ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

የጽሑፉ ዓላማ፥ ኢትዮጵያ፥ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያና ከሱዳን አገራትና መንግስታት መክራና ዘክራ በተፈበረከ የፈጠራ ክስና ሐሰተኛ ውንጀላ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመችው ወረራና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተከትሎ፥ ባርነትን አልቀበልም! በማለት ክንዱን ለትግል ያነሳና ያበረታ የትግራይ ህዝብና ሠራዊት ጎን በመቆም አቅሙ በፈቀደው የታገለ ትግራዋይ ሁሉ፥ ይህ ሁሉ ሞትና እልቂት ሊደርስብንና ሊፈጸምብን የቻለበት ምክንያት ምንድ ነው? ደማችን የገበርልንለትና ህይወታችን እየሰዋንለት ያለ የትግላችን ዓላማና መጨረሻ ምንድ ነው? በማለት ለሚያነሳው/ተብሎ ለሚነሳ ሀገራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እንደ አንድ ትግራዋይ የሚሰጠው ታሪክን መሰረት ያደረገ ምላሽ ተጨባጭና ምክንያታዊ አቋም ለማንጸባረቅ ነው።

የጽሑፉ ውሱኑነት፥ በጽሑፉ ርዕስ እንደ ተገለጸ ጽሑፉ በይዘቱ ጸሐፊው “መፍትሔው፥ ምስረታ ሀገረ ትግራይ እውን ማድረግ ነው” ሲል ለሚያቀርበው ሙግት፤ እንዲሁም፥ ምስረታ ሀገረ ትግራይ ለምን? ለሚለው ጥያቄ ውሱን የሆነ ታሪካዊ ዳርቻው ፖለቲካዊ እሳቤው ማዕከል አድርጎ ጠቅለል ያለ ጽሑፍ እንጅ ለምስረታ አንዲት አገር የሚስያስፈልጉ ግልብአቶች አስመልክቶ የሚያትት ጽሑፍ አይደለም።

ትርጓሜ የምንፈልገው አገር መሆን ነው! ሲባል የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ አገር የመሆን ጥያቄ እያቀረበ እንልሆነና እንዳይደለ ለመግለጽ እወዳለሁ። የትግራይ ህዝብ የሚጠቅመኝና የሚረባኝ ይህ ነው ብሎ ለሚውስነው ማንኛውም ውሳኔ የማንም ፈቃድና ይሁንታ አያስፈልገውም። አገር የመሆንም ይሁን ሌላ አማራጭ የመከተልና የመውሰድ ስልጣንና ኃላፊነትም የትግራይ ህዝብ ስልጣን ብቻ ይሆናል/ነው።

ማሳሰቢያ፥ ይህ የመፍትሔ ሃሳብ፥ ኢትዮጵያ ግፍ ስለ ፈጸመችብን፤ አንድም፥ የኢትዮጵያ ሰዎች “የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው መሄድ ከሆነ መሄድ ይችላሉ” የሚል ከፍርሃትና ከጭንቀት የሚመነጩ ንግግሮች መሰረት ያደረገ ሳይሆን ከተፈጸመብን ግፍ ባሻገር ለተፈጸመብን ዘራዊ ጭፍጨፋ ምክንያትና መንስኤ የሆነ መሰረታዊ የአገሪቱ ችግር ስር ነቀል መፍትሔ መስጠት ስለሚሻው ነው። ውስጥ ለውስጥ በሚደረገው የተለመደ የፖለቲካ ሴራ፣ የትግራይ ገበሬን በዘይትና በስንዴ እያስፈራራህ፣ እንዲሁም ለግላዊ ጥቅምና ለስልጣን ሲባል አዲስ አበባ ተቀመጠህ በሚዶለተው ምክር ሳይሆን በህዝቡ መካከል ተገኝቶ በግላጭ/በይፋ አማራጭ ሃሳብ በማቅረብ ማለትም “ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና መቀጠል አለባት” የሚል ሃሳብ ያለው ከተገኘና ሃሳቡ የትግራይ ህዝብ ከገዛው፣ ድጋፍ ካገኘና አሸናፊ ሆኖ ከወጣ፥ እንደ ተጋሩ አሸናፊ ለሆነው ሃሳብ በመገዛትና ትግራይን በማስቀደም በሚያግባቡን ነጥቦች ላይ አተኩረን አብረን እንሰራለን እንጅ እርስበርሳችን መለያየትና መናከስ አለብን ማለት እንዳይደለም ለማሳሰብ እወዳለሁ። መልካም ንባብ!

