ሙሉቀን ወልድ ጊዮርጊስ
ሰኔ 13/2012
አዲስ አበባ
ይህ ጽሁፍ የዛሬ ሦስት አመት በሪፖርተር ጋዜጣ ታተሞ ለአንባቢያን እንዲሰርስ በፖስታ ቤት በኩል ልኬው በማላውቀው ምክንያት ሳይታተም የቀረ ነው፡፡ አሁን ባለው የሀገሪቱ ሁኔታ በተለይም የምርጫ ቦርድ ቁንጮ የሆኑት ወ/ት ብርቱካን ከስራ ለመገለል ማመልከቻ ባስገቡበት፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ደግሞ ደ/ር ዳንኤል በቀለ ቀጣይ ባለተራ መሆናቸውን በስፋት በሚነገርበት፤ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕረዚደንት የነበሩት ወ/ሮ መአዛም ተሸኝተው በሚገኙበት ወቅት ላይ የምንገኝ በመሆኑ ጽሁፉ ወቅታዊ ነው ብዬ ባማሰብ ቀደም ብሎ በተጻፈ መልኩ ሳይነካካ የተላከ መጣጥፍ ነው፡፡
በተቋሞች የወለፊንዲ ጉዞ በእጅጉ የተፈተነች ሀገር
የዛሬ ሁለት አመት ግድም ከስር የተመለከተው የግጥም ስንኝ ኤፍሬም እንዳለ በአዲስ አድማስ አስነብቦን ነበር፡፡
እንኳን ስድስት መስመር መቶም አይገልጽሽ
እንዳው በደፈናው የጉድ ሃገር ነሽ
ኤፍሬም የተጠቀመበት አውድ በወቅቱ በሃገሪቱ የነበረውን ለከት የለሽ ስግብግብነት ለመግለጽ ሲሆን መታሰቢያነቱም ኢትዮጵያን በግጥም መወድስ ለመጻፍ ለታተረው አንድ ተማሪ ነበር፡፡
በሃገራችን እንዲህ አይነት ስንኝ በስፋት ማህበራዊ ግንኙነትን ለመግለጽ ስንጠቀምበት እንስተዋላለን ዛሬ ግን ለተቋሞቻችን ስንክሳር ብንጠቀምበት አይከፋም ባይ ነኝ፡፡ የተቋሞቻችን የወለፈንዲ ጉዞ በአስተውሎት ለመረመረ በእርግጥም የጉድ ሀገር መሆንዋን መገንዘብ ይችላል፡፡
ተቋሞቻችን በጨረፍታ
ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ በአስተማማኝ መሰረት በኢትዮጵያ ምድር ለማኖር ለምን ተሳነን የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ በዜጎች እየተነሳ የሚገኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን በሚያጠናክር መልኩ ኢትዮጵያ አንድ፤ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ እድሎች አምልጧታል ሲሉ የሚደመጡ ዜጎችም አሉ፡፡ ከሁለቱ ወገኖች የሚቀርቡ ሃሳቦች የጠንካራ ተቋም አስፈላጊነት ለመጠቆም የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ግን ምን ያህል ጊዜ ቢሰጠን ጠንካራ ተቋም መስርተን እንጨርሳለን? እንደየፍላጎታችንና ምኞታችን ይለያያል፣ 2 ዓመት፤ 5፤ 10፤ 50፣ 100 ምናልባትም ከዚያ በላይ የምንል ይመስለኛል፡፡ እልህ፣ ቁርጠኝነትና ሩቅ አሳቢነት ኮርኩሮን በጊዜ የለኝም መንፈስ ከተነሳሳን በቅርብ ጊዜ፤ አልያም ዳተኝነት፣ ደንታቢስነትና አድርባይነት ተከናንበን ከተኛን ደግሞ የምንፈልገው ምርጥ ተቋም ሳናይ እንደናፈቀን እንኖራለን፡፡
ቀለል ባለ አገላለጽ ተቋም ማለት አንድን ዓላማ ለማሳካት የሚያስፈልግ የሰው ሃይል፣ ፋይናንስና ቁሳቁስ አደራጅቶ ተገቢውን መመሪያዎችና ደንቦች በመቅረጽ በተፈቀደ ጊዜና ጥራት አቀናጅቶ የሚሰራ መዋቅር ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን በቂ አይሆንም፡፡ ተቋሙ ለተቋቋመለት ዓላማ ስራውን በብቃትና በታማኝነት በማከናወን በተቋሙ ውስጥ ግልጸኝነት(Transparency) ተጠያቂነት(Accountability) ለማስፈን የሚፈቅድ ሰራተኛ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ለማንም ያልወግነ፣ በተቋሙ መመሪያና መመሪያ ብቻ የሚሰራ፤ ለህሊናው ተገዥና ሙያዊ ነፃነቱ የሚያስጠብቅ ሰራተኛ ሲኖረው ተቋሙ የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ጊዜ፤ ቴክኖሎጂ ወዘተ በተቋም ግንባታ ሂደት የሚጫወተው ሚና የጎላ ቢሆንም ተቋማዊ ግንባታ በጣም አስቸጋሪ፤ በአጭር ጊዜ እውን መሆን የማይችልና ውስብስብ ተደርጎ መቅረብ የለበትም፡፡ ከዚህ ውጭ ‘ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም’ የሚለውን ድርሳን ለማወፈር ከሚረዳ በስተቀር ለጠንካራ ተቋም ግንባታ ብዙ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ እድሜ ጠገብ ተቋሞች ባለቤት ናት፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኢትዮጵያ መንገዶች፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፤ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት፤ የኢትዮጵያ ግብርና፤ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመሳሰሉ፡፡ እነኚህ ተቋሞች በአጠቃላይ ባዶዎች ናቸው ለማለት አልደፍርም፡፡ ለአመታት የካበተ በልምድና በትምህርት የዳበረ የሰው ሃይል፣ በጀትና ዘመን የዋጀ ወይንም በቂ ተሞክሮ ካላቸው አገሮችና ድርጅቶች የተቀዳ መመሪያና ደንብ የላቸውም ብዬም አልከራከርም፡፡ እንዳውም በተቃራኒው የሚገኙ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከዚህ ቀደም በጃንሆይና በኮሎኔል መንግስቱ በኢህአደግም ጊዜ በተቋሞች ላይ ምንም ስራ እንዳልተሰራ አድርገን ራሳችንን የማሞኘት አባዜያችንን ለጊዜው ገታ አድርገን ስለነዚህ ተቋሞች ማሰብ ስንጀምር ሀገሪቱ ሰሚ አጣች እንጂ እስካሁን በተቋሞቿ ላይ ያፈሰሰችው ሰው፤ ገንዘብና ጊዜ ሌላው አለም ከደረሰበት ማማ ለመድረስ ምንም እንዳልቀራት መረዳት ይቻል ነበር፡፡
በትምህርት ዝግጅትም ቢሆን ከቀድሞዎቹ እንደነ አክሊሉ ሀብተወልድ፤ መንግስቱ ንዋይ፤ ይልማ ደሬሳ፤ ከተማ ይፍሩ፤ ክፍሌ ወዳጆ፤ ይድነቃቸው ተሰማ የመሳሰሉ ብርቅየ ሰዎች ነበርዋት፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ (ኢሕድሪ) የመንግስትነት ጊዜም ኮ/ል መንግስቱ፤ ፍቅረስላሴ፤ ፍስሃ፤ በአሉ ግርማ፣ ሺመልስ ማዘንጊያ፣ ደበላ ዲንሳ፤ ሃዲስ ተድላ፣ ፋንታ በላይ የመሳሉ የሀገር ልጆች ተሰይመውባት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ (ኢፌድሪ) በነበረው ስርአትም በሃገሪቱ በሁሉም ክልሎች በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተው በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እየተማሩበት ይገኛሉ፡፡ ኢህአዴግ ለአባላቱም ቢሆን ንፉግ አይደለም፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሎለት በሀገር ውስጥና በውጭ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ትምህርት ያላጠናቀቀ የኢህአዴግ መካከለኛና ከፍተኛ አመራር መፈለግ ከንቱ ድካም ነው፡፡ አብይ፤ ደመቀ፤ አብርሃም፤ ደጉ፤ አርከበ፤ ሃይለማርያም፤ ሙፈሪያት፤ ሙክታር፤ ደብረጽዮን፤ አባዱላ፤ አወል አርባ፤ ጁነዲን፤ በረከት፤ ባጫ ደበሌ፤ አሽዴል ሃሰን፤ ለማ፤ ዳባ ደበሌ፤ ንጉሱ (አንዳንዴም ባልና ሚስት ይገኙበታል) ወዘተ የዚሁ በረከት ተቋዳሶች ናቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ታዲያ ጥያቄው እነኚህ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠሩ፤ በሳል ባለሙያዎች ያሉዋቸውና ተፈላጊ ግብአት ያሟሉ ተቋሞች ለምንድነው የናፈቅነውን ጠንካራ ተቋም ምስል ሊያሳዩን ያልቻሉት? በዚሁ ባለንበት የለውጥ ዘመንስ ለምን ገቢራዊ ለማድረግ አልፈቀዱም ወይንም አልቻሉም?
