ሙሉጌታ ወልደገብርኤል 

መንደርደሪያ፥ ዘራፊውና አመንዝራው የኢትዮጵያ ሰራዊት ካፓሲቲ (Capacity) ሊኖሮው ይችላል፤ ደግሞ አለው። ይህ ማለት፥ የሰው ሃይል ጨምሮ ከቱርክ፣ ከቻይና፣ ከኢራን፣ ከራሽያ፣ ከዩክሬንና ከዐረቡ ዓለም የአገሪቱ ሀብትና ንብረት አሳልፎ በመስጠት እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ የሸመተው ዘመናዊ የጦር መሳሪያና አማካሪዎች ሊኖሮው ይችላል ደግሞም አለው። ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያ ሰራዊት ጦርነት ተዋግቶ ማሸነፍ ይችላል ማለት አይደለም። አንድም፥ የኢትዮጵያ ሰራዊት ጦር ሜዳ ወርዶ ተዋግቶ ማሸነፍ የሚያስችለው ካፓብሊቲ (capability) ጨርሶ የለውም። ኢትዮጵያ የሰበሰበችው ከምርኮ የተረፈ፣ ሞራል የሌለውና አቅመ ቢስ እንዲሁም አዲስ ምልምል ሰራዊት ከብዛት አንጻር ስንመለከተው ስፍር ቁጥር የሌለው ቢሆንም የሰበሰበችው ሰራዊት የተልፈሰፈሰ ሰራዊት በመሆኑ፤ ይህ ማለት፥ በቂ ስልጠና የሌለው በመሆኑ በተጨማሪም ሰራዊቱን መርቶ የመዋጋት አቅም፣ በቂ ወታደራዊ ትምህርትና ተመክሮ፣ እንዲሁም የተፈተነ ችሎታና ክህሎት ያላቸው የበቁ የጦር መሪዎች ያላት አገር ባለመሆንዋ በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ ተዋግታ የምታሸንፈው ጦርነት አይኖርም። በደብዳቤ የተሾሙ ሲቪል የሰራዊት መሪዎች እነ ብርሃኑ ጁላና ባጫ ደበሌ ኢትዮጵያ የምታዘጋጃቸው መንግስታዊ ግብዣዎች ላይ ወታደራዊ ልብስና ማዕረግ አስለብሳ ድግስ ማሞቅያና ማድመቅያ ካልሆኑ በቀር የትግል ምልክት የሆነው የትግራይ ሰራዊት ታግሎ የመጣል አቅም የላችውም።  

ዘራፊውና አመንዝራው የኢትዮጵያ ሰራዊት የመዋጋት አቅም የለውም ሲባል በምክንያት ነው 

ጎበዝ፥ ቤተ ክርስትያኑም፣ መስጊዱም፣ ገበያውም፣ ህዝቡም ወዘተ ሁሉንም ይመታል ይደመሰሳል! እየለ ለሰራዊቱ መመሪያ የሰጠ፤ የመቐለ ከተማን በታንክና በመድፍ ከቦ ላፈርስህ ነው ላደፈርስህ ነው! እያለ በንጹሐን ዜጎች ላይ ሲዝት ዓለም አጀብ ያሰኘ የኢትዮጵያ ሰራዊት ዛሬ ምን ተፈጥሮ ነው ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ አታቾች ሰብስቦ እዩሉኝ ስሙልኝ ለማለት የበቃ? ብሎ መጠየቅ ጥበብ ነው። የኢትዮጵያ ሰራዊት ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ አታቾች ሰብስቦ ሲማፀን እውን ሠራዊቱ ሰላም ወዳጅ ስለሆነ ነው ወይስ የመዋጋት አቅም ስለሌለው ነው? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ አንድ ነገር በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ ይኸውም፥ ህፃናትና ሽማግሌዎች እንዲሁም ያልታጠቁ ወጣቶችና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ አንስት እናቶችና እህቶች ክብረ ንፅህና መጋሰስ፣ መረሸንና መጨፍጨፍ የለመደ የተልፈሰፈሰ የኢትዮጵያ ሰራዊት ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ አታቾች ሰብስቦ ሲማፀን ሰራዊቱ የመዋጋት አቅም ስለሌለው እንጅ ሰላም ወዳጅ ስለሆነ ነው ብሎ የሚያምን ባለ አእምሮ ሊኖር አይችልም።    

“ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነት ለሰላም የተከፈለውንም ዋጋ መረዳት እና ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንደሚገባው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዎት አሳሰበ” የሚለው ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ዜጎች በሚገባቸው የዕለተ ዕለት የአማርኛ ቋንቋ የተረጎምነው እንደሆነ አንድምታው፥ ኢትዮጵያ የትግራይ ሰራዊትን ገጥማ ልታሸንፍ ቀርቶ ልታስቆመው ስለ ማትችል፣ አቅሙ ስለሌለን ስለ ፈጣሪ እርዱን! ካተረፋችሁንና ከደረሳችሁልን አሁን ነው ልታተርፉንና ልትደርሱልን የምትችሉ፤ የትግራይ ሰራዊት እየመጣብን ነው የተለመደ ትብብራችሁ አይለየን፣ በፈጠራችሁ አድኑን የሚል ነው። በርግጥ የአእምሮ ዘገምተኛ ካልሆነ በቀር ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ኢትዮጵያ ቃል በቃል ይህን ታስተጋባለች ብሎ አይጠብቅም፤ ይልቁንስ፥ “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነት ለሰላም የተከፈለውንም ዋጋ መረዳት እና ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንደሚገባው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዎት አሳሰበ” የሚል ዜና ሲሰማ ግን ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ይገባዋል። የኢትዮጵያ የሰራዊት አለቆች፥ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ አታቾች ሰብስበው እያሰሙት ያለ ምህፅንታ ምን ማለት እንደሆነ ባለ አእምሮ ሰው አይስተውም፤ ደግሞም በትክክል ይገባዋል።    

ይህ ብቻም አይደለም፥ ብርሃኑ ጁላም “መቀሌ የመግባት ፍላጎት የለንም” ሲልም ተደምጧል። ለመሆኑ የገራ-ገሩ የብርሃኑ ጁላ አባባል ምን ማለት እንደሆነ ገብቶታል? ፖለቲካዊ አንድምታው ከማስቀመጤ በፊት ግን የዚህ አባባል ፍቺና ትርጓሜ ኩልል ብሎ ይታየን ዘንድ ሰውዬው ትናንት ሲያሰማው የነበረ ቀረርቶና ፉከራ አስታውሶት ዘንድ እወዳለሁ። ይኸውም፥ “በምሥራቁ ግንባር ራያ ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጥቷል፤ ጨርጨር፣ ጉጉፍቶ መሖኒን ሠራዊቱ ነጻ አውጥቷል። በየቦታው የነበሩ ወሳኝ የኮንክሪት ምሽጐችንም አፍርሷል። ሠራዊቱ በአሁኑ ጊዜ ወደ መቀሌ በመገሥገሥ ላይ ነው… በምዕራብ ግንባር ደግሞ በአዲ ነብሪድና በአዲ ዳእሮ የሚገኙ ከባድ ምሽጎችን በማፍረስ ሽሬን ተቆጣጥሮ ወደ አኩስም በመገሥገሥ ላይ ይገኛል” ወዘተ እያለ ሲደነፋና ሲያቅራራ የነበረ ሰው ዛሬ ደግሞ በዛችው ምላሱ፥ “መቀሌ የመግባት ፍላጎት የለንም” እያለ ሲቅለሰለስ የምንሰማው ያለ አገላለጽ በምእመናን አማርኛ ለማስቀመጥ የተገደድን እንደሆነ ፍቺው፥ ያለን ሰራዊት (የኢትዮጵያ ሰራዊት) የትግራይ ሰራዊት የመዋጋት አቅም የለውም ነው። ተዋግቶ ዳግም መቐለ ሊገባና ሊቆጣጠር ስለማይችል “መቀሌ የመግባት ፍላጎት የለንም” እያለ አቅመ ቢስነቱን በውስጠ ዘ እየነገረን ያለ። በርግጥ፥ የዚህ ዓይነቱ አነጋገር ለዐቢይ አህመድ ዓሊ ቅሌታም ስብእና የማይመች በመሆኑ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የብርሃኑ ጁላ ንግግር የሰማውና የደረሰበት እንደሆነ እንደ ከዚህ ቀደሙ ፊትህ እንዳላይህ ብሎ እንደሚቆልፈው ምንም አያጠራጥርም።  