መንደርደሪያ በዓይናችን እውን ሆኖ ያየነው፣ የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ፔካ ሀቪስቶ በሰጡት ምስክርነት መሰረትም፥ ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ ዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ልሒቃን በውንጀላ፣ በፈጠራ ትርክትና በሐሰተኛ ክስ አመካኝተው በትግራይ ላይ የፈጸሙት በዓይነቱ ለየት ያለ ወረራና ወረራውን ተከትሎም በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸሙት የመሰረተ ልማት ውድመትና ዝርፍያ ጨምሮ በሰብዓዊነት የሚፈጸም፣ የጦርና የዘር ማጥፋት ወንጀል ገፊ ምክንያትና ዋና ዓላማ የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ዘር ላይቀርለትና ህልውና ላይኖረው፣ ቅሪት የተገኘ እንደሆነም ዳግም ቀና ብሎ እንዳይሄድና ራሱን ችሎ እንዳይቆም ቅስሙና ሞራሉ በመስበር፣ በማድቀቅና በማዋረድና ዘልአለም ፍርፋርያቸው ለቃሚ፣ ለማኝና የተጣለ፣ ህልውና የሌለው ጎስቋላ ፍጥረት ሆኖ እንዲያዩት ከነበራቸው ሰይጣናዊ ምኞት የተነሳ እንደሆነ ዓለም ያወቀው የአደባባይ ሚስጢር። ኔውዮርክ ታይምስም የአሜሪካ ሴኔት አባል የሆኑት ክሪስ ኩን ጠቅሶ የዘገበው ሐቅ ይህ ነው። ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከውስጥም ከውጭም ኃይሎች ጋር ግንባር በመፍጠር ትግራይ የወረረበትና ያወደመበት፣ አሁንም በቀጣይነት ከበባ ውስጥ አገብቶ ከጥይት ያመለጠ ህዝብ በርሃብና በበሽታ ለመጨፍጨፍ፣ ለመግደልና ለማጽዳት እንዲሁም ድሮኖችና ተዋጊ ጀቶች እየላከ የትግራይ ከተሞች በእሳት እያነደደና የትግራይ ህጻናትና እናቶች ከሰማይ ቦንብ እያዘነበ እየጨፈጨፈ ያለበት ምክንያት ግቡና ዓላማው የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ማብረስና ማንበርከክ አልሞ ስለተነሳ ነው።

ዐቢይ አህመድ ዓሊ በጭፍራና በደሴ ግንባሮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰውና የንብረት ኪሳራና ውድመት አስተናግዶ ወደ ደብረ ብርሃን ከሸሸ በኋላ በእነዚህ ግንባሮች በተለይ በደሴ ግንባር የገጠመው ከፍተኛ ወታደራዊ ሽንፈት፣ ኪሳራና ውርደት ምክንያት ሲገልጽ፥ “የተሸነፍነው ነጮችና ጥቁሮች የውጭ አገር ዜጎች በውጊያው ስለ ተሳተፉበት ነው፤ ወያኔዎች የደሴና የኮምቦልቻ የመኪና ሰሌዳ ለጥፈው አስቀድመው ወደ ከተሞቹ ስለገቡ ነው፣ ተኳሽና አስተኳሽ ከውስጥ ስለ ነበሩ” ሲል የሰጠውን ይፋዊ መግለጫ ሁላችን እናስታውሳለን። ዐቢይ አህመድ ዓሊ ይህን ያደረገበት ምክንያት የገጠመው ወታደራዊ ሽንፈት እንደ ለመደው በውሸት ለማድበስበስ ያለመ ቢሆንም በዋናነት ግን ዓላማው ከትግራይ ውጭ የሚገኙ በአማራና በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ንጹሐን የትግራይ ተወላጆት ዘራዊ ጭፍጨፋ እንዲደርስባቸው ያቀርበው ጥሪ ነው። ንግግሩ ተከትሎም በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የጎበዝ አለቆች በይፋ በንጹሐን የትግራይ ተወላጆች ላይ የሞት መለከት ሲነፉ፥ በኤርትራ መንግሥት የሚዘወረው፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ደም ለመቃባት ዓላማውና ተልዕኮው አድርጎ የተቋቋመው፣ በተለይ በትግራይ ህዝብ ላይ አነጣጥሮ ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና በተደጋጋሚ ማንነት ማሰረት ያደረገ የዘር ጭፍጨፈ እንዲፈጸምበት ጥሪውን ያቀረበ የኢሳት ቴሌቪዥን፥ የደሴና የጭፍራ ምሽጎች በትግራይ ሠራዊት መደርመስ ተከትሎ ያስተጋባው መልዕክት ቢኖር በሁሉም የትግራይ ተወላጆች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ያቀረበው ይፋዊ የዘር ጭፍጨፋ ጥሪ ልብ ይሏል።

