W. Yilma                                              

ቀን 12/05/2022

 መግቢያ

እንደሚታወቀዉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አድጎ የማህበረሰባዊ ሚዲያዎች በጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩበት ግዜ ጀምሮ ተጠቃሚው ማህበረሰብ እነዚህን ግኝቶች ለበጎም ለመጥፎም ተግባር መጠቀም ከጀመረ ግዚያት ተቆጥራል። ዛሬ ኢንፎርሜሽን በህግ ከተቋቋሙት ተቋማት ብቻ ሳይሆን አንድ ስርቻውስጥ ያደፈጠ ግለሰብ ሃሳቡን በኢንፎርሜሽን መልክ ለዓለም ህብረተሰብ ማሰራጨት ይችላል። በድሮው ግዜ በአብዛኛው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች በሥራ ላይ ሲውሉ ህሳቤው ቀሪውን ማህበረሰብ በተለያዩ መልኮች ይጠቅማሉ በሚል ግንዛቤ ነበር። አሁን ግን ይህ ህሳቤ ተለውጧል። ለምን ቢባል እነዚህ ውጤቶች ህብረተሰቡን የሚጠቀሙትን ያህል ከአጠቃቀም ጉድለት ወይንም ሆን ተብሎ ለበጎ ሊውል የሚገባውን የቴክኖሎጂ ውጤት ለእኩይ ዓላማ ማዋል በመቻሉ ነው። ለዚህ አብይ ምሳሌ ደግሞ ጉዳተኛዋ ሀገርና ሕዝብ ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እማኝ ፍለጋ መባዘን አያስፈልግም።

ከላይ የጠቀስኩት እውነት አለው። ምክንያቱም በዛሬዋ ኢትዮጵያ በሬ ወለደ ቢባል ይህ ለብዙዎች ኢትዮጵያውያን ውሸት መስሎ አይታያቸውምና ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ ሐሰት እውነት ሆኖ የተገኘበት በቻ ሳይሆን ውሸት ማውራት ባህል የሆነበት፣ ክፋትና፣ ጭካኔ ቸርነትና፣ አዛኝነት መስለው የሚታዩበት፣ ጦርነት ሰላም ነው ተብሎ የሚሰበክበት፣ የኢኮኖሚ ድቀትና የገንዘብ ግሽበት እድገት ነው ተብሎ የሚደሰኮርበት፣ አገር የማፍረስ ሥራን የአገር አንድነት ማስጠበቂያ እርምጃ ተደርጎ የሚወደስበት፣ ባንዳነት የአገር ጀግና ተብሎ የሚሸለምበት፣ ድሃ ሆኖ ሌላኛውን ድሃ የበለጠ ድሃ እንዲሆን የሚተጋ ህዘብ ያላት ሃገር ናት የዛሬዋ ኢትዮጵያ።

በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ከፍትሕ ጨፍላቂና፣ ከውሸት ጠማቂ ጋር አብሮ እንደሰምና ወርቅ የተዋሃደበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ይህም የማህበረሰባችንን ሁለንተናዊ ዝቅጠትን አጉልቶ የሚያሳይ ክስተት ነው።

ሁላችንም እንደምናውቀው የሥልጣን ጥማት፣ ጥጋብ፣ ትዕቢትና፣ ጥላቻ ብሎም በውሸት መታጀብ በማህበራዊ ሚዲያ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ አነሳሸነት አብይ አህመድ አሊ በትግራይ ህዝብ ላይ ምክንያት አልባ እና ዘርፈ ብዙ አቀፍ የሆነ አውዳሚ ጦርነት በማወጅ ዓለም ከዚህ በፊት አይቶትና ሰምቶት በማያውቀው ደረጃ የህዝብ፣ የንብረትና፣ የተፈጠሮ ሃብት እልቂት፣ ዉድመትና ብከላ ለማድረስ ችሏል።  የውድመቱ እና የጥፋቱ መጠን ሲታይ አብይ አህመድ አሊ ያለዓለም አገራት ትብብር እና ድጋፍ ይህን ያህል ጥፋት ለማድረስ ድፍረቱም፣ አቅሙም፣ ችሎታውም አይኖረውም። እንደሚመስለኝ የዓለም ማህበረሰብ በመጀመሪያዎቹ የጦርነት ሂደቶች እያእንዳላወቀ ዓይኑን ጋርዶት የነበረው “ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚከፋ የትግራይ ህዝብ ይደፉ” በሚል ህሳቤ ነበር። ሆኖም የጥፋቱ መጠን እና ጥልቀት እየከፋ በመምጣቱ ጉዳዩ ያሳሰባቸው የአሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት በአብይ አህመድ መንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደራቸው አብይ አህመድ እየወጋው ካለው የትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን ወትሮም ‘’ለሥልጣኔ’’ ያሰጋኛል ብሎ ከሚያስበው ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ [ሕወኃት] ጋር ተገዶ ለድርድር እንዲቀመጥ ተደርጓል።