ሌላው፥ ሐሰተኛ ትርክት ማስተጋባት የማይሰለችባቸውና የማያልቅባቸው የኢትዮጵያ ባለ-ስልጣትና ከበሮ መቺዎቻቸው ሰሙኑ ሲያስተጋቡትና ሲቀባበሉት የሰነበቱት በሬ ወለደ ድርሳን የሚመለከት ይሆናል። ተስፋዬ አያሌው የተባለ ሰው አውሮፕላኑ የተመታው በሱዳን አድርጎ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሶ በሁመራ በኩል ወደ ትግራይ ሊያልፍ መሆኑን ሲገልጽ፥ ወያነ ሱሪ ያስታጠቀችው ሬድዋን ሁሴን በበኩሉ አውሮፕላን መሳሪያ ጭኖ መቀለ ሲያራግፍ እንደ ተመታ ተናግሯል። እዚህ ላይ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ሊፈጥረው ያሰበና የሚፈልገው አውሮፕላን ጥሎ መምታቱ ሳይሆን የዚህ ዓይነቱ የለየለት ውሸት ፖለቲካዊ ሴራና አጀንዳ ወዲህ መሆኑ ሊገባን ይገባል። ይኸውም፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የትግራይ ሰራዊት ሊቋቋም የሚችል ሰራዊት እንደሌለው ጠንቅቆ ያውቃል፤ በተመሳሳይ፥ ራሽያ በዩክሬይን ቻይና ደግሞ በታይዋን እያካሄዱት ያለ ወታደራዊ ዘመቻና መንግስታዊ መግለጫዎች በቴሌቪዥን መስኮት በዜና እያየና እየሰማ ተመሳሳይ ስልት ተግባራዊ ለማድረግ የሄደበት መንገድ እንደማያዋጣው ስላወቀና ስለገበው የአውሮፕላኒቱ ትርክት ፈጥሮ አወዳደቁን እያሳመረ እንደሆነ ሊገባን ይገባል። ይህ ማለት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ገና ለገና ሽንፈቱን አምኖ መቀበሉ ሲሆን ይህን ዓይነቱ ሐሰተኛ ትርክት ሲያተጋባ ለማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት ደግሞ ትግራይ ብቻዋን አላሸነፈችንም፤ “መትተን የጣልነው አውሮፕላን” ረዳቶች ስላሏ ነው ቀዳሚ መልዕክቱ። የአውሮፕላኒቱ ሐሰተኛ ትርክት መልዕክትና ዓላማ ሌላ ምንም ሳይሆን ለሽንፈቱ መፅናኛ ምክንያት ነው እየፈጠረ ያለው።  