ከ100 ሚልዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ አለኝ የምትለው በርካታ ቁጥር ያለው መደበኛና መደበኛ ያልሆነ ሰራዊት፣ መሳሪያ የታጠቀ ሚኒሻና ሽፍታ ሁሉ ሰብስባ ስታበቃ ይህ ሁሉም አልበቃ ብሏትም ከ100 ሺህ በላይ የኤርትራ፣ እንዲሁም በርከታ ቁጥር ያለው የሶማሊያ ሰራዊት በመጋበዝ ትግራይን ከካርታ የትግራይን ህዝብ በተመሳሳይ ህልውናና ስመ ዝክር እንዳይኖረውና እንዳይቀርለት ከታሪክ ለመፋቅና ለመደምሰስ ያደረገችው ሙከራ ውጤቱ ድፍን ዓለም በአግራሞት የተመለከተው ሲሆን፥ ትላልቅና ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው የዓለማችን መገናኛ ብዙሐንም በመላ፥ እንደ ፈሮዖን ሰራዊት በትግራይ ምድር ሰምጦ የቀረውና የተቀበረውን የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ ሙትና ሙርከኛ እያሳዩ የትግራይ ህዝብ የትግል መንፈስና ጀግንነት እውን መሆኑን በተደጋጋሚ ምስክረነታቸው ሰጥቷል። ጥያቄው፥ እዚህ ውስጥ እንዴት ገባን? በዘላቂነት መፍትሔውስ ምንድ ነው? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ እንደሚከተለው ተጻፏል።

የልባቸው ሃሳብ ቢሰምርላቸው ኖሮ፥ እንደ ህዝብ መታሰቢያ ላይኖረን ተውን ነበር

ዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ልሒቃን የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ በጠላትነት ፈርጀው የኤርትራና የሶማሊያ ሰራዊት ይዘው መጥተው በትግራይ ላይ የፈጸሙት ወራራ ይህን ተከትሎም ያደረሱት የህይወትና የንብረት ውድመት ግልጽ እንዲሆንልና እንዲገባን የወረራው ዘፍጥረት መመልከት አስፈላጊ ነው። ዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ልሒቃን አንድ የሚያደርጋቸውና ሁለቱም የሚጋሩት ባህሪይ ቢኖር እውነት ያልፈጠራቸውና በውሸት የተለከፉ (Compulsive lair) ተብለው ሊታወቁ የሚችሉ መሆናቸው ይጠቀሳል ነው። በመሆኑም፥ በተለይ በራሱ ላይ እየተኮሰ ራሱን በማቆሳሰል የሚስተካከለው የሌለው ዐቢይ አህመድ ዓሊ በትግራይ ላይ የፈጸመው ወረራና የከፈተው ጦርነት መንስኤ አስመልክቶ በተለላዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ሐሰተኛ መግለጫዎች በመስጠት ሐቁን ለማዳፈንና ለማድበስበስ ቢሞክርም፥ በተመሳሳይ በራሱ አንደበትና በሹማሙንቶቹ አማካኝነት የወረራው ዓላማና የጦርነቱ ግብ ምን እንደ ነበረና እንደሆነ ግልጽ አድርገውልናል።

