ኣብዛኛው ኢትዮጵያዊ የራሴ ብሎ የሚያመልካቸው ሃይማኖቶች በዋናነት ተቀብላ ያሰራጨች ኣክሱም፤ የስልጣኔ ብቻ ሳትሆን የሃይማኖትና እምነት ማእከልነቷም ኣክሊለ ዘውዷ እንደ ተሸከመች ኖራለች፡፡ በየትኛውም ዓለም የማይገኙ ኣክሱም ብቻ የተጎናፈቻቸው ዕምቅ ሚስጥራት ኣሁንም ክብሯ እንዳይጓደል መከታ ሆኖላት ኖሯል፡፡ እቺ ራሷን ኣክብራ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እንዲከብሩ ያደረገች ኣክሱም ግን የልግስና እጇ በጩቤ ተወጋ፡፡ ከሃገር የፈለቁና ከባዕድ የተጋበዙ ኣህዛብ ተሰባስበው ክፉኛ ነከሷት፡፡ እኔ የተጓናፀፍኩት ስልጣኔ እና ክብር ለናንተም ይገባችሁዋል እና እንኳችሁ ያለች ኣክሱም ልግስናሽ እንጂ ኣንቺም ኣታስፈልጊም ተባለች፡፡ ፊደል ቀርፃ ሀሁን ያስተማረች፣ ቁጥሮችን ቀምራ ኣሃዱ፣ ክልኤቱ ብላ ያስቆጠረች፣ በብሉይና ሓዲስ ኪዳን ኣስተርጉማ የገደማትና ኣብያተ ክርስትያናት ኣብነት የሆነች ኣክሱም እንድትጠፋ ተወሰነባት፡፡ የኣክሱምን ሚስጥራት ከያዙ ተራሮች ኣንዱ ከሆነው ማይ ኮሖ የሚወነጨፉ የመትረየስ ዓረሮች ቁልቁል እየፈሰሱ ንፁሃንን ፈጁ፡፡ 

ኣክሱም የኢትዮጵያ ታሪክ መነሻ ነች፡፡ የዚህ እውነታ ከመሬት ተነስቶ የተነገረ ሳይሆን ኣሁን ያለቺው ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትከበርና የ3000 ዓመታት ታሪክ ኣለኝ ለማለት ካስቻሏት ዋና ዋና ነጥቦች እንዲሁም የታሪክ ድርሳናት የሚገኙበት ኣክሱምና የቅድመ ኣክሱም ዘመነ መንግስት ጋር የተያያዙ ስለ ሆነ ነው፡፡ የደኣማት መሰረት የሆነው የፑንት ዘመነ መንግስት እና የኣክሱምን መሰረት የሆነው የደኣማት ዘመነ መንግስት የታሪክና የታሪክ መዛግብት እንዲሁም የስነ-ቅርስ ግኝቶች እየጠቃቀሰ በባለ ታሪክነት የሚያውተረትር ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ ምሁር፤ ስለ ኣክሱም እና ኣከባቢዋ እያወራ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለፀጋነት ለመስበክ እና ተኣማኒነት ለማግኘት ከኣክሱም 52 ኪሎ ሜትር የምርቀውን የሓ በዋቢነት ሲያስቀምጥ ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ግልፅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የታሪክ ባለፀጋነት በመጥቀስ ለሚያቀርበው ትንተና እንደ ማስረጃ እየተጠቀመ መሆኑ ለማንም የተሰወረ ኣይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የተመረጠ ምግብ የሆነው የጤፍ መገኛ ማይ ኣድረሻ እንዲሁም ዓዲ ሰግላመንና ጎቦ ዱራ ከኣክሱም ከተማ ያለቸው ርቀት ከግምት የማይገቡ በመሆናቸው፤ ስለ ቅድመ ኣክሱም የሚደረጉ ዲስኩሮች ከኣክሱም ዙርያ ብዙ ርቀት ኣይጓዙም፡፡ የኣክሱምን ዘመነ መንግስት ለመመስረት እነዚህ ስልጣኔዎች መሰረቶች መሆናቸውም ኣየጠያይቅም፡፡

