09/01/2023
ሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ
በ“አብይ አህመድ አሊ” የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ጥቅምት 24/2012 በገዛ ራሱ ህዝብ ላይ ያወጀው ወረራ በጥልቀቱ፣ በዓይነቱና ባደረሰው ውድመት ሲለካ ጄኖሳይዳል መሆኑ ጥርጥር የለውም ሲባል ያለምክንያት አይደለም፡፡ ወረራው ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰድ ታቅዶ፣ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት፣ ከውስጥና ከውጭ አቅምን አስተባብሮ ለሁለት አመታት ያለማቋረጥ በትግራዋይ ላይ የተካሄደ፣ በሰብአዊ ፍጡር ላይ በጭካኔ የተፈፀመ እና የጦር ወንጀልኝነት መስፈርት ያሟላ ወረራ እንደነበር ዓለም በአይንዋ የተመለከተችው እውነታ ነው፡፡ የፕሪቶርያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላም ስምምነቱ የትግራይ ህዝብ ሲደርስበት የነበረው መከራ ሳይታደግ ባለፉት አስር ወራት ተጨማሪ ሞትና እልቂት በማስከተል በአዝጋሚ ጉዞ እየተራመደ ለመገኘቱ ሚስጢር በብልፅግና መንግስት ዳተኝነትና የሴራ ፖለቲካ ምክንያት እንደሆነ በርካታ መንግስታት፣ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች፣ እና ሚዲያዎች የዘገቡትን በምስክርነት ዋቢ መጥራት ይቻላል፡፡ ይህ በታሪክ ይቅር የማይባል መኣትና መከራ በትግራይ ህዝብ ላይ መድረስ ነበረበት ወይ? የሚል ጥያቄ ትተን በወረራው ወቅት ምን ነበር የተከናወነው? የሚል ሃሳብ በማንሳት በጦርነቱ ወቅትና ቀደም ብሎ በከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በወታደራዊ መሪዎች እና በልሂቃን አንደበት ሲነገር የነበረው መሬት ላይ ከተፈፀመው ተግባራዊ ክስተት ጋር አስተሳስሮ መመልከቱ በአንድ በኩል የጭካኔው፣ የሰቆቃው እና የክፋት ጥግ ምን ያህል እንደነበረ በሌላ መልኩም ወረራው የአጋጣሚ ክስተት ወይስ ሆን ተብሎ የተከናወነ? ነበር ብሎ ለመረዳት ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡
- መንግሰት ያሰማራው ወራሪ ጦር በርካታ ሴቶች ላይ ጥቃቱ ካደረሰ በኋላ ፀፀት ሳይሰማው የደረሰው አሰቃቂ አካላዊና ስነልቦናዊ ስቃይን እንደ ተራ ነገር በመቁጠር “ሴቶች የተደፈሩት በወንድ ነው” በማለት በመሪው አንደበት በኩራት በአደባባይ እስከ መግለጽ የደረሰው ቀድሞውንም ቢሆን የ “ሴት ልጅ ገላ” እንደ አንድ የጦር ግንባር ለመጠቀም ፍላጎትና የጦርነቱ አካል የነበረ ለመሆኑ የሚጠቁም ጉልህ ማስረጃ ተደርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ መሰል አስነዋሪ ተግባር በህፃናትና በሴቶች ላይ ሲፈፀም አንኳንስ “እናቶች ይፀልዩልኛል” ከሚል ሰው ይቅርና ለሴቶች አነስተኛ ግምት በሚሰጥ ባህል ውስጥ ያለፈ ሰው ይህ ተግባር የሚፀየፈው እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ በጦርነቱ ወቅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ህፃናት፣ ባለትዳር ሴቶች፣ ልጃገረዶች፣ መነኩሴዎች በወራሪው ጦር በፈረቃና በቡድን ተደፍረዋል፤ በአንድ አከባቢ በማጎር ፆታዊ ባርነት ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ሴቶች በአያቶቻቸው፤ በባሎቻቸው እና በልጆቻቸው ፊት ተደፍረዋል፡፡ በሴቶች ብልት ውስጥ ባእድ ነገር በመጨመር አካላዊ ጉዳት አድርሷል፡፡ ድርጊቱም በተጎጂዎች እና በማህበረሰብ ስነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ጠባሳ ያኖረ፤ ቅርሻቱ ለመጠገን ረዠም ጊዜ የሚጠይቅና በትውልድ ላይ የስነ ተዋልዶ ጤና ሂደት ያናጋና የራሱ አሳራ ያለው ተግባር ሆኖ ሲዘከር ይኖራል፡፡
- ከጄናሳይዳል ጦር መሃንዲሶች መካከል አንዱ የሆነው ”ዳንኤል ክብረት“፣ “በአስር ከተሞች ላይ አንዳንድ ቦንብ ጣል ጣል በማድረግ ፀጥ ረጭ እናናደርጋቸዋለን” የሚል ያስተላለፈው መሪ ቃል እንደዚሁም በአውሮፓው ልዩ ተወካይ ”ሀቪስቶ” በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲነገር ሰማሁት ያሉትን ቃል “ተጋሩ ለመቶ አመት እናጠፋቸዋለን” ጋር ተደማምሮ ጦርነቱ የትግራይን ህዝብ ለማጥፋት ምን ያህል ዝግጅት እንደነበረው ጠቋሚ ነው፡፡ በወቅቱ በባለስልጣኖችና በልሂቃን ሲረጭ የነበረ ጭፍን የጥላቻ ቅስቀሳዎች መካከል የአገኘሁ ተሻገር “ይህ ህዝብ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው”፣ የዮሃንስ ቧያለው “ለተጋሩ ያለን ጥላቻ በእጅግ ማሳደግ አለብን”፣ የአንዳርጋቸው ፅጌ “አረመኔያዊ በሆነ መንገድ እንጨፍጭፋቸው”፣ የቄሱ “እነሱ ከሚገዙን ሰይጣን ይግዛን”፣ የወርቁ አይተነው “እንደፍየል ጠብሰን እንብላቸው”፣ የሃይሌ ገብረስላሴ “ከአምስት ጥይት አንድ አላጣም”፣ የደበበ እሸቱ “በልተን እንቀደስ”፣ የመሳይ መኮንን ”ዘጠና አምስት ለአምስት“ ወዘተ… ጦርነቱን ጥልቅ መሰረት እንዲኖረው ከማስቻሉም በላይ በነኚህ ንግግሮች የተበረታታው ሰራዊት ምድሪቱ የደም ምድር አደረጋት፡፡ በዚህ ጦርነትም ያለምንም የህግ አግባብ ከአንድ ሚልዮን በላይ ሰላማዊ ሰው በአሰቃቂነቱ ወደር የሌለው የጅምላ ግድያ፣ ስወራ፣ እስር፣ ድብደባ እና የዘር ማጽዳት ነው እየተባለም እርጉዞች በሳንጃ መግደል የመሳሰሉ ጨካኝ ተግባራት እንደ ህዝብ በተጋሩ ላይ ተፈጽሟል፡፡ በቁጥጥር ስር የዋሉ የሀገር መከላከያ አባላት ተጋሩ ስለሆኑ ብቻ በጅምላ ተገድለዋል፡፡ ይህ ያለ ልዩነት የጠፋው የህዝብ መጠን የ2007ቱ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ የህዝብና ቤቶች የቆጠራ ሪፖርት ወስደን ለማነፃፀር ብንሞክር በሃገሪቱ ካሉት አራት ዋና ዋና ከተሞች ማለትም ናዝሬት፣ አዋሳ፣ ባህርዳርና ደሴ በ2016 እ.ኤ.አ የህዝብ እድገት ትንበያ/ፕሮጀክሽን መሰረት የነበራቸው የነዋሪ ህዝብ ብዛት አንድ ላይ ያክላል ማለት ነው፡፡
- ጥቅምት 24/2012 በትግራይ የተከፈተው ክልል አቀፍ ጦርነት ከመደረጉ በፊት አብይ አህመድ አሊ ደርግ ሲከተል የነበረው የከበባ ስትራቴጂ አስመልክቶ በቴሌቪዠን ባደረገው ቃለ ምልልስ ደርግ “በከቦ ማስራብ” የሰራው ሰህተት በእኔ ጊዜ “እንደማይደግም” ሲል ተደምጦ ነበር፡፡ የሱ እቅድ “ጦርነቱን በድል እስኪወጣ ድረስ ክልላዊ ወሰኑ ሙሉ በሙሉ ከበባ በማድረግ የሰውን እንቅስቃሴ መገደብ፣ ምግብና መድሃኒት ለህዝቡ እንዳይደርስ ማድረግ” እንደሆነ በተግባር አረጋግጣል፡፡ ከበባውም ትግራይን