ለጥያቄው መልስ ይሆን ዘንድ በአሃዝ ተንተርሶ የሚደረግ ትንተና ለጊዜው ባይኖርም ተገማች የሆኑ ሃሳቦች ማንሳት ግን ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ተጠቃሽ የሚሆነው በተቋሞቹ የሚመደቡ ሰዎች በልዩ ልዩ ጥቅም በመደለል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በማስፈራራት ተፈላጊ ያልሆነ ስራ እንዲሰሩ ማድረግ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ የተመደቡት ባለስልጣኖች ለተመደቡበት ቦታ የማይመጥን፤ የተቀመጠውን የአሰራር መመሪያና ደንብን የሚያፋልስ፤ ብሎም ራስን ወደ ረከሰ የማንነት ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ተልእኮ ያከናውናሉ፡፡ በአጭር አነጋገር ከተቋሙ የአሰራር መመሪያና ደንብ በተጻራሪ ተግባር ላይ መቆም ማለት ለህሊና ተገዥ ያለመሆንን ያመለክታል፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ደፈር ብለው የለም ይህ ሃሳብ በዚህ ምክንያት ማከናወን አልችልም የሚል የማይናወጥና ወጥ የሆነ ትንተና መስጠት አይችሉም፤ ወይንም የዚህ ውሳኔ አካል መሆን አልፈቅድም ማለት እስካልቻሉና፤ ሲበረታም ከዚህ ጋር የተያያዘ ጫና መቋቋም የሚያስችል ወኔ ከሌላቸው ያው ‘ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም’ ውስጥ ራስን የመደበቅ ታማሚ ይሆናሉ፡፡
ተቋሞችና ለውጡ
በዶ/ር አቢይ የሚመራ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ኢትዮጵያዊያን ብዙ ተስፋዎች ሰንቀናል፡፡ ከነኚህ ተስፋዎችም ጠንካራ ተቋም የማየት ተስፋ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያትም አለው፡፡ የጠንካራ ተቋም አለመኖር ሀገሪቱ በእኩልነት፣ በሀብት ተጠቃሚነት፣ ሀሳብን በነጻ የማራመድና የመደራጀት መብት የከፈለችው ዋጋ በመረዳት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ መደላድል መፈጠር አለበት ከሚል ጽኑ አስተሳሰብ የሚመነጭ ጭምርም በመሆኑ ነው፡፡ አሁን መሬት ላይ እየታየ ያለው እውነታ ከአጠቃላይ ቀዳሚ ምኞትና ተስፋ ጋር የሚኖረው ትስስር በጊዜ ሂደት የሚታይ ቢሆንም ተቋሞችን በተመለከተ የለውጡ መንግስት የሚከተለው ስትራቴጂ ባለሁለት ዘርፍ እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ እነሱም 1- የመኳኳያ ቀዶ ጥገና (Cosmetic Surgery) ማድረግ 2- መዋቅራዊ ንቅዘት (Structural Defacement) ናቸው፡፡
ስትራቴጂ (አንድ) የመኳኳያ ቀዶ ጥገና (Cosmetic Surgery)፡፡ በስልጣን ዘመናቸው ቤተመንግስቶቻቸው ሲያፈርሱና ሲያድሱ ያሳለፉ መሪዎች ዓለማችን አይታለች፡፡ የጥንቱን ትተን የቅርብ ጊዜዎቹ ብንመለከት ሳዳምና ጋዳፊ ትላልቅና ዘመናዊ አዳዲስ ቤተመንግስቶች በመገንባት፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ደግሞ ነጩ ክብ ቤተመንግስታቸው በማሸብረቅ ይጠቀሳሉ፡፡ በሀገራችንም ይህ ስትራቴጂ በስፋት ጠቀሜታ ላይ እየዋለ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የቤተመንግስት እድሳት እና የፌዴራል ተቋሞችና የባለስልጣኖቻቸው መኖሪያ ቤት ከውጭ ሀገር በተገዙ ውድ እቃዎች የማሸብረቅ (በሰሪው ቋንቋ-ማዘመን) ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ በእርግጥ ለሥራ አስፈላጊ የሆኑትን ቁሳቁስና የባለስልጣኖች መኖሪያ ቤት ማሟላት የማይታለፍ ጉዳይ ቢሆንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማስታወሱ ደግሞ አይከፋም፡፡ በቅርቡ የ2013 ዓ.ም 476 ቢልዮን ብር በጀት ለተወካዮች ም/ቤት በቀረበበት ወቅት ገንዘቡ ቢሮዎች በማሳመር፤ በውድ ሞባይሎች፤ በተቀናጣ ላፕቶፕና ሌሎችም የግለሰብ ጥቅምን ያተኮሩ ግዢዎች ላይ እንዳይውል ተወካዮቹ በሚያሳዝን መልክ አስፈጻሚውን የተማጸኑበት መንገድ ማስታወሱ በቂ ይመስለኛል፡፡ የተወካዮቹ ተማጽኖ የጠንካራ ተቋም እጦት ተከትሎ የመጣ ችግር መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ ሌሎች ትኩረት የተሰጣቸው አቅጣጫዎችም ተካተዋል፣ እነሱም- ቁልፍ በሆኑ ተቋሞች ሳይታሰብ ጉብኝት በማድረግ ሰራተኛን ማስደንገጥ እና ተቋማዊ ገጽታ ሳይሆን የግል ስብእና ጎላ የሚያደርጉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ስትራቴጂ (ሁለት) መዋቅራዊ ንቅዘት (Structural Defacement)፡፡ ይህ ስትራቴጂ በዋናነት ለጠንካራ ተቋም ምስረታ አገልግሎት የሚውሉ ዋና ዋና ግብአቶች ማለትም የተቋሞች የሃሳብ አመንጪነት፣ የመጠየቅ፣ የአገልግሎት ማሻሻያና የምርምር ነጻነት የመሳሰሉትን መንፈግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ማለት ተቋሞች የሰው ስብስብ ከመሆን ባለፈ ስራ ፈጣሪነትን፤ ጠንቃቃነትንና ምርታማነትን በሚያበረታታ ሥራ ላይ አተኩረው አይሰሩም ማለት ነው፡፡ በንደዚህ አይነት ሁኔታ ላይ የሚገኙ ተቋሞች በራሳቸው የሃላፊነት ክበብ ውስጥ ሆነውም በአንዳንድ ተልእኮዎቻቸው የህዝብን ጥቅምና ሰላም የሚገዳደሩ ስራዎች ላይ ተሳታፊ የመሆን እድላቸው ሰፊ ይሆናል፡፡ ቀሪው የዚህ ጽሁፍ ክፍል የሚያጠነጥነው ከዚህ ስትራቴጂ በመነሳት በተለይም ዲሞክራሲ ይገነባሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ተቋሞች በዚህ በለውጥ ወቅት በታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች (ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ባተኮሩ) ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ይዳስሳል፡፡ ይህንን ስትራቴጂ ለማስፈጸም ከዋሉ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከልም ሌላ አማራጭ ለመቀበል ማንገራገር፣ የይስሙላ ውይይት የማድረግ በሽታ፣ ታላቅ ሀገራዊ የሆነን ጉዳይ ከውስን ባለሙያዎች ጋር ብቻ መወሰን፣ የጥቅም ግጭት መርህ ያለማክበር የመሳሰሉ ይገኙበታል፡፡