ሽንፈቱን አምኖ በመቀበል ፈንታ ሰሚ ጆሮ ጭው የሚያደርግ፣ ተራና ውሃ የማይቋጥር ምክንያት በመደርደር የሚታወቀው ዐቢይ አህመድ ዓሊ በቅርቡ በደሴ ግንባር የተከናነበው ሽንፈት አስመልክቶ ሚኒስትሮቹን ሰብስቦ ያደረገው ንግግር እንኳ ብንመለከት፥ እያካሄደው ያለ ጦርነት እንዲሁ ዋጋ ቢስ ጦርነት ሳይሆን ከመነሻው ዓላማ ያለው ጦርነት መሆኑን ሲያስረዳ እንዲህ ነበር ያለው “ጦርነት ምንድ ነው? ጦርነት ማለት የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ የመጨረሻው ጫፍ ማለት ነው። ማንኛውም ግጭት ዝም ብሎ በግልፍተኝነት የሆነ ግሩፕ ስለ ፈለገ ሳይሆን አንድ ሊያሳካው የፈለገ ዓላማ በውይይት በክርክር በሃሳብ ብልጫ ማሸነፍ ሲሳነው በሃይል ያንን እሳቤ ለመጫን የሚደረግ ነገር ነው። ጦርነቱ ዓላማ ቢስ ግብ አልባ ጉዳይ ሳይሆን የሆነ ነገር ለማሳካት የሚሰራ ጉዳይ ነው የሚለውን ነገር ፖለቲካሊ መገንዘብ አስፈላጊ ነገር ነው” ሲል ነበር በትግራይ ላይ የፈጸመው ወረራና የከፈተው ጦርነት ዓላማ ያስረዳ።

ልብ ይበሉ፥ ሌሊቱ/ምሽቱ እስኪ ነጋ እንኳ መጠበቅ ተስኖት ጥቁር ለብሶ በሌሊት በጨለማ ብቅ ያለው ዐቢይ አህመድ ዓሊ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስምና በትግራይ ላይ ወረራ ሲፈጽም፥ በምክንያትነትነት ያቀረበው የተፈበረከ ክስና ሐሰተኛ ውንጀላ “በዛሬው ዕለት ሰሜን ዕዝ ስለ ተጠቃ” የሚል ሁላችን እናስታውሳለን። ለአንድ ዓመት ሙሉ ሲነገር የከረመው የአዲስ አበባ ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ፥ ማለትም “በሰሜን ዕዝ ተጠቃ” ተብሎ ይህን ተከትሎም ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላበት ጊዜ ውስጥ ጦርነት ውስጥ የመገባቱ ነገር ውሸት እንደ ነበር ግን ከሌላ ሰው ሳይሆን ከራሱ ከዓቢይ አህመድ ዓሊ ልንሰማ ነው። ዐቢይ አህመድ ዓሊን አሁንም በደሴ ግንባር የተከናነበው ሽንፈትና ኪሳራ ተከትሎ ባደረገው ንግግር ውስጥ ጦርነት ተነካሁ ብለህ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የሚለኮስ የምጣድ እሳት እንዳይደለ እንዲህ ነበር ያለው፥ “ግጭት ዝም ብሎ በግልፍተኝነት የሆነ ግሩፕ ስለ ፈለገ ሳይሆን አንድ ሊያሳካው የፈለገ ዓላማ በውይይት በክርክር በሃሳብ ብልጫ ማሸነፍ ሲሳነው በሃይል ያንን እሳቤ ለመጫን የሚደረግ ነገር ነው” ይላል። ይህ በስህተት አለቦታው የተቀመጠ የድራማ ሰው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ይህ ብቻ አይደለም ያለው፥ ጦርነቱ ከመጀመሩ ከወራት በፊት ለጦርነት በሚገባ እንደ ተዘጋጀና ጦሩነቱንም እንደሚያሸንፍ ይህን ብሎ ተናግሮ እንደ ነበር ለፓርላው የተናገረው ንግግር “የዱሮን በሚመለከት እኔ አልደበቅኳቸውም፤ በግልጽ ከጥቂት ወራት በፊት የሚኒሻ ውጊያ አንዋጋም፣ ዘመናዊ ውጊያ እንዋጋለን፣ እንደዚህ ዓይነት ትጥቆችም አለን ብዬ ነግሬአቸዋለሁ” ሲል ተደብቆ ሳይሆን በይፋ ነው። ጎበዝ፥ ውሸት ፋይል የለውም! ይሉሃል እንግዲህ ይህ ነው።