በሚያዋስኑ ሁሉንም የኢትዮጵያ ግዛቶችና በኤርትራ በኩል ያለውን ረዥሙን ድንበር ከበባ በማድረግ ህዝብን በምግብ ማስራብና መግደል እንደ “አንድ የጦር መሳሪያ” ስልት ተፈፃሚ ሆኗል፡፡ እዚህ ላይ የኤርትራን ሙሉ በሙሉ በከበባው መሳተፍ የሚያሳየው ኤርትራ ከቅድመ ጦርነቱ ጀምራ በእቅድ ዝግጅት ተሳታፊ እንደነበረች ያረጋግጣል ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ በዚህ ከበባ የሆነውም ምግብና መድሃኒት በመከልከል በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ማርገፍ ሆነ፡፡
- አንዳንድ በስካር መሃል ላይ የተደረጉ ንግግሮች መጥቀስ ቀድሞውንም ዝግጅቱ “ሁሉን አቀፍ ውድመት ማድረስ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረ እንደሆነ አመላካች አድርገን መውሰድ እንደምንችል እረዳለሁ፡፡ የ “አብይ አህመድ አሊ”፣ “ስንገባ የስበት ማእከል የነበረችው መቀሌ ስንወጣ እንደ በሻሻ ሆናለች” ፣ የ “አበባው ታደሰ”፣ “ፋብሪካዎች እና መሰረተ ልማቶች በሙሉ አውደመናቸዋል” ንግግሮች ያደረሰው ውድመት ሆን ተብሎና በተቀነባበረ ስልት የተካሄደ መሆኑ አሳባቂ ያደርገዋል፡፡ ከህዝብ በተሰበሰበ ግብር፤ እርዳታና ብድር ከተገነቡት በክልሉ ከሚገኙ የጤና ተቋሞች መካከል ከ80 በመቶ በላይ፣ አብዛኛው ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች፣ የግለሰብ (መኖሪያ ቤቶች፤ የእርሻ መሳሪያዎች፤ ቋሚ ንብረቶች፤ ፋብሪካዎች)፣ የህዝብና የመንግስት ተቋሞች፣ በአጠቃላይ በቁሳዊ፣ በባህላዊና የተፈጥሮ ሃብቶች ላይ በርካታ የጀትና የድሮን ምልልስ በማድረግ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡ እነኚህ መሰረተ ልማቶች እና አጠቃላይ የክልሉ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ መልሶ ለመገንባትና ወደ ነበረበት ለመመለስ ከሰላሳ እስከ ሃምሳ አመታት እና ሰፊ መዋእለ ንዋይ እንደሚጠይቅ በተለያየ ጊዜ የቀረቡ የመንግስት እና አለምአቀፍ ድርጅቶች ሪፖርቶች መርዶ አርድተውናል፡፡
- “ትግራዋይ ከምእራብ እና ደቡብ ትግራይ መንቀል” የሚል አባዜ ያናወዘው ሃይል ባስነሳው አምባጓሮ የመከላከያ፣ የአማራ ታጣቂዎችና የኤርትራ ሰራዊት ባደረገው የተዋደደ ስምሪት በመታገዝ ህገ መንግስቱ በሚፃረር መልኩ ለዘበናት ሲኖርበት ከነበረው መሬት ሙሉ በሙለ የማጽዳት ስራ ተሰርቷል፡፡ በአሁኑ ሰአት ከ 2 ነጥብ 5 ሚልዮን ተፈናቃይ በጎረቤት አገርና በሌሎቹ የትግራይ ቦታዎች ተበትኖ የመከራ ፍዳውን እየኖረ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ወደቀየው ተመልሶ ሰላማዊ ህይወቱን የሚመራበት ሁኔታ የሚያመቻች ምንም እንቅስቃሴ አይታይም፡፡
- ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የሲቪል እና ወታደራዊ ስራ ላይ ተሰማርተው ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ ትግራዋይ በመሆናቸው ብቻ ከሥራ ተባርረው ከነመላ ቤተሳባቸው ለችግር እንዲዳረጉ ሆኗል፡፡ ፓስፖርት እየታዬ በረራ እንዳያደርግ የእንቅስቃሴ ገደብ ተደርጎበታል፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ከተሞችም በየመንገዱ ሲዘዋወር የተገኘ ትግራዋይ መታወቂያው እየታዬ ስብእና በሚያዋርድ ሁናቴ በእስር ቤት እንዲታጎር ሆኗል፤ ተንገላትቷል፡፡ በየሰፈሩም “ጁንታ” እየተባለ እንዲሸማቀቅ፤ ከማህበራዊ አገልግሎት መስጫ እና ማህበረሰብ ምስርት ተቋሞች ራሱን እንዲያገል የተቀናጀ ስራ ተሰርቷል፡፡