በቀጥታ ወደ ስትራቴጂውና ውጤቱ ከመግባታችን በፊት በዚህ የለውጥ ወቅት፤ በዚህ አስቸጋሪ በሆነው የሀገራችን ሁኔታ ላይ የተቋሞች ወለፈንዲ ጉዞ የመገኘት ዋነኛ አውድ በመጠኑም ቢሆን በቅድሚያ መተዋወቁ አይከፋም የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ለዚህም ሦስት አበይት ምክንያቶች ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ነጥብ የዶ/ር አብይ መንግስት በውጪው አለም ላይ የተንጠለጠለ ፖለቲካና የስብእና ተክለ-ነቀላ ስራ ላይ መጠመድ በሀገር ውስጥ ላለው ችግር በተለይም ጠንካራ ተቋሞች የመፍጠር ተግባር ገፋ አድርጎታል፡፡ ይህም የሀገሪቱ ተቋሞች ተጠባቂው መሰረታዊ የለውጥ ሃዲድ ስተው በስስ ጎዳና ላይ እንዲቀጥሉ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ከየት እንዳመጣ የማይታወቀውን ‘በለውጥ ወቅት የሚፈጠር’ የሚል እሳቤ በሀገር አቀፍ ደረጃ መጠነ ሰፊ የተቋሞች ምስቅልቅልን ፈጥሯል፡፡ በሶስተኛ ደረጃም ቀደም ሲል የተሰጡት ተስፋና በተግባር እየተገለጸ ያለበት ሁኔታ እየተምታታ ማስቸገሩም ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህም የተነሳ በመንግስት አጉል ‘በለውጥ ወቅት የሚፈጠር’ እምነት የተንተራሰ ቅዠት በዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ ‘የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያልተመለከተ፣ ቅደም ተከተሉ የተፋለሰና የራስን አስተሳሰብ የመጫን’ የአመራር ዘይቤ ተከትሎ አዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እውነታዎች በሀገሪቱ ላይ ለመከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ በፖለቲካው መስክ የለውጡ እምብርት ናቸው የሚባሉት ኦሮሚያና አማራ ክልሎች ሳይቀሩ በየጊዜው ምክንያት እየፈለገ የሚነሳው የማያቋርጥ የህዝብ እሮሮ፣ በደቡብ ክልል ተከድኖ ያደረውን የክልል እንሁን ጥያቄዎች፣ እንደዚሁም የህብረብሄራዊ ፌደራሊዝም በሚል የተሰባሰቡ ሀይሎች የፖለቲካውን አውድ ይበልጥ ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የኢኮኖሚው ግንባር ፈተናም በእጅጉ የሚያስጨንቅ ሆኗል፡፡ ባለሀብቶች በስራ ከሚያሳልፉት ቀናት ይበልጥ ስራ ፈትነትን በግዴታ የመረጡበት፤ በየመስሪያ ቤቱ የሚታየው አይን ያወጣ ዝርፊያ ከምንጊዜውም በላይ ጣራ የነካበት፤ የስራ አጥነት ቁጥር ወደላይ የሚገሰግስበት፣ ጎዳና ላይ ቤቱን ያደረገ የቤተሰብ ቁጥር እንደጎርፍ የበዛበት፤ በአጠቃላይ የኑሮ ሁኔታው እለት በእለት እየቀለጠ የህዝቦች ኑሮ የመቋቋም አቅም ክፉኛ የተፈታተነበት ወቅት ላይ ሀገሪቱ ትገኛለች፡፡ በማህበራዊ ዘርፍም ለረዥም ጊዜ አብረው የኖሩ ህዝቦች እጣ ፈንታ መገዳደል፤ ቤተእምነቶች መቃጠል፤ ገዘፍ ያለ መፈናቀልና ለከት ለሌለው ሰብአዊ ሰቆቃ ሀገሪቱ አጋልጧታል፡፡ እንግዲህ የህሊናችን ጓዳ ስንዳስስ በሁሉም መስክ የምናገኘው ሃቅ ወይንም ሀገሪቱ ያለችበት አውድ ይህ ነው፡፡ በዚህ ምስቅልቅል ሁኔታ ደግሞ ተቋሞች የተረጋጋ እለታዊ ስራቸው ለመፈጸም አዳጋች ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታም ቀስ በቀስ ተጉዞ ከስድሳ በመቶ በላይ የሆነው የሀገሪቱ ክፍል ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደር ዳርጎታል፡፡
ከላይ የተገለጸው የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ መጪውን ለመተንበይ ፍጹም አስቸጋሪ አድርጎታል ቢባል ትክክለኛ ግምት ይመስለኛል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ሀገሪቱ አንድ ወቅቱን ጠብቆ መመለስ የሚገባት ህገመንግስታዊ ጥያቄ ከፊት ለፊትዋ ተደቅኗል፡፡ ምርጫ የሚባለው የሰዎች ዲሞክራሲያዊ መብት፡፡ በእውነቱ ይህ ጉዳይ በንጹህ ልቦና ለመረመረ ሰው መንታ መንገድ ላይ ለመቆም የሚገደድ ይመስለኛል፡፡ የሚይዙትንና የሚጨብጡትም ያሳጣል፡፡ ይህ የምርጫ ‘ምርጫ’ ጥያቄ መመለስ ለሀገሪቱ፤ ለህዝቦችዋና ለተቋሞችዋ ከተግባሮች ቅደም ተከተል መርህ አንጻር የበላይ በላይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ሀገሪቱ ወይ ምርጫውን በተፈቀደለት ጊዜ ማካሄድ ወይንም ማራዘም በሚሉት መንታ መንገድ ላይ ተገኝታለች፡፡ እዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባን ቁምነገር ፖለቲካ ድርጅቶች ሁኔታውን የሚመለከቱበት አይን ለእናት ድርጅቶቻቸው ከሚያስገኝላቸው ጠቀሜታና ጠቀሜታ አንጻር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ታዲያ ሀገር እንዲህ በመሰለ ፈተና ስትወድቅ ተቋሞች የነሱም የመፈተኛ ጊዜ መሆኑን በጥንቃቄና በአስተውሎት መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን መሰል ህገመንግስታዊ ጥያቄ ለመመለስ ተቋሞች ለድርድር የማይቀርበውን የግልጸኝነት፤ ገለልተኝነት እና አሳታፊነት መርህ በተጨማሪ ትጋት፤ ብልህነትና ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈቃደኝነት መሰረት ያደረገ መሆን ይገባዋል፡፡ ለነኚህ መርሆዎች ተገዢ መሆን ጥቅሙ ለሀገርና ለህዝብ ብቻ ሳይሆን ተቋሞቹንም በሰሩት የሰለጠነ ሥራ የህዝብ ክብር፤ እምነትና ሞገስ ያገኙበታል፡፡
ኢትዮጵያም በሁለት ጎራ ማለትም ምርጫው ይራዘምና አይራዘም በሚሉት ውጥረት ላይ ተገኝታለች፡፡ ይህ ችግር ከማንኛውም በላይ ለምርጫ ኮሚሽን ፈታኝ ነው፡፡ ኮሚሽኑም በዚህ መንታ መንገድ ላይ ሆኖ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ይበልጥ ተጠባቂ ያደርገዋል፡፡ ወይ ጠንካራ ተቋም ሆኖ መገኘት ወይም ልፍስፍስ መሆን ናቸው፡፡ በጊዜውም በተከተለው የልፍስፍስነት መንገድ እንደአጋጣሚ ሆኖ ሁለት ተአምር ሊባሉ የሚችሉ ቅጽበታዊ እድሎች በተለይም ለአብይ መንግስት በሩን አንኳኩተውለታል፡፡ አንደኛው ስራዬ በአግባቡ ስላላሟለሁ እስከ ነሃሴ 2012 የይራዘመልኝ ጥያቄና፤ ትንስ ዘግየት ብሎም በኮቪድ-19 ምክንያት የህዝብ እንቅስቃሴና መሰብሰብ የሚገድብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስት በማወጁ ምርጫ ለማካሄድ አልችልም የሚል የውሳኔ ሃሳብ በማቅረቡ ነበር፡፡ የሁለቱም እድሎች ቅደም ተከተል አንዳንዴም በተጠና አንዳንዴም በአጋጣሚ ወጣ ገባ እያሉ በመጡ ሁነቶች ታጅበው የተከናወኑ ሲሆኑ ቀሪው ታሪክ ነው እንዲሉ ተቋሞቹ ጉዳዩን ያስኬዱበት መንገድ ከላይ ከጠቀስኳቸው የተጠያቂነት፤ ግልጸኝነት፤ አሳታፊነት፤ ገለልተኝነት፤ ዝግጁነትና ተነሳሽነት መርህ አንጻር መመልከቱ ከተነሳንበት የጠንካራ ተቋም የማየት ናፍቆት የራሱ የሆነ ትምህርት ይሰጠናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በኋላ ላይ እንደሆነው ሂደቱ በምርጫ መራዘም መቋጨቱ ምናልባትም