን ስንነጋገርና ስንመካከከር ነውና ለመፍትሔ ተጻፈ።
የጽሑፉ ውሱኑነት፥ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትና ዓላማ ሙሉ በሙሉ የትግራይ የውስጥ ችግር (በተለይ በታሪክ በትግራይ አመራር የሚስተዋለው ተደጋጋሚ ደካማ ባህሪያት) የሚዳስስ፣ በተነሳ ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶም አጭርና መሰረታዊ የመፍትሔ ሃሳብ የሚያካፍል ጽሑፍ ነው። ይህ ማለት ግን የትግራይ ጥፋትና ውድመት የሚመነኙ በትግራይ ዙሪያ የሚገኙ የትግራይ ህዝብ ጠላቶች የሉም የሚል አንድምታ የለውም። የውስጣችን ችግር የፈታን እንደሆነ ዘልአለም የማይተኝሉን፣ ቅናትና ምቀኝነት ያሳረራቸው የቅርቡም የርቁም ጠላቶቻችን መልዕክቱ ይደርሳቸዋል ነው። “የትግራይ ህዝብ ጠላት ህዝብ ነው” ብለው በጎረቤት አገራትና መንግስታት ጀርባ ላይ ታዝለውና ተንጠላጥለው የመጡ ወራሪ ሃይሎች እናውቃቸውለን ደግሞም በሚገባቸው ቋንቋ አናግረናቸውል እያናገርናቸውም ይገኛል። በተረፈ፥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የትግራይ የውጭ ጠላቶች እምነትና ስትራቴጂ መዳሰስ ጸሐፊው ጊዜ ከማባከን ያለፈ ሌላ ትርጉም የለውም አይኖረውምም አስፈላጊነቱም እጅግ አነስተኛ ብሎ ያምናል።
የጽሑፉ ይዘት፥ በጽሑፉ ውሱኑነት እንደተገለጠ የጽሑፍ ትኩረትና ዓላማ ሙሉ በሙሉ የትግራይ የውስጥ ችግርና መፍትሔው ያተኮረ ሲሆን ጽሑፉ በይዘቱ በሁለት ዓበይት ጉዳዮች የሚያጠነጥ (አመራርና ህዝብ) በአራት ክፍሎች ተከፍሎ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው።
ክፍል አንድ፥ ዋና ርዕሳችን የሚያስተዋውቅ፣ አጠቃላይ ግንዛቤ የሚያጨብጥና የሚዳስስ ይሆናል፤
ክፍል ሁለት፥ የምን ንስሃ ነው፣ ነገሮችን በለመደነው መንገድ ለማስኬድ በቀድሞ ማንነታችን ተመልሰን መጥተናል! ትናንትም ዛሬም የነበረን ነገም የምንኖረው እኛ ብቻ ነን! እያሉን ያሉ ስም ብቻ ይዘው የቀሩ የህወሓት መሪዎች የፖለቲካ አጀንዳ ዓላማና ተልዕኮ የሚዳስስ ሲሆን፥ “የህወሓት መሪዎች ከትግራይ የፖለቲካ መድረክ መወገድ አለባቸው” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ነው።
ክፍል ሦስት፥ “የትግራይ ጀኔራሎች- ህወሓት ወይ ሞት! የሚሉበት ያሉ ምክንያት ምንድ ነው?” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን “የጀኔራሎቹ” ለህወሓት መሪዎች የሚያሳዩት ያለ ያልተገራ ወገንተኝነትና ፖለቲካዊ አቋም በትግራይ ፖለቲካ የሚፈጥረው መቃወስና በትግራይ ህዝብ መጻኢ ዕድል ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያስነብብ ይሆናል።
ክፍል አራት፥ “እንደ ህዝብ ድካም አለብን፤ ድካማችንም አውቀን እናስተካከል” የሚል ሲሆን ጽሑፉ እጅግ አጭርና ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ታስቦ የተዘጋጀ ጽሑፍ ይሆናል።
ማሳሰቢያ፥ የጥበብ ወዳጆች “የእውነት መጨረሻ ቁጣ ነው” እንዲሉት እውነት ሲነገር ጸጉራቸው የሚነጩና ፊታቸው የሚባጭሩ የሉም አይባልም። ጠንካራ ጎኑና አውንታዊ ገጽታው ብቻ ማንበብና መስማት የለመደ፣ ያልተገባ ስግደትና ክብር ያሳበጠው ግለሰብና ቡድን የማንነቱ አካል የሆነ ጉልህ/የተገለጠ ድካም፣ ግድፈቶቹና ስህተቶቹን የመስማት ፍላጎት ስለሌለውና ላይኖረውም ስለሚችል ጽሑፉ በይዘቱ ሁሉም ያስደስታል ተብሎ አይጠበቅም። ዓይኔን ግንባር ያድርገው! እያሉ እውነትን መሸጠና መለወጥ የለመዱ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲሁም የእነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ተላላኪዎችና ፍርፋሬ ለቃሚዎች እውነት ሲነገር ስለሚያከስራቸውና ቁልቁል ስለሚሰዳቸው “ጊዜው አይደለም፣ ይህ ከፋፋይ ሃሳብ ነው፣ ትግሉን ለማዳከም ሆነ ተብሎ የተሸረበ ሴራ ነው” ወዘተ እያሉ ዘራፍ ማለታቸው የማይቀር ነው። በመሆኑም፥ ጸሐፊው ስለ ህወሓት መሪዎች አስመልክቶ የሚያነሳቸው ነጥቦች ከሞላ ጎደል የግሉ እምነትና አስተሳሰብ ሳይሆን ፓርቲው ራሱ ከዚህ ቀደም “ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌለሁ” ሲል የበሰበሰ ማንነቱ በማስመልከት በይፋ የሰጠው መግለጫ መነሻ ያደረገ ለመሆኑ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ከዚህ ጋር በተያያዘ፥ ማንም ሰው ማየትና መስማት የሚፈልገውን ብቻ የማየትና የመስማት መብት አለው። መብቱን ተጠቅሞና ምርጫውን ተከትሎ ለሚመጣ የህይወት ስብራትና ኪሳራ ግን የመምረጥ ሆነ የማምለጥ ምርጫ የለውም። በመሆኑም፥ በዚህ ሰዓት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ስንወያይ ለህወሃት መሪዎች ይሁን ለፓርቲያቸው እንዲሁም ለሌሎች አካላት ያለንና ሊኖረን የሚችል ማንኛውም ዓይነት ውግንና መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል ይህን ጽሑፍ ስናነብ የሚባለው ያለ እውነት ነው እውነት አይደለም? በማለት መመርመርና መጠየቅ እንጅ ዘራፍ ማለትን እንድንተው ሳሳስብ በአክብሮት ነው።
መንደርደሪያ፥ ማንም ይሁን ምን የሰው ኃይማኖታዊና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተሳሳተ ለመሆኑ ለማሳየት፤ በሌላ አነጋገር፥ ሰው ይህ የእኔ ነው ብሎ ቀድሞ የያዘው ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ እምነትና አስተሳሰብ ለማስጣልና ለመለወጥ ታስቦ ስፍር ቁጥር የሌለው ምክንያታዊና ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ በማቅረብ ብንሞግተውም ዓለትን ውሃ የማጠጣት ያህል ከንቱ ድካም የሚሆንበት አንዱ ምክንያት፥ ሰው መስማት የሚፈልገው ብቻ መርጦ የመስማት ባህሪያዊ ዝንባሌ ስላለው ነው። አይሁድ ኢየሱስን “ይህስ የሳደባል” እንዳሉት (ማቴ 9፥3)፤ ይህን የመሰለ የሰው ድካምና ባህሪይ እያውቁ እውነት ለመናገርና ለመምስከር በመቁረጥ አፍዎን የከፈቱ እንደሆነ ደግሞ፥ ዊልያም ሼክስፔር “የእውነት መጨረሻ ቁጣ ነው” ሲል እንደ ተናገረው የአድማጭ ሰላም መንሳትዎና ግጭት ውስጥ መግባትዎ አይቀሬ ነው። በርግጥ ሰው ሁሉ እውነቱ ሲሰማና ሲነገረው፥ ተነካሁ ብሎ ይበሳጫል፣ ይናደዳል፣ ይቆጣል፣ ግርግር ይፈጥራል፣ ለጥቆም ካልገደልኩት! ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል ማለት አይደለም። በግሌ ይህ አባባል እውነት ቢሆንም ለሁሉም የሚሰራ አባባል ነው የሚል እምነት ግን የለኝም። ምክንያቱም፥ እውነቱ ሲነገረው ሁሉም ሰው ያኮርፋን፣ ይቆጣል ማለት አይደለምና። በአንድም በሌላም መንገድ ከውሸት ጋር ሲተሻሽ፣ ውሸትን የእውነት ያህል ተቀብሎ በውሸት ዓለም የሚመላለስ ሰው እውነት የመስማት ዕድልና አጋጣሚ ሲያገኝ፥ ነው እንዴ? አላወቅኩም ነበር፣ ያን ሁሉ ዘመን ስኖር ይህ ነገር በዚህ መልኩ አይቸው አላውቅም ነበር፣ ይህ ዓይነቱ ጥያቄ በማንሳት ይህን ነገር በዚህ መልኩ ለመመርመር ራሴን ጠይቄም አስቤውም አላውቅም ነበር፣ ለዚህ ያህል ዘመን እንዴት ልታለል እችላለሁ፣ ይህ ሁሉ ዘመን በውሸት ነው እንዴ ስደግፍና ስኖር የኖርኩ?፣ ለካ እንዲህ ያለ እኔ የማላውቀው መጥፎ ባህሪይ ተሸክሜ ኖሬአለሁ! በማለት የሚጸጸት፣ ከስህተቱ ለመማር በጎ ፈቃድ የሚያሳይ፣ ትክክለኛ ነገር ለማድረግ እንቅልፍ ተኝቶ የማያድርና የቀድሞ አስተሳሰቡ ወደኋላ ትቶ አዲስ ህይወት አዲስ መንገድ ለመጀመርና ለመቀላቀል የሚናፍቅ ብዙ እውነት የተጠማና እውነት ፈላጊ ቅን ልብ ያለው በርካታ ሰው አለ ብዬ ስለማምን ነው። ቀጥሎ በሚነቡ የትግራይ መሰረታዊ ችግርና የመፍትሔ ሃሳብ፥ በንባቡ ተቆጥተው ይራገማሉ ወይስ ያነቡትን ይዘው ራስዎን ይመረምራሉ? የሚለው ጥያቄ ለእርስዎ ልተዎውና ወደ ንባቡ ላዝግም።
ችግር አለብን፤ ችግራችን ደግሞ ሚካኤል ወይም ገብርኤል መጥተው አይነግሩንም
ትግራዋይ ሆኖ ትግራይ ውስጥ “ችግር የለም!” የሚል ሰው ይኖራል ተብሎ አይታመንም። ምናልባትም ትግራይ ውስጥ “ችግር የለም፣ ሁሉም ነገር ሰላም ነው፣ ገነት ነው!” የሚል ሰው/ቡድን የተገኘ እንደሆነም ይህ የሚለው አካል በሌሎች ህመምና የልብ ስብራት ላይ ቤቱን የገነባ፣ የሰው ህመም ስቃይና ሃዘን ምኑ ያይደለ፣ የደላውና በድሃ እንባ የደለበ ሰው (ቡድን) ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ትግራይ ውስጥ ችግር አለ የለም ተብሎ ለሞገትና ለክርክር የሚቀርብ ርዕስ ሳይሆንም ትግራይ ውስጥ በድህነትና በጦርነት የታጀበ ችግር አለ፤ ዘመናት ያስቆጠረ፣ እንደ ህዝብ ያደቀቀንና ያጎበጠን ያለ ምህረትና ርህራሄም እየፈጀን ያለ ስር የሰደደ ችግር የማይገልጸው በሽታ አለ። ጥያቄው፥ የችግሩ ምንጭ ምንድ ነው? እንዴትስ ልንፈታው እንችላለን የሚል ነው።
ቀደም ሲል በጽሑፌ ዓላማ እንዳሰፈርኩትም፥ አለ ተብሎ የሚታመነውና በተጨባጭ ያለው ችግር መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው ችግር አለብን ችግራችን ለመፍታት ደግሞ እርስበርሳችን እንመካከር ሲባል በይሉኝታ ተይዘን ከአንገት በላይ በሆነ አቀራረብ ለመሸናገል ሳይሆን እውነት እውነቱን ተነጋግረን ለመፈወስ ነውና በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በዋናነት የትግራይ ነባሩ አመራርና አስተሳሰቡ እንዲሁም የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ በባህል ደረጃ የእኔ ነው ብሎ የያዘው አደገኛ አስተሳሰብ እንመረምራለን። ወደ ምርመራው ከመዝለቄ በፊት ግን፥ የምትለው ያለኸው ችግር ቅዱስ ሚካኤል ወይም ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ካልነገረኝ/ን፣ ለእኔ የማይታየኝ ለሌላ ሰው ግን የሚታው ተጨባጭ ችግር ብትጠቁመኝ/ን አልሰማህም እንሰማህም፤ በተለይ አንተ ስትነግረንና ስትጠቁመን አንተ የምትነግረንና የምትለው የመፍትሔ ሃሳብ ሰምተንና ተቀብለን ከምንፈወስና ከምንተርፍ ገደል መግባት እንመርጣለን! ባዮች ከሆንም ምርጫችን ስለሚሆን እዚህ ላይ ሃሳቡን ከማካፈል የዘለለ ስሙኝ ብሎ የሚናገር ሰው እንደሌለ ማወቁ አስፈላጊ ነው ለማለት እወዳለሁ። አሁንም ቢሆን፥ ችግራችን ሚካኤል ወይም ገብርኤል መጥተው አይነግሩንም።
ምርመራ
የትግራይ የአስተዳደር ብልሹነት የሚመነጨው ከምዕራብ ወይም ከምስራቅ በሚመጣ ሃይል ሳይሆን ትግራይን ያኮሰሰ በዋናነት በአንድም በሌላም መንገድ የትግራይ ፖለቲካ በፈላጭ ቆራጭነት የመምራት ዕድልና አጋጣሚ የሚገጥማቸው ባለስልጣናት፤ አንድም፥ በፖለቲካ ሥልጣን ላይ የሚቀመጡ የአመራር አባላት ኢ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የሚመነጭ ስስትና ራስ-ወዳድነት የማይገልጸው አደገኛ ባህሪይ ነው። ከሰው በፊት የነበረ ህዝብ የሰው መጨረሻ ያዳረገው ከምንም በላይ በሁሉም ዘመናት የተነሱ የትግራይ የፖለቲካ አመራር ብልሹ አስተሳሰብ ነው። ይህ ዓይነቱ ችግር ደግሞ ለጠላቶቻችን የምናሸክመው ጣጣ ሳይሆን የራሳችን የውስጣችን የአመራር ችግር ነው። የጥንቱም የዛሬውም የትግራይ ችግር ምንጩ በድሃ ማህበረሰብ መሰልጠን የሚያምርበት ራዕይ አልባው የትግራይ አመራር ነው። ትግራይ ውስጥ የነበረና ያለ አመራር ነባራዊ ሁኔታ ይህ ነው።
የራሶች፣ ፊታውራሪዎች፣ ቀኛዝማቾች፣ ግራዝማቾችና ብላታዎች ዘመን ትተን የቅርቡን እንመለከት። የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በኢሳይያስ አፈወርቂ የሚመራ የኤርትራ አውራ ፓርቲ አስመልክተው እንዲህ ብለው ነበር፥ “ለኤርትራ ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚታገል ድርጅት ሳይሆን አሁን ስልጣን ይዞ ህዝብን እየጨፈጨፈ ያለ መንግስት ነው” ሲሉ ነበር የገለጹት። አቶ መለስ ዜናዊ የእኔ ዓይነቱ ለማንኛው የፖለቲካ ፓርቲ ያላደረ፣ እውነትን እውነት ውሸትን ደግሞ ውሸት የማለት ችግር የሌለበት ነጻ ሰው ቢሆኑና ስለ ህወሓት መሪዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ቢቀርብላቸው በእርግጠኝነት የሚሰጡት መልስ “ለትግራይ ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚታገል ድርጅት ሳይሆን አሁን ስልጣን ይዞ ህዝብን እየጨፈጨፈ ያለ መንግስት ነው” ማለታቸው የማይቀር ነው።
ላለፉት 30 ዓመታት እንደ መዥገር ጀርባችን ላይ የተጣበቀ፣ በአፉ ፍትህና ዲሞክራሲ እየሰበከ በመስዋዕትነት የተገኘ ፍትሕና ዲሞክራሲ ያሳጣን፣ ዛሬም ከዚህ ሁሉ ሞትና ዕልቂት በላኋም ቢሆን ለህዝቡ ምህረትና ርህራሄ ማሳየት የተሳነው፣ በሞት ካልተሰበሰበ በቀር በንጹሐን ህይወት መቆመር የማይተው የትግራይ ብቸኛ ገዢ ፓርቲ (የህወሓት መሪዎች) ትግራይና የትግራይ ህዝብ ማዕከል/መነሻ ያደረገ ዓላማ፣ ራዕይና ህዝባዊ አጀንዳ የሌለው አመራር በመሆኑ ጥፋታችን ለለውጥና ለዕድገት እንዳንጠቀምበት ይሄው የአመራሩ የግልና የቡድን ጥቅምና ስልጣን ለማስጠበቅ ይቻለው ዘንድ ህዝቡን ከኪና ሽርጥ እያለበሰ በዘፈንና በድራማ አስክሮ ዘልአለም ቁስላችን እያከክን እንድንኖሮ ለማድረግ ወጥመድና መሰናከያ ሆኖ ለመቀጠል ራሱን እያዘጋጀ ይገኛል። ይህ ምላሱ እስኪደማ ድረስ ዲሞክራሲ! ዲሞክራሲ! በማለት የሚታወቀው ልቡና አእምሮው በጸረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የጠቆረ ላለፉት 30 ዓመታት የሰለጠነብን የህወሓት መሪዎች አመራር (Totalitarianism) እስስታዊ ባህሪይ ከርዕሳችን በተያያዘ ከብዙ በጥቂቱ እንመለከት።
