ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
መንደርደሪያ፥ ከሱዳን ጋር መክራ፥ የኢምሬት፣ የሶማሊያና የኤርትራ መንግስታትና አገራት አስከትላ መጥታ በተፈበረከ ሐሰተኛ ውንጀላና ትርክት በትግራይ ላይ ወረራ የፈጸመችና በትግራይ ህዝብ ላይ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም የጦርና የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ያካሄደች ኢትዮጵያ በትግራይ መሬት ብቻ ሳይሆን በሜዳዋ ጭምር ከገጠማት ወታደራዊ ሽንፈትና ኪሳራ የተነሳ ይህ ተከትሎም በመላ አገሪቱ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሽቅብ የወጣ የኢኮኖሚ መቃወስና የዋጋ ግሽበት ተጨምሮበት ኢትዮጵያ እንደ አገር የመቀጠልዋ ጉዳይ (የህልውናዋ ጉዳይ) መላ ዜጎችዋን ጨምሮ ለብዙዎች በማሳሰቡ አገሪቱ ከገባችበት መቀመቅ ለመውጣት ታሳቢ ያደረገ መድረክ በማዘጋጀት፥ ኢትዮጵያም በበኩልዋ፥ ችግሬን በውይይትና በድርድር ለመፍታት በማንኛውም ሰዓት በየትኛው ስፍራ እገኛለሁ! እያለች በትግሉና በመስዋዕትነቱ ህልውናውና ደህንነቱ ክብሩና ማንነቱ ካስጠበቀ ህዝብ (ትግራይ) ጋር ይፋዊ የሆነ ውይይት ለመጀመር ሽር-ብትን በማለት እንደምትገኝ ይታወቃል። በዚህ ዙሪያ ላይ ማለትም፥ በውይይቱና በድርድሩ ጉዳይ ላይ ከወዲሁ ብዙ ጥያቄዎችና መላምቶች እየተንሸራሸሩም ይገኛል። በርግጥ ይህ ባህሪያዊ ነው። በተለይ በተጋሩ በኩል የሚነሱ ያሉ በርካታ ጥያቄዎች ከብዙ በጥቂቱ የተመለከትን እንደሆነ ግን የሚነሱ ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ከትግራይ ዕድል ፈንታ የተገናኘ ሲሆን ሌሎች በርካታ በቅንነት እንዲሁም በእውቀት የሚነሱ ጥያቄዎችም ይገኙበታል።
በቅንነት ከሚነሱ ቀላሉ ጥያቄዎች መካከል፥ የትግራይ አገር መሆን ከምዕራቡ ዓለም ምን ያገናኘዋል? የእነሱ ድጋፍ ማግኘትና አለማግኘት አገር መሆንና አለመሆን የሚውስን ከሆነ የምዕራቡ ዓለም ድጋፉ ቢሰጠን የትኛው ስቁ ይከስራል? የሚሉ ጨምሮ፥ ርዕሰ ሃያላኑ ምን የሚያውቁት ሚስጢር ቢኖራቸው ይሆን የትግራይ አገር መሆን በዚህ ደረጃ አልዋጥ ያላቸው? የሚል እጅግ ሚዛን የሚደፋ ጥያቄ አንዱ ነው። ከትግራይ ዕድል ፈንታ ጋር በተገናኘ ለሚነሳ ጥያቄ “በድርድር የሚወሰን የትግራይ ዕድል ፈንታ የለም፥ የትግራይ ዕድል ፈንታ የሚወስነው የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው!” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ራሱን የቻለ ጽሑፍ ላይ ሃሳቤን አካፍያለሁ። ከምዕራቡ ዓለም በተገናኘ አገራቱ በትግራይ ላይ የሚያንጸባርቁት ዕይታ በሚገባ እንዲበራልን የምዕራቡ ዓለም እንደ ርዕሰ ሃያል አገር የሚያራምደው ፖለቲካና ሌሎችን የሚያዩበት መነጽር ማወቅና መረዳት አስፈላጊ ስለሚሆን በዚህ ጉዳይ ላይ በአጭሩ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንመለከታለን። በዋናነት ደግሞ የትግራይ የሀገራዊነት ጥያቄ ብስጋት የሚመለከቱት ያሉ ርዕሰ ሃያላን የትግራይ አመራር የዚህ ዓይነቱ አለመናበብ የሚፈጥረው ስጋት ለመቅረፍ ምን ማድረግ ይችላሉ? ተብሎ ለተነሳ ጥያቄ ከብዙ በጥቂቱ ሦስት ነጥቦች አንስቶ በአጭሩ የሚያስነብብ ጽሑፍ ይሆናል።
ሐተታ፥ የኢትዮጵያ ዓይነቱ የሦስተኛ ዓለም አገር ለምዕራቡ ዓለም ሆነ ለምስራቁ ርዕሰ ሃያላን (ራሽያና ቻይና) ገበያ ናቸው። የሦስተኛ ዓለም አገራት ከዚህ የዘለለ ሌላ ምንም ዓይነት ሊጠቀስ የሚችል እዚህ ግባ የሚባል የረባ ሚና የላቸውም። ዲፕሎማሲም ቢሆን ርዕሰ ሃያላኑ የሚፈልጉትን ነገር በሎህሳስ የሚያገኙበት መንገድ እንጅ እነሱም እንደ እኛ አገር ናቸው ህዝብ ናቸው ብለው ስለሚያምኑና ስለተቀበሉን አይደለም። ይህ የርዕሰ ሃያላን አገራት መሰረታዊ መገለጫ ባህሪይ ነው። ርዕሰ ሃያላን አገራት ሌላውን ዓለም የሚያዩበት መነጽር ይህ ነው። ወዳጅም ጠላትም የላቸውም ሁሉም ነገር የሚያዩት ከራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም አንጻር ነው። ጥቅማቸው ለማስከበርና ለመጠበቅ ደግሞ ሰማይ ብቻ ነው ሊያስቆማቸው የሚችል። ይህ ማለት፥ ሀገርና መንግስት (ከዚህ በላይ የለምና) ማውደምና ማፍረስ መጨፍጨፍና መበተን ካለባቸው ያልነበሩ ያህል ያፈራርሳቸዋል። ይህ ደግሞ ታሪክ ሳይሆን በዘመናችን ሆኖ ያየነውና ይህ ጽሑፍ በሚጻፍበትና በሚያነቡበት በዚች ዕለትና ሰዓት እንኳ በተጨባጭ እየሆነ ያለ ድርጊት ነው።
ኢትዮጵያ እንደ ማዕከላይ ምስራቅ አገራት የተፈጥሮ ዘይት ሆነ ነዳጅ ያላት አገር አይደለችም (አገራትና መንግስታት ያጠፋ ዘይትና ነዳጅ ነውና)። ይህ ማለት ግን ከርዕሰ ሃያላኑ ዕይታ ውጭ ናት ማለት አይደለም። በተመሳሳይ ሁሉም ርዕሰ ሃያላን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ጥቅምና ፍላጎት በተመለከተም አንድ ነው ማለትም አይደለም። በሶማሊያና በኬንያ የባህር አዋሳኝ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ክምችት ያለ እንደሆነ ይህ የተፈጥሮ ሀብት ገንዘቡ ለማድረግ የሚሻ ባለ ጉልበት ስለሚኖር ጎረቤት አገር ጥይት ማብረጃ የማድረግ ዓላማ ይኖሮዋል። በመሆኑም፥ ኢትዮጵያ በቀጠናው ውሳኝ አገር ናት ብሎ ያምናል። ወሳኝነትዋ? በሰላም አስከባሪ ስም የሰው አገር መሬት ገብታ የሰው አገር ጦርነት ለማካሄድ ይሆናል። ሌላው ኢትዮጵያ አሁን ባለው ጥናትና ትንበያ መሰረት በሚቀጥሉ ጥቂት አስርት ዓመት ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ብዛት ባለቤት ትሆናለች ተብሎ ስለሚታመን ይህ ደግሞ ለአንዳንዶቹ ገበያ ነው። ሸቀጣ ሸቀጡን ሊያራግፍባት፣ ሊነግድባትና ሊያተርፍባት የሚሻ ይኖራል ማለት ነው። ሦስተኛው ባለ ጉልበት በተመሳሳይ ኢትዮጵያ እንደ ገበያ ከማየቱ ባሻገር ሸቀጡን ለሌሎች አገራት በማዳረስ ረገድ በርና መንገድ ናት ብሎ ስለሚያምን ነው። በመሆኑም ሁሉም ርዕሰ ሃያላን ኢትዮጵያ በተመለከተ የሚያራምዱት አቋም ለኢትዮጵያ ህዝብ አስበው ሳይሆን እንደውም በአንጻሩ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ጥሬ ዕቃ ስለሚመለከቱትና ሊያተርፉበትም እንደሚችሉ ስለሚያምኑ ነው። የራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም መሰረት ያደረገ በመሆኑም አገሪቱ ግዛታዊ አንድነትዋ እንደያዘች መቀጠል አለባት ብለው ያምናሉ። በዚህ መልኩ ብትቀጥል የበለጠ ትርፋማዎቹ እነሱ ናቸውና። እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ ያለ እምነታቸው (የሁሉም) ይህ ነው። ነገ አንድ ጅንዬስ ከመካከላቸው ተነስቶ ኢትዮጵያ አስር ቦታ ላይ ብንከፋፍላት የበለጠ ተጠቃሚዎች ያደርገናል ብሎ ማለፊያ የሆነ ሃሳብ ይዞ ከመጣ ደግሞ በተመሳሳይ የሚያዋጣቸው አገሪቱ አስር ቦታ ላይ መክፈል ነውና ያደርጉታል። ስለ ርዕሰ ሃያላኑ ፖለቲካና መገለጫ ባህሪያት እዚህ ላይ ላቆምና ቀደም ሲል የተመለከትነው ሐተታ መንፈስ እንደጠበቅን የትግራይ ጉዳይ በግርድፉ እንመልከት።
ርዕሰ ሃያላኑ፥ በተለይ በአፍሪካ አገራት ላይ መሰረት እያጡ በመምጣት ላይ የሚገኙ ምዕራባውያን የትግራይ ሀገራዊነት የሚመለከቱት በቀጣው ፈጽመው ከጨዋታ ውጭ እንዳወጡ ካላቸው ስጋት አንጻር ነው። የትግራይ አገር መሆን ኢትዮጵያን ያዳክማ፣ የትግራይ አገር መሆን ሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች የሀገራዊነት ጥያቄ እንዲያነሱ ያበረታታል፣ የትግራይ አገር መሆን ቀጠናው አሁን ካለበት በከፋ ስርዓት አልበኝነት የተንሳራፋበት የሁከትና የብጥብጥ ሰፈር ይሆናል ብለው ሰለሚያኑ ነው። በርግጥ፥ አሁንም ቢሆን ይህ ዓይነቱ የርዕሰ ሃያላኑ ስጋት ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ካላቸው ተቆርቋሪነት የሚመነጭ ሳይሆን ከቁጥጥራቸው ውጭ የሆነ በቀጠናው ሊፈጠር የሚችል አለመረጋጋት ለገበያችን ጠንቅ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው። ጥያቄው ይህን ዓይነቱ የርዕሰ ሃያላኑ ሞልቶ የማይሞላ የጥቅም ፖለቲካ የሚፈጥረው ስጋት ለመቅረፍ የትግራይ አመራር ምን ማድረግ ይችላል? የሚል ነው። በርግጥ የትግራይ አመራር የትግራይ ህዝብ ጥያቄና መሻት ተቀብሎ የማስፈጸም ዓላማና ተልዕኮ ካለው፥