ለዚህ ጽሑፍ ፀሃፊ ምንም እንኳን በድርድሩ አካሄድና ሂደት እንዲሁም የድርድሩ ሰነድ የያዛቸው ነጥቦች ብዙ የተወሳሰቡ፣ ግልፅ ያልሆኑ እና ያልተስተካከሉ ጉዳዮች አሉበት ብሎ ቢያምንም ለግዜውም ቢሆን ጦርነት ቆሞ አንፃራዊ ሠላም መምጣቱ በራሱ አንድ ውጤት ነው ብሎ ያምናል። ለምን ቢባል የአብይ አህመድ መንግስት ያለማንም ከልካይ ከውስጥ እና ከውጭ አጋሮቹ ጋር በመሆን በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ እና በደል በቃላት መግለፅ ማስቸገሩ ብቻ ሳይሆን የጥፋቱ መጠን እና ክብደት ለመግለፅ የሚችል ቃል አሁን ካሉት መዝገበ ቃላት ፈልጎ ማግኘት የሚከብድ ይሆናልና ነው። ይህ የዘመናችን የሰው እልቂትን እያስተናገደ ያለውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ነው።  እንግዲህ ቀድሞ በደቡብ አፍሪቃ በቅርቡ ደግሞ በኬንያ የተደረገውን ስምምነት በተግባር ለማዋል ጥረት እየተደረገ ያለው።

 የሰላም ድርድሩ

 በተደራዳሪ ደጋፊዎች ያለው ምልከታ

እንደሚታወቀው ከአስከፊ ጦርነት በኃላ ሠላምን ለማስፈን የሚደረጉ ድርድሮች ቀላል አይሆኑም። የኛም ሁኔታ እንዲሁ ነው። ሆኖም እኔ እንደሚመስለኝ በጦርነቱ የደረሰውን የሰውና የንብረት እልቂት እና ውድመት እንዲሁም ጦርነቱ በዚህ መልክ ከቀጠለ ሊያደርስ የሚችለውን የጂኦ-ፖለቲካ ቀውስ ግምት ውስጥ በማስገባት አደራዳሪዎቹ እና ከኃላ ሆነው ዋና ጉዳይ አስፈፃሚ ከሆኑት በይበልጥም አሜሪካ ከፍተኛ ጫና ማድረግ በመቻሏ የፕሪቶሪያና የናይሮቢው ድርድር እስከ-ስንክሳሩ ሊሳካ ችሏል መጨረሻውን ያሳምርልን። እኔ ከላይ እንዳልኩት ‘’የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው’’ እንዲሉ ማንም ያደራድር ማንም ተፅዕኖ ያድርግ ለግዜው ጦርነቱ ቃታ ከመሳሳብ ጋብ ማለቱ በበጎ የማየው ብቻ ሳይሆን አሜሪካ ወይም የሆነ ጉልበተኛ ይህንን አስከፊ ጦርነት ለማስቆም እስከቻሉ ድረስ እኔ ድጋፌን ከመስጠት አላቆምም። ለጉልበተኛ ሌላ ጉልበተኛ ያስፈልገዋል። ያውም ልክ የሚያስገባ !! ይህንን ስል ግን አደራዳሪዎቹ ብዙ ጥሩ ነገሮችን የሰሩትን ያህል የተወሰኑ ጉዳዮችን ችላ ብለው ማለፋቸውን ቆየት ብዬ የግሌን አስተያየት እሰጥበታለሁ። የአሁኑ ትኩረቴ የሚያጠነጥነው ድርድሩን ኢትዮጵያውያን (ተጋሩን ጨምሮ) እንዴት ይመለከቱታል የሚለው ላይ ይሆናል።

