Tue. Sep 27th, 2022

በአሌክስ ደዋል
27 ነሐሴ 2014 ዓ.ም.
(The Baffler በሚባል መጽሄት እ.ኤ.አ. September 2, 2022 የታተመ)

በዓለም እንዲህ እንደ ኤርትራው ፅድት ያለ አምባገነንነት ያለው አገር የለም፡፡ ሃገረኤርትራ ማለት አንድ ሰው ነች፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ፡፡ ከኢትዮጵያ ነጻ የመውጣት ጦርነቱ በ1983 ዓ.ም የተሣካለት ጠንካራ የሚባል የአማጽያን ሠራዊት ለሃያ ዓመታት ያህል የመሩ፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህም ያላንዳች የሥልጣን ልጓም ፕረዚደንት ሆነው እየመሩ ያሉ ናቸው፡፡ እንግዲህ ነጻነት ካገኘች ከሠላሳ ዓመታት በኋላ፡ በኤርትራ ሕገ-መንግሥት የለም፡፡ ምርጫ ባዕድ፡ ሕግ አውጪ ተቋምም ዘበት ነው:: በውል የሚታወቅ ብሄራዊ በጀት እሚባልም ፈጽሞ የለም፡፡ የፍትህ ተቋሙ ከሰውየው እጅ ውልፍት አይልም፣ ሜዲያ የሚባል ነገር የለም፡፡ በሥራ ላይ አሉ የሚባሉት ጦሩ እና የደህንነት ተቋሙ ብቻ ናቸው፡፡ የግዴታና በጊዜ ያልተገደበ ብሔራዊ አገልግሎት የሚባል አለ፡፡ በመሠረቱ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት፡ የጦሩ ጀኔራሎች፣ የፕረዚደንቱ አማካሪዎች፣ እና ዲፕሎማቶች አንዳቸውም ሣይቀየሩ፡ እንዳሉ ነው ያሉት፡፡ ከዚህች 3.5 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር፡ ከግማሽ ሚሊዮኑ በላይ ተሠዷል፡፡ ይህ ከፍተኛ ጥምርታ በዓለም ደረጃ ከሶሪያ እና ከዩክሬይን ቀጥሎ የሚሠለፍ ነው፡፡

ዋናው ጉዳያቸው ሥልጣን ብቻ በመሆኑ ነው ፕረዚደንት ኢሳያስ፡ (ቀድሞዉኑ) ይህን ቦታቸውን ያገኙትና አምርረውም የያዙት፡፡ አገሪቱ እንዲህ ግልብ ግለሰብን የማምለክ፣ ለመሪ ባደባባይ ማጐብደድ ብሎ ነገር የላትም፡፡ ኢሳያስ ግና፡ ልብ ያልተባሉ ምሥጢረኛ፣ ያልተነቃባቸው የጭካኔ ማዕከል ናቸው፡፡ አምባገነኖች መልኮቻቸውን በሚቀያይሩበትና አዳዲስ ዘዴዎችን አበጥረው በሚያስተናግዱበት በዚህ ዘመን፡ እርሳቸው እንደሁ ያረጀ-ያፈጀውን ፍፁማዊ አምገነንነት መንፈስ ይሁነኝ ብለው እንደገፉበት ነው፡፡ ለመለወጥ ስንኳ ማስመሰል አልቻሉበትም፡፡ አዳዲስ የውጭ መሪዎች እና ዲፕሎማቶች እንዳመጣጣቸው በመርሣት አዙሪት እንደሚሠጥሙ፡ ወይንም በማባበል ቁማር እንደሚዋኙ፡ ወይንም እስከናካቴው ሰለ ሠብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲ ግድ አይኖራቸውም ብለው በማለም ሁነኛ ተቃዋሚዎቻቸውን ጸጥ-ለጥ አርገዋቸዋል፡፡

የኢሳያስ አምባገነንነት የወዲህኛው ሙከራ በኢትዮጵያ መንግስትና ትግራይ ክልል ባሉ ተቀዋሚዎቹ መካከል ጦርነት መጫር፡ እናም ሁለቱም ተዳክመው ማየት ነው፡፡ በተለይም ትግራይ እጅጉን ተዳክማ፡ እንደ አንድ የፖለቲካ አካል ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት ነው ግቡ፡፡

የኢሳያስ አመክንዮ የዘር ማጥፋት ነው፡፡ በዚያ ዓለም ትኩረቱን በአሜሪካ ምርጫ ባደረገበት የጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም፡ ኢሳያስ ትግራዬቹን “ለመደምሠሥ” በተቀሰቀሰው ጦርነት ውሥጥ ሠራዊታቸው ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኃይሎች ጋር እንዲቀላቀሉ ላኩ፡፡ አብይም ስለ ኤርትራ ሚና በመዋሸት የፖለቲካ ሽፋን ሰጧቸው፡፡ ከአንድ ዓመት በትግራይ የጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እና ረሃብ ማንገሥ እንዲሁም በተቀረው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሥፋት ጥፋት ካዛመቱ

በኋላ የትግራዩ ጦርነት ጋብ አለ፡፡ ይህም በዚህ ወር መጨረሻ በትግራይ ኃይሎችና በኢትዮጵያ ጦር መካከል በተካሄደው ከባድ ውጊያ ተተካ፡፡ የመጀመሪያው ዙር በትግራይ ኃይሎች አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡

ሁለተኛው ዙር ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን በጠዋቱ ነው የተጀመረው፡፡ የኢትዮጵያ ምልምሎች ወደ ውጊያው ለመቀላቀል የኢሳያስን ምልክት እየተጠባበቁ ሳለ የኤርትራ መድፈኞች በትግራይ መከላከያ ይዞታዎች ላይ በሥፋት መተኮሱን ተያያዙት፡፡

ኤርትራ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ በተካሄደው አፍሪካን የመቀራመት ሂደት ዘመን ከፊውዳል የኢትዮጵያ ኢምፓየር የሰሜኑ ጫፍ የተቆረሰች የጣሊያን ቅኝ ግዛት ነበረች፡፡ አሳያስ፡ ጣሊያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተሸነፈች በአምስት ዓመቷ በ1938 ዓ.ም. ነው የተወለዱት፡፡ የርሳቸው ትውልድ ኤርትራዉያን: ከቀድሞ ገዢያቸው ጋር ፍቅር-ጥላቻ የሚፈራረቁበት ባለ መንታ-ጫፍ ግኑኝነት ነው ያላቸው፡፡ ጣሊያኖች ኤርትራውያንን አንደ ቀን ሠራተኛ በዝብዘዋቸዋል፤ ትምህርትም ነፍገዋቸዋል፡፡ ነገር ግን ቅኝ ገዢዋ ኤርትራን ልዩ አደረገቻት፡፡ የጣሊያን ቀዳሚ ፍላጐት ያኔ እንዳሁኑ ሁነኛ ስትራተጂካዊ አካባቢ በነበረው የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ያነጣጠረ ነበረ፡፡ ልክ እንዳሁኑ፡ የስዊዝ ካናል በ1861 ዓ.ም. ሲከፈት 1/8ኛው የዓለም የባህር ንግድ