ሲካሄድ የነበረው ረዥሙን የቴሌቪዝን መስኮት ውይይት እንደ አንድ ስትራቴጂ ጥቅም ላይ መዋሉን ልንረዳ እንችላለን (እዚህ ላይ ገሚሱ በምክንያታዊነት፣ ከፊሉ የገዢውን ጭፍን ደጋፊነት፤ ገሚሱ ደግሞ በየዋህነት ሲሳተፍ እንደነበረ ማስታወሱ ጠቃሚ ይሆናል)፡፡ ሌላው በዚህ ሂደት ውስጥ ሀገሪቱ እያለች በኢትዮጵያ ተቋሞች ታሪክ አንድ ድንቅ ክስተት ተከናውኖ ማለፉን መግለጽ የሚያስፈልግ ይሆናል፤ የፌዴሬሽን አፈጉባኤዋ የስልጣን መልቀቅ እርምጃ፡፡ እኔ በግሌ ክብርት አፈጉባኤዋ ለወሰዱት አቋም አድናቆቴን ችሬያቸዋለሁ፡፡ እርምጃው በግልና በአጠቃላይ ደግሞ ለሀገራችን ተቋሞች የሚኖረው ትሩፋት አስተሳስሮ ማየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ አንድ የፓርቲ አባል የሚወግነው የፓርቲው ሃሳብና ውሳኔ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እሳቸውም ያደረጉት ይህንኑ ነበር፡፡ እርምጃው ግን ተራ የሚባል አይደለም፣ በሁለት ምክንያት፡፡ አንደኛው ይዘውት የነበረውን ትልቁን ስልጣን የሚለቁበት ምክንያት በግልጽ ቋንቋ አስረድተው ነው፡፡ ሁለተኛው ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አንስቶ እስከ አጣሪ ጉባኤው የዘለቀው፣ በኋላም በምክር ቤቱ እንደታየው ሌላኛው ህሊናቸው ቢጠቀሙ ኖሮ ‘የፌዴሬሽኑ ዘመን ያልቋጨው’ የማራዘሚያ ክኒን ተጠቅመው በስልጣናቸው መቆየት የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም ነበር፡፡ በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት እሳቸውን የማጥላላት ‘የህዝብ አደራ ጥላ ሄደች’ የተሰጠ አስተያየት ግን ውስጡ ለቄስ ብሎ ከማለፍ ውጪ አስተያየት መስጠት ጉንጭ አልፋነት ነው ባይ ነኝ፡፡ የአፈጉባኤዋ ‘ወደፊት ከታሪክ ፍርድ ይጠበቃል’ የሚለው አባባላቸው የሚመጥን ሀሳብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
በሃገራችን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ታሪክ ሁለት መልክ አለው፡፡ አንዱ በግዴታ ሲሆን ሌላው ደግሞ በውዴታ ነው፡፡ የድሮውን ትተን የቅርቡን ብንመለከት ከሃገሪቱ ፕሬዚዳንት (ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ) አንስቶ እስከ ታችኛው እርከን በርካታ ሃላፊዎች የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ አቅርበው እንደለቀቁ ሲነገር አድምጠናል፡፡ የሌሎቹ ምን እንደሆነ ያለኝ መረጃ ውስን ሲሆን የሁለት ሰዎች (አቶ ሀይለማርያምና ወ/ሮ ኬሪያ) የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ግን አውራ ርእስ አድርገን መውሰድ የምንችል ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ሁለቱም ሰዎች በቴሌቪዝን ቀርበው የመልቀቂያው ምክንያት ምን እንደሆነ ከራሳቸው አንደበት አዳምጠናል፤ ያስከተለው ውጤትም ምን እንደሚመስል በአይናችን ተገንዝበናል፡፡ ሆኖም የሁለቱ ባለስልጣኖች መልቀቂያ ስናነጻጽር ጣጣው ለየቀል መሆኑ ልብ እንላለን፡፡ የአቶ ሃይለማርያም ‘ለውጡን የመደገፍ’ እንድምታ ያለው ንግግር በመሪነታቸው ጊዜ የተፈጸመ ችግር ለማንጻት በፈቃደኝነት መሰል ግን በውስጠ ድርጅት የተደረገ ፍልሚያ ያመጣው ግፊት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባትም ወደ ስልጣን ለመውጣት ያሰፈሰፈ ሃይል ባደረሰባቸው ጫና ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በግዴታ የተከናወነ፤ እሳቸውም ‘ከጠበሉ ልራቅ’ ብለው የተቀበሉት እንደሆነ መገመትም ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ የድርጅታቸው የደህዴን አባላት ያደረሱባቸው መዋከብ ከፍተኛ እንደነበር በስፋት ሲወሳ እንደነበር እናስታውሳለን፣ ይህ ደግሞ አቶ ሃይለማርያም ስልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት አልነበራቸውም ወደሚል ጥግ ይገፋፋናል፡፡ በሌላ በኩል ወ/ሮ ኬሪያ ‘ለህሊዬና ለህገመንግስቱ ባለኝ ታማኝነት ይህንን መቀበል አልችልም’ ከዚያም ባለፈ ‘መታገል አለብኝ’ ብለው እኚህ ወጣት፤ ሴት፤ ሙስሊም እና ቆንጆ ስልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ከአንደበታቸው አዳምጠናል፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ በመርህ ከሚገዛ መሪ የምናገኘው መስዋእትነት ነው፡፡ (እዚህ ላይ ምንአለበት ቆንጆ ብለን ብናደንቃቸው፡፡ በእርግጥም ቆንጆ ናቸው፡፡ ስለቁንጅና ሲነሳ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በአንድ በየወሩ የሚዘጋጅ የወግ ምሽት ላይ ዶ/ር አቢይ ከቀደሞቹ መሪዎች ጋር በማነጻጸር ቆንጆ ናቸው ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ በትክክልም የወንድ ቆንጆ ናቸው፡፡ ሆኖም ማድነቁ ለቁንጅና ብቻ ሳይሆን ለስራና ለሰብእናም ቢለመድ ጥሩ ነው፡፡ በእለቱ በዳኛቸው አገላለጽ ላይ ትንሽ ነገር ጣል አድርጎ ማለፍ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ዳኛቸው ስለኤስቴቲክስ ሲናገር ሁለት ጊዜ ተመልክቸዋለሁ፡፡ አንደኛው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለህንጻ ማስፋፊያው የግቢውን ዛፎች በቆረጠበት ጊዜ የአዲስ አበባው ፕሮፌሰር አድማሱ እና የጎጃሙ ፊትወራሪ አድማሱ ያነጻጸረበት ነበር፤ ሁለተኛው ደግሞ ከላይ የገለጽኩት የመሪዎች ቁንጅና የደሰኮረበት፡፡ በሁለቱም ምልክታዎቹ ምሁራዊ ቅብ ያለው ነገር ግን በአመዛኙ ጥላቻ ያጠላበት ነበር፡፡ ዳኛቸው ስለ ሎምብሮዞ ቲዮሪ ማወቁን አላውቅም፤ በዚያ የወግ ምሽት ግን ንፉግነትን፤ አድላአዊነትን፤ አድርባይነትን፤ ጥቅመኝነትን ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥላቻን አይቼበታለሁ፡፡ ለመልከቀናዎች ‘የብጽእና’ ካባ ለፉንጋዎቹ ‘የዲያብሎስነት’ ማእርግ ሲያከፋፍል ነበር ያመሸው፡፡ ወደ ቆንጆዋ ጉዳይ ስንመለስም ምንም እንኳን በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት እንደ ከሃዲ ቢያስቆጥርባቸውም እንደዚህ የመሰለ ጀግንነት መለመድ አለበት፡፡ ለዚህም ነበር የእሳቸው መልቀቅ እንደተራ ድርጊት ልንወስደው አይገባም ያልኩት፡፡
ተስፋ የተጣለባቸው ሦስቱ ህገመንግስታዊ ተቋሞችና ግብረመልሶቻቸው
