ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
የጽሑፉ ዓላማና ይዘት፥ ጽሑፉ በይዘቱ የህግ ምክር ለመለገስ የተዘጋጀ ሰነድ አይደለም። ይልቁንም፥ አሁን በዚህ ሰዓት በሰፊው መወያያ ርዕስ ሆኖ የሚገኝ አጀንዳ (የሽግግር ፍትህ) በተመለከተ ታችኛው የማህበረሰብ ክፍል በቀላሉ በሚገባው ቋንቋ ለማወያየት ዓልሞ በአዘጋጁ በራስ ተነሻሽነት የተዘጋጀ ግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ ነው።
መንደርደሪያ፥ የሽግግር ፍትህ ምንድ ነው? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ ሃይለ ቃሉ ልዩ ልዩ መገለጫዎችና በርካታ ዓይነቶች ቢኖሩትም በትግራይና በኢትዮጵያ መካከል የተካየደ አፋሳሽ ጦርነት ዓውድ መሰረት እንዲሁም ጠቅለል ባለ መልኩ ያለው ትርጉምና አንድምታ አንፃር ያየነው እንደሆነ የሽግግር ፍትህ ማለት በዐቢይ አህመድ ዓሊ ዓይነቱ አምባገነን ቡድንና የአገዛዝ ስርዓት የተፈፀሙ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎች በግጭትና በጦርነት ምክንያት በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ፣ የጦርና የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎችንና አረመኔያዊ ድርጊቶች በሚገባ የማየትና ጉዳዩም በሙላት ዕልባት እንዲያገኝ ማለትም አንድን ማህበረሰብ ወይም አገር ወደ ዲሞክራሲያዊና ፍትሓዊ ኑሮ/ህይወት ለመሸጋገር ወይም ለማመቻቸት (ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሲታሰብ) የማድረግ ሂደት ነው። ዓላማውም ቢሆን የተፈፀሙ በደሎች አጣርቶ ወንጀሎችን ለፍትህ በማቅረብ ተጠያቂዎች ማድረግ፣ የዚህ አረመኔያዊ ምክርና ድርጊት ሰለባ የሆኑ ህዝቦች ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግም ተጎዢዎች የመፈውስና የመካስ ስራ መስራት እንዲሁም በሁሉም ዘንድ ዘላቂ የሆነ ዕርቀ ሰላም ማውረድ መቻል ነው።
አፈጻጸሙ በሚመለከትም፥ የሽግግር ፍትሕ በተለያዩ መንገዶች ተፈጻሚና ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ይኸውም፥ ለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ መሆን ያለባቸውና የሚገባቸው ሁሉ የወንጀል ክስ በመምስረት፣ የሆነውና የተፈጸመውን ወንጀል ሁሉ በሚገባ መግለጥና ይፋዊ እውቅና መስጠት፣ በተጨባጭ ለተረጋገጠ አመጽና ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ተጎጂዎች ካሳ መክፈል፣ አሁንም የዚህ ዓይነቱ ወንጀል ለወደ ፊቱ ድጋሜ እንዳይከሰት ተቋማዊ ለውጥና ማሻሻያዎችን ማድረግ የሚጨምር ነው። የተሳካና ውጤታማ የሽግግር የፍትህ ሂደት ማካሄድ የሚቻለው ሂደቱ በማን አስተባባሪነትና መሪነት ሲከናወን ነው? መሆን ያለበትና የሚገባውስ እንዴት ነው? ለሚለው ቁልፍና ወሳኝ ጥያቄም እንዲሁ ምላሹ ግልጽና አጭር ነው። ይኸውም፥ የሽግግር የፍትህ ሂደት መመስረትና መምራት ያለበት የወንጀል መሃንዲስ በመሆን ወንጀል በፈፀመው ቡድን ሳይሆን ወንጀሉ በተፈፀመበት ማህበረሰብ ነው። ይህን ተበግሶ በመደገፍ የፍትህ ሂደቱን በማስተባበር፣ በማሳለጥ ረገድና የሽግግር የፍትህ ሂደት አካልም በመሆን አክቲቭ የሆነ አስተዋፅኦ ያላቸውና ሊኖራቸው የሚችሉ አካላት የተመከትን እንደሆነም በዋናነት፥ ሰላባ ለሆነው ማህበረሰቡ ቅርበት ያላቸው አገር በቀል የሲቪል ተቋማት፤ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት ማለትም የሆነውና የተፈፀመ ሳይጨምር ሳይቀንስ ለማጥናትና ለማሳውቅ የተቋቋመ ኮምሽን ያለ እንደሆነ የዚህን ዓይነቱ ኮሚሽን፣ የሰብአዊ መብት ተቋም (በርግጥ በዳንኤል በቀለ የሚመራ አዱላዊ ቢሮ በዚህ በትግራይ ጉዳይ ላይ የወንጀሉ አካል እንጅ ገለልተኛ ነው ተብሎ አይታመንም)፤ የተባበብሩት መንግስታትና የአውሮፓ ህብረት የመሳሰሉ የገንዘብና በሚገባ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማቅረብ ረገድ ውጤታማ ስራ ሊሰሩ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይጠቀሳሉ። የዐቢይ አህመድ ዓሊ ዓይነቱ (ለተፈፀመ ወንጀል መነሻና መዳረሻ የሆኑ) አረመኔ አገረ ገዢዎች እዚህ ላይ ምንም ስፍራ የላቸውም።
በጽሑፉ ዓላማ እንደ ተገለፀ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ፥ እውነተኛና ትክክለኛ የሽግግር የፍትህ ሂደት ምን መምሰል እንዳለበት፣ ውጤታማና ስኬታማ የሽግግር የፍትህ ሂደት ለማካሄድ መሟላት ያለባቸውና የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ ወንጀለኞች ከተጠያቂነት ለማስመለጥ የሚፈጠር የሽግግር የፍትሕ ሂደት በአንጻሩ ምን እንደሚመስል፣ እንዴትስ ማስቆም ይቻላል? እውነትንና ፅድቅን ፍትህንና ፍርድን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰዎች ከሃይማኖትም ከባህልም አንፃር ምን ይመስላሉ? የሚሉና ሌሎች ሰፋፊ ተያያዥ ጥያቄዎችን አንስተን ነገሮችን በጥሞና እንመረምራን።
እውነተኛ የሽግግር ፍትህ ምን ይመስላል ምንስ ማሟላት ይጠበቅበታል?
በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ “የሽግግር ፍትሕ” የሚለውን ቋንቋና ፈሊጥ በተደጋጋሚ በማስተጋባት ፍትህ እንደ ተደረገና እንደ ተሰጠ በማስመሰል በማህበረሰቡ አእምሮ ላይ ከፍተኛ የሆነ ብዥታ በመፍጠርም ከተጠያቂነት ለማምለጥ በብርቱ እየሰራ የሚገኝ ዐቢይ አህመድ ዓሊና ይዞት የመጣ ገዳይና ዘራፊ ባለተራ ቡድን የዚህን ዓይነቱ አጀንዳ ሲያራግብ የነገሩ አቅጣጫና ዓላማ በሚገባ መረዳት አስፈላጊ ነው። ሲጀመር፥ የሽግግር ፍትህ ሲባል እንዲሁ በቁሙ “ፍትህ ተገኘ!” ማለት እንዳይደለ በሁሉም ዘንድ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ስለታም ቢላ እንደ አጠቃቀማችን ለጥቅምም ለጥፋትም እንደሚውል ሁሉ “የሽግግር ፍትሕ” ሲባልም በውጤቱ እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። ነገሩ ቅንነት በራቀባቸውና በክፍዎች ሰዎች እጅ የወደቀ እንደሆነ ማለትም የዐቢይ አህመድ ዓሊ ዓይነቱ በንጹሐን ደም የጨቀዩ የኢትዮጵያ ባለ-ስልጣናት ከተጠያቂነት ለማምለጥ ያስችላቸው ዘንድ የሽግግር ፍትሕን እንደ መጠቀሚያና የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላቸው ዘንድ የሰሩት እንደሆነ የሽግግር ፍትሕ የሚባለው ነገር በውጤቱ ቀድሞ ከተፈፀመ ጥፋት ይልቅ የከፋ ስብራት የሚያስከትል ነው ሊሆን የሚችለው። በአንፃሩ ሂደቱ በዓላማና በአሰራር የፖለቲካ መሳሪያ ከመሆን በፀዳ መልኩ የተከናወነ እንደሆነ ደግሞ አንድን የተጎዳ ማህበረሰብና የተቃወሰ አገር እንደ ገና ለመገንባትና ለመፈወስ በሚደረግ መነሳሳት የህዝቡንና የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ፍትሓዊና ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ በመገባት ረገድ የሽግግር ፍትህ እጅግ አስፈላጊ ለመሆኑ አያጠራጥርም።
እዚህ ላይ፥ እውነተኛ የሽግግር ፍትህ ምን ይመስላል? በምን ዓይነት መልኩ ቢከናወንስ እውነተኛና ትክክለኛ፣ ዘላቂም የሆነ ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው? የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ግን ቀደም ሲል እንደ ተመለከትነው ከሃይለ ቃሉ ትርጉምና ዓላማ በተጨማሪ አሁን በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ነገሩን (የሽግግር ፍትሕ የሚለውን) በዚህ ደረጃ ለማራገብ ያስገደደባት፤ አንድም፥ የሽግግር ፍትህ የሚባለው ነገር ለማሰብ ሆነ ተግባራዊ ለማድረግ ምክንያት የሆነው ምክንያት ማወቅ መረዳትና እውቅና መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። የሽግግር ፍትህ ሲባል ብዙውን ጊዜ በፖለቲካ ሹሞኞችና በባለ ስልጣናት መካከል የሚፈጠር ጥቅምንና ስልጣን መንስኤ ያደረገ የስልጣን ሽኩቻ የሚፈጥረው ፖለቲካ ቀውስና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተከትሎ የሚፈጠር የእርስ በርስ ጦርነት፣ በአንድም በሌላም ምክንያቶች እውን የሚሆን የፖለቲካ ሽግግር፣ ህዝባዊ ነውጥና ማዕበል ተከትሎ የሚፈጠረውን ክስተት ሁሉ መቋጫ ለማበጃጀት ብሎም ያልፈውን ላለመድገምና አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ታሳቢ ተደርጎ አገልግሎት ላይ የሚውል አሰራር መሆኑ ይታወቃል። ነገሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አጀንዳ የሆነበት ታድያ ሌላ ምንም ሳይሆን ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራትና መንግስታት መክራና ዘክራ በትግራይ ህዝብ ላይ ያከናውነችው ወረራ ይህን ተከትሎም ግንባር ፈጥሮ ወደ ትግራይ የገባ ሰራዊት በትግራይ ህዝብ ላይ በህይወቱና በንብረቱ ላይ ያደረሰው ጥፋትና ውድመት ማለትም እህልና የመድሃኒት ክልከላን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀሎች ጨምሮ በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈፀመ የኢትዮጵያ የሰራዊት አለቃ የሆነ አንዱ አበባው ታደሰ በይፋ በቴሌቭዥን መስኮት ቀርቦ እንደ ተናገረውም የህዝቡን መሰረተ ልማት የማውደም የጦር ወንጀለኝነትና ማንነት መሰረት አድርጎ የተፈፀመ የዘር ጭፍጨፋ፤ በትግራይ ላይ የተፈጸመ ወረራና ጦርነት ተከትሎም እንደ ወረርሽኝ በመላ አገሪቱ የተዛመተ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ጥግ ደርሶ የብሔር ብሔረሰቦች አገር የሆነውን ኢትዮጵያ ዜጎትዋ ዓይናቸው እያየ በጣጥሶ እንዳይበትናት ለማይስቆም ነው ሊሆን የሚችለው። ነገሩ ይህ ከሆነ ዘንዳ እየተባለ ያለ የሽግግር ፍትህ እውነተኛና ትክክለኛ መፍትሔና ዕልባት ሊያገኝ የሚችለው የሽግግር ፍትሁ ምን ዓይነት መልክና ቅርጽ ሲይዝና ምንስ ሲያማላ ነው የተሟላ አጥጋቢና አመርቂ ውጤት ሊያስመዘግብ የሚችለው? ብሎ ነገሩን በስፋትና በጥልቀት የማየቱን አስፈላጊነት ሊያጠያይቀን አይገባም።
በመሆኑም፥ ዘላቂና አስተማማኝ የሆነ ሰላምና መረጋጋት (ዕርቀ ሰላም) ሊያመጣ የሚችል ውጤታማና የተሳካ የሽግግር የፍትህ ሂደትን ለማካሄድ በዋናነት፥