አራተኛ ነጥባችን፥ “የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ቆቦ ለቀን ወጥተናል” የሚለው የተለመደ የኢትዮጵያ ባለ ስልጣናት ልክ የሌለው ውሸትና ቅጥፈት ነው። በከተሞች መኸል ታንክና ከባድ መድፍ ተክሎ በመተኮስ የሚታወቀው የሰራዊት ግብረ ገብና ዲስፕሊን የሌለው ዘራፊና አመንዝራ የኢትዮጵያ ሰራዊት “የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ቆቦ ለቀን ወጥተናል” የሚለው ያለ ለሦስት ቀናት ተዋግቶ ሲሸነፍ መሆኑ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፥ ሽንፈቷን በውሸት መደጎስ የለመደች ይህች ባለ አመል አገር ይህ ሁሉ የምትለው ያለ በትግራይ ከተሞች የሚገኙ መዋእለ ህፃናት ከሰማይ ቦምብ እያዘነበች የንጹሐን ዜጎች እየቀጠፈች ባለችበት ሰዓት ነው። የትግራይ ከተሞች ዛሬም ቦምብ ከሰማይ እያወረደ እያወደመ፣ በእሳት እያጋየና የንጹሐን ህይወት እንዲሁ በከንቱ እየቀጠፈ ባለበት በዚህ ሰዓት እንዴት ነው “ንጹሀን ላይ እንዳትተኩሱ፤ ወደ ኋላ ተመለሱ የሚል ትዕዛዝ ተሰቶናል” እያለ ህዝብ የሚያወናብደው? ግራ ቀኛቸው የማያውቁ፣ ሃጢአት የሌለባቸውና የማይገኝባቸው ንጹሐን የሆኑ ህጻናት ያልራራ ሰራዊት አቅም ቢኖረው ነው ከተሞቹን ለቆ የሚወጣው? ነገና ከነገ ወዲያ ወልዲያ ከተማ ለቆ ሲሄድስ ለህዝቡ ምን ይለው ይሆን? ሐቁ፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ኢትዮጵያውን ሁሉ አሰልፎ ከጀርባቸው እየሸናባቸውም ሳለ ዝናብ እየዘነበ ነው! ቢላቸው ህዝቡም አሜን! ብለው እንደሚቀበሉት ስለሚያምን ሌላስ ቢል ምን ይደንቃል? በውሸት የተካነ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሚደንቀው ባይዋሽ ነው እንጅ ዋሸ ብሎ የሚደነቅ ከወዴት ቢገኝ ነው?  

አፍቃሬ ኢትዮጵያ የህወሃት አመራር አጀንዳህ ምንድ ነው? 

ሁለት ዓመት ሊሞላው ሁለት ወራት የቀረው በትግራይ ላይ የተፈጸመ ወረራና ጦርነት የተነሳ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ ወላጆቻችን፣ ወንድም እህቶቻችን እንዲሁም ዘመዶቻችንና መላ የትግራይ ህዝብ ከምንም በላይ ከምግብና ከመድሃኒት እጦት የተነሳ ህዝባችን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ የሚሰወረው ፍጥረት ይኖራል ተብሎ አይታመንም። ህዝባች በጨለማ ነው እየኖረ ያለው፤ በጨለማ እየኖረ ያለ ህዝብ ብርሃን ያወጣለት ዘንድም ሰራዊት ፈጥሮ በመታገሉ (የምዕራብ ትግራይ እንዳለ ሆኖ) ወራሪ ሃይሎችን የረገጥዋት መሬት መቃብራቸው በማድረግ የትግራይ ህዝብ ህልውናውና ድህንነቱ ክብሩና ማንነቱ በትግሉና በመስዋእትነቱ ለመጠበቅ ተችሎታል። ከዚህም ያለፈ ጠላት የገባባት ስፍራ ሁሉ እየገባ ሲሰብረውና ሽንፈት ሲያከናንበው ደብረ ብርሃን መድረሱን ይታወቃል። የትግራይ ሰራዊት የማንም ግዛት የመቆጣጠር ዓላማ አነግቶ የተነሳ ሰራዊት ባለመሆኑም ደም መፋሰሱን ለመግታት ታሳቢ አድርጎ በፈቃዱ ወደ ቦታው መመለሱ ይታወቃል። ይህ ለስድስት ወራት የቆየ ይፋዊ ያልሆነ ድርድር ሲደርግ ከቆየ በሃላ የገጠው ሽንፈትና ኪሳራ እንቅልፍ ያሳጣው ዐቢይ አህመድ ዓሊ የተከናነበው ውርደት ለማካካስ አስልቶ ዳግም ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነትን ከፍቷል። ይህን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነትም ይሄው ቆቦ አልፈን እየገሰገስን ነው እየተባለ ነው። አሁን የተጋሩ ጥያቄ አጭርና ግልጽ ነው፥ ወዴት ነው የምንገሰግሰው ያለ? ግልጽ የሆነ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስትራቴጂ የሌለው፣ መዳረሻው የማይታወቅ ግስጋሴ ጥቅሙም ሆነ ዓላማው ምንድ ነው? ቆቦን አልፋችሁ ሮቢጥስ ደረሳችሁ ከዚያስ? መገስገሳችን እስከ ምን ድረስ ለመሄድ ነው? አሁንም ደብረ ብርሃንና ሸኖ ደርሰን ለመመለስ ነው? የአማራ ሰራዊት ታጣቂና ሚኒሻ አይደለም የትግራይ ሰራዊት ሊገጥም የጦርነት ባህልና ታሪክ እንደሌለው ሁሉም ያውቃል። የትግራይ ሰራዊት ለአማራ ፕሩፍ የሚያደርገው ነገር የለውም። ሐቁ ይህ ከሆነ ዘንዳም ስመ ዝክራችን ለማጥፋት የዘመቱብን ጠላቶቻችን ፈጽሞ ለማቃበፅ ካልሆነ በቀር የተሸነፈ ልፍስፍስ የኢትዮጵያና የአማራ ሰራዊት በዚህ ደረጃ ማሳደድና መማረክ ምንድ ነው ጥቅሙ? የራሳችን ህዝብ መቀለብ ያልተቻለን ሰዎች የሰው አገር ሙርከኛና ቁስለኛ መቀለብና ማካም ሌላ ሸክም መሸከም አይሆንም ወይ?   