ኢትዮጵያ ከ27 አመት በፊት አሁን የምትመራበት ህገመንግስት አርቅቃ እሰከዛሬ ድረስ ስትተዳደርበት ቆይታለች፡፡ ሀገሪቱ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በቀጣይነት ለማስቀጠል ጉልህ ሚና የሚኖራቸው ሦስት ህገመንግስታዊ ተቋሞች የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤ (አንቀጽ 82) ፤ የምርጫ ቦርድ (አንቀጽ 102) እና በምእራፍ ሶስት የሰፈሩትን የመሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ የሚከታተለው ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲዋቀሩ አድርጋለች፡፡ በነኚህ ተቋሞች ከዚህ ቀደም ስለደረሰው አላስፈላጊ ነገሮች አሁን መልሼ እዚህ ላይ አልደግመውም፡፡ ነገር ግን በሃገሪቱ ከሁለት አመት ወዲህ አዲስ ለውጥ በመፈጠሩ ከለውጡ ማግስት አንስቶ በነኚህ ሦስት ተቋሞች የሰላማችን፣ የልማታችንና የዲሞክራሲያችን መሰረት ሊሆኑ ተስፋ ጥለንባቸዋል፡፡ ተቋሞቹ በአዲሱ የለውጥ ጎዳና ጋልበው ውጤታማ እንዲሆኑ ተልእኮውን ያሳካሉ የተባሉት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከበሩ ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፣ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተከበሩ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ፣ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ የተከበሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንዲመሩት ተሹመዋል፡፡ ወደ ስራ መግባታቸው ተከትሎም ህዝቡ በአንክሮ እየተከታተለ እንደሆነ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡
እነኚህ የተከበሩ ዜጎች ሁሉም በርቀት አውቃቸዋለሁ፡፡ ስላለፈው ስራቸው በመጠኑም ቢሆን የማወቅ እድል አግኝቻለሁ፡፡ ክብርት ወ/ሮ መአዛ በተለይም የሴቶች መብት ለመታገል የኢትዮጵያ ሴቶች የህግ ባለሙያዎች ማህበር በግንባር ቀደምትነት አቋቋመው በርካታ ስራዎች አከናውነዋል፡፡ እንደዚህ የተከበረ ሰብአዊ መብት መሰረት አድርጎ የሚሰራ ድርጅት ከሌሎች እህቶቻቸው ጋር በመሆን አቋቁመው ጥብቅና መቆማቸው በእርግጥም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ከልቤ መደሰቴን አስታውሳለሁ፤ ምክንያቱም በህግና በህሊና ብቻ በመመራት አጠቃላይ የፍትህ ስርአቱን ወደ ተሻለ ከፍታ ያሸጋግሩታል ብዬ ተስፋ በማድረግ፡፡ ክብርት ወ/ት ብርቱካን በአንድ ወቅት ህሊናቸው መሰረት አድርገው ያስተላለፉት የፍርድ ውሳኔ መቼም ቢሆን በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ዘወትር ሲወሳ ይኖራል፡፡ በተጨማሪም ተቃዋሚን በመምራት የማይናቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ክቡር ዶ/ር ዳንኤልም የሲቪል ማህበረሰቡ በማንቃትና ለትግል በማዘጋጀት ቀጥለውም በአለምአቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋም እያገለገሉ በነበሩበት ወቅት የመንግስትን ስርአት በመሞገት የሚታወቁ ናቸው፡፡
ሃላፊዎቹ ወደ ስልጣን ከመጡ ከአመት በላይ ያስቆጠሩ እንደውም ገሚሶቹ ከስርአቱ ጋር እኩል የመጡ ናቸው፡፡ እኔ በበኩሌ በሃላፊነት የተሾሙባቸው ተቋሞች ለመምራት ብቃት የላቸውም ብዬ መከራከር አልችልም ሆኖም ግን እነኚህ ተቋሞች ወደምንፈልገው ጠንካራ ተቋምነት ለመለወጥ የተሰጣቸው ተልእኮ ያከናውናሉ ብዬ ግን አላምንም፡፡ ምክንያቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በነኚህ ተቋሞች ላይ እየተደመጡና እየተከናወኑ ያሉ ተስፋ አምካኝ ድርጊቶች የጠንካራ ተቋሞች የመፍጠር እምነቴን የሚሸረሽር ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ድርጊቱ የምንናፍቀውን የሚያርቅ ብቻም ሳይሆን ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ እንዲኮላሹ በመደረጋቸው ጭምርም ነው፡፡ ዛሬ ላይ ደርሰን እነሱ በሩቁ ሲያዩት የነበረውን ተቋም በእጃቸው ሲገባ ምነው ወደ ጠንካራ ተቋምነት ቀይረው ስቃያችንን ሊያስታግሱልን አልቻሉም? የሚል ቁጭት አዘል ጥያቄ ብናቀርብ ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡
ምርጫ ቦርድ ዋናው ተግባሩ ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት ሚዛናዊ ምርጫ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲያከናውን አበክሮ መስራት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቦርዱ ሰው ከተሾሙበት ቀን አንስቶ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስፈልግ ዝግጀት በማድረግ ምርጫ በወቅቱ ማካሄድ ህገመንግስታዊ የህዝቦች መሰረታዊ መብት ማረጋገጥ እንደሆነ ለተሿሚዎቹ የተሰወረ ጉዳይም አይደለም፡፡ ህዝብ በተሿሚው ላይ ተስፋና እምነት ሲጥል የተሿሚው ድርሻ ደግሞ በአደራ የተሰጠውን ተቋም ተጠቅሞ ቀጠሮ የተያዘለትን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ በማስፈጸም በቀጣይም በዚች ሀገር ላይ ለምርጫ ጠንካራ መደላድል እንዲያኖር በማመን ነበር፡፡ ተሿሚውም በዚያ ተቋም ውስጥ ከዚህ የበለጠና የተለየ አስቸኳይ ስራ የለውም፡፡ ሊኖረውም አይገባም፡፡ ሹመት ከተሰጠበት የአንድ አመት ከሰባት ወር ቆይታም ይህንኑ ለማከናወን በቂ ጊዜ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የወቅቱ የቦርዱ ሰብሳቢ አንዳንዴ በሚዲያ ብቅ እያሉ ለዝግጅታቸው በቂ ጊዜ አለማግኘታቸው ሲናገሩ አዳምጠናል፡፡ ለምሳሌም የምርጫ ቦርድ አባላት አለመሟላታቸው አስመልክተው ‘መንግስት በጊዜው አልመደበም’ ነበር ያሉት፡፡ ይህ ምን ማለት ነው፡፡ ለረዢም ጊዜያት ቦርድ ባልተሰየመበት መ/ቤት ብቻቸው ምን ሲያደርጉ ነበር? ለብቻቸው ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እያወቁ ለምን ጊዜው በከንቱ እንዲቃጠል ተባባሪ ሆኑ? በመንግስት በኩል ቦርድ መሰየም ያልተፈለገበት ምክንያት ምን እንደሆነ መረዳት እንኳንስ እሳቸው ከመሰለ ፖለቲከኛ (ይቅርታ የድሮው ስራቸው በማስታወስ ነው) ለሌላውም የሚሰውር አይሆንም፡፡ ከዚያ በኋላ የቦርዱ ረዥሙ ጊዜ የወቅቱ ታላቅ ስራ የሆነውን መስሪያ ቤት የማሸብረቅና መመሪያዎች የማዘጋጀት ተግባር ተጠመዶ ቆየና