ይህ አመራር በዋናነት ከሚታወቅባቸው ጸባያት አንዱ ያለ ማቋረጥ የሚያሰማው ክስ ሲሆን ሻዕቢያና ኢትዮጵያ እያነሳ የሚያነሳቸው ነጥቦችና የሚያሰማቸው ክሶች በጥንቃቄ እንመርምር። የህወሓት መሪዎች በሻዕቢያና በኢትዮጵያ የሚያሰሟቸው ክሶችና አቤቱታዎች መቶ በመቶ እውነት ናቸው። ሌላ እውነት ደግሞ ምን እንደሆነ ያውቃሉ? የህወሓት መሪዎች አመራር በተለይ በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሱት አስተዳደራዊ በደልና ባርነት በተመሳሳይ ሚዛን ያስቀመጥናቸው እንደሆነ የህወሓት መሪዎች በትግራይ ህዝብ የፈጸሙትና እየፈጸሙት ያለ ወንጀልና የፖለቲካ ሴራም በተመሳሳይ እውነት ነው። የህወሓት መሪዎች በሌሎች ላይ ክሳቸው ሲያሰሙ የሚያሰሙት ክስ የተዋጣለት ያደረገው አንዱ ምክንያትም ሰዎቹ (የህወሓት መሪዎች) ለክሱ ዓይነት ቅርብ ስለሆኑና እነሱም በተመሳሳይ እንወክለዋለን በሚሉት ህዝብ ላይ የሚያደርሱት አስተዳደራዊ ግፍና በደል የማይገልጸው ጭቆና ጠንቀው ስለሚያውቁ ነው።
አሁን አንስተን የምንመለከታቸው የምርመራ ውጤቶች እንደ ሰናፍጭ ፍሬ ከመሆናቸው የተነሳ ከዚህ ቀደም በይፋ መወያያ ርዕስ ሆኖው አያውቁም ግን ደግሞ የትግራይ ህዝብ ልብና ኩላሊት ያቆሰሳሰሉና ያደሙ ናቸው። በተጨማሪም፥ የአመራሩ የግለሰብና የቡድን ጥቅምና ስልጣን የማስጠበቅ ተልዕኮ እንቅፋት ሳይገጥመው ለማስቀጠል በሚያስችለው መንገድ ትግራይ ውስጥ ተግባራዊ ካደረጋቸው ሴራዎች መካከል አንዱ የትግራይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉ ሲሆን ይህን ለማድረግም በተጋሩ መካከል አድሎ በመፍጠር ተሳክቶላቸዋል።
ኢትዮጵያ፥ በትግራይ ላይ የምትከተለው የማግለል ፖሊሲ፣ የሀብትና የስልጣን ክፍፍል አድሎ ሁሉ ትግራይ ውስጥ በእኛ በተጋሩ መካከል ያለና በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋ በሽታ ነው። ትግራይ ውስጥ ሁላችን ተጋሩ ከመሆናችን ያለፈ ሁሉም ትግራዋይ እኩል የስልጣንና የኢኮኖሚ ተካፋይና ተቋዳሽ አይደለም። ይህ የምለው የትግራይ የፋይናንስ፣ የጸጥታና የፍትሕ ተቋማት ያለው ዓይኑ ያፈጠጠ አድላዊ አሰራር ሳይጨምር ነው።
ትግራይ፥ በኢትዮጵያ ላይ ስታነሳውና መከበርና መጠበቅ አለብት ብላ ስትሞግት የመጣችው ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄ ነው። በአምስት ዞኖች የተከፋፈለች ትግራይ ግን ህዝቡ በመረጠው በአከባቢው ሰው እንዲመራ አይፈቀድለትም። ላለፉት 30 ዓመታት ትግራይ የገዛ ማዕከላይ ኮሚቴ የሚባለው ኮሚኒስታዊ አደረጃጀት የትግራይ ዞኖች ሁሉም እኩል አስተዋጽዖና ተሳታፊነት ኖሮት አያውቅም። በተለይ ፖሊት ቢሮው ሆድ ይፍጀው ነው። ፓርቲው “ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌለሁ” ሲል በሰጠው ቃለ ኑዛም በፓርቲው ውስጥ ከባቢያዊነት ክፉኛ መንሰራፋቱን አምኖበታል። ይህ የከባቢያዊነት በሽታ ታድያ ሁሉም የትግራይ አከባቢ የሚመለከት አይደለም። አንድም፥ ሌሎቹ የትግራይ ከባቢዎች ምን ዓቅም አላቸውና ይህ የሚያደርጉ። አንድ የራያ አከባቢ ተወላጅ የሆነ አቶ ጌታቸው ረዳ እያነሱ የህወሓት መሪዎች “አሳታፊነት” የሚሞግቱ ካድሬዎች በርካታ ናቸው። ከዚህ ቀደም “አንደመርም” ኋላም “የተከበሩ ወንጀለኞች” በሚል ርዕስ ተሻሽሎ በወጣ መጽሐፌ ላይ በስፋት እንደ ዳሰስኩት ጌታቸው ረዳ ተራ መልዕክተኛ (useful idiot) ነው። ሀብታም ሰው ቤት የማይታጣ፣ ለቤቱ ታማኝና ብርቱ ተላላኪ የድሃ ልጅ፣ ከባለ ሀብቱ ልጆች እንደ አንዱ የሚመላ ለስ ሳያውቁ አይቀሩም ፤ እንግዲያውስ ጌታቸው ረዳ ማለት ያ ሰው ነው። የሚነገረውና ተጽፎ የሚሰጠው ጽሑፍ እንደ ተማሪ አጥንቶና ሸምድዶ በምርቀና መንፈስ ሚድያ ላይ ቀርቦ የተሰጠውን መልዕክት የሚናገር ሰው እንጅ በትግራይ ህዝብ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር የፖለቲካ ፖሊሲና ፕሮግራም ጸሐፊም ወሳኝም አይደለም። ጌታቸው ረዳ አይደለም በውኑ በህልሙም ቢሆን የሚሽረውም የሚያጸድቀውም ፖለቲካዊ ሆነ ማህበራዊ ውሳኔ የለውም። የህወሓት መሪዎችና ካድሬዎቻቸው ግን ጌታቸው ረዳን የፓርቲያቸው “አሳታፊነት” ለመደስኮር በቀጣይነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