- ዓለም አቀፍ ድጋፍና ተሳትፎ መፍቀድና መሻትን ይጠይቃል። ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራትና መንግስታት በመጋበዝ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀመችው በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም የጦርና የዘር ማጥፋት ወንጀል በማጣራት ለተበዳዩ የትግራይ ማህበረሰብ ፍትህና ፍርድን ታደርጋለች ብሎ መጠበቅ ከጅብ አጥንት ከዝምብም ማር መጠበቅ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ውጤታማና የተሳካ የሽግግር ፍትህ ለማከናወን በዋናነት በጥንቃቄ ማቀድ፣ ማስተባበርና መተግበርን ይጠይቃል። ይህ ማለት፥ የኢትዮጵያ ሰዎች ይህን የማድረግ አቅም፣ ትምህርት፣ ስልጠና፣ ክህሎትና ችሎታ ብቻ ሳይሆን የሌላቸው ፍላጎቱም ቢሆን ሊኖራቸው ስለ ማይችል (የላቸውም) ኢትዮጵያዊ የሽግግር የፍትህ ሂደት እውነተኛና ትክክለኛ ውጤት ሊያስገኝ አይችልም። የሽግግር የፍትህ ሂደቱ እውነተኛና ትክክለኛ ውጤት እንዲመጣ ከተፈለገ ግን የገንዘብና የቴክኒክ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ድጋፎችን ከመለመንና ከማግኘት ያለፈ በዚህ መስክ ከፍተኛ ልምድና ተመክሮ ያላቸው ዓለም አቀፍ የወንጀል ምርመራና የፍትህ ተቋማት ቀጥተኛ ተሳትፎ ግድ መሆኑን ሊያጠያይቀን አይገባም። ትናንት ለጥፋት፣ ለሞትና ለእልቂት የአገሩን ሉአላዊነት አሳልፎ የሰጠና የሸጠ ማህበረሰብ ዛሬ እውነትንና ጽድቅን ፍትህንና ፍርድን እናድርግ ሲባል ደግሞ “ይህ ጣልቃ ገብነት ነው” ብሎ ማለት ከግብዝነትም ያለፈ ግልሙትና ነው።
- አካታችነትና ተሳትፎ ማረጋገጥ። ለሽግግር የፍትህ ሂደት ስኬት አንዱ የተጎጂዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በአማራ ታጣቂዎችና ሰራዊት ከፍተኛ የሆነ የህይወትና የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ትግራይ ውስጥ የሚገኙና ከትግራይ ውጭ በስደት የሚገኙ ተጋሩ በሙሉ በማንነታቸው ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት የደረሰባቸውና የተፈጸመባቸው ግፍና በደል የማይገልፀው መዓት በዝርዝር እንዲያስረዱ፣ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ፣ እንዲናገሩና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥም እንዲሳተፉ ማድረግ ሲሆን አካታችነትም በተመሳሳይ የሚገለል ሊኖር ስለ ማይችልና ስለ ማይገባ ነው።
- ግልጸኝነት፥ እውነተኛ የሽግግር የፍትህ ሂደት ሲባል በር ዘግተህ በድብብቆሽ የሚሰራና የሚከናወን አንድም በቆርጦ ቀጥል ዜና ህዝብን ማደናገርና ማወናበድ ሳይሆን በሂደቱም ሆነ በውጤቱ ተአማኒነት እንዲኖረው “ሀ” ብሎ ከተጀመረበት ዕለት ጀመሮ (አፈጣጠሩን ጨምሮ) ጉዳዩ ፍትህና ፍርድን በማድረግ እስኪገባደድ ድረስ የሂደቱ ውሎና አሰራር ለሰፊው ህዝብ በቀጥታ መታየትና ክፍት ከመሆን በተጨማሪ በተጨባጭ መረጃ ለህዝብ ማቀበልን ግድ ይላል።
- ተጠያቂነት፥ የሽግግር የፍትህ ሂደት አንዱና ዋነኛው ዓላማ ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረግ ፍትህና ፍርድ ተፈጻሚ ማድረግና ዕርቀ ሰላም ማውረድ እንደ መሆኑ መጠን በተለይ በዚህ ሂደት ላይ የነገሮች ማዕከል የሆነው የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ እልቂትና ጭፍጨፋ እንዲፈጸምበት እንዲበርስ በዕቅድና በዓላማ ከጎረቤት አገራትና መንግስታት መክሮና ዘክሮ የሰው አገር ሰራዊት ጋብዞ፣ የውስጥ ሃይልም አስተባብሮ የትግራይን ህዝብ የጨፈጨፈና ያስጨፈጨፈ ሃይል ማለትም ዐቢይ አህመድ ዓሊንና ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ በሚንስትር ማዕረግና ከዚያም በታች የሆነ ሲቪልና ወታደራዊ ባለ-ስልጣን፣ የመንግስት ልሳናትና ሚድያዎች፣ የወንጀለኞቹ ቀንደኛ ደጋፊዎችና የሁከትና የነውጥ ፊተውራሪዎች ላይ የሚመሰረተው የወንጀል ክሶችና የተጠያቂነት ዓይነቶችን በግልጽ የማሳወቅ ገዴታ ይኖርበታል።
- የካሳ ክፍያ መፈፀም። ካሳ ለፈውስና ለእርቅ ሂደት አስተዋጽኦ ያደርጋል ወይም አለው ተብሎ ከታመነ ላለፉት ሁለት ዓመታት እህልና መድሃኒት እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም በርሃብና በበሽታ እንዲረግፍ የተፈረደበት የትግራይ ህዝብ አይደለም “በጀትህ ተቃጥለዋል” ተብሎ ድጋሜ ሊሾፍበትና ሊቀጣ ቀርቶ ሆኖ ተብሎ በላዩ ላይ ከተፈፀመበት ወረራ የተነሳ ለደረሰበት ከፍተኛና መጠነ ሰፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት እውቅና ከመስጠት ባሻገር ካሳ የሚያገኝበት ግልጽና ፈጣኝ አሰራር መኖር።
- ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ፥ የሽግግር የፍትህ ሂደቱ ሌላኛው ተልዕኮ ወደ ፊት የዚህን ዓይነቱ በንጹሐን ላይ ያነጣጠረ ሞትና እልቂት ድጋሜ እንዳይከሰት ማድረግ ሲሆን ይኸውም እንደ የሕግ ለውጥና አዳዲስ ማለትም ወቅቱን በሚገባ ታሳቢ ያደረጉና ያገናዘቡ የቁጥጥር ዘዴዎችን በመስራትና በማስቀመጥ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ከማድረግና የህግ የበላይነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ ለአገሪቱ ተደጋጋሚ ቀውስና ደም መፋሰስ ምንጭና መንስኤ የሆነ ችግር መለየትና መፍትሔ ማበጃጀት ይጠበቅበታል።