በጥባጭ ካለ ንፁህ ወሃ አይጠጣም !! እንዲሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ከድርድሩ በፊት ሆነ በኋላ ስለ ሠላም ማውራት ፍላጎት አልነበራቸውም። አሁንም ይህን ድርድር አጥብቀው ይቃወማሉ ወይም አቃቂር ያወጡለታል ወይም ደግሞ የራሳቸውን ያልተገራ ትርጉም በመስጠት ተጠምደዋል።

ይህም ማህበረሰባዊ ጦርነት ምን ያህል ስር እንደሰደደ መምጣቱን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰባችንን ሁለንተናዊ መስተጋብር ምን ያህል አደገኛ፣ ምናልባትም ሊጠገን ወደማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ከዚህም አልፎ በውሸት እና በተንኮል የተሞሉት ኢትዮጵያውያን የመሃበራዊ ሚዲያ ተምቾች እና የነሱ ጭፍን ተከታታዮች የበሬ ወለደ ብቻ ሳይሆን እርሳቸውን የድርድሩ ወሳኝ አካል አድርገው በመቁጠር በከፍተኛ ደረጃ ድርድሩን ዋጋ ለማሳጣት የአፍራሽነት ሚናቸውን በመጫወት ላይ ይገኛሉ። ይህ ዓይነት የአፍራሽነት ድርጊት የሚታየው በሁሉም ወገን ቢሆንም እኔ ትኩረት ልሰጠው የፈለኩት ከዚህ ቀደም ተጎጂ ከሆነው የትግራይ ህዝብ ጋር በአጋርነት ቆመው ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና ሲያበረክቱ የነበሩ አሁን ግን ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ አቋማቸውን በመቀየር የትግራይን ህዘብ መከራ ሊያበዛበት ወደሚችል አቅጣጫ እየተጓዙ ባሉት ጥቂቶች ላይ ይሆናል።

ብዙዎቹ በይበልጥ በውጭ የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች እና ደጋፊዎቻቸዉ ትግራይ ውስጥ ሆነው ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ላይ ካሉት የፖለቲካ እና የወታደራዊ አመራሮች እንዲሁም በየደረጃው ካሉት ታጋዮች ህዝቡንም ጨምሮ የሰው ልጅ ሊሰራው ወይንም ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ተአምር እንዲሠሩ ይጠበቃሉ። ይሄ ያለማወቅ ነው ብዬ የማልፈው ጉዳይ ሳይሆን እራስን ከነሱ ጫማ ውስጥ ከቶ ካለማየት የመነጨም ነው።

መስዋዕትነት፣ መከራ፣ ችግር፣ እርዛት፣ ረሃብ የሠው ልጅ ሊቋቋመውና ሊሸከመው የሚችለው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ነው። የትግራይ ሕዝብ ግን ሌሎች ህዝቦች ሊያደርጉት ከሚችሉት እጥፍ ታሻግሮ እስካሁን ተደራራቢ ችግሮችን እየሞተም፣ እየተታገለም ተቋቁሞታል። አሁን ግን ይበቃዋል። እኔን የሚገርመኝ በዚህ ሁሉ ሚሊዮን አረመኔ ሠራዊት ተከብቦ ይህንን ያህል ግዜ መቋቋም መቻሉ ነው።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መታወቅ ያለበት ጉዳይ አብይ አህመድ አሊና ግብራበሮቹ የትግራይን ህዘብ በሚመለከት ያወጡትን ዕቅድ በጠራራ ፀሐይ ያለማንም ከልካይ እየተገበሩት ይገኛሉ። አንድ የሰልቻሉት ነገር ቢኖር የትግራይን ህዝብ መለያየት ነው። አሁን ግን ከምታዘበው ‘’ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል’’ እንዲሉ ይህ ላይሳካላቸው ይችላል የሚል ሙሉ እምነት የለኝም። መታወቅ ያለበት በተጋሩ መካከል በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሊኖር ይችላል መኖሩም የሚበረታታ ነው። ትልቁ ቁምነገር እና መረሳት የሌለበት እውነታ ግን ይህ ልዩነት የትግራይን ሕዝብ ህልውና የሚፈታተን መሆን የለበትም። በአጭሩ ከዓፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ በትግራይ የተፈጠረው ነገር መደገም የለበትም።