የአማራ ልሒቃን የሚያሉሟት ኢትዮጵያ፥ በኢትዮጵያዊነት ስም ከአማራ እየተነሱ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ጋንቤላ ወዘተ መግዛትና ማስተዳደር ነው። ይህ ዓይነቱ ቅዠት ግን በተለይ የፌዴራል ስርዓተ መንግስት ያስተዋወቀ የህወሓት አመራር ፈጽሞ የማይቀበለውና የማያስበው ነው፤ ደግሞም እውነት ነው። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአከባቢው ሰውና በሚመርጠው አመራር ነው መመራትና መተዳደር ያለበት። ትግራይ ውስጥ ታድያ ይህ የሚታሰብ አይደለም። አይደለም በዞን ደረጃ የወረዳ አመራር ሳይቀር ሹሞ የሚልክ የፓርቲው ጸሐፊ በግሉ ነው። ጥጉ፥ ትግራይ ውስጥ የህወሓት ቢሮ ሳያውቅ የሚሾም የቤተ ክርስትያን ቄሰ ገበዝ የለም። የአመራሩ ኋላ ቀርነትና አምባገነንነት በዚህ ደረጃ የተገለጠ ነው። የትግራይ ህዝብ ዛሬም ከድህነት አለመላቀቁ ሊደንቀን አይገባም። የህወሓት አመራር እንዳለ እንደ ቆሻሻ ንብረት ከአዲስ አበባ ተጠራርገው ሲባረሩና ትግራይ መደበቂያቸው ሲያደርጉ የትግራይ ህዝብ አንቀበልም አላላቸውም። ሰዎቹ እንደ ድሮ የለመዱትን እንዲያደርጉ ግን አልፈቀደላቸውም። የትግራይ ዞኖችና ወረዳዎች እናንተ በምትልኩት ሳይሆን እኛ በምንመርጠው አመራር ነው የምንተዳደር በማለት ህዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ አምጾባቸዋል። ራያ ጥያቄያችን ካልተፈታ ወደ አማራ እንሄዳለን! በማለታቸው ከሃያ ምናምን ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝቡ የመረጠው ሰው ባይሆንም የአከባቢያቸው በሆነ ሰው ለመመራት ግን በቅቷል። የራያ ዓይነቱ ተፈጥራዊ ብልጫ ለሌላቸው አከባቢያዎ ታድያ በአመራሩ የተሰጣቸው/የሚሰጣቸው ማላሽ “ሁሉም ትግራዋይ ነው” የሚል ነው። ይህ የሚለውን ያለው እንግዲህ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው” የሚለውን የኢትዮጵያ አባባል የማይቀበል አመራር ነው። አመራር የሚመደበውና መመደብም ያለበት “በእውቀትና በችሎታ ነው” እያሉ ህዝቡን ለማወናበድ የሞከሩበት አጋጣሚም በርካታ። በርግጥ፥ ፊተኛውም ሆነ ኋለኛው አባባሎች በራሳቸው (በትግራይ ‘ኮንቴክስ’) ችግር የለባቸውም። እውነት ነው፥ ሁላችን ተጋሩ ነን፤ አመራርም መመደብ ያለበት በእውቀትና በክህሎት ነው። የህወሓት መሪዎች ይህን ሲያደርጉና ሲሉ ታድያ ሁሉም ትግራዋይ እኩል ነው፤ አመራርም መሾም ያለበት በእውቀትና በክህሎት ነው ብለው ስለሚያምኑ ሳይሆን አባባሎቹ የልባቸውን መሻት ይፈጽሙ ዘንድ በር ስለሚከፍትላቸውና ደንበኛ ሽፋን ስለሚሰጥላቸው ነው። ይህ ዓይነቱ ትግራይን ወደኋላ ያስቀረ ብልሹና አሳፋሪ የአስተዳደር ስርዓት በትግራይ ህገ መንግስት ውስጥ ተፈልጎ የማይገኝ/ያልተጻፈ ዳሩ ግን ገዢ ህግ ሆኖ ትግራይን ያደቀቀ አሰራር ነው። ከሁመራ ይምጣ ከዓጋመ ራያ ይሁን እንደርታ ሁሉም ትግራዋይ ነው። ላለፉት 30 ዓመታት ትግራይ ሁሉም ትግራዋይ በእኩልነት ተቀብላ አስተናግዳ ቢሆን ኖሮ የት በደረስን ነበር ተብሎ ሊዘረዘር የሚችል በርካታ አውንታዊ እድገቶች መዘርዘር ቢቀርብን እንኳ መጪ ዘመናችን ብሩህ ነው ብለን አምነን ካለፈው ስህተትና ድካም ተምረን ለመለወጥ ሆነ ነግደን ለማትረፍ የተለወጠ አመራር ሊኖረን ይገባልና አንድ ነገር ለማድረግ ልንወስን ይገባል። ስለሆነም፥ ሲደላው በእጁ ሲተኩሶው በማንኪያ እያለ የሚያውከን አመራር ቆርጠን የመጣል ሃላፊነትና ግዴታ አለብን።