የሃይማኖት እኩልነትን ቀድማ የተገበረችና ያስተማረች ኣኩሱም፤ ሃይማኖት ሳይለዩ በሚያርዱ ጨካኞች ተደፈረች፡፡ ለመፀለይና ለመሳለም ወደ ኣክሱም ሲመላለሱና በኣክሱም ተኣምራት እየተመኩ በኢትዮጵያና ከኢትዮያ ውጪ የሚኮፈሱ መእመናን ነን ባይ ኣህዛብ በኣክሱም ላይ ጨከኑ፡፡ ርእሰ ኣድባራት ወገዳማት ኣክሱም በማለት ሲዘምሩና ሲማፀኑ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያቆናት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ጳጳሳት ኣክሱምን ከምድረገፅ ለማጥፋት ከሚወረወሩ ኣፍላፃትና ጉራዴዎች ተባበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ጳጳሳት ድንበር ተሻግረው በመሄድም ጭምር ኣክሱምን ኣምርረው ከሚጠሉ ባዕዳን ጉልበትና የጥፋት ሰይፍን ጋበዙ፡፡ የኢትዮጵያ ሸኮችና የመጅሊስ ኣለቆች የነብይ ሞሓመድ ሰሓባዎች በሁለት እጇ የተቀበለችና ሊያጠፏቸው ከሚንደረደሩ የካዓባ ሽፍቶች የጠበቀቺውን ኣክሱም እንድትረከስና ህዝቧ በኣደባባይ እዲታረድ የድጋፍ መግለጫዎች ኣወጡ፡፡

ኢትዮጵያ የምትመካበትንና በዓለም ኣደባባይ የፅላተ ሙሴ መኖርያ የሚል ስያሜ ያሰጣትን ሰፈር ኣጥፍታ ምን ለማግኘት ነበር ያ ሁሉ ዘመቻ ለሚለው ጥያቂ በቂ ምላሽ ለመስጠት ባይቻልም፤ ከሕዳር 19 እስከ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በኣክሱም ከተማ ላይ የተፈፀመው ግን ኢትዮጵያንን እንደ ህዝብ፤ ኢትዮጵያን ደግሞ እንደ ሃገር ያዋረደ፤ ከመንግስት ኣለቆች እስከ ጀነራል መኮነኖች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎችና የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ለዘላለማቸው የሚፀፀቱበት ሁናቴ ሆኖ ኣልፈዋል፡፡ በሶስት ቀናት ብቻ በዚች ቅድስት ከተማ ከ1000 በላይ ንፁሃን ሰዎች በተጨፈጨፉበት ሁኔታ ዘገባ ያስተላለፉ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች፤ “ከጁንታው መደምሰስ በኋላ ሕዳር ፅዮን በኣክሱም ከተማ በድምቀት ተከበረ” በማለት ነበር የግዴታ ሆኖባቸው በፅላቷ ውስጥ የነበሩ ካህናትን ብቻ ቀርፀው ውሸታቸውን ያሰራጩት፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=cenOEyfdss4

ከሕዳር 19 ቀን ጀምሮ በኤርትራ ሰራዊት የተጨፈጨፈው ሰላመዊ ህዝብ ኣስካሬኑ እንኳ መቅበር ባልተቻለበት ሁኔታ በቦታው ተገኝተው፤ የውሸት ዘገባቸውን ያሰራጩት የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ኣሁን በምን ኣንደበት ይሆን ስለ ከተማዋ ሁኔታ መዘገብ የሚችሉት ? እነዛ የኤርትራ ሰራዊት ኣልገባም በማለት ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ የኣራት ኪሎ ቤተ መንግስት ውትፍ ነቃዮች ኣሁን ምን ይውጣቸው ይሆን ? የንፁሃን ኣስካሬን ከኣስፋልትና ኮብል ስቶን ባልተነሳበት ሁኔታ፤ የዓድዋን ተራሮችና የኣክሱም ፅዮን ማርያም ቤተ ክርስትያንን ባክ ግራውንድ ኣድረገው በዓሉ በሰላም ተከበረ በማለት የተናገሩት ውርደተኛ ጀነሎች ኣሁን ምን ይሉ ይሆን ? የኢትዮጵያ መእመናንና ካህናተ ደብተራ ኣሁን ኣክሱምን እውነት በሁለት እግራቸው ተራምደው ለመሳለም ይመጣሉ ? የሚሉ ጥያቄዎች ለእነዛ መርህ ኣልባ ተደማሪዎች ትተን እውነታውን እናውራ፡፡