ከፍ ሲል ከተመለክትናቸው ስድስት ነጥቦች በተያያዘ፥ የሽግግር የፍትህ ሂደት አቅም በመስጠትና በማጎልበት ረገድ ሌሎች ተጨማሪ ነጥቦችን ስንመለከት፥ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊነት ግልጽ ነው ተብሎ ይታመናል። አንድም፥ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ በሚደረግ ሂደት አዳዲስ ህጎችን ማቋቋምና ያሉትን ህጎች ማሻሻልን ሊያካትት ይችላልና። በተመሳሳይ፥ ለሽግግር የፍትህ ሂደት ስኬት የላቀ ሚና የሚጫወት መረጃን የማግኘት ማለትም የመረጃ ምንጭና ተደራሽነት ሲሆን የሽግግር የፍትህ ሂደት አካል የሆነው የወንጀለኞች ክስ ላይ ተሳታፊዎች የሆኑ አካላት ላይ ሊያጋጥም የሚችል አደጋ ለመካላከል የሚያስችል የደህንነት ጉዳይም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተጨማሪም፥ ውጤታማ የሽግግር የፍትህ ሂደት ለማካሄድ፥ የገንዘብ ድጋፍ፣ የሰው ሀይልና መሠረተ ልማትን እንዲሁም ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋምን ጨምሮ በቂ ግብአቶችን የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ረገድ ክፍተትና ጎደሎ ሊኖር አይገባም። ጥያቄው፥ የኢትዮጵያ ሰዎች ሽርብትን የሚሉለት ያለ “የሽግግር ፍትህ” ሌላው ቢቀር የአቅም ገደብ እንዳለው አምኖ የዓለም አቅፍ የፍትህ ተቋማት ተሳትፎ ያምናል ወይ? እውነትስ በአፈጣጠሩ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያለው ነው? እነዚህንና ሌሎች ተጨማሪ ተዛማች ጥያቄዎች በሚመለከት በሚቀጥለው ንዑስ ርዕሳችን በስፋት አንስተን አንዳስሳዋለን ንባቡን ይቀጥሉ።
ወንጀለኛው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከተጠያቂነት ለማስመለጥ
ኢትዮጵያ እያሳለጠችው የሚገኝ የሽግግር ፍትህ ሐሰተኛ፣ ከእውነትም የራቀ ነው
በዚህ ጉዳይ ላይ “ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ከባለ ድርሻ አካላት ግብአት ለመሰብሰብ የተዘጋጀ” በሚል ርዕስ ጥር 2015 ዓ.ም ይፋ የሆነው ንባብ ገጽ 19 ላይ “እርቅ የሽግግር ፍትህ ሂደት አንደኛው ግብ ወይም አላማ ነው” እንዲል በርግጥ ችግሩ ከአባባሉ ጋር ሳይሆን አባባሉ ዓውዱ ያልጠበቀ በመሆኑ፣ አንድም፥ ይህ የሽግግር ፍትህ እያለ የሚገኝ አካል ዓላማ፥ ፍትህና ፍርድን በማድረግ ሊገኝ ስለሚችል ዕርቀ ሰላም ሳይሆን ይልቁንም የሽግግር ፍትህ በሚል ሽፋንና ይህን ተከትሎም ለይስሙላ በሚሰሩ ስራዎች አማካኝነት ፍትህና ፍርድ በማዳፈን ማለትም ተጠያቂ መሆን ያለበትና የሚገባቸው የኢትዮጵያ ባለ-ስልጣናት በነጻ አሰናብቶና ተደላድለው እንዲኖሩ በመፍቀድ በደምሳሳው ዕርቀ ሰላም ወረደ! ብሎ ድግስ ለመብላት ጥድፊያ ላይ ያለ ቡድን ለመሆኑ ይህ ይህ የሰነዱ ንባብ ብቻውን በቂ ምስክርነት ነው።
ዐቢይ አህመድ ዓሊ ራሱ በፈበረከው ሐሰተኛ ትርክትና ጥቁር ውሸት ትልቁም ትንሹም ሼኩም ሊቀ ጳጳሱም በውሸት አሳብዶ፣ የአማራ ልሒቃንን እንደ ፈረስ እየጋለበ፣ ከኤርትራው አገረ ገዢ ከኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ግንባር በመፍጠርም በትግራይ ህዝብ ላይ በጋራ የፈፀሙት በሰብአዊነት የሚፈፀም የጦርና ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ጭፍጨፋ በተመለከተ፥ ለባዊት ነባቢትና ሕያዊት ነፍስ ኖሮት ፈጣሪውን የሚፈራና ቅን ልብ ያለው ሰው ሁሉ ዘንድ ነገሩ እኔ በጽሑፍ ላሰፍረው ከምችለው በላይ የተገለጠ ሐቅ ነው። እንግዲያውስ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂና አስተማማኝ የሆነ ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ተፈልጎ ፍትህና ፍርድ የሚደረግ ከሆነ የመጀመሪያ ተከሳሽና ወንጀለኛ ሰው ሌላ ማንም ሳይሆን ይህን ዓይነቱ ድግስ በማዘጋጀት ከፍትህና ከፍርድ አመልጣለሁ! ብሎ የሚያምነው ከዚህ የሽግግር ፍትህ ጀርባም ያለ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ራሱ ነው። ሰውዬው ይህ የሽግግር ፍትህ እንዴት ሊጠቀምበት ነው እያደባና እየሰራ ያለ? ለሚለው ጥያቄ፥
