ባለ አገሩ 01-16-22
የትግራይን ጄኖሳይድ ማስቆም ባለመቻሉ በስንፈት የተሸኘው የአሜሪካኑ ልዩ ልኡክ አምባሳደር ፊልትማን አዲስ አበባ ድረስ የመጣው በአብይ አህመድ ጋባዥነት መሆኑን ከወደ አሜሪካ ተሰምቷል ፡፡ የመረጃ ነፃነት ከሌለባት የኢትዮጵያ መዲና ብዙ ጠብቀን ስለማናውቅ ዜናው ከወደዛ መሰማቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ታዲያ አቢይ አህመድ ቀጠሮ አልሰጥም እያለ ደጅ ጀግና ጀግና ለመጫወት ሲሞክር ከርሞ በራሱ ተነሳሽነት በ ዲፕሎማት በ11ኛው ስአት የድረስልኝ የጥድፊያ ግብዣ ማድረጉ አብይ የፈለገው ጨዋታ እንዳለ ያመለክታል ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ፈላጊ በመሆኑ አምባሳደሩ አዲስ አበባ መከሰቱ ለሰላም ስንዝር ውጤት ካስገኘ የሚደገፍ ነው ፡፡ የሰውየውን መምጣት ተከትሎ ከጥቂት ቀናት በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በስልክ በትግራይ ሰቆቃ ላይ መነጋራቸውአሁንም በበጎ የሚታይ ነው፡፡
አብይ ኢሳያስን በመከተል ቴሌቪዥን ላይ ወጥቶ አሜሪካ ያለባትን ዕዳ ከመዘርዘር በፀባይ ከአሜሪካ ጋር መነጋገሩ ይበጀዋል ፡፡ አብይ ሌላው ማሻሻል ያለበት የየማታለል ዲፐሎማሲው የተበላ ቁማር መሆኑን ነው ፡፡ማታለል እስሊታወቅብህ ብቻ ነው ፡፡ አብይ ራሱን ደብቆ ለተወሰነ ወራት ማታለል መቻሉ ሊገርመን አይገባም፡፡ አለም እስኪያውቅህ እድል ይሰጣሃል፡፡ ሲያውቅህ ግን አካፋ አካፋ ነው ማለቱ የሚገታው የለም፡፡
አብይ ወደ ስልጣን በመጣበት ሳምንት “አዲስ ሊበራል ተገኘ” ተብሎ የተወደሰበት ግዜ ማስታወስ ይቻላል፡፡ የቀድሞ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚካኤል ፓምፕዮ “የኛ ሰ ው” በአዲስ አበባ ብሎት ነበር፡፡ አብይ ከኖቬል ኮሚቴ ሽልማት ያገኘው በማታለል ነበር ፡፡ሆኖም አብይ ያገኘው እቁብ ቶሎ የበላ መሪ ነው፡፡ አብይ ፈጣን ግን ዙሩን ሳይጨርስ ከዲፕሎማሲ ጨወታ የወጣ መሪ ነው ፡፡ የተዘረረ መሪ ነው፡፡
አብይ ግራ አጋብቶ ትርፍ ለማግኘት የሚጥር መሪ ነው ፡፡ ግራ የማጋባት ፖለቲካ ከአሜሪካ ጋርም ሲጠቀምበት ይታያል ፡፡ ከአሜሪካ ጋር የጀመረው አዲስ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴም ለምን ዓላማ እንደፈለገው ማጤን ያስፈልጋል ፡፡ የህዝብን ስቃይ ለማርዘም መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ከጆ ባይደን ጋር በስልክ በተነጋገረ በነገታው በተፈናቃዮች ሰፈር የቦንብ ናዳ ማውረዱ የአብይ ፍላጎት ምን እንደሆነ አሳይቷል ፡፡ በአንድ እጁ ተስፋ ሰጥቶ በሌላኛው የሚነሳ ነው ፡፡ የአብይ የዲፕሎማቲክ ልምምድ መለስ ብሎ ማየትን ይጠይቃል ፡፡ የአብይ መሰረታዊ የፖለቲካ ይዘት መተንተን የሚጠይቅ ነው ፡፡