በዚህ በኤርትራ እና በየመን ባለው ሠርጥ ነበር የሚያልፈው፡፡ በዚህም ምክንያት፡ አለሁ የሚል ኃያል አገር በቀይ ባህር መገኘት ይፈልጋል፡፡ የቻይና የመጀመሪያው የባህር-ማዶ ይዞታ ከጎረቤት ጂቡቲ ነው ያለው፡፡ ራሺያም የባህር ኃይል ቦታ ለማግኘት ከኤርትራ ጋር እየተደራደረች ነው፡፡

ቤኑቶ ሙሶሊኒ ኤርትራን ማዕከል ያደረገ፡ ሊቢያ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያን ያካተተ በአፍሪካ የሮማዊ ኢምፓየር የመገንባት ህልም ነበረው፡፡ ቅኝ ግዛቷም ከጆሃንስበርግ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛዋ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ሆነች፡፡ የሥነ-ኅንጻ ታሪክ ተመራማሪዎችም የአርት ዴኮ (ከ1925-1940 መካከል የታነፁ ድንቅ ግንቦች/ቤቶች) ማሣያ ነች በምትባለው አስመራ እጅጉን እንደተመሠጡ ነው፡፡ በተለይ በአውሮፕላን ቅርጽ የተሠራው የፊያት ታሊየሮ ነዳጅ ማደያ- እንደሚባለውም ኢሳያስን ጨምሮ- በዚያ ዘመን ሥነ-ኅንጻ ፍቅር በተለከፉት አድናቂዎች ዘንድ የተከበረ ነው፡፡ ተከታታይ ጦርነቶች ከተማይቱ ሳትጐዳድልና ሳትለማ፡ የዘመናዊነት ቤተመዘክር ሆና እንድትቀር አድርገዋታል፡፡ በ1987 ዓ. ም. ገደማ አንድ ትልቅና አስቀያሚ ህንጻ ካጠገቡ ተገንብቶ የዚህ ድህረ-ዘመናዊ የፊያት ማደያውን ሲሻማው ጊዜ፡ ፕረዚደንቱ ጣልቃ ገብተው መኃል አስመራ የራሷን መልክ ይዛ እንድትቀጥል እንዳደረጉ ነው የሚነገረው፡፡ ይህም የፋሺሽት ዓርማ ከሚታይባቸው ጥቂት የከተማይቱ ህንጻዎች አንዱ ያደርገዋል፡፡

በአጋር አገሮች በ1933 ዓ.ም “መጀመሪያ ነጻ የወጣው” አዲሱ የሙሶሊኒ ሮማዊ ኢምፓየር ነው፡፡ ተከትሎ የመጣው የእንግሊዝ ወታደራዊ አስተዳደርም በካሣ ሥም አብዛኞቹን የኤርትራ ኢንዱሰትሪዎች ነቃቅሎ በመውሰድ የግዛቲቱን ዕጣ በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት እንዲወሰን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ድርጅቱም ኤርትራ “በኢትዮጵያ ዘውድ በፌዴሬሽን” እንድትተዳደር የሚለውን ሥስና አሻሚ መፍትሄ አቀረበ፡፡ ግዛቲቱን በማራቆት፡ ነገር ግን የፓርላማ ሥርዓትና ጋዜጦች በማስተዋወቅ የሚዘከሩት እንግሊዞችም በ1944 ዓ.ም ለቀው ሄዱ፡፡ የፌዴራል አደረጃጀቱ፡ ንጉሡ በገደብ እንዲገዙ የሚደነግግ ቢሆንም ከአሥር ዓመታት የግዴታ ውህደት በኋላ ራሱን የቻለው የኤርትራው ፓርላማ እንዲወገድ ተደረገ፡፡ አነሥ ያለ ዓመጽም ተቀሠቀሰ፡፡ የመጀመሪያ የጥይት ድምጾችም በመስከረም 1953 ዓ.ም ተሠሙ፡፡ ወዲያውኑ ከዓመት በፊት በካይሮ የተቋቋመው የተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ (ጀብሃ)፡ ነፃነትን ብቸኛ ግቡ በማድረግ የሽምቅ ውጊያ ጀመረ፡፡

ኢሳያስ በሱዳን አቋርጦ ጀብሃን ሲቀላቀል አዲስ አበባ በነበረው (የቀ,ኃ.ሥ.) ዩኒቨርሲቲ የሣይንስ ተማሪ ነበር፡፡ ዓማጺያኑ በብዛት ድጋፍ የሚደረግላቸው በዓረብ አገሮች ስለነበረ ዓረብኛን መማር አጥብቆ ተያያዘው፡፡ በ1959 ዓ.ም. ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ቻይና ሄደ፡፡ ወደ በርሃ ሲመለስም፡ ጀብሃ አብዮታዊ አስተሳሰቦቹን በተግባር በማዋል ረገድ በሚያሣየው መዋዠቅና ደጀን መሬት ማጠናከር የሚለው የማኦ አስተምህሮ (ማንኛውም ኤርትራዊ ብሄረተኛ ሊቀላቀል እንደሚችል፣ ሊኖሩ የሚችሉ የአስተሣሰብ ልዩነቶች የሚፈቱትም የተለያየ የፖለቲካ ዝንባሌ ያላቸው ሠዎችን በተለያዩ ክፍሎች በመመደብና ወይንም የማይቋጩ ሥብሰባዎችን ማካሄድ) መከተል ባለመቻሉ ደስተኛ አልነበረም፡፡ አብሮት ቻይና ከተማረው የግራ ፖለቲካ አቀንቃኙ ሮሞዳን መሃመድኑር ጋር በመሆንም በ1962 ዓ.ም. ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ህግሓኤ፡ ወይም ህዝባዊ ግንባር፡ ወይም ሻዕቢያ) መሠረተ፡፡ ብሄረተኛም፤ አብዮታዊም ነበር፡፡