አሁን በዚህ ሰዓት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ጦርነት ተዋግቶ ሊያሸነፍ የሚችል ሰራዊት እንደሌለው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ የዓለም ማህበረሰብ ዳግም ይታደገው ዘንድ ይሄው ረዳት ፍለጋ በቀንም በሌሊትም ጩኸቱን እያቀለጠው ነው። አሁንም ጥያቄው፥ የትግራይ አመራር ለዚህ ዓይነቱ የሸፈጥ ፖለቲካ አልፎ ዓላማውን ለማሳካት ያለው ዕቅድ ምንድ ነው? በተማጽኖ ተኩስ አቁም ሲባል ለማቆም፣ ተመለስ ሲባል ለመመለስ ነው ወይስ የትግራይ ህዝብ ከከባ ነጻ ለማውጣት ፈፅሞ የመታገል ዓላማ ነው ያለው? የቀደመውን ስህተት ላለመድገም ፖለቲካውንና ወታደራዊውን ትግሉን ለይቶ ለመታገል ምን ያህል ዝግጁ ነው? ወይስ ዛሬም እንደ ትናንት ምንም ዓይነት የውትድርና ሽታ የሌላቸው ሲቪል የህወሓት የፖለቲካ ካድሬዎችና ባለ ስልጣናት ሰራዊቱን እንዲዘውሩት በመፍቀድ ተመሳሳይ ስህተት ለመፈፀም ራሱን ለኪሳራ ይማግድ ይሆን? መንእሰይ ትግራይ ለህልውናውና ለደህንነቱ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ነው፥ አፍቃሬ ኢትዮጵያ የህወሃት አመራር ግን አጀንዳችሁ ምንድ ነው? ዛሬም እኛን እየገደላችሁ ሌባና ዘራፊ ብላ ያባረረቻችሁ ኢትዮጵያ የመታደግ ዓላማ ነው ያላችሁ? ሐቁ መጽሐፍ፥ “በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው” እንዲል፥ በዚህ አያያዛችሁ (mediocre) ብትሄዱ አትቀበላችሁም ሌላ ቀሚስና ማስክ ቅጥልቃላችሁ አዲስ ቀሚስ አሰፍታችሁ (ተደባብቃችሁ) ብትቀርቡም አታከብራችሁም። ይልቁንም፥ ከሄድክና ከገሰገስገስክ እንደ ብርቱና ተዋጊ ሠራዊት ነው መሄድና መገስገስ ያለብህ። ህግና ስርዓት እንዲከበር ከሄድክ ብቻ ነው ኢትዮጵያ ብትወድም ባትወድም ብትስማማ ባትስማማ ከግብህ ልትደርስና ዓላማህን ልታሳካ የምትችለው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ድብቅ አካሄድ ትርፉ መላላጥ ነው የሚሆነው። 