ዐቢይ አህመድ ዓሊና ሠራዊቱ ከትግራይ (ምዕራብ ትግራይ እንዳለ ሆኖ) በኃይል ተመንግለው ከወጡ በኋላ ለገጠመው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሽንፈትና ኪሳራ ለማድበስበስ አዝማሪዎች ሰብስቦ ባደረገው ንግግር ላይ ደግሞ፥ ትግራይ (መቐለ) ለቀን የወጣንበት ምክንያት የሄድንበት ምሽን (ተልዕኮ) ስላሳካን፤ የቀድሞ ውበቷ አሳጥተን ከተሟ የሌባና የወንበዴ መዓት አድርገን፤ በሻሻ አድረገናት ነው የወጣነው! ነበር ያለው። እዚህ ላይ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሚለው ያለ ሃሳብ ሁሉ ትክክል ነው። ጦርነት በግልፍተኝነት እንደማይጀመርና በዓላማ የሚካሄድ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ በትግራይ ላይ ወረራ ስትፈጽም የፖለቲካ ልዩነት ስላላት ሳይሆን ዓላማ እንደነበራትና ይህን ዓላማ አሳክታም እንደወጣች ነው ዐቢይ አህመድ ዓሊ እየተረከልን ያለው። አንድም፥ “ጦርነት ምንድ ነው? ጦርነት ማለት የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ የመጨረሻው ጫፍ ማለት ነው። ማንኛውም ግጭት ዝም ብሎ በግልፍተኝነት የሆነ ግሩፕ ስለ ፈለገ ሳይሆን አንድ ሊያሳካው የፈለገ ዓላማ በውይይት በክርክር በሃሳብ ብልጫ ማሸነፍ ሲሳነው በሃይል ያንን እሳቤ ለመጫን የሚደረግ ነገር ነው። ጦርነቱ ዓላማ ቢስ ግብ አልባ ጉዳይ ሳይሆን የሆነ ነገር ለማሳካት የሚሰራ ጉዳይ ነው የሚለውን ነገር ፖለቲካሊ መገንዘብ አስፈላጊ ነገር ነው” ብሎ ስለሚያምንና በትግራይ ላይ የፈጸመው ሁሉ በእውቀትና በዓላማ መሆኑን ነው።

መጽሐፍ፥ ምስክርነት በሁለትና በሦስት ይጸናል እንዲል መቋጠር ያልፈጠረበት ዐቢይ አህመድ ዓሊ በትግራይ ላይ የፈጸመው ወረራ አስመልክቶ፥ እንዲሁም ትግራይን ቀበርናት! እየተባለ በሚጨፈርበት ወቅት የወረራውና የጦርነቱ አጠቃላይ ምስልና ግንዛቤ ለመሳልና ለመስጠት የእግር ኳስ ምሳሌ በመጠቀም በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ ያደረገው ንግግር እንመልከት። እንዲህ ያላል፥ “አሁን ሰሙኑን ካለው የኳስ ጨዋታ አንጻር እንኳን ወስደን ብንመለከት፥ ሁለት የሚቃረኑ ቡድኖች በአንድ ሜዳ ውስጥ ኳስ ይጫወታሉ፣ በዚህኛው ቡድን ያለ በA ቡድን ያለ አንድ አጥቂ ሰው ኳሱን ይዞ ለማጥቃት ቢንደረደር ከሚቃረነው ኃይል ሊገጥሙት የሚችሉት ጉዳዮች ከሞላ ጎደል ይታወቃሉ። አንደኛው በብቃት በልጦ በችሎታ በልጦ ኳሱ መቀማት ነው። ምንም ህግ ሳይጣስ በተሻለ ብቃት ካሱን ቀምቶ በወገን ኃይል ላይ ግብ እንዳያስቆጥር ማድረግ ነው፤ በብቃት የማትበልጠው አስቸጋሪ ሰው ከሆነ ሰውየው የሚያጠቃው ግለሰብ፥ ዳኛ ሳያይህ፣ ራስህን ደብቀህ፣ ጎንትለህ ጎትተህ ጠልፈህ ኳስዋን እንድትቀር እንድትጨናገፍ ማድረግ ነው። በችሎታም ካልበለጥክ፣ ዳኛም ደብቀህ ማስቀረት ካልቻልክ ሦስተኛ ነገር ዳኛም እያየ ቢሆን ፋዎል መስራት ነው” ይላል “ሰሜን ዕዝ ተጠቃ” በሚል የተፈበረከ ሐሰተኛ ውንጀላ በትግራይ ላይ ጦርነት የከፈተ ዐቢይ አህመድ ዓሊ።