የህወሓት መሪዎች ስለ ፌደራሊዝም በማውራት የሚስተካከላቸው ፍጥረት የለም። ሲተርኩትም የስርዓተ መንግስቱ ፍልስፍና ጸሐፊዎች/ፈጣሪዎች ነው የሚመስሉ። ሐቁ ግን፥ ኩናማና ኢሮብ ተጋሩ ናቸው ብለን አምነን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅማ ጥቅሞች እኩል ተጠቃሚዎች ሊሆኑና ልናደረጋቸው ትግራዋይ በትግርኛ ለዛው የተነሳ የሚያገሉ ሰዎች ናቸው። ትግርኛ እዚህ ቦታ ተወለደች፣ እዚህ ቦታ አደገች፣ እዚህ ቦታ ሞተች፣ እዚህ ስፍራ ተቀበረች ሲባል ያልሰማ ትግራዋይ ያለ እንደሆነ ምናልባት ትግራይ ውስጥ ተወልዶ ትግራይ ውስጥ ያላደገ ሰው ብቻ ነው ሊሆን የሚችልው። እነሱ ብቻ ምሑራን ሌላው ትልቅ አምባሻ ጋግሮ ከመብላት ውጭ ሌላ ቁም-ነገር የሌለው፤ ለአንዱ ከእባብ ልብ ጋር ለሌላው ከትልቅ በሬ ጋር ስናስተካክለው፣ አንዱ መሪ ሌላውን የአብርሃም በግ የሚሉ አገላለጾች እንዲሁ ተራ አባባሎችና ቀልዶች ከመሰለን ተሳስተናል። በርግጥ አባባሎቹና ተረቶቹ ምንኛ የሰው ስነልቦና የመስለብ እቅምና ጉልበት አንዳላቸው የሚያውቅ፣ በእነዚህ አባባሎችና ተረቶች ተደብቆ ስራውን የሚሰራ ሴረኛ አመራር “ቀልዶችና ተረቶች” ናቸው ብለን እንድናስብና እንድናምን ነው የሚፈልገው። ሐቁ ግን፥ አባባሎቹ ደምበኛ የፖለቲካ ሴራ ናቸው። የጥንቱም ይሁን አሁን ያለው የትግራይ አመራር ለገዛ ወገኑ ሳይቀር የማይመለስ መሰሪ አመራር ለመሆኑ ቀደም ሲል በጨረፍታው የተመለከትናቸው አባባሎች ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው። በነገራችን ላይ፥ ይህን ሐቅ አፍረጥርጦ የሚናገርና የሚገልጥ ሰው ሲገኝ ከፋፋዮቹ ተናጋሪውን፥ ከፋፋይ፣ ጎጠኛ፣ ባንዳ ወዘተ የሚሉ ስፍር ቁጥር የሌለው ታፔላ እየለጠፉ በትግራይ ህዝብ ስም ተናጋሪው ለማጠልሸት አገር ምድሩን የሚያስሱ ሰዎች ስንመለከት የሚያስጮሃቸው ሌላ ማንም ሳይሆን እውነተኛ ከፋፋይና ጎጠኛ ማንነታቸው ሲገለጥ ቁጣቸው የሚገልጹበት መንገድ መሆኑ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
በርግጥ፥ እኔን ጨምሮ ይህ አዲስ ትውልድ ለእንደዚህ ዓይነት ርካሽ ፖለቲካ ስፍራ የለንም። የትግራይ ህዝብ የሞራል ጥንካሬ የሚያስደነግጠው የትግራይ አመራር ግን በዘመናት መካከል ለአስተዳደር ያመቸው ዘንድ የፈጠራቸው እክሎች ጠባሳቸው ዛሬም ድረስ በግላጭ የሚታይ ለመሆኑ የሚካድ አይደለም። እውነት ነው በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደ ምንመለከተው ትግራይ ውስጥ አንተ ከደቡብ ነህ አንተ ከምስራቅ ነህ ብሎ ነገር በህዝቡ ዘንድ የለም። በኢትዮጵያም በኤርትራም የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንዱ ምኞትና ጸሎትም እንደ ትግራይ ህዝብ አንድ አድርገን! የሚል ነው። ትግራዋይ፥ አይደለም እርስበርሱ በዞንና በወረዳ ሊከፋፈል ቀርቶ ዛሬም ድረስ ትግራይ ውስጥ የሚገኝ የአማራ ይሁን የኦሮሞ ተወላጅ በክፉ ዓይን የማይመለከት ምስጉን ህዝብ ነው። ይህ ሐቅ ጠላቶቻችን ጭምር የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። የህወሓት መሪዎች በአንጻሩ ጥቅማቸውና ስልጣናቸው ለመጠበቅ አመጽና ሁከት በትግራይ ህዝብ መካከል ለማስተጋባትና ለማስተዋወቅ ያላደረጉትና ያላሴሩት ሴራ የለም። በስፓርት ሽፋን ይሁን በሚድያ በኩል የህወሓት መሪዎች ትግራዋይ እርስበርሱ ለመከፋፈል፣ ለማባላትና ለማናከስ ያልመከሩት ምክር የለም። ይህ ዓይነቱ ችግር ታድያ አሁንም ኢትዮጵያ የጫነችብን ችግር ሳይሆን የኛው የራሳችን የፖለቲካ መሪዎች የራሳቸውን ጥቅምና ስልጣን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ሆነ ብለው የፈጠሩትና የሚፈጥሩት ችግር ነው። ውጤቱ? የአክሱም ሓውልት ያቆመ ህዝብ በሴፍትኔት ታቅፎ በልመና በሚገኝ ስንዴና ዘይት የሚኖረውን የድህነት ህይወት መመልከት በቂ ነው።
እንደ ህዝብ ያቀጨጨንና ያኮሰሰን የራሳችን አመራር ነው
የትግራይ አመራር፥ አምባገነን መንግስታትና ነገስታት ሲነሱበትና ወራሪ ሃይሎች ትግራይን ለመጉበጥ ሲመጡ ‘መግነዙ ፈትቶ’ የሚያብር፣ ታግሎ በማታገልና በጀግንነቱ የማይታማ፣ ለመስዋዕትነት የሚሽቀዳደም፣ ብርቱና ታጋይ የሆነው የትግራይ ህዝብ አካል ሲሆን፤ በሰላም ጊዜ በአንጻሩ፥ እርስበርሱ የማይደማመጥና መቀባበል የማይችል፣ አብሮ መስራት የማያውቅና የማይሆንለት፣ እርስበርሱ ሲናከስ የሚጠፋ አውሬ ነው። ቀለል ባለ አማርኛ፥ የትግራይ ህዝብ በታሪኩ (በተለይ በሰላም ጊዜ) ጤና ያለው አመራር ያገኘበት አጋጣሚ በጣም አነስተኛ ነው። ብዙሓኑ ጥቅመኞች፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊና ብልሹ አስተሳሰብ የነገሰባቸው ሲሆኑ አሁን በዘመናችን ያለው አመራርም በተመሳሳይ የትግራይ ህዝብ የሚያደማበትና የሚገዘግዝበት የትግርኛ ቋንቋ ማስተር ያደርገ፣ በትግራይ ህዝብና በትግራይ ሰማዕታት ስም መነገድ የሚችልበት፣ ከጥቅምና ከስልጣን ውጪ ፈጽሞ ሌላ ራዕይ ዓላማና ተልዕኮ የሌለው፣ የበሽታዎቻችን ሁሉ ምንጭ የሆነ፣ የራሱ ወገን ጥሎ ከሌሎች ጋር መወዳጀትና መተሻሸት የሚመርጥና የሚያምርበት፣ እርስበርሱ የማይስማማ የማይደማመጥና የማይቀባበል፣ ምህረትና ርህራሄ የሌለው፣ አስመሳይና አታላይ፣ ሌባ ዘራፊና ነፍሰ ገዳይ አመራር ነው ያለው።