የአብይ የውስጥና የውጭ ፖሊሲ በተግባር ለመረዳት የሄደበት መንገድ ማየት ይጠይቃል፡፡ ሰውየው በቅርፅ (ፎርም)እንጂ በፖሊሲ ቁምነገር (ይዘት) አያምንም፡፡ ይህ ማለት አብይ መሰረታዊ ለሆኑ ችግሮች መሰረታዊ መፍትሔ ለማምጣት አይሞክርም፡፡ ጊዜያዊ ጫና የማቅለል ስልት ይጠቅማል፡፡አቢይ ለሁሉም ተስፋ የመስጠት፤ ቃል የመግባት ፤በቆንጆ ቃላት በመደለል መሻገር ይቻላል ብሎ የሚያምን ነው ፡፡ ዛሬ ፊት መንሳት ነገ በፈገግታ ማስተናገድ ታክቲክ ይከተላል፡፡መሰረታዊ ችግሮች ድህነት መቀነስ ብሎ መናገር አድካሚ ነው ፡፡ ብልፅግና ካልክ በቂ ነው ፡፡ ቤተ መንግስት በማስዋብ የኢትዮጵያን ገፅታ መቀየር ይቻላል የሚል እምነት አለው፡፡ በገቢ ማደግ፤ በህዝብ ኑሮ መለወጥ ሳይሆን ፓርክ በማስዋብ ገፅታ መቀየር ይቻላል ብሎ የሚያምን ነው፡፡ ራሱን በማስዋብ የድህነትን ገጽታን ለመቀየር የሚሞክር ነው ፡፡ የህዝበኝነት ፖለቲካ ማለት ነው፡፡ ውብ አማላይ ስንኞች ቃላቶች በመጠቀም ህዝብን ማግተልተል ይቻላል ብሎ የሚያምን ነው ፡፡
አብይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃርኖ የመረዳት አቅም የለውም፡፡ የሚያማልሉ ሃረጎች አገር የሚያድኑ ይመስለዋል ፡፡ ስንኖር ኢትዮጵያ ስንሞት ኢትዮጵያዊ የሚለው ስንኝ ትልቅ ግኝት እንደሆነ ያስባል ፡፡ መደመር የአለም ምርጥ ቃል ይመስለዋል ፡፡የኢትዮጵያ ችግር ከበደል፤ ከመገለል ፤ ከማንነት መነጠቅ ወዘተ እንደሚነሳ ሊገባው አልፈቀደም ፡፡መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር የማንነት ጥያቄ መሆኑን በመካድ ለመሸሽ ይሞክራል ፡፡ ይህን መሰረት ስናደርግ የአቢይ አህመድ ዲፕሎማሲን መረዳት እንችላለን፡፡ አብይን በዚህ ደረጃ ስናውቀው ስለ ሌላ ነገር መናገር እንችላለን፡፡ የአብይ የውጭ ግንኙነት መርህ የሳምንት ዕድሜ ይስጠኝ የሚል መነሻ ያደርጋል፡፡ ሽፍታ ስለ ራቱ ያስባል ይባላል፡፡አብይም ስለ መሰረታዊ አገራዊ ጥቅም ማሰቢያ የለውም፡፡
አብይ ወደ ስልጣን እንደ መጣ ብዙ የዲፕሎማሲ ቅጥፈቶች ፈፅሟል ፡፡ የኤርትራ ጉዳይ የግሉ ጉዳይ እንደሆነ ያስባል ፡፡ የአረብ ኤሜሬት ግንኙነት የግሉ ነው ፡፡ አብይ አስመራ ና አረብ አገራት ለምን ያህል ግዜ በድብቅ እንደተጓዘ አይታወቅም፡፡አብይ በራሱ መንገድ የሄደባቸው ሁሉ የጥፋት መንገዶች ናቸው፡፡የታላቁን የህዳሴ ግድብ ወደ ዋሽንግተን እንዲሄድ የወሰነው ራሱ ብቻውን ነው፡፡ በመጨራሻም ጭራው ተቆርጦ ተመልሰዋል፡፡ ግብፅ ሄዶ ውሃውን አልነካም ብሎ ሲምል ምን እያሰበ ነበር ፡፡በልቡ ችግሩን ፈትቶታል ፡፡ ሌላ ግዜ ደግሞ ችግሩ የኢትዮጵያ ሳይሆን የተደራዳሪዎች ነው ብሎ ያምን ነበር፡፡ የኤርትራውን ጋኔን ጎትቶ ሲያመጣብን ብዙ ሰው ችግር ላይ መግባታችንን ያውቅ ነበር ፡፡ኢሳያስ ጋር የዋለ ምን ተምሮ ሊመጣ እንደሚችል የሚገመት ነው፡፡ አሁንም ብዙ ኢትዮጵያዊያን ኢሳያስን ሲጠረጠሩ ከጥላቻ የተነሳ ይመስለዋል፡፡