ዓፄያዊ ይሁኑ ኮሙኒስት፡ ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት በኤርትራ ያካሄዷቸው ጦርነቶች በመጠናቸውም ሆነ በማያቋርጥ ጭካኔያቸው ወደር አልነበራቸውም፡፡ በዓመት አንዴም ሆነ ሁለቴ ሠፊ የምድር ጥቃት ያካሂዱ ነበር፡፡ የንጉሡ ኃይሎች መንደሮችን ያቃጥሉ፣ የተጠረጠሩ ብሄረተኞችንም ለእሥራትና ለግርፊያ ይዳርጉ ነበር፡፡ ኃይለሥላሴ በ1966 ዓ.ም. አብዮት ከሥልጣን ሲወገዱ የወታደራዊ ሁንታው መሪ መንግሥቱ ኃይለማርም ወደ ሶቪየት ዕቅፍ ተቀላቀለ፡፡ ሶቪየት ህብረትም የጦር መሣሪያ ድጋፍና የኦፊሰሮች ሥልጠና ትሠጥ ገባች፡፡ በየጊዜውም የህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ይዞታዎችን በመድፍ በመደብደብ ላልተሣካ ተከታታይ የበርካታ የእግረኛ ሠራዊት ማዕበል ክፍት ያደርጉ ነበር፡፡ በየቀኑ፡ በጠራራ ፀሃይ የዓየር ድብደባ ማካሄድ ማለት ደግሞ ቁሳቁስና አቅርቦቶችን ከማመላለሥ ጀምሮ እስከ ምግብ ማብሠልና ልብሥ ማጠብ ሁሉም የህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) እንቅስቃሴዎች በውድቅት ሌሊት ሆኑ ማለት ነው፡፡ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ፡ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎችም ዓማጺያኑ ከተሸሸጉበት ብቅ ሲሉ፡ ሥም-ዓልባ ኮረብታዎች በቅጽበት እልም ወዳለ እንቅስቃሴ ይቀየራሉ፡፡

እኩልነትና ለዲሲፕሊን መገዛት የ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) መርሆዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ያልተቋረጠ ጥቃት ውሥጥ መትረፍ የመቻሉ ሚሥጥርም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ እና ዘጠኙም ብሄሮች እኩል እንደሆኑ መሪዎቹ በተደጋጋሚ፡ አበክረው የሚናገሩት ነው፡፡ አብዮታዊ አጃንዳቸውን እስከ ጦርነቱ ፍጻሜ ይቆይ ሣይሉ “በነጻው መሬት”፡ የመሬት ሥሪቱን፣ የሴቶች ነጻነት ሲያውጁ ለታጋዮችና ለሲቪሉ ማህበረሰብ የሚያገለግሉ ት/ቤቶችና ሆስፒታሎችን አቋቁመዋል፡፡ በሃያ ዓመት

የትጥቅ ትግልም ለተወሰኑ ተግባራት የሚሆኑ የአዛዦች ምደባ ውጭ ምንም ዓይነት መደበኛ የሥልጣን ዕርከን አልነበረም፡፡ ከነጻነት በኋላ ለተሠው ታጋዮች መታሠቢያ ሲያቆም ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) የመረጠው ኮንጎ ጫማ (የፕላስቲክ ጫማ) ነበር፡፡ ይህ የየቀን የዓየር ድብደባ ለማምለጥ ከተራራ፡ ከመሬት በታች ተቆፍሮ በተሠራው ፋብሪካ የሚመረቱት የፕላስቲክ ጫማዎች የሁሉም ታጋዮች መለያ ነበሩ፡፡

ኢሳያስ በውጭው ዓለም የፈጠሩትም ይህንን ያንድ ቆራጥ አብዮታዊና ከሁሉም ጓዶቹ በተለየ ነጥሮ የወጣ ምሥላቸው ነበር፡፡ ብዘውን ጊዜ ያልተነገረው ግን በአወቃቀርም ሆነ በዲሲፕሊን የህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ሌኒኒስትነት ነው፡፡ አንዴ ከጸደቁ በኋላ የማዕከላዊ ኮሚቴው ውሣኔዎች ካለምንም ጥያቄ ይተገበራሉ፡፡ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ከመግደል ወደኋላ የሚል ድርጅትም አልነበረም፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሠላዮች ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ጥርጣሬ ብቻ በርካታ የህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) አባላት ተረሽነዋል፡፡ በነዚህ የማስወገድ እንቅስቃሴዎችም በርካታ ኤርትራውያን “መሠዋዕት” ሆነዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩም ከጀብሃ ጋር በተደረገው አሠቃቂው የእርስበርስ ጦርነት አልቀዋል፡፡ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ከተመሠረተ በኋላ በአንድ የመጀመሪየው አጋጣሚ ኢሳያስን ለመፈታተን በመድፈራቸው ምክንያት እጅግ የተማሩ ታጋዮች እንዲወገዱ ተደርገዋል፡፡ በሌሊት ነው የሚያሴሩት ተብለው በመንካዕወይንም የሌሊት ወፍየሚታወቁት፡፡ የተሠጣቸው ሥምም ስለ ገዳዮቹም ሆነ ስለ ተጎጂዎቹ የሚገልጸው ነገር አለ፡፡ (ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ የኢሳያስ ባልንጀራ የነበረው ሙሴ ተስፋሚካኤል ከነሱ አንዱ ነበር፡፡) ቢያንስ በመንካዖቹ ላይ የሆነ ምርመራ፡ በዕጣቸውም ላይ ሠፋ ያለ ክርክር የተካሄደበት ነበር፡፡ በብዛት በጣም የተማሩ የነበሩበት፡ ቀጥለው ኢሳያስን የተጋፈጡት የሚን (በአረብኛ “ቀኞች”) ተብሎ የተሠየመው ቡድን አባላት ግን ካለምንም ደብዛ ነው እንዲጠፉ የተደረጉት፡፡ ይህ ምህረት የለሽ ተቃዉሞን የማጥፋት ዘዴ የበርካታ አብዮታዊ እንቅስቃሴዎች የመጀመሪያው ኃጢያት፡ ከቶውኑ ሊፋቅ የማይቻለው ጥቁር ነጥብ ነው፡፡

በመጨረሻም፡ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) የሚገርም ዉጤታማ ወታደራዊ ተቋም በመሆኑ ምክንያት ያፈነግጣሉ ተብለው የሚገመቱ ሁሉ ልክ ገቡ፡፡ የ”ሽምቅ ተዋጊ” ነው ማለት የሚገልፀው አይመስለኝም፡፡ በየተራራው ምሽጐች የሚገኙትን የደጀን ቦታዎችን የሚከላከልና ትላልቅ ብረት ለበስ ውጊያዎችን የሚያካሂድ መደበኛ ሠራዊት ነው የሆነው፡፡ በኢትዮጵያ ተዋጊ ጄቶች የየዕለት ድብደባ የፈራረሰችው ግና ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) አሳልፎ ያልሠጣት ከቀይ ባሕር ግድም በኮረብታማ በርሃ የምትገኘው የናቅፋ ከተማም የአይበገሬነታቸው ምልክት ሆነች፡፡ (የአገሪቱ የድህረ-ነፃነት ገንዘብ ናቅፋ ነው የሚባለው)፡፡ ከዓመታት ዕልህ አስጨራሽ ጦርነት በኋላ፡ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ወታደራዊ ማዕበሉን ቀየረው፡፡ በ1982 ዓ.ም. በምጽዋ ከተማ በተካሄደው ውጊያ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ዘጠና ዘጠኝ ሶቪየት ሠራሽ ታንኮችን ሲማርኩ በሺዎች የሚቆጠሩት ወታደሮችን ገድለዋል፡፡ በ1983 ዓ.ም. ወሳኝ ድል ተጐናጸፉ፤ ከዛም በ99% ድምጽ ነጻነታቸውን አገኙ፡፡