የትግራይ ህዘብን ከመጥፋት ለማዳን ህይወታቸውን እየሰው ያሉት ታጋዮች እኮ አንድ አይነት የፖለቲካ አመለካከት የላቸውም። እስከ ሁሉ ልዩነታቸው ውድ ህይወታቸውን ሳይሳሱ ይሰዋሉ፣ ደማቸውን ይፈሳሉ፣ አካላቸውን ያጣሉ፣ ሲሰውም አንድ ጉድጓድ ውስጥ አፈር ይለብሳሉ። ወይንም በሁኔታዎች አስገዳጅነት አስከሬናቸው ቀባሪ አጥቶ የአሞራና የአውሬ ሲሳይ ይሆናል፣ ቅጠል ሸምጥጠው ቆርጠው ከአፈር ጋር የተቀላቀለ ድፍርስ ውሃ ጠትተው ሆዴን ጎረበጠኝ ሳይሉ፣ መሳሪያ ከጠላቶቻቸው ማርከው። ለነሱ ሳይሆን ለሌላው ብለው፣ ቁርና ሃሩር ሳይበግራቸው፣ ላይና ታች ይላሉ፣ በወል ለሚሠሩት ገድል እንጂ ለግላቸው እንደ ስስታም የእግር ኳስ ተጫዋች እኔ ጎል ላግባ ሳይሆን፣ እኔ ቀድሜ ልሙት ብለው በተቀበረ ፈንጂ ላይ ለመረማመድ እራሳቸውን ያዘጋጅ ምርጥ ጀግኖች ናቸው። እነዚህን ጀግኖች ለመርዳት የሚደረግ የሰላም ሂደትን ማገዝና መርዳት እንጂለማደናቀፍ አቃቂር ማውጣቱ ተገቢ መስሎ አይታይም። እነዚህን ጀግኖች የሚመሩትን የፖለቲካና፣ ወታደራዊ አመራሮችን ካላመንን ማንን ነው ታዲያ የምናምነው..? ከነሱ በላይስ በውጭ አገራት ያለነው የትግሉ ደጋፊዎች ለዚያ ሕዝብ እናስባለንስ ወይ..? መልሱን ለዓንባቢያን ልተወው።

 በድርድሩ ላይ ያሉኝ ስጋቶች

ነገሩ እንዴት እንደታየ አላውቅም እንጂ እኔ እንደሚገባኝ በፈረንጆቹ አጠራር Disarmament , Demobilization and Reintegration {DDR} በተግባር ለመፈፀም እጅግ ውስብስብ ሂደትን የሚጠይቅ ሲሆን የሚጠይቀው ግዜ፣ የሰው ኃይል፣ ሎጅስቲክ፣ ፋይናንስ የግጭት አፈታት መርህን በተግባር ማዋል ወ.ዘ.ተ አስፈላጊነት በቀላል የሚታይ አይደለመ። ይህ ሰፊ ሃተታ የሚጠይቅ ቢሆንም በዋናነት ያሉትን ስህተቶች ልጥቀስ።