1. የትግራይ አማራር ተልዕኮ የትግራይ ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር፣ የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥና መጠበቅ ከሆነና ትግራይ እንደ አገር የማቆም ራዕይ ካለው አሁን ማድረግ የሚጠበቅበት ነገር ቢኖር ትግራይ እንደ አገርና እንደ መንግስት የቀጠናው ሰላማና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ የሚኖራት ማህበራዊ፣ ኢኮሚያዊ ሆነ ፖለቲካዊ አውንታዊ ሚናና አስተዋጽዖ የሚገልጽ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርጾ አቋሙን በግልጽና በውሳጣዊ ቻናሎች ማሳወቅና ራሱን ማስተዋወቅ ይጠበቅበታል። ይህ ኣካሄድ የትግራይ አገር መሆን ከብሔራዊ ጥቅማቸው ጋር የሚቃረን የሚመስላቸውና የትግራይ ህዝብ ጥያቄና መሻት በአሉታዊ ገጽታው የሚመለከቱ አገራትና መንግስታት ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚረዳ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባለፈ አገራቱ ፖሊሲያቸው ድጋሜ እንዲመረምሩና አንዲያጤኑ የሚረዳና የሚያስገድዳቸው ስለሚሆን ጭምር ነው። ወገን፥ እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፥ የምዕራቡ ዓለም ዛሬም ድረስ ትግራይ የሚያይበት መንገድ፥ ፈጽሞ ሊለወጥ አይችልም ተብሎ የሚታመን ኮሚኒስታዊ የህወሓት መሪዎች ቡድን በሚያይበት መነጽር ነው። ይህ ዓይነቱ የምዕራቡ ዓለም አስተሳሰብና ዕይታ ደግሞ ሰዎቹ ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ ካልሆነ በቀር ለትግራይ ህዝብ ተብሎ በሙሉ ልብ የሚሰጡት ድጋፍ እንዳይኖራቸው አድርጓል። ይህ መለወጥ አለበት። ሊለወጥ የሚችለው ደግሞ በሌላ በምንም ዓይነት መንገድ ሳይሆን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰ እንደ ህዝብ ግልጽ የሆነ ሀገራዊ አቋን ይዘን ስንቀርብ ይሆናል። ይህን የምናደረግው ደግሞ ለአሜሪካ ወይም ለአውሮፓ ተብሎ ሳይሆን በዚህ የሚጠቀመውና የሚረባው እኛ ራሳችን ነውና ጋሬጣ የሆነብ ነገር ለይተን ካወቅን ችግራችን ለማስወገድ ልንተጋ ይገባል።
2. ትግራይ፥ አይደለም በጭንቅ (በጨለማ) ወቅት የፈጠረችው፣ ከደረሰብን ይልቅ የከፋ እልቂትና ጥፋት ሰለባ ከመሆን ያተረፈን፣ ትግራይ የጠላት መናገሻና ታሪክ ከመሆን የታደጋትና ሞገስ ያለበሳት ልበ ሙሉ ብርቱና ተዋጊ ሰራዊት ልትቀንስና ልትበትን ቀርቶ፥ አሁን ያለው ሰራዊት በሚገባ ተጨማሪ ስልጠና የሚወስድበትና የሚያገኝበት፤ በተጨማሪም፥ የትግራይ ሰራዊት የመቀላቀል ፍላጎት ያላቸው ለአቅመ አዳም የደረሱ የትግራይ ወንዶችና ሴቶች በመረጡትና አቅማቸው በሚፈቅደው ሰልፍ አሁንም በቀጣይነት በመመልመል (ይሄ አስራ አምስት ቀናት አራሩጠህ በሚገባ ያልመለከውን መሳሪያ ማሸከም ሳይሆን) እንደ