ኣልጃዚራ ኣምንስቲ ኢንተርናሽናልን ዋቢ በማድረግ “የኣክሱም ጭፍጨፋ” (Axum massacre) በማለት ባሰራጨው ዘገባ፤ በሶስቱም የጨለማ ቀናት በኣክሱም ከተማ የተፈፀመው ግፍ ለዓለም በማስተጋባት የቀደመው ኣልነበረም፡፡ ኣልጀዚራ እና ሲኤንኤን የመሳሰሉት ዓለም ኣቀፍ ሚዲያዎች ትግራይ ከይትኛውም መገናኛ በተዘጋችበት ሁኔታ እውነትን ኣነፍንፈው ሲያጋልጡ፤ እነ ኢቲቪ፣ ፋና እና ዋልታ የመሳሰሉት የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ግን በተጨፈጨፉ ንፁሃን ዜጎች ኣስካሬን ላይ ቆመው፤ ካሜራው ኣስካሬኑን እንዳይቀርፅ በመጠንቀቅ ኣለቆቻቸውን ከወገብ በላይ እያሳዩ የዓለምን ማሕበረሰብ ዋሹ ሊንክ ኣልጃዚራ፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=Xg-Q457Wzb0

እንደ ኣውሮፓዊያን ኣቆጣጠር እስከ 1948 ዓ.ም ዓለማችን ጀኖሳይድ የሚል የወንጀል ክስ ኣልነበራትም፡፡ ከዛ በፊት የነበሩ ክሶች የጦር ወንጀል፣ በሰብኣዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችና የሰብኣዊ መብት ረገጣ የሚሉ ብቻ ነበሩ፡፡ ዓለም እውነታው ኣልገባትም በማለት የሞገተው የህግ ባለሙያ ራፋኤል ላምኪን ግን ጀኖሳይድ የሚለውን የወንጀል ህግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቀባይነት እንዲያገኝ ኣስቻለ፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል እና ቅጣትን የሚመለከት ስምምነት (1948) Convention on the Prevention and Punishment of the Crime of Genocide በሚል ተቀባይነት ያገኘው የወንጀል ክስ በመጀመሪያ ተፈፃሚ የተደረገው በናዚዎች ላይ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ላምኪን ጀኖሳይድ የገለፀበት መንገድ ከጦር ወንጀልና በሰብኣዊነት ላይ ከሚፈፀመው ወንጀል ለየት ባለ መልኩ እንዲታይ ካስቻሉት 10 መመዘኛዎችና 5 ደረጃዎች መካከል ወንጀልን መካድ፣ ማላከክና ማዳፈን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በኣክሱም ጀኖሳይድ ዘንድ እነዚያ ፕሮፌሰር ራፋኤል ላምኪን ያስቀመጣቸው ነጥቦች በተግባር ሲፈፅም ታይቷል፡፡ በመጀመሪያ ከሑሞራ እስከ መቀሌ ኣንድም ሰው ኣልገደንም በማለት ፓርላማው እንዲያጨበጭብ ተደረገ፡፡ በመቀጠል ሎሌች ማሕበረሰቦች የኣክሱምን ጀኖሳይድ እንዳያይሰሙና እንዳያገናዝቡ ደም መጣጭ ሚዲያዎቹን ኣስከትሎ ኣክሱምን ሰላም ኣስመስሎ ነገሮች እንዲዳፈኑ ሞከረ፡፡ በኣክሱም የተፈፀመው እውነታ በዓለም ኣቀፍ ሚዲያዎችና በዓለም ኣቀፍ ማሕበረሰብ ትኩረት መሳብ ሲጀምር ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን በቦታው ተጉዤ ምርመራ ኣካሄድኩ፤ በማለት በኣክሱም ኣንድ መቶ የማይሞሉ ሰዎች በጦርነት ተገደሉ በማለት እውነተኛ ሚዲያዎች የዘገቡትን ቀልብሶ የዓለምን ማሕበረሰብ  ሌላ ስእል ለማስያዝ ቻለ፡፡ ዓለምም በዚህ ኣግባብ መዳኘት እንዳለባት ኣምና ተቀበለች፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=moByGLA7FDc