- መርጦ በማልቀስ (Selective justice)። የሽግግር ፍትህ እያሉ እዚህም እዚያም መታየት ያበዙ የዐቢይ አህመድ ዓሊ የዙፋኑ ተሸካሚዎች የሆኑ እነ ዳንኤል በቀለና ጌድዮን ጢሞቲዎስን ይመልከቱ። እነዚህ ሰዎች በትግራይ ግዛት በማይካድራ ኖዋሪዎች በሆኑ የትግራይ ተወላጆች ላይ ማንነት መሰረት ያደረገ ዘራዊ ጭፍጨፋ በተመለከተ ሳምንት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ “በአማራ ተወላጆች የጅምላ ግድያ ተፈጽማል” ብለው መንግስታዊ መግለጫ የሰጡ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሌላው ቀርቶ በአክሱም፣ በማሪያም ሸዊቶና በማህበረ ዴጎ ላይ ከህግ አግባብ ውጭ የተፈፀሙ ዘግናኝ የጅምላ ግድያዎችና ጭፍጨፋዎች የዓለም የሰብአዊ መብትና ትላልቅ የሚድያ ተቋማት ክስተቱን በተጨባጭ በማረጋገጥ በተጋሩ ላይ የተፈፀመ ጅምላዊ ግድያ በአንድ ድምፅ ሲያወግዙ እነዚህ የስርዓቱ አገልጋዮችና ተጠቃሚዎች የሆነ ባለ-ስልጣናት (ዳንኤል በቀለና ጌድዮን ጢሞቲዎስን) በአንፃሩ ትንፍሽ አላሉም። አንድም፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ዓይነቱ ነውርና ሃፍረት የሌለውና የማያውቅ ሰው እየመረጠ በማልቀስ ረገድ እንከን የማይገኝበት አረመኔ እንደ መሆኑ መጠን እነዚህንና መሰል መደዴዎች አሰባስቦ “የሽግግር ፍትህ” በሚል ስምና ሽፋን ሊሰራው ያቀደውን ሸፍጥ ለመረዳት ፊደል መቁጠር አይጠይቅም። ቀለል ባለ አማርኛ፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ዓይነቱ አምባገነን ገዢዎች የሽግግር ፍትህ እንደ ፖለቲካ መሳራያ በመጠቀም ከተጠያቂነት ለማምለጥ፣ ለራሳቸው አጀንዳና ጥቅምም የሚያውሉበት አንዱ መንገድ ሰውዬው መርጦ ሲያለቅስ ተቀብሎ ምሾ የሚያወርድ በእጁ መዳፍ የተቀረፁ ያገር ቤት ፍርድ ቤቶችና ዳኞችን በመተማመን ነው። ዐቢይ አህመድ ዓሊ የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ኮሚቴ ጨምሮ ዓለም አቀፍ የፍትህ ተቋማት እንዲሁ ስማቸው በተነሳ ቁጥር ብርክ የሚይዘው ያለ ምስጢርም ሌላ ምንም ሳይሆን ሰውዬው ስራውን ስለሚያውቅና ከተጠያቂነትም እንደማያመልጥ በሚገባ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው። ማንም አይግባብኝ! የራሳችን ፍርድ ቤቶች አሉን! እያለ በመጮህ የሚገኝበት ተጨማሪ ምክንያትም ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ጥቃቅን ዓሳዎችን በመሰዋት (በወንጀል ተጠያቂዎች በማድረግ) በማህበረሰቡ ዘንድም ፍትህ ተደረገ! የሚል ስሜት በመፍጠር እሱና ግብረ-አበሮቹ ግን የሽግግር ፍትህ በሚል ፈሊጥ ጥላ ተከልለው ከተጠያቂነት የማምለጥ ዕቅድና ዓላማ ስላለውና ስላላቸው ነው።
- ሂደቱን በማጭበርበር (Manipulation of truth-telling processes)። አሁን በዚህ ሰዓት ሰዎቹ ጭራሽ የጽድቅ ሰባኪዎች ሆነዋል። ለመሆኑ ከፓርላምም ከአዳምም ሰዎች በተደጋጋሚ በብርቱ የሚነገርና የሚሰማ ያለ ድምጽ ልብ ብለው ኖራል? የፓርላማ ሰዎች እንባ እየተናነቃቸው እየተረኩሎት ያለ ምፀት የሰላም ዋጋ ምንኛ ውድ እንደሆነ ነው። ዜጎች ምንኛ ሰላም መጠማት እንደላባቸውና እንደሚገባ ሳያፍሩ እየነገርዎት ነው። ርግጥም፥ የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ! የሚባለው ይሄ ነው። ተረኩ፣ ድምጹና ቅላጼው ሁሉ ተለውጣል። የተለወጠው ታድያ የጦርነት ድምጽ ማስተጋባት ቀርቶ ሰላም ወደሚል ድምጽ መሸጋገሩን ሳይሆን ቁምነገሩ የጦርነቱ ፈጣሪዎች ከተጠያቂነት የሚያስመልጥ፣ አልፎም ተርፎ ህዝቡን ተጠያቂ የሚያደርግ አዲስ ተረክ የመፍጠርና ምንም እንዳልተፈጠረ በመሆንም እንደ ተለመደው ሁሉም ባለበት እንዲረግጥ የማድረግ አደገኛ አሰራርን ነው። በሉአላዊነት ፈሊጥ የተደጎሰ “ማንም ድርሽ እንዳይልብን!” የሚለው የዐቢይ አህመድ ዓሊ መፈክር ዓላማ የሽግግር ፍትህ ሂደት የማጭበርበር አንዱ አካል ሲሆን ፍቃድ በመከልከል ምርመራውን በመገደብና ለሚካሄደው መጣራትም ወሳኝ የሆነ የመረጃ ምንጭ ማሳጣትን ያለመ ስራ ላይ መጠመዱን ልብ ማለቱም አስፈላጊ ነው። አንድም፥ የአገሪቱ የፍትህ ስርዓት ሙሉ በሙሉ በዐቢይ አህመድ ዓሊና እሱ በሚመራው ገዳይና ዘራፊ ባለተራ ቡድን መዳፍ በወደቀባት በዚህ ሰዓት የኢትዮጵያ ሰዎች የሽግግር ፍትህ እያሉ የሚያስተጋቡት ያለ ድምጽ በእውነቱ ነገር ባዶ ፕሮፓጋንዳ ከመሆን ያለፈ ትርጉም የለውም። ኢትዮጵያ ውስጥ የዐቢይ አህመድ ዓሊ ፖለቲካ የሚቃወምና የማይቀበል ሰው ሁሉ በህግ ስምና ሽፋን ለመስቀልና ለማስወገድ የሚተጉ ፍትህ አልባ ዳኞችና የፍትህ ተቋማት እንጅ ህግና ስርዓት የሚጠብቁና የሚያስከብሩ አይደሉምና። በተጨማሪም፥ ወንጀለኞች በፈፀሙት ወንጀል ልክና መጠን ተጠያቂዎች ላለመሆን በትግራይና በኢትዮጵያ መካከል የተካሄደ የሚልዮኖች ንጽሐን ህይወት የቀጠፈና ተጨማሪ ሚልዮኖችን ያፈናቀለ ደም አፋሳሽ ጦርነት መጀመሪያውኑ በውውይት መፍታት ይቻል የነበረ የፖለቲካ አለመግባባት የፈጠረው ችግር እንደሆነም እየነገርዎት ነው። ይህ ዓይነቱ ፍትህንና ፍርድን የማሳጣት አሰራርና አካሄድ ደግሞ በአምባገነን መንግስታት ዘንድ በሚገባ የታወቀና የተለመደ ህዝብና አገር የማወናበድ ስልት ከመሆኑ ባሻገር የሽግግር የፍትህ ሂደቱን ማጭበርበር መሆን ልብ ይሏል።