አንድ ማለዳ ላይ ምርጫው በሦስት ወራት እድሜ እንዲራዘም ጠየቀ፡፡ በኔ እምነት ይህ እርምጃ በራሱ ቦርዱ ህገመንግስቱ የጣለበት ሃላፊነት ገፋ እያደረገው መሆኑ የተገነዘበው ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ተወካዮች ም/ቤትም ፈቀደ፡፡ ቦርዱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኮቪድ 19ኝን ተከትሎ ምርጫውን ማካሄድ አይቻልም የሚል ምክረ ሃሳብ ለተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በወቅቱ ሲደረጉ የነበሩ ጎልህ የፖለቲካ እንቅስቃሴውች (ለብልጽግና ፓርቲ የሚደረጉ ገንዘብ የማሰባሰብ ፕሮግራሞች፤ በስፋት ሲደረግ የነበረውን የችግኝ ተከላ ስራዎች እንደዚሁም ህዝብን በፓርቲው ዙሪያ ለማሰባሰብ የሚደረጉ በርካታ ስበሰባዎች) እንደዚሁም በመንግሰት አገልግሎት ሲጪዎችና በትራንስፖርት አገልግሎት ወቅት የሚደረጉ ትፍፍግ የበዛባቸው እንቅስቃሴዎች ለተመለከተ በመንግስት በኩል ወረርሽኙ እንደስጋት ያልተቆጠረበት መሆኑን መገንዘብ ይችላል፡፡እዚህ ላይ ሃላፊነት ያለበት መንግስት ያልተጨነቀበትን ጉዳይ አንስቶ ሲባዝን የሚታየው ምርጫ ቦርድ የተጨነቀበትን ምክንያት ለመረዳት አጥብቆ መጠየቅ ምናልባትም የስንካሳሩ ድሪቶ ለማወቅ ይረዳል የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የማስተላለፍ የውሳኔ ሃሳብ ከምርጫ ቦርድ የቀረበለትን ማመልከቻ ተከትሎ የሀገሪቱ ላእላይ ተቋም የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት በውስጥ ለውስጥ በመንግስት የቀረበለትን ብቸኛው የህገመንግስት ትርጉም አማራጭ ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ እንዲመለከተው አዟል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ አዟል ማለት አይቻልም አስተላልፏል ቢባል ይቀላል፡፡ ይህ አገላለጽ ለተቋሙ ክብር ከማጣት ሳይሆን ተወካዮች ምክር ቤት ይህ በመንግስት የቀረበለትን የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄ መነሻ በማድረግ የአስተላላፊነት ሚና የሚያከሽፍበትን፣ እንደዚሁም ተቋሙ ወደ ሌላ የተቋም እመርታ (አስፈጻሚው አካል የመቆጣጠር፤ የመግራትና የመምራት) ሊያሸጋግረው የሚችል ወርቃማ ጊዜ ሳይጠቀምበት ማለፉ ትክክለኛ መንገድ አለመሆኑ በማመን ነው፡፡ በሌላ በኩልም ጉዳዩ የጤናና ወረርሽኝ እንደመሆኑ መጠን ወረርሽኙን ለመግታት ስለተደረገው የረዥምና የአጭር ጊዜ ዝግጅቶችና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፣ እሳቸው የሚመሩት ታስክ ፎርስና የጤና ተቋሞች በመጥራት በጥንቃቄና በሃላፊነት በመመርመር ትክክለኛነቱ ማረጋገጥ እግረመንገዱንም ከህዳሴ ግድብ በስተቀር የግዘፉ የፕሮጀክቶች ወጪዎች (የቤተ መንግስት እድሳትና የማስፋፊያ ስራዎቹ፣ የቢሮ እድሳቶች፣ ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ የተያዘው እድሳት) ለወረርሽኙ መከላለከያና በዚሁ ሳቢያ ወደፊት ሊደርስ በሚችል ሀገራዊ ጉዳይ በተያያዘ እንዲውል መመሪያ በመስጠት እድሉ ቢጠቀምበት ኖሮ በኢትዮጵያ የተቋሞች ታሪክ ለድፍረቱ ወደር አይገኝለትም ነበር፡፡ ይህ ግን አልሆነም፡፡ ነገር ግን ቀላሉን መንገድ ብቻ ነበር የተከተለው፣ ጉዳዩ ወደ አጣሪ ጉባኤው መሸኘት፡፡
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የአጣሪ ጉባኤው ሰብሳቢ እንዲሆን ህገ መንግስቱ ያዛል፡፡ ተወካዮች ምክር ቤት የላከው ጉዳይ ወደ ጉባኤው ሲያመራ መጀመሪያ ህገመንግስቱ እንደሚያዘው ጉዳዩ በሁለት ተከራካሪ ወገኖች መሀከል የተደረገ መሆኑን ማረጋገጥ የሚለውን የሂደቱ አካል በዝምታ አልፎታል፡፡ ሁለተኛ ሌሎች መደመጥ ያለባቸው አካሎች በበቂና በስፋት የማሳተፍ ጉዳይ አልተከናወነም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በተለይም የጠንካራ ተቋም ተጻራሪ የሆነውና አደገኛ የማግባባት ስራ በሌሎች ተቋሞች ሰርቷል፡፡ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር፤ ቀጥሎም በፌዴረሽን ምክር ቤት፡፡
የጉባኤው ሰብሳቢ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተገኝተው ካደረጉት ንግግር መካከል ሦስት ለጠንካራ ተቋም ግንባታ ጥቅም ላይ የማይውሉ መልእክቶች እናገኝበታለን፡፡ አንደኛው ‘ማስፈራሪያ’ ሁለተኛው ‘ስላቅ’ ሲሆን ሦስተኛው ‘ወገንተኝነት’፡፡ በቅድሚያ ‘ከህገመንግስት መፍትሄ እናገኛለን’ የሚለው ንግግር ቀደም ብሎ በሌላን አካል የተሰጠ ማስፈራሪያ ተቀጥላ እንደሆነ መገንዘብ ያቻላል፡፡ እሱም ‘መንግስት አራዝሜዋለሁ ብሎ እቅጩን ቢነግርህ ምን ታመጣለህ’ የሚል ማስፈራሪያ አዘል ንግግር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ያስተላለፉት በተቋሞች ላይ ‘እምነት’ የማሳደሩ ጉዳይ በተመለከተ አንድ ነገር አስታወሰኝ፡፡ አንዲት ወ/ሮ እቤታቸው ውስጥ ምግብ ለማዘጋጀት የሚውል ምንም የተፈጨ ነገር ባለመኖሩ ለባለቤታቸውና ለልጆቻቸው በእለቱ የሚያቀርቡት ምሳ አልነበረም፣ እህል እንደይፈጩ ደግሞ ቀኑ የማርያም በአል ስለነበረ ሃይማኖታቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ ታዲያ ጭንቀት የወጠራቸው ሴት አንድ መላ ዘየዱ ቀኑን አላውቀውም ብለው ራሳቸውን አሳመኑና እህል መፍጨቱን ተያያዙት፡፡ የሚበቃቸው ከፈጩ በኋላ አይ ዛሬ ለካ የማርያም በአል ነበር እንዴት ያሳዝናል አሉ ይባላል፡፡ የጉባኤው ሰብሳቢም ያደረጉት ይህንኑ ነበር የፈለጉትን አደረጉ ከዚያም ህዝቡ በተቋሞች ላይ ያለውን እምነት ለደቂቃም ቢሆን እንደይሸረሸር ጠየቁ፡፡ ሦስተኛው መልእክታቸውም ‘አሳታፊ’ እንደነበር ገልጸዋል ግን በመድረኩ ላይ የተደመጠው ጭብጥ አንድ ብቻ፤ የሙያ ስብጥሩም ወደ አንድ ያጋደለና በጥንቃቄ የተመረጡ ሰዎች ተዋናይ የነበሩበት መደረክ ነበር፡፡ ለዚች ሀገር መፍትሄ የሃሳብ የበላይነት ብቻ ነው ከተባለ አጣሪ ጉባኤው ለምን ሁለተኛውን አማራጭ ‘ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተከላከልንና እየተቆጣጠርን ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ መንገድ እናካሂድ’ የሚለው ሃሳብ በድፍረት ሊመለከተው አልፈቀደም? ለመድረኩ ምጥቀትም ሌሎች የሙያ መስኮችን ለምሳሌ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የስነልቦና፤ የቋንቋና ሌሎች የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎች ሃሳብ እንዲካተት ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ እንደዚያ ሆኖም ባለኝ መረጃ መሰረት አለምአቀፍ የኦሮሞ የህግ ባለሙያዎች ማህበር ሃሳባችንን ሊቀበሉን አልፈለጉም ብለዋል፡፡ በዚህ ላይ የሌሎች ሁለት የሲቪክ ድርጅቶች ያቀረቡት አቤቱታ ሲታከልበት ደግሞ በሂደቱ ላይ ጥያቄ ይጋብዛል፡፡ በአናቱ ላይም በአሁኑ ወቅት በአለማችን ምርጫቸውን የሰረዙ አገሮች እንዳሉ ሁሉ በተነጻጻሪው ምርጫ ያካሄዱና ቀጠሮ የያዙ ሀገሮች መኖራቸው በግብአትነት መጠቀም ይገባውም ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ በርካታ አከባቢዎች እየተፈፀመ ያለ ግዙፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ የአለምአቀፉ ሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ላወጣው ሪፖርት ‘ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ያላገናዘበ ሪፖርት’ ነው በማለት ያወጣው መግለጫ አለምን አስደምሟል፡፡ ዶ/ር ዳንኤል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰራተኛ በነበሩበት ወቅት ድርጅታቸው ለሚያወጣው የሰብአዊ መብት ጥሰት የድሮው ስርአት የድርጅቱን ሪፖርት ሲያጣጥል የነበረበት መንገድ ተራምደው በተራቸው ሪፖርቱን ለማውገዝ መሞከራቸው አሳዛኝ ድርጊት ያደርገዋል፡፡ ሃላፊነት ያለመወጣት ድርጊት ከመሆኑም በላይ ብዙ ተመልካች ባለበት ትዝብት ላይም ይጥላል፡፡ እዚህ ላይ መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ለመሆኑ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ አላገናዘበም ሲባል ምን ማለት ነው? ለሰብአዊ ጥሰት መፈጸም ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ይቻላል ወይ? ኮሚሽኑ ይህንን አይነት አስተያየት በመሰንዘሩ በአለም የመጀመሪያው ተቋም የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ ኮሚሽኑ አሁን የተጠመደበት ስራ ለይስሙላም ይመስላል፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ጥሰት የየእለት ዜና በሆነበት በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ያተኮረው በኮቪድ-19 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ‘የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አላደረጋችሁም ብሎ ፖሊስ ሰዎች ደብድቧል’ ሲል ይጠይቃል የመንግስት ሌላው ተቋም ደግሞ ‘መግለጫው የአካዳሚክ ልምምድ ከመሆን አያልፍም’ ብሎ ውድቅ ያደርጋል፡፡ አለፍ ሲልም ይህችን መሳይ መግለጫ በማውጣቱ ‘መንግስትን የሚሞግት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳገኘት’ በከፍተኛ መሪ አንደበት በስላቅ ሲነገር ማዳመጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ ኮሚሽኑ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አላየሁም በማለት ሰብአዊ መብትን ወደ ታችኛው ወለል በማውረድ ጊዜውን በጥቃቅን ስላንቲያ ማጥፋቱ ይገርማል፡፡ በሌላው የሀገሪቱ ክፍሎች ያለውን ትተን በአሁኑ ሰዓት እኮ እዚሁ አፍንጫው ስር መሃል አዲስ አበባ ላይ ተዘጋ ተብሎ በተለፈፈው ግን ስራውን ባላቆመው ማእከላዊ የተባለ እስር ቤት እያጨናነቁት ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ጉዳይ አላውቅም ሊለን የሚችል አይመስለኝም፡፡
ከኮሚሽኑ የሚጠበቀው በሀገሪቱ ልዩ ልዩ አከባቢዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይልና በታጣቂ ቡድኖች እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያለምንም ወገንተኝነት ጥናት አካሂዶ ለሚመለከተው አካል ማቅረብና የሚወሰደውም የማስተካከያ እርምጃ እየተከታተለ እርምት ማስደረግ ነው፡፡ እዚህ ላይ ‘እኛ ጥፍር አንነቅልም’ የሚለውን የዘወትር አፍ ሟሟሻ ንግግር ኮሚሽኑ ጠበቅ አድርጎ ቢይዘው መልካም መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ ምክንያቱም ባለስልጣኖቻችን ሁሌም የሚነግሩን ተቃራኒውን ነው (የሌባ አይነደረቅ የሚሉት ሆነና የገንዘብም ሆነ የምርጫ ዘራፊው ባለስልጣን ልባችን እስኪወልቅ ድረስ ስለሱ መልካምነት ሲሰብክ፤ ሌላውን ሲኮንን ይውላል፣ ነቃዩም እንደዚሁ- አቀባዩ፣ ነቃዩ፣ ተነቃዩ ማን ሆነና ነው? እንዴት ነው ጎበዝ ሀፍረት የሚባል ቀረሳ! ታጋሽነቱ ለበዛለትና የኖረበትን ለሚያውቅ ህዝብ እንደ ደንቆሮ በመቁጠር ክፍያው በደልና አረመኔነት ከሆነ የሚያስከፍለው ዋጋ ከታሪክ አለመማርን ያስቆጥራል)፡፡
በዚች ሀገር ተቋሞችን በማሽመድመድ ስራ ላይ የተጠመዱ ተቋሞች ቢኖሩ የተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክርቤቶች፣ እና ሚዲያ የመሳሰሉ የሚያህል የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የነሱን ለጊዜው እዚሁ ተወት አድርገን ወደ እነኚህ ሶስት የተከበሩ ተቋሞች ስንመለስ በቀና መንገድ ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ መቅረጽና ማኖር ይጠበቅ ነበር፡፡ ይህንን መርህ ሳይከተሉ ጠንካራ ተቋም ማኖር አይቻልም፡፡ ይህ ገቢራዊ ለማድረግ የጠንካራ ስብእና ባለቤት መሆን ይጠይቃል፡፡ ከጅምሩ ያየነው እውነታ ግን ይህንን አያንጸባርቅም፡፡ ከወገንተኛነት የጸዳና በህሊና የመገዛት መርህ ወደ ጎን ተገፍቶ ከዚህ ቀደም በተቋሞቻችን አመካኝነት ሲካሄድ የነበረውን ስውር ፖለቲካዊ አጀንዳ ተሳትፎ ስመለከት ቀድሞውንም ለነኚህ ሦስት ሰዎች የጫንባቸው ተስፋ ትክክል እንዳልነበረ ለመረዳት ከበቂ በላይ እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ፡፡