ኣክሱም ከ4 ዓመታት በውሃላ በተነፃፃሪ ደማቅ ክብረ ብዓል ለመደገስ እላይ እታች እያለች ነው፡፡ በኣደባባይዎቿና በየጓዳዋ የተጨፈጨፉ ልጆቿ በመዘከርም በዓልዋ ኣንድ ብላ ጀምረዋለች፡፡ ዓለም ኣቀፍ ተቋማት እውነተኛ ምርመራ ኣድረገው በኣክሱም እና በኣጠቃላይ በትግራይ ህዝብ ጀኖሳይድ የፈፀሙ ወንጀለኞች በዓለም ኣደባባይ እስኪ ፈረዱና በትግራይ ፍትሕና ርትዕ እስኪነግስ ድረስ፤ የኣክሱም ህመም ኣይድንም፡፡ ሕዳር 1ቀን 2013 ዓ.ም በማይ ካድራ ሀ ብሎ የተጀመረ ጀኖሳይድ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ በኣክሱም ከተማ ተደግመዋል፡፡ ከዕዳጋ ሓሙስ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ማርያም ደንገላት ላይ የተፈፀመው ጀኖሳይዳዊ ጭፍጨፋም ከማይ ካድራ እና ኣክሱም ልምድ መበውሰድ ከከተማ ወጣ ባለ መልኩ የተፈፀመ ወንጀል ነው፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=sov6A_VbwB4

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በትግራይ ህዝብ ላይ ጀኖሳይድ ስትፈፅም ኖራለች፡፡ ዓለም ኣቀፍ ፍርድቤት በተቀበለው የጀኖሳይድ ወንጀል መመዘኛዎች መሰረት በማድረግ በትግራይ ህዝብ ላይ ከሽዋ ቤተመንግስት የኣሁኑ ጨምሮ ኣራት ግዜ እንዲሁም ከጎንደር ቤተመንግስተ ኣንድ ግዜ ጀኖሳይድ ተፈፅሞበታል፡፡ የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያዊነቱ በነበረው ኣቋምና ቂምን ከመርሳት ባህሪው ተነስቶ ያለፉትን ኣራቱም ጀኖሳይዶች በተለያየ ሁኔታ በማስታወስ ኣብሮነቴን ይሻላል በማለት ለኢትዮጵያ የነበረውን ቀናኢነት ሲያንፀባርቅ ኖሯል፡፡ ዘመነ “ሸ” ኣንድና ሁለት፤ እንዲሁም “ማይ እንዳ ኣቦ” እና 11 ቁጥርን ግንባር ላይ መከላት የእስጢፋኖሳዊያንን ጭፍጨፋ ለማስታወስ እየተጠቀመበት መጥቷል፡፡ “ብዘመን ውቤ ዝፀመመ ብዝባን ውቤ እናበለ ይነብር” የሚል ደግሞ ከጎንደር ቤተመንግስት የተፈፀመበትን ጀኖሳይድ ለማስታወስ የሚጠቀምባቸው ዜዴዎች እንደሆኑ ኣበው ያስረዳሉ፡፡