ባለሞያ ሁሉም በየደረጃውና በዓይነቱ ሰልፉ የሚጠይቀው የጊዜ ሰሌዳ ተመድቦለት ሰልጣኞች ደረጃውን የጠበቀ ወታደራዊ ስልጠና የሚወስዱበት በቂ ስልጠና ትምህርትና እውቀት ባላቸው ባለሞያዎች የሚመራ ተቋማዊ አሰራር ተፈጥሮ በሚገባ የሰለጠነና የታጠቀ (በሞራልና በቁመና የታነጸ) ሰራዊት መገንባት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ደግሞ ጦርነት መናፈቅ ሳይሆን ከጦርነት ለመትረፍና ራስህን ለማዳን የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት እንዲሁም የጭምት አመራር አርቆ አሳቢነትና በሳል ውሳኔ ምልክት ነው። የትግራይ ህዝብ በተፈጥሮው ተንኳሽ (ጸበኛ) ህዝብ አይደለም፤ እንዳይደለም ሰውም ወፉም ያውቃል። ይህ ማለት ግን መቅረዛችን ዘይት ሳንሞላ ተኝተን እንደር ማለት አይደለም። አይደለም እንደ ህዝብ እንደ ግለሰብ ተኝተህ የምታድርበት ዘመን አይደለም። ከእኛ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ ካልነቃን መጪው ዘመንም ቢሆን እየከፋ የሚሄድ ዘመን እንጅ የተሻሻለ ነገር የምታይበት ዘመን አይደለም አይሆንምም። በመሆኑም፥ ግፍና በደል ስለተፈጸመብን ብቻ ሳይሆን ትግራይ የምንኖርባት ዓለም አካል እንደ መሆንዋ መጠን በዙሪያዋ እየሆነ ያለና ዓለማችን እየሄደችበት ያለ ጎዳና በማጠን ለራሳችን ደህንነትና ህልውና ክብርና ማንነት ለመጠበቅ ሲባል ማድረግ የሚጠበቅብን ሁሉ ማድረግን ስለሚገባ በሚገባ የምናደራጀው እንጅ የምንቀንሰውና የምንበትነው ሰራዊት አይኖርም። ትግራይ የገነባችው ሰራዊት እንደ ኢትዮጵያና እንደ ኤርትራ ሰራዊት መሳሪያውን ሽጦና የሴት ቀሚስ ለብሶ የሚፈረጥጥ ቅጥረኛ፣ ሌባ፣ ዘራፊ፣ ሰብዓዊነት ያልፈጠረበት ዙሙተኛና አማጺ ወታደር ሳይሆን ከሰራዊነትም ያለፈ በልቡም በአእምሮውም ተዋጊ የሆነ፣ ርሃብና የውሃ ጥም የማይፈታው፣ በቁሩም በሃርሩም የተፈተነ፣ በዲሲፕሊን የታነጸ፣ የትግል ጓዱን ወደኋላ ጥሎ የማይሄድ፣ የበላዮችን ትዕዛዝና አመራር ተቀብሎ ግዳጁን በብቃት የሚወጣ፣ ለራሱ ለወገኑና ለሰው ሁሉ ክብር ያለው፣ የዓላማ ሰራዊት እንደሆነ ምዕራቡም ምስራቁም ሊያውቅ ይገባል። ይህ የማድረግና የማሳወቅ ድርሻ ደግሞ የአመራሩ ሃላፊነት ነው። የትግራይ ሰራዊት አማጺ ሰራዊት ተብሎ የሚጠራና የሚታወቅ ሳይሆን ትግራይና ህዝቦችዋ ከአማጺ መንግስትና ሰራዊት የታደገ ጦረኛ ህዝብ የፈጠረው ታዋጊ ነው። የምዕራቡ ዓለም የቀጠናው ሰላም ያሳስበኛል ከሆነ ስጋቱ፥ የትግራይ ሰራዊት ከምንም በላይ ለቆመለት ዓላማና ተልዕኮ ሲል ማለትም ለሀገሩና ለህዝቡ ሲል የአከባቢ ሰላም