ሌላው መነሳት የሚገባው ጉዳይ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋሞች ሚና ነው፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር ሙያዊ ነጻነቱን በመግፋት የአስፈጻሚው ድምጽ ሆኖ ለመቆም ያሳየው ድፍረት ሙያውን ያረከሰ ተግባር ሲሆን ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ከሰብአዊ መብቶች ጋር በተያያዘ ሰርተፊኬት ወስደው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሲቪክ ማህበረሰብ ተቋሞች በጉዳዩ ያሳዩት ዝምታም በጣም ያሳስበኛል፡፡ በእነኚህ ተቋሞች ውስጥ ያለው የፋይናንስና የአቅም እጥረት ብረዳም ቅሉ እንደዚህ ያለ ሀገራዊ ጉዳይ በርቀት መመልከታቸው አሁንም ለጠንካራ ተቋም ግንባታ የራሱን አሉታዊ አተዋጽኦ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶችም በተሳከረ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በአፍዝዝ አደንግዝ ተሸብበው፣ የውጭ ተመልካች እስኪመስሉ ትዝብት ላይ ወድቀዋል፡፡ ገሚሶቹ በሚሰፈርላቸው ዳጎስ ያለ ዳረጎት፣ ገሚሶቹ በተደረገላቸው ምህረት፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ሀገርና ህዝብ መላቅጡ በጠፋበት እና ተቋሞች በግለሰብ ፍላጎት ሲንከላወሱ ምን ስራ ለመስራት እንደተቀመጡ ማስታወስ ተስኖአቸዋል ብንል ተጨባጩን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ በቅርቡ አንድ ጎምቱ ፖለቲከኛ (ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ) በቴሌቪዝን የተናገሩትን ማስታወስ በቂ ይመስለኛል ‘እኛ እኮ መቃወም ተስኖን አይደለም፣ ከዚህ ቀደምም ተቋሞቻቸውን ተጠቅመው ምን ሲሰሩ እንደነበሩ እናውቃለን፣ ግን እስቲ እንታገሳቸው ብለን ነው፣ ጉዳዩ በምርጫ ይፈታል ብለን ነው’ ብለው ነበር፡፡ በኮቪድ-19 ስም ህዝባዊ መብትን እየተገፋ፣ የተቋሞች ህልውና ሲፈራርስ በእድሜ ጠገብ ፖለቲከኞች ይህንን አይነት አስተያየት ማዳመጥ እጅግ ያማል፡፡ ታጋሽነቱ ለስልጣን ወይስ ለህዝብ? የታገሱለት የምርጫ ቀን ላይ ተደርሶ ገዢው ፓርቲ እንደለመደው ምርጫውን አሸንፊያለሁ ቢልና የቋመጡት ስልጣን ሳያገኙ ሲቀሩ ያኔ ለእልቂት ይጋብዙን ይሆን? ይህ የመጠምዘዝ ተግባር ተሄዶ ተሄዶ መከላከያ በር ላይ ሲደርስ ምን ይሉን ይሆን? የአባቶች ብሂል ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ ማስቀደም ቢማሩ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
ወንድማዊ ምክር
በአጠቃላይ የሀገራችን ተቋሞች እየሄዱበት ያለው መንገድ የምንፈልገው ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ አያመጣልንም፡፡ እንደእነ አሜሪካ የመሳሰሉ ሀገሮች ዛሬ የሚመኩት በጠንካራ ተቋሞቻቸው ነው፡፡ በየትኛውም የአለም ክፍል አሜሪካን ጠንካራ ያደረጋት በገነባቻቸው ተቋሞችዋ ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስዋ ዋናው ምክንያትም የመንግስት በትረ ስልጣን የጨበጡ ዜጎችዋ ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ ብዙ መስዋእትነትም መከፈሉ ታሪክን ማየት በቂ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ፈታኝ ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ሀገራዊ ችግሮቻችን ለመፍታት በተቋሞቻችን የምናስተላልፋቸው ውሳኔዎችና የምንወስዳቸው እርምጃዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ለችግሮቻችን የመፍቻው አንዱ ቁልፍ ተግባርም ለተቋሞቻችን የምናደርገው ጥበቃና እንክብካቤ መጨመር ይኖርበታል፡፡ ተቋሞቻችን ላይ አበክረን ሳንሰራ የምንፈታው ችግር መልሶ ማደባበስ ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች ውጤት መሆንዋን የሚክድ ወይንም የሚዘነጋ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ለያዘችው ቁመናና የብሄሮች እኩልነት (በጅምር ላይ ያለ ቢሆንም) በርካታ ወድ ህይወት መከፈሉ መገንዘብ የሚያሻ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው መሄድ ህዝቡ ለተቋሞች የሚሰጠው አመኔታ ላይ ውሃ መቸለስ ከመሆኑም በላይ ከእውነታው ጋር መጣረስ ብቻ ነው፡፡
እዚህ ላይ አጽንኦት አድርጌ ማለፍ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር ያለንን ተፈጥሮአዊና ግላዊ አቅም አሟጥጠን እንድንጠቀም ህዝብ ሙሉ እምነት ይሰጣል፣ ሆኖም ይህንን እምነት ለጥጠነው ጥቅሙ ሊቃረን በሚችል መልኩ ስናውለው የሰጠንን እምነት ስቃይና ጭካኔ በተሞላበት አኳሃን መካድ መሆኑ መገንዘብ እንዳለብን በዜግነቴ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላስታውሳቸው እወዳለሁ፡፡ ስናወግዘው የነበረውን የተቀሞቻችን ‘ወገንተኝነት’ ‘ተጠያቂነት እና ግልጸኝነት’ ያለመኖር ዛሬ መልሰን በዚያው መንገድ ለመራመድና ለመድገም መሞከር ሀገሪቱ ወደሌላ የተቋሞች የማዝቀጥ ምእራፍ እየገፋት ይገኛል ባይ ነኝ፡፡ ውጤቱም የተቋሞችን የመሽመድመድ እሽክርክሪት ጉዞ ላይ መዳከር ብቻ ይሆናል፡፡ በራስ የሚተማመኑ ተቋሞችና ተከታይ መሪዎችን ለማፍራት ብዙም የሚጠቅም ድርጊትም አይሆንም፡፡ በእርግጥ መሪዎች ካለው የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተነስተው ተቋሞች ይቀርጻሉ፡፡ በጽኑ መሰረት ለማኖርም ተግተው ይሰራሉ፡፡ በተጻራሪው ተቋሞቹን ለግል ፍላጎት ማዋል ደግሞ አሁን የምናየውን ሸባ የሆነ ተቋም ለትውልድ ማውረስ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
አሁን መንግስት እፎይ ብሏል፡፡ ይህ ጊዜያዊ ደስታ ነው፡፡ ምክንያቱም ያልታሸ ሀሳብና ውሳኔ ከጊዜያዊነት አያልፍምና፡፡ ነገ ምን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል እኔም እናንተም አናውቅም፡፡ በዚህ በጥድፊያ፤ አግላይና የወገነ ሂደት ላይ የተሳተፉት ተቋሞች አይገነዘቡትም ብዬም አላስተባብልም፡፡ ምክንያቱም የጠንካራ ተቋም ልእልና የሚገለጽበት በህሊናና በህግ የመገዛት መሰረታዊ መርህ አሽቀንጥረው በመጣል ረዥም ርቀት ተጉዘዋል፡፡ ለተቋሞቻችን መጥፎ ትምህርት አኑረዋል፡፡ እናም ሀገሬ መቼም ቢሆን ሰው አይወጣልሽም ብዬ መርገሜ ለጊዜው ተስፋ ከቆረጠ ዜጋ የሚጠበቅ እንደሆነ ባውቀውም ከቶም ቢሆን ተስፋ አልቆርጥም፡፡ ይህ አሁን እየተሰራ ያለውን ታሪክ ቀጣዬ ትውልድ ሲያውቀው ምንኛ እንደሚያዝንብን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ይቺ ሀገርና ህዝቦችዋ ጊዜያቸው የሚያቃጥሉት ለወደፊት ትውልድ ተስፋ በማያጭሩ፣ ጊዜና ሀብት በሚያባክኑ ጉዳዮች መሆን የለበትም፡፡ ቀልባችን በገንዘብና ስልጣን ላይ ጥለን ቀጣዩን ትውልድ የምናወርሰው ሽባ ተቋም ሊኖር አይገባም፡፡ ለዛሬው ልሰናበት፡፡