የትግራይ ህዝብ ያለፉትን ጀኖሳይዶች “ሾላ በድፍኑ” በማለት በኣብሮነት የኖረባትን ኢትዮጵያ ኣሁን በራሷ ተነሳስታ ተዋርዳለች፡፡ የትግራይ ህዝብ በልበ ሰፊነት እንዳይነሱ ኣድረጎዋቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ወንጀሎች ኣሁን ማስታወስ ተያይዞታል፡፡ ታሪኮቹን ከገዳማቱና ከኣዛውቶቹ መሰባሰብ ጀምሯል፡፡ በየጊዜው ቁጥሩ ከመቀነስ እና ርስቱ እየተቆራረሰ ከመደህየት ውጪ በኢትዮጵያዊነቱ ያገኘው ፋይዳ ምን እነደ ሆነ ማሰላሰልም ተያይዞታል፡፡  ከኣለወሃ እስከ ቆቦ እንዲሁም ከኣብርሃ ጁራ፣ መተማ ዮሃንስና ራስ ደጀና የጠፋው የትግራይ ህዝብ ቁጥር ኣያሰላሰለ ነው፡፡ ቱርኪ በኣርማኒያ ህዝብ ላይ የፈፀመቺው ጀኖሳይድ እንዳይነሳባት ዓለምን የምትማፀነው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፍፃሜ ነው፡፡ የዘመነ ሸ ኣንድና ሁለት ፍፃሜዎችም ደግሞ የ1882 እና 1935 ዓ.ም ናቸው፡፡ በ2013 ዓ.ም የተፈፀመው ጀኖሳይድ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ኣይደለም ዓለም የሚያፍርበት ሆኗል፡፡ በቅርቡ ስራው ያቋረጠው እና በተባበሩት መንግስታት የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሙያዎች የምርመራ ውጤት እንደሚያመለክተው በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈፀመው ወንጀል የተወሳሰበ እና በየትኛውም ዓለም ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ሃገሮች ተፈፅመው የተመዘገቡ ጀኖሳይዶች በብሄሮች መካከል ወይ ደግሞ መንግስታት በህዝባቸው የፈፀሟቸው ናቸው፡፡ በትግራይ ህዝብ የተፈፀመ ግን ብዙ ተዋናዮችና የዘላለም ቂም መወጣጫ የተደረገ ነው፡፡ በኣንድ በኩል በህዝቡ ላይ ጀኖሳይድ ያወጀ መንግስተ ኣለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትግራይን በማጥፋት ብቻ የታሪክ ባለቤቶች እንሆናለን በማለት የተሰለፉ የኣማራ ልሂቃን ትግራይን ከስር መሰረት የማጥፋት፣ ርስቶችን የመውረርና ሃብቱን የማውደም ዘመቻ ኣከናውኗል፡፡ ከሃገር ውጭ ተገብዞ በትግራይ ጀኖሳይድ ከፍተኛ ወንጀል የፈፀመ ኋላ ቀር የኤርትራ ሰራዊት ደግሞ በሳዋ የተማረውን ጥላቻ በቀጥታ የተገበረበት ነው፡፡ ለዚህ ነው የባለሞያዎች ቡድን ኣስተባባሪው መሓመድ ቻንዴ የተወሳሰበ ሲሉ የጠሩት፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=Sm7NaNZ9Z9k&t=628s

ያም ሆነ ህይ ኢትዮጵያ ህዝቤ ነው በምትለው የትግራይ ህዝብ እና የታሪክ መመኪያየ ነው በምትለው ኣክሱም ላይ የፈፀመቺው ጀኖሳይድ በዓለም ፊት በጥቁር መዝገብ ሰፍሯል፡፡ ለዘመናት ጀኖሳይድ እየፈፀመች ተሸፍኖላት የቆየች ኢትዮጵያ እና በወንጀላቸው የማይጠሩት ነገስታቷ ኣሁን እውነተኛ መጠሪያ ስማቸው የሚያገኙበት ኣጋጣሚ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በዚችው ገዳዮች ሰብስባ ህዝቦቿ በምትጨፈጭፍ የተዋረደች ሃገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም በወገኑ ላይ ጀኖሳይድ ሲፈፀም ከበሮ ደላቂ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከቀጠለች ታሪኩ እንደ ጎደፈ ይኖራል፡፡ ያች የተዋረደች ሃገር እኔ እና መሰሎቼ እንደሚመኟት ከሆነች ደግሞ ለዘላለሙ በሓዘን ይቆዝማል፡፡

ገ/ሄር ከመቐለ

By aiga