  1. የትግራይን ታጣቂዎች ትጥቀ ማስፈታት የሚለው ( እኔ የትግራይ ህዝብ መከላከያ ኃይል ብዬ ብጠራው  እመርጣለሁ ) እንደ ቀላል ነገር ታይቶ የታለፈ ይመስለኛል። ለኔ ይሄ ችላ ሊባል የማይገባው ሲሆን ምክንያቱም ደግሞ ይሄ ጉዳይ ዋናው የድርድሩ ማዕከል ሆኖ መታየት ያለበት መሆኑን ስለማምን ነው። እንኳን በመቶ ሺህ የሚቆጠር በመግፋት፣ በቁጭት እና በንዴት በዳዮች፣ ጠላቶቹን ለመበቀል የታጠቀ ሰራዊቱን በ30,ቀናት ትጥቅ ማስፈታት ቀርቶ ( ለዛውስ ማን ቆጥሮ ለመሳሪያ ግምጃ ቤት አስረክቧቸዋል ) ራስ መስፍን ስለሺ ከጥቂት ታጣቂ ተከታዮቻቸው ጋር ሸፍተው ደርግ እጃቸውን እንዲሰጡ በጠየቀበት ወቅት እንኳን ራስ መስፍን እጃቸውን ለመስጠት ከዚህ የበለጠ ግዜ ፈጅቶባቸዋል። ምስኪኑ መስፍን ግን እጃቸውን መስጠታቸው በግፍ ከመገደል አላዳናቸውም።
  2. መተማመን ሳይፈጠር፣ ነገሮች ወደነበሩበት ላይመለሱ፣ በእስር ላይ ያሉና ቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ እና ፀጥታ አስከባሪ አባላት የነበሩ የትግራይ ተወላጆች እንዲሁም አሁን ካሉት የትግራይ ታጣቂዎች የተወሰኑቱ በኢትዮጵያ መከላከያ ጦር እና ፀጥታ ላይካተቱ ምን ዋስትና ተገኝቶ ነው ትጥቅ ወደመፍታቱ በፍጥነት የተገባው..?
  3. “ምን ተይዞ ጉዞ’’ እንዲሉ ጨካኙና ፣ አረመኔው የሻዐቢያ ጦር : እና የሱ ተላላኪ ጉዳይ አስፈፃሚ ባንዳዎች አሁንም በትግራይ ህዝብ ላይ በደል እያደረሱ ባሉበት ወቅት እንዲሁም አብይ እና ኢሳያስ በሚስጥር ውል የተግባቡበት የሁለቱ አገራት የጦርና ደህንነት ሥምምነት ዓላማውና ግቡ ምን እንደሆነ በማይታወቅበት የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማሰፈታቱ ያትግራይን ህዝብ ደህንነት ችላ ማለት አይሆንም ወይ?
  4. አሜሪካ ይህ ድርድር እንዲሳካ ከፍተኛውን ጫና ማሳደሯ ግልፅ ነው። ስጋቱ ግን አሜሪካ የትግራይ ህዝብ ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስ ለማገዝ እስከምን ድረስ ትሄዳለች?
  5. ስምምነቱ በተግባር መተግበሩን የሚከታተል አካል አለመኖሩ አንዱ የስምምነቱን ደካማነት የሚያሳይ ሲሆን ይህሰላምን ለማይፈልገው ሻዕቢያነ እና ተባባሪዎቹ አመቺ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል።

ከላይ እንደጠቀስኩት ድርድሩ ችግር የለውም አይባልም። አንዳንዴም ችኮላው እንዳለ ሆኖ ‘’ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ’’ የሚመስሉ ሁኔታዎች ይታያሉ።  በኔ ግምት ምንም እንኳን የድርድሩ አዘጋጆችና አስፈፃሚዎች በተደራዳሪዎች ላይ ወደሰላም እንዲመጡ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳደሩ መሆናቸውን የምገነዘብ ብሆንም በድርድሩ ሂደት ላይ ያልተካተቱ ወይንም ማረሚያ ሊደረግባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉ ተነጋግሮ ማሻሻል፣ ማካተት ወይንም ማስወገድ ይቻላል። ቁም ነገሩ ሰላምን ለማምጣት ተግቶ የመስራቱ ጉዳይ ነው።