- የሰላም፣ የምህረትና የይቅርታ ሐሰተኛ መዝሙር እጅግ በተቀናጀ ሁኔታ በመዘመር። ሲፈጥረው ፀረ-ሰላም የሆነ፣ የደም ሰው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ልክ እንደ ሰላም ወዳድ ሰው “ሰላም፣ ምህረትና የይቅርታ ነው የሚያሻግረን!” እያለ ሲመጻደቅብን፤ በአፉ ሰላም፣ ምህረት፣ ይቅርታ! እየለ ህዝብና አገር ሲያዋክብ በአንፃሩ ደግሞ መሬት ላይ በተጨባጭ ምን እየሰራ እንዳለ ዓይናችን ከፍተን የማየት ገዴታ የሁላችን ነው። ሰዎቹ ሰላም! ሰላም! ሲሉ በእውነት ሰላም ወዳጆች ስለሆኑ ሳይሆን በፈፀሙት ወንጀል ከተጠያቂነት ለማምለጥ የመከሩት ሰይጣናዊ ምክር መሆኑን ሊገባንና ልንነቃ ይገባል። ዐቢይ አህመድ ዓሊ፥ የሰላም፣ የምህረትና የይቅርታ ሐሰተኛ መዝሙር መዘመር ሲያበዛ፤ አንድ፥ የተፈጸመው ግፍና በደል በማንኳሰስና በማድበስበስ ራሱንና ግበረ-አበሮቹን ከተጠያቂነት ለማምለጥ ዓልሞ ሲሆን፤ ሁለት፥ ይህን በተደጋጋሚ በማለትና በማስተጋባት ነገሩ የዕርቀ ሰላም ሂደት ደጃፍ እንደሆነም በህዝቡ ዘንድ ብዥታ በመፍጠር ራሱን እንደ ሰላም ወዳድ ሰውና የሰላም ሓዋሪያ አድርጎ የመሳል ጥልቅ ምኞትና ፍላጎት ስላለው ነው። የሽግግር ፍትህ ሰባኪዎች ይመልከቱ። እነዚህ ሰዎች ትናንት የዐቢይ አህመድ ዓሊ መጠቀሚያና በውሸትና በንጹሐን ደም የጨቀየ ፖለቲካው መሳሪያ በመሆን በትግራይ ህዝብ ለተፈፀመ ግፍና በደል አፋቸውን ሞልተው “ህግ የማስከበር ዘመቻ ነው!” ብለው ሽፋን ይሰጡ የነበሩ፣ ለእውነት ለፍትህና ለፍርድ በመቆም ፈንታም ስልጣን የሚያስገኘው ጥቅም አስምጣቸው ፍትህና ፍርድን በማጠመም ላይ ሲተጉ ከሚታወቁ ሰዎች መካከል ዳንኤል በቀለና እንደ ጆሰፍ ጎብል ዓይነቱ የሂትለር ልብና ሳንባ በመሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተጋሩ ከያሉበት እየታደኑ በማጎሪያ ስፍራዎች እንዲታጎሩ፣ ኮንቴነር ውስጥ ታሽገው በአፋር ክልል ውስጥ እንዲቀመጡና በሙቀት እንዲቀልጡ ያደረገ ጌድዮን ጢሞትዎስ ነው። ጥጉ፥ ይህ የሽግግር ፍትህ የሚሉት ያለ ኢትዮጵያዊ ድራማ ከቀልድም ያለፈ ባጫ መሆኑን የሚስተው ባለ አእምሮ የለም።
- የሽግግር ፍትህ! የሚል ባንዴራ በማውለብለብ ጊዜ መሸመትና በሂደትም ፍትህን የማጠልሸት አጀንዳ። ዐቢይ አህመድ ዓሊና ይዞት የመጣ ገዳይና ዘራፊ ቡድን እሱ ራሱን ተጠያቂ የሚያደርግ የሽግግር ፍትህ ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈጠራል፣ ይኖራል! ብሎ ማመን ቀርቶ በሃሳብ ደረጃ ማሰቡ ራሱ ለባለ አእምሮ ሰው የሚከብድ ነው። ለራሱ ክብር ያለው ሰው እንደሆነም እንደዚህ ዓይነት ቅሌት ውስጥ ራሱን እንደማይዘፍቅ የታወቀ ነው። ጥጉ፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊና ይዞት የመጣ ገዳይና ዘራፊ ባለ ተራ ቡድን እውነትንና ጽድቅን ፍትህንና ፍርድን የማድረግ ዓላማ ሆነ ፍላጎት ፈጽሞ የለውም። እየሆነ ያለ ታድያ ምንድ ነው? ያሉኝ እንደሆነ ግን፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሽግግር ፍትህ የሚል ባንዴራ እያውለበለበ ሊያስቆጥረው የሚፈልገው ነጥብ ቢኖር ሰፊው ህዝብ የሽግግር ፍትሁ ዓላማና ግብ እስኪዘነጋና ግራ እስኪጋባ ድረስ በነገር በማድከምና በማሰላቸት በአዳዲስ ክስተቶችና ኹነቶች ከድጡ ወደ ማጡ እያገለባበጠና እያንከባለለ ከተጠያቂነት ማምለጥና መንበረ ስልጣኑን መጠበቅ ነው። ጥያቄው፥ ይህን ዓይነቱ የፖለቲካ ሸፍጥና ሸቀጥ እንዴት ማስቆም ይቻላል የሚል ነው።
በርግጥ፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሽግግር ፍትህ እንደ ስልትና ማምለጫ መንገድ በመጠቀም ከህግ ከተጠያቂነት እንዳያመልጥ ከተፈለገ መንገዱ (መሆንና መደረግ ያለበት በተመለከተ) ሲበዛ ግልጽና ቀላል ነው። ይህን ለማድረግም የጠፈር ተመራማሪ መሆንን አይጠይቅም። አንድም፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሽግግር የፍትህ ሂደት እንደ ፖለቲካ መሳሪያ ተጠቅሞ ከፍትህና ከፍርድ እንዳያመልጥ ከተፈለገ።
- ዓለም አቀፍ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ። ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራትና መንግስታት ጋር መክራና ዘክራ በምድር የኤርትራ የሶማሊያ ሰራዊት በሰማይ የኢምሬቶች ተዋጊ ድሮኖት በማሰለፍና በማስዘመት በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀመችው በሰብአዊነት የሚፈፀም የጦርና የዘር ማጥፋት ወንጀል መጣራትና ፍትህ ማግኘት ያለበት የወንጀሉ ፈፃሚዎች በሆኑ የኢትዮጵያ ባለ-ስልጣት ይሁንታና ፈቃድ በሚዘወር ቀልደኛ የሽግግር ፍትህ ሳይሆን ነፃና ገለልተኛ በሆኑ ዓለም አቀፍ አጣሪዎችና የፍትህ ተቋማት ነው። እንደ አገርና እንደ መንግስት ለተፈፀመ ጥፋት በትክክል ፍትህና ፍርድ ማድረግና መስጠት የሚችል የወንጀሉ ፈፃሚ ራሱ በሚያደራጀው አካል ሳይሆን በወንጀለኛ መንግስት ላይ ጠንካራ ምት ሊያሳርፉ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግስታት በቀጥታ ተሳታፊ ያደረገ ሂደት እንደሆነ ብቻ ነው። አንድም፥ ይህ በዐቢይ አህመድ ዓሊ ፈቃድና ይሁንታ የተፈጠረ ኢትዮጵያዊ የሽግግር ፍትህ ተራ ወታደርና እታች ያለውን የቀበሌ ሊቀ መንበር ተጠያቂ ከማድረግ ያለፈ አውራ ቂሱን ዐቢይ አህመድ ዓሊን ለመመርመር ሆነ ለመቅጣት የሚያስችል እዚህ ግባ የሚባል ዓቅምም ሆነ ስልጣን የለውም፤ አይኖሮውምም።