ለኤርትራ ከነጻነት በኋላ የነበሩት ሰባት ዓመታት የተሥፋ ወቅት ነበሩ፡፡ ታጋዬቹ ጉልበታቸውን ወደ መልሶ ግንባታ አዞሩ፡፡ የኤርትራ ዲያስፖራዎች ተመለሱ፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የተመለሡቱ ሞያተኞች በንግድ ሥራ፣ በዩኒቨርሲቲ ማስተማር፣ ከጡረታ ወዲያ የሚሆናቸው ቤት በመሥራት ላይ ተጠመዱ፡፡ ዕርዳታ መግባት ጀመረ፡፡ ኤርትራ የዓለም ቀልብ የገዛችበት ወቅት ነበር፡፡

ሆኖም ግን፡ ገና ከመጀመሪያው፡ ዳዴ የሚለው አምባገነንነት ምልክቶች ይታዩ ነበር፡፡ በጦርነቱ ጊዜ እጅጉን ዉጤታማ የነበረው ምሥጢራዊና የተማከለ የአመራር መዋቅር ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ሲቪል ነኝ ብሎ ሥልጣን ከያዘ በኋላም እንዲሁ አልጠፋም፡፡ ነጻነት ከመታወጁ ከጥቂት ቀናት በፊት ታጋዮች ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት ካለደመወዝ ማገልገል እንዲቀጥሉ የተወሠነባቸውን ተቃውመው ወጡ፡፡ አካል-ጉዳተኛ ታጋዮች የጡረታ መብታቸውን ለማስጠበቅ ወደመናገሻ ከተማዋ አቅጣጫ ሲተሙ መቸም ቢሆን የዛ የተሸከርካሪ ወንበር፣ ሠው-ሰራሽ እግሮች እና ዱላዎች እርግጠኛና የጋራ ግሥጋሴ የሚገልጽ ግሥ ከቶዉኑ አይገኝም፡፡ ጥይት ተተኮሰባቸው፡፡ አንዳንዶቹ ወዲያው ሞቱ፤ ሌሎቹ ታሠሩ፣ ተሠወሩ፡፡ በ1986 ዓ.ም. በተደረገ (የፖለቲካ) ጉባኤ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ራሱን በማክሠም ህዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲና ለፍትህ (ሀግደፍ) የሚባለውን የሲቪል ፖለቲካ ፓርቲ መሠረተ፡፡ በመድብለ-ፓርቲ ሥርዓት ከሚኖሩት በርካታዎቹ አንዱ ይሆናል ተብሎ ነበር የተገመተው፡፡ በተግባር ግን ህግደፍ ከመንግሥቱ ራሱ የሚለየው ነገር አልነበረም፡፡ የጦር መሣሪያ በድብቅ ለመሸመት ሲባል የተቋቋመው ሥውሩ የህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) የፋይናንስ መረብም መንግሥት በባለቤትነት ወደሚያስተዳድረውና ኋላ በተለያዩ በርካታ ሕገወጥ ሥራዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምርመራ ትኩረት የነበረው የቀይ ባሕር የንግድ ኮርፖሬሽን ወደሚባለው ተቀየረ፡፡

የጥንቱ-የጠዋቱ ታጋዮች አንድ በአንድ ይሸሹ ጀመር፡፡ ሮሞዳን መሐመድኑር ፖለቲካውን እርግፍ አርጐ ተወው፡፡ አንዴ የነጻነቱ ጦርነት ጀግና የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጴጥሮስ ሰሎሞን ወርዶ ሲያበቃ የባህር ሃብቶች ሚኒስትር ሆነ፡፡ በመላው አገሪቱ ከተካሄደው ሠፊ ምክክር በኋላ የተቀረጸው ሕገ-መንግሥት፡ ለሕገ-መንግሥት ጉባኤ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ በብሔራዊ ስታዲዮም በተደረገ ዝግጅት ፕረዚደንቱ ቢረከቡትም ከዚያች ቀን በኋላ ስለ ምርጫ፣ ስለ ገለልተኛ የፍትህ ተቋም ወይንም ስለ የፕሬስ ነጻነት አንዳች ነገር ተወርቶ አያውቅም፡፡ ኢሳያስ እያንዳንዱን ኤርትራዊ በውል በማወቅ፣ ማንንም ባለመርሣትና የያንዳንዱን ሚሥጢር በመፈልፈል ችሎታቸው ይታወቃሉ ይባላል፡፡ የስለላ መረባቸውም ሥውርና ሁሉም ቦታ የሠፈረ ነው፡፡

በግንቦት 1990 ዓ.ም. ኢሳያስ የድንበር ግጭቱን በወቅቱ ወደ በእህት አብዮታዊ ድርጅት– በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲየዊ ግንባር (ኢህአዴግ)— ትተዳደር ከነበረችው ኢትዮጵያ ጋር ወደ ጦርነት አሳደገው፡፡ ኢትዮጵያ፡ የኤርትራዉ መሪ የሚፈሩት ረዥም የጦርነት ልምድ ነበራት፡፡ ባድመ የምትባለውን ትንሽ ከተማ የያዘው የኢሳያስ ድንበር ዘለል ወረራም ያንን የኢትየጵያን ወታደራዊ መንፈስ ነበር የቀሠቀሰው፡፡

እየተካሄደ የነበረው ውጊያ መንታ ባኅርይ– የጓዶች ጦርነት፡ የአጎት ልጆች ግጭትም– ነበረው፡፡ ሁለቱም ወገኖች በደንብ ይተዋወቁ ነበር፡፡ የእህአዴግ ግንባር በ1967 ዓ.ም. በተመሠረተው በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የበላይነት ይመራ ነበር፡፡ በሚቀጥሉት 17 ዓመታትም ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) እና ህወሓት በጋራ፡ በተመሣሣይ ጉድጓዶች መሽገው፡ በማያቋርጥ የመድፍና የዓየር ድብደባ የታጀበ የእግረኛ ማጥቃት የመሣሠሉት የሶቪየት ዘዴዎች የተጠቀመው የመንግሥቱን ሠራዊት መክተዋል ማለት ይቻላል፡፡

በዚያን ወቅት ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) እና ህወሓት በሚገርም አቅል ተከላክለዋል፡፡ ሆኖም ግን በዶክትሪን ሆነ በታክቲክ ዙሪያ ይጣሉ ነበር፡፡ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) በሰሜን ኤርትራ የበርሃው ተራሮች ያለውን የደጀን ቦታ ለመከላከል ምሽጎችን ሲቆፍር፤ ህወሓት ግና በገበሬ መንደሮች ውስጥ በመንቀሣቀስ– ማለትም የመንግሥት ጦር ሲያጠቃ ወደ ኃላ በመዝለቅ፡ በራሳቸዉ ሠዓት ደግሞ አጸፋዊ ማጥቃት በማድረግ– ሁነኛ የሽምቅ ውጊያውን ያካሂድ ነበር፡፡ በፖለቲካ ዶክትሪን ዙሪያም እንዲሁ አይግባቡም ነበር፡፡ ለብዙዎች እንግዳ የነበሩ ክርክሮቻቸውም ጊዜው ካለፈ፡ ከአንድ ትውልድ በኋላ፡ ሲታዩ ከማርክሲት ጽንሰ-ኃሳብ ሊቃውንት ስብሰባዎች የሚመደቡ ይመስሉ ነበር፡፡ ሶቪየት ሕብረት፡ ምንም ዋና የመንግሥቱ ደጋፊ ብትሆንም “ሶሺያል ኢምፔሪያሊስት” ነበረችን? ወይስ፡ ዞሮ ዞሮ ወዳጅ ልትሆን ትችላለችን? በማርክሲስት ፍቺ “ብሄረሰቦች/ብሄሮች” ተብለው የሚታወቁት የተለያዩ የኢትዮጵያ ህዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት ይኖራቸዋልን? የሚሉቱ መከራከሪያዎች ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡

የከፋው መለያየት የመጣው ግን በ1977 ዓ.ም. ታላቁ ድርቅ እጅጉን መቆንጠጥ ሲጀምር፡ ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) ከሱዳን የእህል ዕርዳታ የሚመጣበትን ዋናው መንገድ መዝጋቱን ተከትሎ ነው፡፡ ሆኖም ግን፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ መንግሥቱን ለማሸነፍ ሲሉ ልዩነቶቻቸውን አቻቻሉ፡ ይህም በግንቦት 1983 ዓ.ም. ተሣካላቸው፡፡ ለቀጠሉት ሰባት ዓመታም ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) በአስመራ፡ ህወሓት/ኢህአዴግም በአዲስ አበባ ጥሩ ወዳጆች መስለው ቀጠሉ፡፡ ሆኖም ግን ልዩነቶቻቸው ከግራ ፖለቲካ ቡድናዊ ንትርክ እጅግ የባሱ ነበሩ፡፡

ኢሳያስ ህወሓትን እና መሪዎቹን በንቀት ዓይን ነበረ የሚያዩዋቸው፡፡ እርሳቸውና በርካታ ሌሎች ኤርትራውያን መሪዎች በታሪክ ከትግራይ ጋር ከሚገናኙት ከደጋማው የኤርትራ ክፍል የመጡ ናቸው፡፡ ትግርኛ የሚባለውን አንድ ቋንቋ የሚናገሩ፣ እስከ 1ኛው ዓ.ዓ. የሚዘልቀውን የአክሱም (መንግሥት) ታሪክ የሚጋሩ ሆኖም ግን በተደረገው የቅኝ ግዛት ድንበር የማካለል ሂደት የተለያዩ ናቸው፡፡ ብዙ ኤርትራውያንና ትግራውያን ቤተሰቦች በጋብቻ የተዛመዱ ናቸው፡፡ ኢሳያስ፡ አባቱ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለመግባት የመጀመሪያዎቹ ኤርትራውያን ከሆኑባት ከአስመራ ከተማ ነው ያደጉት፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የባለ መካከለኛ ገቢ አዝማሪኖ (የአስመራ ልጆች) የቤት ሠራተኞች ከሰሜኑ የትግራይ ዳር ክፍል ከዓጋመ የሚመጡ ሲሆን፤ ጐዳና ጠራጊዎች ሆነ በለስ ሻጮች እንደዚሁ ከዚያው (የፈለሱ) ናቸው፡፡ ትግርኛቸው ትንሽ ለየት ያለ ዘዬ አለው፡፡ ለብቻቸው ሲሆኑ፡ መሪዎቹን ጨምሮ የአስመራ ልሂቃን ህወሓትን “ዓጋመ”- ማለትም የቤት ሠራተኞቻቸው ልጆች- ሲሉ ያንቋሹሿቸዋል፡፡ ለነሱ፡ ትግራዉያን በውትድርና እኩያዎቻቸው ሆነው፡ ወይንም የትግራይ ዕድገት የኤርትራን ሊያልፍ ይችላል ብሎ ማሰብ አይቻላቸውም፡፡

ከላዩ ሲታይ የ1990ው ጦርነት የተቀሰቀሰው በባድመ ከተማ ዙሪያ በተነሳው እዚህ ግባ በማይባል የግዛት ክርክር ምክንያት ነው፡፡ ዋናው ግን በአፍሪካ ቀንድ ማን ቁጥር አንድ ይሁን ከሚለው ጥያቄ ላይ ነው፡፡ ኢሳያስ አንደኛ ከመሆን ውጭ የሚያረካቸው

ነገር የለም፡፡ ከጥቂት ሣምንታት አስቀድሞ፡ ፕረዚደንት ክሊንተን የአፍሪካ “አዲስ ዓይነትየሚሏቸውን መሪዎችን ለማግኘት ሲጓዙ (ሌሎቹ ሦስቱ- የዩጋንዳው ዩዌሪ ሙሶቬኒ፣ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ እና መለስ ዜናዊ ነበሩ) ዋይት ሀውስ የመገናኛ ከተማ ብሎ የመረጠው ካምፓላን ነበር፡፡ የዋይት ሃውስ ባልደረቦች ኢሳያስ ጥሪውን ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ተገርመዋል፡፡ በስብሰባው ጐልተው እንደማይታዩ የገባቸው ኢሳያስ የዚህ ሊመሩት የማይቻላቸውን ጥምረት አካል መሆን አልፈለጉም፡፡