እንግዲህ በትግራይ በተደረገው ወረራ ባስከተለው ዳፋ ሁኔታው መሻሻል ሳያሳይ ጊዜው እየቆጠረ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህልም ክልሉ በርካታ መሬቶቹ አሁንም በጉልበተኞችና በተጋባዥ የውጭ መንግስት ወታደሮች በነጠቃ፣ ግድያና ሰቀቀን ያጠላበት ክልል መሆኑ፣ በርካታ ህዝብ በረሃብና በመድሃኒት እጦት የሚሰቃይበት ወቅት ላይ እየተስተዋለ ያለ መሆኑ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች በቅጡ ያልተጀመረበት፣ በትምህርት ገበታ ላይ መኖር የነበረባቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ የወደፊትዋ ትግራይ ገንቢዎች ከትምህርተ ገበታ ውጭ የተደረገበት፣ አጥፊው ምንም ፀፀት በማያሳይበት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂዎች ለፍትህ እንዳይቀርቡ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ሥራ እየተደረገ ያለበት ወቅት፣ በተለይም የ “አብይ አህመድ አሊ” ገፅታ መልሶ ለመገንባት በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ አመካኝነት አለምአቀፍ ባለሙያዎች ተመልምለው ስራ ለመጀመር በዝግጅት በሚገኙበት ወቅት ላይ ያለን መሆኑ መረዳት በጣም ጠቃሚና ለወደፊት ምን መንገድ መከተል እንደሚገባ የሚያስታውስ ሆኖ ይሰማኛል፡፡
መቸስ “ጉድ ሳይሰማ መስከረም ኣይጠባም” እንዲሉ በዛች ምድርና ህዝብ የፈሰሰው ደምና የደረሰውን መአትና መከራ ምንም አንዳልተደረገ በመቁጠር “አብይ አህመድ አሊ” ወደ መቀሌ ሊያቀና ነው ተብሎ እየተነገረ ይገኛል ፡፡ ይህ እብደት በህዝብ ላይ ቀልድ ከመሆን በላይ በቁስል ላይ እንጨት መስደድ ነው ፡፡ ለነገሩ እስካሁን ካየሁት የ“አብይ አህመድ አሊ” ወጥነት የሌለው ሰብእና ተነስቼ ይህ የማድረግ ፍላጎት ከቶውንም አይኖረውም ብዬ መከራከር አልፈልግም፡፡ ካደረገም የሚያደርግበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ ለዚሁም ሦስት ገፊ ምክንያቶች ማቅረብ ይቻላል፡፡ 1) ትግራይ ህዝብ ላይ ላደረሰው በደልና መከራ ከልብ ተፀፅቶ ሳይሆን የሰላም ሰው ነኝ ብሎ ለቀሪው ኣለም የማስመሰያ ድራማ ለመስራት፣ 2) በአለም አቀፍ እየደረሰበት ያለው የሰብአዊነትና የጦር ወንጀለኛነት ተደጋጋሚ የ“ይጣራ” ጫናና ግፊት ለማለዘብ እንደዚሁም 3) የደረሰበት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ክስረት ለማስቀየስ የተዘየደ መላ ነው ባይ ነኝ፡፡ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲል ኣለም ያወቀው በደልና ግፍ በገለልተኛ አካሎች እንዳይጣራ ከሰማይ በታች አቅሙ የፈቅደውን ሁሉ የሰራ ግለሰብና መንግስት አሁን ደርሶ የሰላም ሰው መመሰል አይናችሁ ጨፍኑና ላሞኛችሁ ከሚል የደፋሮች ደፋር ከሚቀርብ ጥያቄ ውጭ ምንም ሊሆን አይችልም (በተባበሩት መንግስታት የተቋቋመው የኤክስፐርቶች ኮሚቴ ስራውን እንዳይሰራ፣ በጀት እንዳይመደብለት፤ የቆይታ ጊዜ እንዳይታደስለት ወዘተ… የተሰራው ሰፊ ስራ ልብ ይሏል)፡፡ “አቢይ” ምን ያስብ ምን እሱ እንደሚለው “ሾርት ሜሞርያም” ሳይሆን ትግራይ የደረሰባት ዘርፈ ብዙ በደልና መከራ ትረሳዋለች ብዬም ራሴን ማጃጃል አልፈልግም፡፡ ይልቁንስ ይህ ታሪካዊ ክስተት ትግራይና ትግራዋይ እስካሉ ድረስ ለዘለአለም ሲታወስ ይኖራል፡፡
በአሁኑ ሰአት በውጪም በውስጥም የሚገኝ ትግራዋይ ከምንጊዜውም በበለጠ የሚጠበቅበት ቁልፍ ስራ በፕሪቶርያው ስምምነት ላይ የተጠቀሰውን “ፍትህ ማስፈን” ጉዳይ ያለምንም መሸራረፍ ተፈፃሚ እንዲሆን መታገል ነው፡፡ በዚህ በተሳከረ ዓለም የምንፈልገው ፍትህ በቀላሉና በቅርብ ጊዜ አውን ሆኖ ላናይ እንችል ይሆናል፡፡ መሰል በደልና መከራ የደረሰባቸው ህዝቦች ለፍትህ ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ይህንኑ መራር ሃቅ ነው የሚነግረን፡፡ ለምሳሌም ከጄኖሳይድ የተረፉት “እስራኤላዊያን” ድምፃቸው በመሰማቱ እርካታቸውን ለኣለም የገለፁት ቀንደኛው የጄኖሳይድ ወንጀለኛ “አዶልፍ ኤክማን” የተባለ ጀርመናዊ ስሙን ቀይሮ በድብቅ ይኖርበት ከነበረው አርጀንቲና ከአስራ አምስት አመታት ብርቱ ልፋት በኋላ ተይዞ ሜይ 11/1960 በእየሩሳሌም ከተማ ፍርድ በተሰጠበት ቀን ላይ ነበር፡፡
በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ተሳታፊዎች ብዛት በርካታ መሆንና በተለያየ የተሳትፎ ደረጃ የሚገለፅ ስለሆነ የፍትህ አሰጣጥ ሂደት ውስብስብ ሊያደርገው እንደሚችል ይገመታል፡፡ እንደዚህ አይነት ውስብስብና ከፍተኛ የወንጀል ተግባር በሀገር ውስጥ የ “ሽግግር ፍትህ ስርአት” በማኖር ብቻ የሚፈታ አይሆንም፣ ምክንያቱም የውጭ ተዋንያን/በደለኞች ተጠያቂነት በሀገር ውስጥ የህግ ማእቀፍ ሊሸፈን የማይቻል ይሆናል፡፡ አሁናዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁናቴም የሀገር ውስጥ የ “ሽግግር ፍትህ ስርአት” በማኖር ፍትህ መጠበቅ ቀማኛም ዳኛም እንዲሉ ነውረኛው ከፍትህ እንዲያመልጥ መንገድ የሚጠርግ ነውና ጭራሽኑ ባይጀመር ይመረጣል፡፡ ስለሆነም በነኚህ ሃይሎች በአጠቃላይም በደረሰው ጥፋት ልክ ፍትህ እንዲመጣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑ በመረዳት የተቀናጀ የጋራ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እናም እናቶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አረጋዊያን በአጠቃላይ ትግራዋይ ከሌሎች ፍትህ ወዳድ ህዝቦች ጋር በመሆን በትግራይ ህዝብ ጄኖሳይድ ያወጁበት እና በጄኖሳይዱ በቀጥታ የተሳተፉት ሁሉ ለፍርድ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት አግኝተው እንደእስራኤላውያን እርካታ የሚያገኝበት ጊዜ ለማየት በፅናት መቆምና ያለእረፍት መስራት ይጠይቃል፡፡ ትግሉ በበለጠ ተጠናክሮ፣ መቀዛቀዝ በሚታይበት ወቅትም ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን በማጥበቅ መታገል፤ መታገል አሁንም መታገል ይገባል እላለሁ፡፡
ቸር እንሰንብት