- በተለይ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግኙንነት ያላቸው የአገር ውስጥ የፀጥታና የፍትህ ተቋማትን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ቢሮ እንደገና ማደራጀትና ማጠናከር። ቢሆን በዚህ ረገድ ሰፊና ጥልቅ የሆነ ልምድና ተመክሮ ካላቸው ዓለም አቀፍ የምርመራና የፍትህ ተቋማት ጋር ህብረት ፈጥሮ መስራት የሚችል በኮሚሽን ደረጃ የሚቋቋም እውነት ፈላጊና እውነት ተናጋሪ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል። አንድም፥ የስርዓቱ አገልጋዮችና የጥቅም ተጋሪዎች የሆኑ እነ ዳንኤል በቀለና ጌድዮን ጢሞትዎስ በማስወገድ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋማትን እንደገና መፍጠርና ማደራጀት የሽግግር የፍትህ ሂደት ግልጽና ሁሉን አቀፍ ከማድረጉ በላይ ውጤታማ እንዲሆን ስለሚረዳ ነው። የዐቢይ አህመድ ዓሊ ዓይነቱ ገዳይና ዘራፊ መንግሥት በንጽሐን ላይ የፈፀመው መጠነ ሰፊ ወንጀል የተነሳ በህግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆን በማድረግ ሂደት ላይ የሲቪል ማህበራት፣ ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቀጥተኛና አክቲቭ የሆነ ተሳትፎ ሊዘነጋ አይገባም። እውነቱን በመግለጥና ለእውነት በመቆም ፍትህና ፍርድ በማረጋገጥ ረገድ ነጻና ገለልተኛ ሆነው የሚቋቋሙ ተቋማት የሚጫወቱት ሚና የላቀ ነው።
ኢትዮጵያዊነትና እውነት ማዶ ለማዶ ተያዩ
እኔምለው፥ ትልቁም ትንሹም፣ ሼኩም ጳጳሱም፣ ዘማሪውም አዝማሪውም፣ ፓስተሩም ባለ-አውሊያውም፣ ባለ ሀብትና ሙሑር ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ የትግራይ ህዝብ ጠላት ህዝብ ነው! ብሎ ትግራይ ከካርታ የትግራይ ህዝብም ስመ ዝክሩ በታሪክ መታሰቢያ ላይኖሮው ላማጥፋትና ለመደምሰስ ከጎረቤት አገራትና መንግስታት ጋር ግንባር ፈጥሮ የዘመተ ማህበረሰብ አካል የሆነ (የአማራ ሆነ የኦሮሞ ደም ባላቸው) ዳኞችና የህግ ሰዎች አማካኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቋመው ፍርድ ቤት ምን እያለ ነው በትግራይ ህዝብ ላይ ማንነት መሰረት አድርጎ የተፈፀመ፣ አይደለም የሆነውን ለመናገርና ለመፃፍ ቀርቶ ለማሰቡ የሚከብድ፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም የጦርና የዘር ማጥፋት ወንጀል በእውነትና በቅንነት በመመልከት ይህን አረመኔያዊ ወንጀል የፈፀሙ እነ ዐቢይ አህመድ ዓሊ፣ ሽመልስ አብዲሳ፣ ብርሃኑ ጁላ፣ ባጫ ደበሌ፣ አዳነች አበቤ፣ አገኘሁ ተሻገር፣ ደመቀ መኮነን፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዮሓንስ ባያለ፣ ዳንኤል በቀለ፣ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ አበባው ታደሰ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ ጌድዮን ጢሞትዎስ ወዘተ ተጠያቂዎች የሚያደርጋቸው?
ይህ ኢትዮጵያዊ የሽግግር ፍትሕ ተጋብዞ ይሁን ተገዝቶ በትግራይ ላይ ወረራ በመፈጸም በትግራይ ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የዘር ጭፍጨፋ የፈጸመ፣ የህዝብና የመንግስት ንብረት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ የዘርፈና ያወደመ የኤርትራ ገዢ ኢሳይያስ አፈወርቂና የሰራዊት አለቆቹስ በምን ዓይነት አሰራርና ሂደት ነው ተጠያቂዎች የማድረግ ዕቅድ ያለው? ካልሆነ ይህ ኢትዮጵያዊ የሽግግር ፍትሕ እውነትም ፍርድና ፍትህ በማድረግ አገርና ህዝብ ወደ ተሻለ ምዕራፍ የማሸጋገር ዓላማና ተልዕኮ ሳይሆን ያለው ዐቢይ አህመድ ዓሊና መሰል ወንጀለኞች በፈፀሙት ወንጀል ተጠያቂዎች ከመሆን የማስመለጥና የማዳን ተልዕኮ ብቻ ነው ሊኖሮው የሚችለው። ጻፍክ፣ ተናገርክ፣ ሃሳብህን ገለጽክ፣ አልደገፍከኝም፣ ተቃውመሃኛል! ወዘተ እየተባለ አላፊ አግዳሚው ወጪ ወራጁ በገፍ ወደ ውህኒ በሚወረወርባት አገር ዐቢይ አህመድ ዓሊና ይዞት የመጣ ዘራፊና ነፍሰ ገዳይ ባለተራ ቡድን (ወዶ-ገብ የአማራ ልሒቃንን ጨምሮ) በትግራይ ህዝብ ላይ ማንነት መሰረት ያደረገ ወንጀል ከመፈፀም ያለፈ የሰው አገር ሰራዊት በመጋበዝ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት አስደፍራቸዋል ብሎ በአገር ክህደት ተጠያቂ የሚያደርግ ራሱን “የሽግግር ፍትሕ” ብሎ የሚጠራ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይም ይኖራል ብሎ ማሰብ ሲበዛ ጅላንፎነት ነው። አንድም፥ የዚህ ዓይነቱ አሰራር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ከሆነም በዐቢይ አህመድ ዓሊ ይሁንታና ፈቃድ የሚንቀሳቀስ ለሰውዬው ጥቅምና አጀንዳ የሚሰራ ቡድን ብቻ ሊሆን የሚችለው።