ጦርነቱ በተቀሰቀሰ ጥቂት ሣምንታት ጊዜ ውስጥ፡ ከጳውሎስ ተስፋጊዮርጊስ ጋር በመሆን ኢሳያስን ለማግኘት ሄድኩኝ፡፡ ጳውሎስ በትግሉ ወቅት Eritrean Relief Association (የኤርትራ ዕርዳታ ማሕበርን) የመራ፤ ከነጻነት በኋላም፡ Regional Center for Human Rights and Development የተባለውን የአገሪቱ ብቸኛ የሠብዓዊ መብት ድርጅት እስከሚዘጋ ድረስ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ያስተዳደረ ሰው ነው፡፡ ኢሳያስ እያንዳንዷን ግኑኝነት በጥንቃቄ ነው የሚያደራጁት፤ እንግዳ ሲያገኙም (አንድም) ማስታወሻ እሚይዝ ረዳት ሳይኖር- ብቻቸውን ነው፡፡ የባድመው ጦርነት ግን ያናወጣቸው ነው የሚመስለው፡፡ ከቢሮአቸው ስንደርስ ጥበቃዎቹ በአለባበስም፡ በባኅርይም የተለየ ነገር አይታይባቸውም፡፡ ፍተሻው እስከዚህም ነበር፡፡ የወታደር ልብስ ያደረገችው እንግዳ ተቀባይዋ ወደ ደረጃው አመላከተችን፡፡ እንደ ትግሉ ጊዜ የጓዳዊነት ድባብ ያለ ቢመስልም የያንዳንዱ እንግዳ እንቅስቃሴ በሆነ (የሠላዮች) ክትትል ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡

የፕረዚደንቱ ቢሮ ሠፋፊ ኮሪደሮች፣ ከፍ ያሉ ጣሪያዎች ካሉት በቅድመ ዓየር ማቀዝቀዣ ዘመን በሜዲትራኒያን አርኪቴክቶች የሚመረጥ ልብ የማትለው የጣሊያን ጊዜ ሕንፃ ነበር፡፡ የራሳቸው የኢሳያስ ቢሮም፡ ሠፊ፣ ቀለል እና ጨለምለም ያለ ነው፡፡ መጋረጃዎች ሣብ ስለተደረጉም አንዲት ቀጭን ብርሃን በተገኘው ቀዳዳ ሾልካ ከቡና ጠረጴዛው ላይ ተዘርግፋለች፡፡ ኢሳያስ ራሳቸው ከአንድ ግዙፍ ጠረጴዛ ጀርባ ራሳቸውን በእጃቸው አቅፈው ተቀምጠዋል፡፡ እንድንቀመጥ ለማመላከት ብቻ ነበር ቀና ያሉት፡፡ ካኪ የመሥክ ልብስ ለብሰው፡ ኮንጎ ጫማ ተጫምተው ነበር፡፡

ተቀመጥን፡፡ መጠበቁንም ተያያዝነው፡፡ ከዛ፡ ኢሳያስ– ምንም ረዥምና ቀጭን ቢሆኑም– በትግል ብድግ አሉ፡፡ ተቀላቀሉን፡፡ ጥቂቶቹ እርምጃዎቻቸው የመደካከም ሥሜት ያመለክታሉ፡፡ ዝቅ ካለው ወንበርም እንዠጭ አሉ፡፡ ቡና አዘዙ፡፡ በሰፊው ተነፈሡ፡፡ ከፊታቸው ምንም ማንበብ አይቻልም፡፡ በዚያች ሠዓት ግን ድክም፡ ቁሥል ያሉ ይመሥሉ ነበር፡፡ ከየት እንደሚጀምሩ ግራ የገባቸው ዓይነት፡፡ “ምን አደረግን?” ሲሉ ጠየቁን፡፡ “ምን አደረክሁ እኔ?” ይህን ሲሉ፡ የመጸጸት ወይም በራሥ ያለመተማመን ምልክት ሊያሳዩን ፈልገዉ ከሆነ ግን ተሣክቶላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡

ይህ የኢሳያስ የማለቃቀስ ሁኔታ ግና ያንዲት ደቂቃ ያህል ዕድሜ እንኳን አልነበረውም፡፡ መናገር ሲቀጥሉ መቀያየር ጀመሩ፤ ይበልጥ ትኩረት፡ ይበልጥ ጉልበት ተላበሱ፡፡ ከአንድ ሠዓት በላይ ስለ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሁኔታው፣ የዓለም ጂዮ-ፖለቲካ፣ እና ስላለፉት ሰባት ዓመታት ውድቀቶች ደሰኮሩልን፡፡ ቡናቸው አልተነካም፡፡ አንዴ ወደ ጳውሎስ፡ አንዴ ወደኔ እያፈራረቁ ቀጠሉ፡፡ በቁጥጥራቸው ሥር ነን፡፡ ቡናችንም ድብን ብሎ በረደ፡፡

በጦር ሜዳው ውሎ ኤርትራ የመጀመሪያው ድሎች ተጎናጽፋለች፡፡ ሻለቃ በሻለቃ የተፈጸመውን ዝርዝር በማካተት ሠፊ መነባንባቸውን ሲያወርዱብን፡ ኢሳያስ ድል ስለማድረጋቸው ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ ያላቸው አይመስሉም ነበር፡፡ ከአንድ ተለቅ ያለ አገር ነው የገጠሙት፡፡ ግና፡ ኢትዮጵያ የጦር ዝግጅቷን ማጧጧፍ ስትጀምር፡ በወታደርም በትጥቅም ታናሿ ጎረቤቷ ኤርትራን እንደምታጣጥፋት ነው፡፡ ሆኖም፡ ረዥም ወታደራዊ ችግሮችን መወጣት ለኢሳያስ አዲስ አይደለም- ይልቁንም የሚመቻቸው ነው፡፡ በአስራ ዘጠኝ ስድሳዎቹ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው በርሃ ዘልቀው በአፍሪካ እጅግ የተዋጣለት የዓማጺያን ጦር ካደራጁ ወዲህ ኢትዮጵያውያኑን (በጦርነት) መብለጥ ነበር የተያያዙት፡፡ በራሳቸው የብቃት ስብዕና ስለማመናቸው እርግጠኛ አልነበርንም፡፡ ሆኖም ግን ካለጥርጥር አሳማኝ ነበሩ፡፡ ጳውሎስ እና እኔ ባነሡት ዝርዝር ጉዳይ ላይ ልንገጥማቸው አልተቻለንም፡፡

የጦራቸውን አሠላለፍ፣ የሎጂስቲክስ ይዞታና የመዋጋት ዓቅም ሲዘረዝሩልን፡ ኢሳያስ ራሳቸውን እንደ ስትራተጂስት፣ ዲፕሎማት፣ ዘዋሪ እና የውትድርና ሊቅ ነበር የሚቆጥሩት፡፡ ባለፈው ጦርነት ታጋዬችን መርተው ያዋጉት ያንዳቸው አዛዦች ሥም አላነሱም፡፡ በእርግጥ አባዛኞቹ በእዙ ቀጥተኛ ተሣትፎ እንዳይኖራቸው ተደርገዋል፡፡ ኢሳያስ ድሉ የብቻቸው እንዲሆን ወስነዋል፡፡ ስብሰባውን ጨርሠን ስንወጣም የተረዳነው ነገር ቢኖር የኢሳያስ የጦርነቱን ሂደት እስከታች የመቆጣጠር ልጓም-የለሽ አባዜና ከበስተጀርባው የሚኖረውን ድብን ያለ ባዶነት ፍንጭ ነው፡፡ ከጦር ሜዳ ድል ውጭ ምንም ዓይነት ራዕይ አልነበረም፤ ከዛ ባለፈ የማይቀረውን ታሪክ ለመኖር የማይለወጥ አቋምን የማራመድ ሂደት ነው የነበረው።