እውነት ነው፥ የትግራይ ሰራዊት የጠላት ሃይል ደምሥሶ ግዛት መያዝና መቆጣጠር ስለ ተሳነው ሳይሆን (በተግባር እያሳየ ነው) በባህሪው የማንም ግዛት የመቆጣጠርና የመግዛት ተልዕኮ የለውም። የአማራ ሆነ የአፋር መሬት የአማራና የአፋር ህዝብ ነው። የትግራይ ሰራዊት የእነዚህ ህዝቦች መሬት ሆነ ግዛት የመቀራመት ፍላጎቱም ዓላማውም የለውም። ይህ ማለት ግን፥ ገና ለገና ወደ ሰላም ይመጣሉ እየተባለ ግማሽ መንገድ እየደረስክ መመለስ ማለት አይደለም። የሚሰማ የትግራይ የሰራዊትና የፖለቲካ አመራር ካለ፥ ትግራዋይ ለህልውናውና ለደህንነቱ እያካሄደው ያለ ትግል/ጦርነት ፍሬ ሊያፈራ ይገባል! የሚል ነው። በእነዚህ ግዞቶች ላይ የመሸገ የጠላት ሃይል ሁሉ መደመሰስ ከጀመረ ፈጽሞ እስኪያጠፋቸው ድረስ ማረፍ የለበትም። ይህ ዓይነቱ የጦርነት ህግ ለፖለቲከኞች የተሰወረ ሊሆን ይችላል፤ በወታደር ቤት (ትምህርት ቤት) ያለፈ የጦር ሰው ግን ይህ መሰረታዊ የጦርነት ህግ ይስተዋል የሚል እምነት የለኝም። አንድም፥ የጦርነት ዓላማና ግብ አንድና አንድ ነው፤ ይኸውም፥ የጠላት ሃይል ሙሉ በሙሉ መደምሰስ፣ የእኔ ከሚለው ግዛት ላይ ማጽዳት መቻል ነው። ሳስበው ግን፥ ፖለቲካውን ተቆጣጥሮ በሰራዊት አለቆቹ በኩል የትግራይ ሰራዊት እየተቆጣጠረ የሚገኝ፣ ግቡና ዓላማው በግልጽ አስቀመጦ መታገል የተሳነው የህወሓት አመራር ኢትዮጵያ ለማዳንና ለማትረፍ የትግራይ ህዝብ በርሃብና በበሽታ ይርገፍ! የሚል አቋም ለመያዙ አንዳች ጥርጥር የለኝም። ይህ ባይሆን ኖሮ የኢትዮጵያ እጅና እግር እየጠበቀ ሳይሆን ትግራዋይ ሰራዊት ፈጥሮ ለመታገል የተገደደበት ከግቡ ለማድረስ ጦርነቱ ለማሸነፍ የሚያስችለው ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ ነድፎ በራሱ ተርም፣ ጊዜና ሰዓት ወስኖ በታገለ ነበር። ኢትዮጵያ ጦርነት ስትከፍት የሚዋጋ ኢትዮጵያ እደራደራለሁ ስትል ደግሞ ለድርድር የሚቀመጥ ከሆነ ግን ይህ ትግል ሳይሆን ለሰው ነፍስ ምንም ክብር የሌላቸው፣ ሌላው እየሰዉ መክበር የሚያምርባቸው፣ የቆሻሻ አእምሮ ባለቤት የሆኑ የፖለቲካ ሰዎች የሚጫወቱት ቁማር ነው። 

በተረፈ፥ የዓለም ማህበረሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ ማወቅ ካለበት ማወቅ ያለበትና የሚገባው፥ በትግራይና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዳያገኝ ወጣ ገባ እያለ በቀጣይነት እንቅፋት በመሆን ላይ ያለና የሚገኝ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ራሱ እንደሆነና የራሽያ መንግስት በዩክሬን ሀገረ ቻይና በተመሳሳይ በታይዋን እያደረጉትና እየሰሩት ያለ ወታደራዊ ዘመቻና መንግስታዊ መግለጫዎች በቴሌቪዥን መስኮት እያየ ከዜና የሚሰማውን ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ በሚያደርገው ሙከራ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል። ትግራይም ይህን የማሳወቅ ግዴታ አለባት።   

ከታገልክ ለመጣል ታገል! 

By aiga