የትግራይ አመራር (እርስበርሱ) ሰላም የሚያሳክከውና አላርጅክ የሆነበት አመራር ነው። ትግራይ ዛሬ በዓይናችን እየመሰከርነው ያለ መዓትና ሰቆቃ የማገዳትም ይህ ዓይነቱ የአመራሩ አውሬ ባህሪይ ነው። የትግራይ አመራር ጠላት መጣ ሲባል የሚያሳየው ህብረትና አንድነት በሰላም ጊዜ የሚያሳየውና እርስበርሱ የሚቀባበል አመራር ቢሆን ኖሮ ሻዕቢያም ኢትዮጵያም በዚህ ደረጃ ሊወሩንና ሊጨፈጭፉን ቀርቶ በህልማቸውም አያስቡትም ነበር። የህወሓት መሪዎች እርስበርስ መከፋፈልና መገነጣጠል፣ መባላትና መናከስ፣ ከዚህም አልፎ በጠላትነትና በደም መፈላለግ ሲመለከቱ ታድያ ጊዜያቸውን ሳያባክሩ ትግራይ የምናጠፋበትና የምናምበረክክበት ጊዜው አሁን ነው! ብለው ኢትዮጵያና ኤርትራ ከርዕሰ ሃያላኑ ባገኙትና በተሰጣቸው ቡራኬ፥ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከኢምሬት ጋር መክረውና ዘከረው በላያችን ላይ የፈጸሙብን ግፍና በደል ለመፈጸም ተችሏቸዋል። በርግጥ፥ የአገራቱ (ኢትዮጵያና ኤርትራ) የተሳሳተ ስሌትና ውሳኔ ዛሬ ምን ውስጥ እንደከተታቸው ምስክርነት የሚሻው ጉዳይ አይደለም። በዝግ በር እንደ መከሩት ምክር የትግራይ ህዝብ መታሰቢያ ላይኖረው ስመ ዝክሩ ያጠፉት ዘንድ አልተቻላቸውም። በጥቂቱ፥ የቱርክ፣ የኢራን፣ የቻይና፣ የዩክሬይንና የራሽያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ ፓለቲካዊና ወታደራዊ ድጋፍ ይዘው መጥተው ሲያበቁ፥ በቁጥር አነስተኛ የተባለ ህዝብ የረገጥዋት ምድር እንዴት መቃብራቸው አንዳደረገው፣ እንዳብረከረካቸው፣ እያሳደደም እንዳደናቸውና እንዳጥመለመላቸው አሁንም ዳኝነቱ ለዓለም ማህበረሰብ እተወዋለሁ።
እውነት ነው፥ በሚሰጠው የመግለጫ ብዛትና በቴሌቪዥን መስኮት የህወሃት መሪዎች አንድ አዳራሽ ውስጥ ቁጭ ብለው ሲነጋገሩ ለሚመለከት ሰው፥ ሰዎቹ ህብረት ያላቸው ሊመስለው ይችል ይሆናል፤ ሐቁ ግን ከዚህ ሁሉ የራቀ ነው። አሁንም፥ የህወሃት መሪዎች በሚሰጡት ስፍር ቁጥር የሌለው የመግለጫ መዓት ለዓቢይ አህመድ ዓሊ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው ሊመስለን ይችል ይሆናል ዳሩ ግን ሰዎቹ በመካከላቸው ያለ ጥላቻና አመጽ ከዚህም ሁሉ የከፋ ነው። ኢትዮጵያ ትግራይን ባትወርና ይህ አሁን ያለው ጦርነት ባይከሰት ኖሮም ሰዎቹ ምን ያህል ጊዜ ስልጣን ላይ ሊቆዩ ይችሉ እንደነበር ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። አንድም፥ አንዱ ለሌላውን ገመና አሳልፎ ሲሰጥ፣ ሌላውም በተመሳሳይ ይህን ሲያደርግ፣ የተቀረው ደግሞ ነፍሱን ለማትረፍ የፓርቲ ጉድ ሲቸበችብ ሁሉም ተያይዘው የሚጠፉት ጊዜ ሩቅ አልነበረም። ወራሪዎቹ ጥቂት ቢታገሱ ኖሮ የህወሓት አመራር እርስበርሱ ሲናከስ ህልውናው በገዛ እጁ ባከሰመ የትግራይ ህዝብም በዚህ ደረጃ ባላለቀ ነበር። ምክንያቱም፥ በክፉ የሚፈልጉን ሁሉ የአዲሱ ትውልድ ራዕይ ዓላማና ተልዕኮ ጠንቅቀው ስለሚያቁ ያደረጉትን ባላደረጉ ነበር።
የህወሓት መሪዎች የውስጥ መቆራቆስና የፓርቲው ነፍሰ ገዳይ ባህሪይ ታድያ ለትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ የተሰወረ ነው ባይባልም በሚገባ የሚታውቅ ግን አይደለም። በተለይ በህወሓት ከፍተኛ አመራር አባላት ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለ የመጣ የጥቅምና የስልጣን ሽኩቻ፣ የእርስበርስ መናከስና መጠላለፍ ለማርገብ ታስቦ በልዩ ሁኔታ የታጨና ወደ ስልጣን እንዲመጣ የተደረገ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፥ የህወሓት መሪዎች በስልጣን ዘመናቸው በሀገርና በህዝብ ላይ የፈጸሙት ወንጀልና ገመና ከሰፊው ህዝብ በተለይ ከትግራይ ማህበረሰብ በመሰወር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በአንጻሩ የትግራይ ህዝብ ለደረሰበት ሞትና ዕልቂት ግን የደብረጽዮን ገብረሚካኤል መላ የጠፋበት፣ ግራ የተጋባ፣ ከህዝብ ይልቅ ግለሰቦችና ፓርቲ ማዕከል ያደረገ ወላዋይና ደካማ አስተዳደር ለጥፋታችን ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽዖ በታሪክ ተወቃሽ እንደሆነ ይታወሳል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንባር ፈጥረው በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸሙት አረመኔያዊ ድርጊት አስመልክተን ስንናገር አንድ መረሳት የሌለበትና በሁሉም ዘንድ በግልጽ መታወቅ ያለበት ዓቢይ ጉዳይ ቢኖር ቀደም ሲል እንደተጠቀሰ የህወሓት መሪዎች አስተዋጽዖ ነው። በትግራይ ላይ የተፈጸመ የህይወትና የንብረት ሞትና ውድመት የምክንያታቸው ምንጭና ዘፍጥረት ቢለያይም የአገራቱ (የኢትዮጵያና የኤርትራ) የረጅም ጊዜ ዕቅድ በዚህ ዘመንና በዚህ ሰዓት የደረሰብንን እንዲደርስቡን በር የከፈተና ምክንያት የሆነው ሌላ ማንም ሳይሆን የህወሓት መሪዎች ናቸው። እዚህ እሳት ውስጥ የከተቱን የህወሓት መሪዎች ናቸው። ለእልቂታችን የመጀመሪያ ተጠያቂ የህወሓት መሪዎች ናቸው። ትግራይ፥ በህግ የበላይነት የሚዳኙ የበለጸጉ አገራት ተብለው የሚታወቁ መንግታት መካከል እንደ አንዷ ብትሆን ኖሮ እያንዳንዱ የህወሓት አመራር ስልጣን መልቀቅ አይደለም በህግ ከመጠየቅና በህግ ከመዳኘት አያመልጡም ነበር። የጨፈጨፈን፣ የገደለንና ያበረሰን የኢትዮጵያና የኤርትራ ነፈሰ ገዳይ ሰራዊት ቢሆንም ለሞታችንና ለእልቂታችን ምክንያት የሆነና ዋና ተጠያቂ የህወሓት መሪዎች ናቸው። ጥቅማቸውና ስልጣናቸው ለመጠበቅና ለማስጠበቅ የትግራይ ህዝብ እንደ ግል ንብረታቸው አስይዘው የቆመሩብንና ያስበሉን የህወሓት መሪዎች ናቸው። ይህን ሳያውቅ ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚራገም ሰው ቢኖር ታድያ የችግሩ አካል ከመሆን አልፎ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። በነገራችን ላይ አታየውም ያለ እንደሆነ ነው እንጅ ትናንት የቆመሩብህ ሰዎች ዛሬም እየቆመሩብህ ነው።
የትግራይ ህዝብ ከማንም ይልቅ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ሉዓላዊት የህይወት መስዋዕትነት የከፈለ ህዝብ ቢሆንም የተለየ ነገር እንዲደረግለት ሆነ እንዲሆንለት የጠየቀም የሚጠይቅም ህዝብ አይደለም። የትግራይ ህዝብ እንደ ማንኛውም ማህበረሰብ የሚፈልገውና የሚያስፈልገው የስልጣን ባለቤትና ፍትሓዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ነው። የህወሓት መሪዎች ለትግራይ ህዝብ ያሳጡት ሁለት ወሳኝና መሰረታዊ ነገሮች ታድያ እነዚህ ናቸው። የትግራይ ህዝብ የሚፈልገውና የሚያስፈልገው በሰፍትኔት ታቅፎ የእርዳታ ስንዴ እየጠበቀ እንዲኖር ሳይሆን ሰርቶ እንዲለወጥና እንዲያድግ ነው። የህወሓት መሪዎች ያደረጉት ግን ለገበሬው በደደቢት ብድርና በማረት ማዳበሪያ ብድር እንዲጎብጥ ሲያድርጉ፤ በአንጻሩ ለነጋዴው ማህበረሰብ ደግሞ ሆነ ተብሎ ከአቅሙ በላይ ታክስ እንዲከፍል በማስገደድ እንዲከስርና አገር ጥሎ እንዲጠፋ ነው ያደረጉት። ከትግራይ ውጭ የሚኖር ትግራዋይ ነጋዴ ከትግራይ የወጣበት ምክንያት ቢጠይቁት የሚነግሮት ሐቅ ይህ ነው። በጅማና በሌሎች የኦሮሚያ አከባቢዎች ቡና ለቀማ የተሰማራ የትግራይ ገበሬ የሚነግሮት የስደት ህይወቱ መንስኤም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። ይህ በስመ መንግስትነት የሚሸቃቅጥ፣ በመንግስትነትና ህጋዊነት ሽፋን ጥቅሙን የሚያሳድድ፣ ለህግና ለስርዓት የማይገዛ፣ የትግራይ ህዝብ እንደ ባሪያ ንግድ የፊውዳል ስርዓት (feudal oligarchy) ዘርግቶ የሚመዘብር፣ ለአንድ በመውስቦና የጥቅም ትሥሥር የተሰባሰበ ቡድን የሚሰራ መርህ አልባ አመራር የስልጣኔ ባለቤት የሆነው ህዝብ (የትግራይ ህዝብ) ለዚህ ሁሉ ውድቀትና የህይወት ስብራት ዳርጎታል።
በመቀጠል፥ የትግራይ ፖለቲካ ችግር ከራሱና ከቤተሰቡ ያለፈ ነገን አሻግሮ ለትውልድ የሚስብ አመራር ማጣት ነው በሚል ማጠንጠኛ ሃሳብ፤ እንዲሁም፥ የህወሓት መሪዎች መወገድ አለባቸው ሲባል በምክንያት ነው ለሚለው አንዳንድ ነጥቦችን አንስተን እንመለከታለን፥
ይቀጥላል …