መጠበቁ ግድ ነው። ጥጉ፥ ኢትዮጵያ ሆነች ኤርትራ የምክራቸው ሃሳብ እንዳይፈጽሙ ያስቆማቸው ሰራዊት የትግራይ ሰራዊት ነውና፥ አሁንም እነዚህ አገራትና መንግስታት ትግራይን መተናኮስ ለወደፊቱ በህልማቸው ጭምር እንዳያስቡት የሚያስቆማቸውና የሚከለክላቸው ሌላ ምንም ሳይሆን አሁንም የትግራይ ሰራዊት ተጠናክሮ የቆመና የቀጠለ እንደሆነ ብቻ ነው። አንድም፥ ካኪና ሽርጥ እያስለበሳችሁ በዘፈንና በድራማ የሰው አእምሮ ከማፍዘዝ፣ ከማደንዘዝና ከመስለብ ይልቅ፥ የነቃ፣ በስነ ምግባር የታነጸ፣ ሞራል ያለው፣ ለሀገሩና ለህዝቡ የተሰጠ፣ ለክፉም ለደጉም ዘወትር ዝግጁ የሆነ፣ በየትኛውም ሰዓት በተፈለገበት ቦታ ደርሶ ተልዕኮ የሚያሳካ የዓላማ ትውልድ/ዜጋ መፍጠር ይሻላል። ዛሬ የትግራይ ሰራዊት መቀነስና መበተን ጥቅማቸውና ስልጣናቸው ጠብቀው የማስጠበቅ ፍላጎት ያላቸው ግልሰቦችና ቡድኖች አዋጪ መንገድ ሊሆን ይችላል ይሆናል፥ ውሎ አድሮ ግን ድርጊቱ አገርና ትውልድ እንዲጠፋ መፍቀድ ስለሚሆን የሚመለከተው አካል ሊታረም የማይችል ስህተት ከመፈጸም እንዲቆጠብ ከወዲሁ ይመከራል።
3. ሌላኛው ነጥብ፥ ከተፈጸመብን ወረራ የተነሳ ትግራይ አሁን በዚህ ሰዓት ከምትገኝበት ውድመትና ጨለማ ወጥታ እንዴት የሰለጠነው ዓለም አካል ትሆናለች? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ የትግራይ አመራር በተጨባጭ አጥጋቢ ምላሽ መስጠትና ማሳመን ይጠበቅበታል። በሌላ አባባል፥ ዳግመ ህንጸት ትግራይ በተመለከተ የትግራይ አመራር ከወዲሁ መክሮበት ግልጽ የሆነ ፖሊሲና አቅጣጫ ይዞ መቅረብ ይጠበቅበታል። ሰዎች አንደሚገምቱትና አንደሚፈሩት ሳይሆን የትግራይ አገር መሆን ለቀጠናው ተጨማሪ ሸክምና ዕዳ ሳይሆን በአንጻሩ የመፍትሔ ኣካል ሆኖ የለውጥ መሳሪያና ምሳሌ ለመሆንዋ ማሳየት መቻል ግድ ነው። አንደ አገርና አንደ መንግስት ማሰብ ሳትጀምር አገርና መንግስት መሆን አይቻልምና የትግራይ አመራር ዓላማና ተልዕኮ ከምንም በላይ የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለሚሆን ትግራይ ከገጠማትና ከተፈጸመባት ወረራ የተነሳ የወደመው መሰረተ ለማቶችዋ እንደ ገና በማነጽና በመገንባት ልማቱን ያረጋገጠ ህዝብ ለመፍጠር የሚያስችለው ምዕራቡም ምስራቁም የሚያሳምን ግልጽ የሆነ የኦኮኖሚ ፖሊሲና ፕሮግራም ከነአፈጻጸሙ በግልጽ የሚጠቁምና አቅጣጫ የሚያስቅምጥ ፍኖተ ካርታ ነድፎ ራሱን ማስተዋወቅ ህዝቡን ለዳግመ ህንጸት ትግራይ እጁን እንዲያበረታና እንዲሰበሰብ ማስተማር (ማነቃቃት)፣ ማደራጀትና ማዋፈር ይጠበቅበታል።
ናይ ሙልጌታ ወ/ገብርኤል ፅሑፍ የንብቦ እየ:: ትሐሳብ ዘከራኽር ክኸውን ይኽእል እዩ:: ቅድሚ ናብኡ ምኻዱ ግን ንፀላእቲ ምኽሪ ከይመስል ብትግርኛ ዶክፅሕፍ አይኽእልን እዩ::ብዛዕባ ትግራይ ዓድነት ናፀሐፍካ አምሐርኛ አይግብኡን::