አብይ አህመድ እያዋዛ አገራችንን መቀመቅ ያወረደው የግል ስልጣን ሊገቱ የሚችሉ ጠንካራ ተቛማት ያለመኖራቸው ውጤት ነው ፡፡ የፖለቲካ ምርጫ ሲያራዝም ከትግራይ በስተቀር የተቃወመ አልነበረም፡፡ አብዲሌ በመፈንቅለ መንግስት ሲታሰር ዝምታ ነበር፡፡ ጄኔራል ሰዓረ ሲገደል የጮኸ የለም፡፡ ለማ ሲባረር ዝም ነበር የተባለው፡፡ አምባቸው ሲገደል የጮኸለት የለም፡፡ ትግራይ ወረራ ሲጀመር ደስታ የተቀላቀለበት ሰው ነበር ፡፡
አብይ አህመድ ድርድርና ሰጥቶ መቀበል አያውቅም፡፡ ራሱ ሁሌ እንደሚናገረው puffing and bluffing ይከተላል፡፡ መዋሸትና ማታለል ነው፡፡ የሽፍታ ሎጂክ አይሰራም፡፡ አሜሪካን በተለመደው የድብብቆሽ ዲፕሎማሲ ለማታለል ይሞክራል ፡፡ ፌልትማንን የጋበዘው ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ከእስር በመፍታት ዋጋ ለማግኘት በማሰብ ነው፡፡ ያልተሳካለት ዲፕሎማት ፌልትማን በመውጫው ሰዓት ትንሽ ነገር ለማግኘት እንዲችል ነው፡፡ ውለታ ለመክፈል ነው፡፡ ፊልትማን ጆኖሳይድን የፈፀመን መሪ ያሽቃበጠ ዲፕሎማት ነው ፡፡በአብይ እና በኢትዮጵያ መካካል ያለውን ልዩነት መለየት ያልቻለ ዲፕሎማት ነው ፡፡ ከስራ የተባረረውም በዚህ ምክንያት ነበር ፡፡
ሰሚ አጣ እንጂ አብይ ጦርነት ሊበራል ፖለቲካ እንቅፋት የሆነውን የብሄር ብሄረሰብ መብት መሰረት ያደረገ ፖለቲካ በመዋጋት ላይ መሆኑም ጭምር ያሳወቀበት ወቅት ነበር ፡፡የርእዮተአለም ጦርነት ነው ብሎት ነበር ፡፡ ትላንት ለብሄረሰብ መብት እንዋደቃለን ሲሉ የነበሩት ሰዎች የብሄር የእኩልነት ጥያቄ አፍራሽ ነው በማለት ከምዕራባዊያን ፊት ቀርበው የሞገቱበት አንደበት ነበር፡፡ ለብሄር ፖለቲካ ባለቤትነት ደግሞ ትግራይ ህወሓትን መወንጀሉ ቀላል ሆኖ ተገኘ፡፡አንዳንድ ሊበራል ምእራባዊያንም በመንግስት ይዞታ ያሉትን ንብረቶች ለመግዛት በመቛመጥ ዝምታን መረጡ፡፡ አብይ የርእዩተ አለም ጦርነት ሊያደርገው ሞከረ፡፡ በዚህ በኩል የሄደበት መንገድ ብዙ ሳይርቅ ከሸፈበት፡፡ የአማራ የመሬት ወረራ፤ የኤርትራ ጣልቃ መግባት ከፈፀሙት ጆኖሳይድ ሁኔታዎች ተወሳሰቡ ፡፡ ወደ ገደለው ይላሉ የዘመኑ ልጆች፡፡ ወደ ገደለው ለመግባት የአብይ ዲፕሎማሲ የማታለልና የመዋሸት ፖለቲካ ነው ፡፡ፌልትማን የጋበዘው ትንሽ ጫና ለማቅለል ብቻ ነው፡፡ ዘላቂነት የሚባል የለም፡፡ የሽፍታ ፖሊሲ ነው ፡፡ የእለቱን ነው የሚያስበው ፡፡ አብይ ሰላም ይቀበላል ማለት ከእባብ እንቁላል እርግብ መፈልፈል ያህል ነው ፡፡ ያለው አማራጭ መታገል ብቻ ነው ፡፡