ኢሳያስ ጦርነቱን አካሄዱት፤ ተሸነፉም፡፡ በነዚህ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት የምዕራቡ ክንፍ ጋር የሚመሣሉት ውጊያዎች በሁለቱም ወገን ምናልባትም ሰማንያ ሺ ያህል ወታደሮች ሞተዋል፡፡ በሚያዚያ 1992 ዓ.ም. ኢትዮጵያውያን የኤርትራ ምሽጐችን በመሥበር ማጥቃቱን ጀመሩት፡፡ የህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) አዛዦች በፍጥነት የተበታተኑት አሃዱዎቻቸውን አሰባስበው የሞት የሽረት መከላከል በማድረግ የኢትዮጵያን ግሥጋሴ አዘገዩት፡፡ በማናቸውም የተኩስ ማቆም ኃሳብ ሲሳለቁ የነበሩት ኢሳያስ ወደ ዋሽንግተን በመደወል አሺታቸውን ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ ዜናዊም ሠራዊታቸው ውጊያውን እንዲያቆም ትዕዛዝ ሠጡ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ኤታ ማዦር ሹሙ ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ በዚህ ትዕዛዝ ለሃያ ዓመታት ያህል እንደተጸጸቱ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ፃድቃን የትግራዩ ማዕከላዊ ኮማንድ አባል በመሆን የኤርትራን ጥቃት እየተከላከሉ ይገኛሉ፡፡

የመለስ ስሌት ኢሳያስ ይወገዳሉ ወይንም እዛው ታጥረው ይቀራሉ የሚል ነበር፡፡ መጀመሪያ ይሆናል ተብሎም ነበር የተገመተው፡፡ ለጉምቱዎቹ ኤርትራውያን ታጋዮች በጦርነቱ ማን እንዳበላሸና ከሽንፈቱ ማን ትንሽ እንዳተረፈ ግልጽ ነበረ፡፡ የለውጥ ጥያቄዎችም ይበልጥ እየጎሉ መጡ፡፡ ጳውሎስም ገለልተኛ ኤርትራውያን በማሠባሰብ አንድ ለሰብዓዊ መብትና ለዴሞክራሲ የሚሟገት ቡድን አደራጀ፡፡ በጀርመን አገር ተገናኙ፤ አገራቸው የገባችበትን ቅርቃር በመዘርዘር ኤርትራ ወደ ዴሞክራሲ መንገድ እንድታቀና የሚጠይቅ ደብዳቤም ለኢሳያስ ጻፉ፡፡ (ይህ ጉዳይ The Eritrean Letter Writers “የኤርትራ ደብዳቤ ጸኃፊዎች” በሚል ርዕሥ Stephany Steggall በጻፈው መጽኃፍ በጥልቀት ተመርምሯል፡፡) እኒህ “የ13ቱ ቡድን” ወይንም “Group of 13” (G-13) ተብለው የሚጠሩት በጥቅምት 1993 ዓ.ም ከኢሳያስ ጋር በአስመራ ተገናኙ፡፡

ይህ ግንኑነት ኢሳያስ ያልፈለጉት እና በሚገርም ሁኔታም በደንብ ያልተዘጋጁበት ነበር፡፡ ብቻቸውን ቡድኑን ሲያገኙት በቀጥታ ኤርትራን በመካድና ለጠላቶች ድጋፍ በመሥጠት በሚል ውንጀላ ጀመሩ፤ ይቅርታ እንዲጠይቁና ደብዳቤያቸውንም እንዲቀዱ ጠየቋቸው፡፡ አልተቀበሉትም፡፡ ከ “የ13ቱ ቡድን” አባላት አንዱ የሆኑት የታወቁት የህክምና ሞያተኛው ሃይለ ደባስ የደብዳቤያቸውን ፍሬ ነገር ሲያነቡ የኢሳያስን አስተያየት ልብ እያሉ ነበር፡፡ ፕረዚደንቱ ይቁነጠነጣሉ፡ ፈጽሞ አልተመቻቸውም፤ እንዲህ ዓይነቱን በደንብ የተዋሃደ ፈተና መሸከም አልተቻላቸውም፡፡ ከስብሰባው ሲወጡ ሃይለ ለጳውሎስ “የገጠመን ፈተና ከገመትኩት በላይ ነው፡፡ ሰውየው የዓዕምሮ ጤና ችግር አለባቸው፡፡” አሉት፡፡

ከጥቂት ወራት በኋላ፡ “G-15” ተብለው የሚታወቁት አስራ አምስት የህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) መሪዎች ተመሣሣይ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ኢሳያስም ችላ አሏቸው፡፡ አላስፈላጊ ጊዜ በመሥጠት አደገኛ ጥፋት ፈጸሙ፡፡ በግል ውይይቶች (አንዳንዶቹ Conversations with Eritrean Political Prisoners በሚለው የDan Connell መጽሃፍ ተገልጸዋል) ኢሳያስ እንዴት ራዕዮቻቸውን እንዳጨናገፉባቸውና የፈፀሟቸውን በደሎች አንስተው ፊት ለፊት ሊጋፈጧቸው አለመቻላቸው የቱን ያህል እንደሚቆጫቸው ይናገራሉ፡፡ ኢሳያስ ግና ወቅት እየጠበቁ ነበር፡፡ በሴፕተምበር 9/11 ምክንያት የዓለም ትኩረት አቅጣጫ መዛባቱን ተከትለውም በሳምንቱ በተካኑበት ጭካኔያቸው ማጥቃታቸውን ተያያዙት፡፡