ዐቢይ አህመድ ዓሊና ይዞት የመጣ ዘራፊና ነፍሰ ገዳይ ቡድን፥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አጀንዳ ሰንቆ ሊያገኘው የሚችል የውስጥም የውጭም ሃይል ሁሉ አስተባብሮ ትግራይን መትቶ ለመጣል ከሱዳን ጋር መክሮ በምድር የኤርትራና የሶማሊ ሰራዊት በሰማይ ኤምሬቶችን በማሳተፍና በመጋበዝ እግሩን ሲያነሳ የአማራ ልቃን ይህን እንደ ትልቅ አጋጣሚ በመጠቀም ትግራይን ለመውረርና ለመዝረፍ (በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀሙትን በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም የጦርና የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ለመፈፀም) ዓይናቸውን አላሹም። በትግራይ ላይም ቢሆን ፍትሓዊ ያልሆነ ምክርና አጀንዳ መያዝና ተፈጻሚ ማድረግ ትክክል አይለም ማለት ቀርቶ ንጉሳችን ዐቢይ አህመድ ዓሊ ሺህ ዓመት ንገሥ፣ የትግራይ ህዝብ ጠላት ህዝብ ነው! ተጨምሮበት ትግራዋይ የሚባል ህዝብ እንደ ህዝብ መታሰቢያው ከምድረ ገጽ ለማጥፋትና ለመደምሰስ በአማራ በኩል የተኬደው ርቀት ሰውና ሰይጣን የሚያውቀው ሐቅ ነው። የአማራ ተወላጆችም ቢሆኑ ይህችን ዕለትና አጋጣሚ አይክድዋትም። የአማራ ልሒቃን ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሰጣቸው “ሰሜን ዕዝ ተነካ” የሚለው የተፈበረከ ትርክትና ሐሰተኛ መፈክር አነግበው በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀሙት ግፍና በደል መቼም ቢሆን የሚረሱት አይደለም። ጥያቄው፥ ትናንት፥ ንጉሳችን ዐቢይ አህመድ ዓሊ ሺህ ዓመት ንገሥ! ሲል የነበረ የአማራ ህዝብና አመራር ዛሬ ምን ቢገኝ ነው፥ ባለ ተራው አምባገነን ዐቢይ አህመድ ዓሊ ሌባ! የሚለውን መፈክራቸው “ጠጅ መስሎን ነበር ምርጊቱ ሲከፍት፤ ጠላነው መልሱት ወደነበረበት!” የሚለው አባባል ተጨምሮበት ህዝቡ አንጀቱ እስኪሳብና ምላሱም ከትናጋው ጋር እስኪጣበቅ ድረስ በመጮህ ላይ የሚገኘው? ዛሬ በሚልዮኖች የአማራ ክልል ተወላጆች ዘንድ ሌባ! እየተባለ እየተጠራና እየተገለፀ የሚገኝ ሰው (ዐቢይ አህመድ ዓሊ) ትናንት የእግር ካስ ምሳሌ እየሰጠ አንድ ሚልዮን ቁጥር ያለው የንጹህ ሰው ደም ያፈሰሰ አረመኔ አይደለምን? ከአራትና ከአምስት ወራት በፊት ማለትም ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ድፍን የዓለም ማህበረሰብ የዐቢይ አህመድ ዓሊን አረመኔያዊ ድርጊት ሲቃወም ኢትዮጵያ ውስጥም ያለ ይሁን ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖር የአማራ ክልል ተወላጅ የሆነ ማህበረሰብ ግን በተቃራኒው የዐቢይ አህመድ ዓሊ ሰይጣናዊ ድርጊት ደጋፊ ነበር። የዓመታት ጸሎታችን ነው/ነበር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አባትና ጠባቂ የሆኑ የቅዱስ ፓትሪያሪኩን ቃልና መግለጫን ቤተ ክርስትያንን አይወክልም፣ ኢትዮጵያን መንካት ተዋህዶን መንካት ነው፣ የናንተ ሰፕተርበር ኢለቨን ለእኛ ኖቨምበር አራት ነው፣ ሰይጣን ቢገዛን ይሻለናል! ወዘተ እያሉ ለደምነትና ለእልቂት የተሰለፉ፣ ሰውና ፈጣሪ የተፀየፋቸው ወናፎችና ውታፍነቃዮች የኢትዮጵያ ሰይጣናዊ ሲኖዶስ አባላትና ሊቃነ ጳጳሳት ከዚህ ክልል የተገኙ ናቸው። ኢትዮጵያዊነትና እውነት ማዶ ለማዶ ተያዩ! ይሉሃል ይሄ ነው።
የኦሮሞ ህዝብም ብንመለከት የወለጋ ዓይነቱ የኦሮሞ ህዝብ እንደ ህዝብ የዐቢይ አህመድ ዓሊ ሰለባ እንጂ ተጠቃሚ አይደለም። በለነደንና በአሜሪካን አገር መቀመጫቸው ያደረጉ ከጥቂቶች በቀር ትምህርት ቀመስ ነን የሚሉ የኦሮሞ ተወላጆችም ቢሆን ብዙሓኑ ትናንት ሲያስጮሃቸው የነበረ አጀንዳ ዛሬ የለም። ቢጮሁም ድሃ ተበደለ ፍትህ ተጋደለ! ብለው ሳይሆን የዐቢይ አህመድ ዓሊ፣ የሽመልስ አብዲሳ፣ የአዳነች አበቤ፣ የታከለ ኡማና የሌሎች (የኦሮሞ ተወላጆች በባለ ተራነት መንፈስ የተቀራመቱት ከፍተኛ መንበረ ሰልጣን) ለምን እኔ እልተቀመጥኩበትም ነው በመካከላቸው የሚገኝ ኩርፊያ ምንጭ። በመሆኑም ኦሮሞም ይሁን የአማራ ልሒቅ (የኢትዮጵያ ደም ያለው ሰው በአብዛኛው) ከእውነትና ከጽድቅ ፈጽሞ የማይተዋወቅ ከፍትህና ከፍርድም የተፋታ ዜጋ ነው። ራሱን ጨምሮ ወገኔ ለሚለውና ለሌላው ማህበረሰብ ያለው ምልከታ ሚዛኑ ክፉኛ የተዛባ ነው። ድህነትና ስራ አጥነት ሃይማኖት እንዲያከር ያስገደደው የኢትዮጵያ ሰው ክፉኛ አጉል ሃይማኖተኝነትና መመፃደቅ የነገሰበት ዜጋ ከመሆኑ ያለፈ እውነትና ጽድቅ፣ ፍትህና ፍርድን በቁማቸው ለማየት የታደለ ማህበረሰብ አይደለም። ይልቁንም፥ እሱን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደረገውን ሲያነፈንፍ፥ እውነትና ጽድቅ፣ ፍትህና ፍርድን በእውቀትና በድፍረት ገፍትሮ የሚጥልና የሚያሳጣ ማህበረሰብ ነው። ይህን ዓይነቱ ርካሽና የወደቀ እምነትና አስተሳሰብ ሳይለወጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር የሚችል ኢትዮጵያዊ የሽግግር ፍትሕ ቀልድ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው።
በተረፈ፥ የኢትዮጵያ ባለ ስልጣን ከጎረቤት አገራትና መንግስታት መክረውና ዘክረው በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀሙት በ21ኛ ክፍለ ዘመን ይፈፀማል ተብሎ የማይታሰብና የማይታመን የግፍና የበደል ዓይነት የተነሳ ተጠያቂዎች ሊሆኑ የሚችሉ ባለ-ስልጣናቱ ያደረጉትን ያደርጉ ዘንድ፣ ያደረጉትን አድርገው ምንም እንዳልተደረገና እንዳልተፈጠረ በማስመሰልም ሁሉም ዓይነት ሽፋን በመስጠት ላይ የተጉ ፈርጣማ መንግስታትና አገራት በአንድም በሌላም ያስቆጡና ከተለመደው የመታዘዝ አሰራር የፈነገጡ ዕለት ብቻ ይሆናል። እስክዛው ድረስ ያለው ሂደት ሁሉ ታድያ ሃያላኑ በተለመደው ተለዋዋጭ ክንፈራቸው ያደክሙሃል አንተም በተስፋ ስትጠባበቅ ትደክማለህ እንጅ ፍትህና ፍርድ ለትግራይ ህዝብ አሁን በዚህ ሰዓት የህልም እንጀራ ነው።