ማጠቃለያ

በመካሄድ ላይ ያለውን እጅግ አስቸጋሪና ውስብስብ ህዝባዊ ትግል የሚመሩትን የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ነገሮችን በቅጡ ባለመረዳት ተቻኩሎ ድርድሩን አስመልክቶ አቃቂር ለማውጣት መሽቀዳደሙ እጅግ ትዝብት ውስጥ ያሚከት ነው። “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ’’ እንዲሉ ሰሞኑን የታዘብኩትም ይሄንኑ ነው። እኔ ያማውቀው ህዝብ ለደቦ የሚጠራው እርሻ ለማረስ፣ ለመዝራት፣ አረም ለመጎልጎል፣ ለመኮትኮት፣ ለመሸልሸል፣ ሰብል ለመሰብሰብ፣ ለመውቃት፣ እንጂ አውጫጫኝ ይመስል ሰላምን ለማውጣት በሚደረግ ድርድር የማኀበራዊ ሚዲያ አቀንቃኞች በዳቦ መልክ ሊካፈሉ ወይንም ሊወከሉ አይችሉም።  ደግሞ ሺህ ቅል ራስ ቢሰባሰብ ፍሬ ከርስኪ  ከማውራት በስተቀር ምን ሊፈይድ? ይህ አላዋቂ ሳሚ መሆን ነው። ብዙ ጊዜ እለዋለሁ፣ አንድ መቶ ኢትዮጵያውያን ቢሰባሰቡ መቶ ልዩነቶችን ፈጥረው ከመበተን ውጭ አንድ ነገር ላይ በመሰረታዊ ሃሳብ ተስማምተው የመውጣታቸው እድል ከዜሮ በታች ነው።

የአንድ የፖለቲካ አመራር በወልም ይሁን በግል ብስለት የሚለካው ቱሪናፋ ወሬኛ ምን ይለኛል ብሎ ማሰብ ሳይሆን ለማስተዳድረው ህዝብ ምን እርባና ልሰራለት ብሎ በእውቀት ለይ የተመሰረተ ውሳኔ መወሰን ሲችል ነው። ማወቅ ያለብን የሠላም ድርድር ማለት ሰጥቶ መቀበል ማለት ነው። ለኛ ይህ አዲስ ነገር ስለሆነ አብይ አህመድ ያጣውን ወይም ሊያጣ የሚችለውን እያወቀ ለሾርት ሚሞሪ ተከታዮቹ ‘’እኛ የጠየቅነውን መቶ ፐርሰንት አግኝተናል’’ ብሎ ለፈፈላቸው። ጭብጨባ ..!! አሁንም ጭብጨባ..!! ማሞ ቂሎ ደስ እንዲለው.!

መቶ ኘርሰንት ካገኘ ምን ድርድር ውስጥ አስገባው? ይልቁንስ ካለፈው ትምህርት አግኝተን ሁላችንም ሰላሙን ለማደናቀፍ ላይሆን ለማገዝ እንትጋ። ከዚህ በሗላ ምን ቀርቶናል? ሞተናል፣ ቆስለናል፣ ደምተናል፣ ሁሉን አጥተናል ግን ለቀረው ህዝብ ደግሞ ሰላም ያስፈልገዋል። ሰላም የሁሉም እድገት መሠረት ነው። በሰላም ለመኖር ሰላምን መመኘት ብቻ ሳይሆን ለሰላም መረጋገጥ ተሳታፊ መሆን ይጠይቃል። ይህ ሲባልም ሰላም አፍራሾችን በትጋት መታገል ማለት ነው። በፅናት መታገል አለብን። ለምን ቢሉ የሰይጣኖቹ ብዛት ከመልአክቶቹ በዝተዋልና። በመጨረሻም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት:-

(አንደኛ)., ድርድሩ የፖለቲከኞች ገደብ የለሸ ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን የህዝብን ጥቅም ያማከለ መሆን አለበት። (ሁለተኛ) ማንኛውም፣ ከየትኛውም ወገን የሚነሱ ሃሳቦችን ለማስተናገድ መዘጋጀት ይኖርብናል። ሁላችንም በሰፌድ ላይ ያለ ፎሬ እንጂ ከሰፌዱ ለይ እፍ ሲሉት የሚበተን ገለባ አድርገን አንይ። የዘመኑ ሠው መስሎ መታየት ሳይሆን የዘመኑ ሰው አስተሳሰብ ይኑረን።

ሠላም ለሁሉም

By aiga