ጴጥሮስ ሰሎሞን ከንጋት ሶምሶማ ሩጫው ሲመለስ የደኅንነት ሠዎች ቤቱ በራፍ ሲጠብቁት ነበር፡፡ ቤት ውሥጥ ህጻናት ልጆቹ ገና ከእንቅልፋቸው እየነቁ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ አይተውትም፡ ከርሱ አንደበት ሰምተውም አያውቁም፡፡ ያኔ፡ እናታቸው አስቴር ዬሃንስም አሜሪካን አገር ከፍተኛ ትምህርቷን እየተከታተለች ነበር፡፡ ከፕረዚደንቱ ቢሮ ከተደራደረች በኋላ ወደ አገሯ ተመለሰች፡፡ አስቴር የተሳፈረችበት አውሮፕላን አስመራ ኤርፖርት ሲያርፍ የደህንነት ሠዎች ወደ አውሮፐላኑ በመግባት በቀጥታ ይዘው ወደ ወህኒ ቤት ወሰዷት፡፡ ልጆቿ ግን፡ አበባ ይዘው ተጓዡ ሁሉ ጨርሶ ወጥቶ ኤርፖርቱ ባዶ እስኪሆን ድረስ እየጠበቋት ነበር፡፡ እርሷም፡ ከዚያ ወዲህ ታይታም፡ ተሠምታም አታውቅም፡፡ ሴት ልጃቸው ሃና ወላጆቿ እንዳይረሱ በትዕግሥት ዘመቻዋን ታካሂዳለች፡፡ ታሪኳንም ያለፈው ዓመት Frontline በሚባለው የ PBS ፕሮግራም በተላለፈው Escaping Eritrea የሚል ዶኩሜንታሪ ውስጥ ዘርዝራለች፡፡

ከ“G-15” ተቃዋሚዎች አንዱ የተነሣበትን ሣተ፡፡ ሦስቱ ውጭ (አገር) ነበሩ፡፡ በመኃላቸው የታወቁ የነጻነቱ ትግል መሪዎች ያሉበት አሥራ አንዱ ወደ ኢሳያስ ማጎሪያ ተወረወሩ፡፡ አንዳንዶቹ ሞተዋል፡ ሌሎቹ መንቀሣቀስ እስከማይቻላቸው ድረስ ጉዳተኛ ሆነዋል ይባላል፡፡ ማንም አያውቅም፡፡ አንድም ክሥ አልተመሠረተባቸውም፡፡

በ2010 ዓ.ም. አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ፡፡ እኒህ የለውጥ አራማጅ እና ጀማሪ ፖለቲከኛ ለኢሳያስ የሠላም ጥሪ አቀረቡ፡፡ አንዱ ጉምቱ ዲፕሎማት (ይህን ሁኔታ) ‘ከእባብ/ኮብራ ጋር ራት ለመብላት ከምትጠይቅ ጥንቸልጋር ያመሳስለዋል፡፡ ሁለቱም የኢትዮጵያና የኤርትራ ግጭት ማብቃቱን አወጁ፤ አብይም የኖቤል የሠላም ሽልማት ተቀበሉ፡፡ ነገር ግን፡ የሥምምነቱ ዝርዝር ለአፍሪካ ህብረትም ሆነ ለኢትዮጵያው ፓርላማ አልተገለጸም፡፡ በአፍሪካ ህብረት ጭምር በመደበኛ

አሠራርነት እንደተቀመጠው፡ የሠላም ሥምምነት እንዲጸና ለዓለም ዓቀፍ ክትትልና እና ግምገማ ክፍት የሆኑ፡ ዲሞክራሲያዊ አሠራር፣ ሰብዓዊ መብቶችና ከልክ ያለፈ ሠራዊትን ቁጥር መቀነሥ የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ማካተት አለበት፡፡ ይህኛው ሥምምነት ግን በበጐ-ፈቃድ ቃላት ላይ ብቻ ነው የተመሠረተው፡፡ የኖቤል ሽልማቱ ህልማዊ ምኞት ድል ያደረገበት አብነት ነው፡፡ ሆኖም የኖርዌዩ የኖቤል ኮሚቴው በመሸወድ ብቸኛ ተጠያቂ አልነበረም፡፡ ሥምምነቱ በአቡዳቢው ልዑል መሐመድ ቢን ዛይድ ደህና ተደርጐ ተቀብቷል፡፡ የአሜሪካው (መንግስት) የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት (ጸኃፊ) ቲቦር ናጅም ግንኙነቱ ሞቅ ያለና ወንድማዊ እንደሚሆን ገምተዋል፡፡ ኢሳያስም ማዕቀቡን አስነሡ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የደህንነት ሥምምነት አደረጉ፣ ሶማሊያን ጨምሮ ብቅ እያለ የነበረ የሦስቲዬሽ የአምባገነኖች ጥምረቱን በተጽእኖአቸው (ሥር) አስገቡ፡፡

ኤርትራ ከነበረችበት መገለል ስትወጣ ኢሳያስ ዘና አላሉም፡፡ የሠፊ ሠራዊታቸውን ቁጥር ከመቀነሥ ይልቅ አዳዲስ መሣሪያዎች ይሸምቱ ገቡ፡፡ የራሣቸውን ህዝብ በነጻ እንዲንቀሳቀስ እንደማድረግ የደኅንነት ሠራተኞቹን ወደ አዲስ አበባ ላኩ፡፡ ኮቪድ-19 ሲነሣ አጋጣሚውን ተጠቅመው አገሪቱን በሙሉ ቆለፉባት፡፡ እንደሚባለው፡ ፕረዚደንት መሐመድ አብዱላሂ “ፎርማጆ” በምርጫ ከተንገጫገጩ እንዲገለገሉባቸው በሚል ሥሌት የሶማሊ ልዩ ኃይሎችን አሠለጠኑ፡፡ ነገር ግን አምባገነኖችን ለመሆን የሚሹትን ሁላ አደብ በማስያዝ በኩል የተካኑት ሶማሌዎች በግንቦት ምርጫቸውን አካሂደው አምባገነኑን ሠውዬ አስወገዱ፡፡ ኢሳያስ ሱዳን የገባችበትን ውጥረት እንደ ጥሩ አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ነው፡፡

ነገር ግን፡ ለኤርትራው አምባገነን እነዛ ሁሉ የጐን ትርዒቶች ናቸው፡፡ ከትግራይ ጋር ያለው ፍልሚያ ነው ዋናው ነገር፡፡

ለኢሳያስ ከጦርነት ውጪ ሌላ መፍትሄ የለውም፡፡ ካለ (ምንም) ምህረትም ይዋጋሉ፡፡ እንግዲህ ኢሳያስ ከሆነላቸው፡ የአፍሪካ ቀንድ ጌታ የመሆን የዕድሜ ልክ ምኞታቸው ሊጨብጡት ነው ማለት ነው፡፡ ካልሆነላቸው ደግሞ በትንሹ የሚረካው የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለኢሳያስ አምባገነንነትና ትርምሡ ማብቃት አንዳችም ምሥጋና ላያገኝ ነው፡፡ ተሥፋ አለኝ፡ ኤርትራውያንም ከአንድ ትውልድ ዕልቂት በኋላ ለረዥም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረውን ነጻነት ያጣጥሙት ይጀምራሉ፡፡

By aiga

Leave a Reply

Your email address will not be published.