ዓቢይ አህመድ ዓሊ፥ የራሱ፣ የኤርትራና የሶማሊያ ሰራዊት እንዲሁም የአማራ ኢንተርሃምወይ ሚኒሻና ታጣቂ በማሰለፍ ትግራይ በሁሉም አቅጣጫ በመክበብና በመውረር የስልክ የኢንተርኔትና የሚድያ አገልግሎት ሁሉ ሙሉ በሙሉ ዘግቶና ቆራርጦ በትግራይ ህዝብ ላይ ለፈጸመው በሰብዊነት የሚፈጸም የጦርና የዘር ጭፍጨፋ መሰረቱ “በብቃት የማትበልጠው አስቸጋሪ ሰው ከሆነ ሰውየው የሚያጠቃው ግለሰብ፥ ዳኛ ሳያይህ፣ ራስህን ደብቀህ፣ ጎንትለህ ጎትተህ ጠልፈህ ኳስዋን እንድትቀር እንድትጨናገፍ ማድረግ ነው” ሲል በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ እየተረከልን ያለ አባባል መሰረት ያደረገ ነው። ያሰለፈው ስፍር ቁጥር የሌለው ሰራዊትና ሚኒሻ የቀናው ሙርኮ እናቱ የረገመችው ደግሞ የሞት ሲሳይ ሲሆንበትና የዓለም መሳቂያ መሳለቂ ሆኜ አለሁ ብሎ ሲያምን ደግሞ ታግሎ ያቃተው ህዝብና ሰራዊት በምግብና በመድሃኒት እጦት ለመበቀል ይሄው “በችሎታም ካልበለጥክ፣ ዳኛም ደብቀህ ማስቀረት ካልቻልክ ሦስተኛ ነገር ዳኛም እያየ ቢሆን ፋዎል መስራት ነው” እንዲል ዓለም እየየና እየሰማ የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ለማብረስ ከበባውን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።

በትግራይ ላይ የተፈጸመ ወረራ፣ የተካሄደ ጦርነትና አሁንም ያለው ህዝብን እንደ ህዝብ በምግብና በመድሃኒት እጦት የመፍጀት ጀኖሳይዳል ወንጀል በተፈበረከ ሐሰተኛ ውንጀላና ፕሮፓጋንዳ ላይ የተመሰረተ ለመሆኑ ከዚህ ቀደም በዐይጋ ፎረም ለንባብ በበቁ በርካታ ጽሑፎቼ በስፋትና በጥልቀት አስረድቻለሁ። ከብዙ በጥቂቱ ለማስታወስ ያህል ታድያ፥ በወቅቱ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ የነበረ ኋላ በዐቢይ አህመድ ዓሊ ቀጥተኛ ትዕዛዝና በጓዶቹ የአማራ ልሒቃን እጅ የተገደለ አበረ አዳሙ የትግራይ ህዝብ ሞት እልቂት በማስመልከት ደስታቸውን ለመግለፅ በተዘጋጀ የደስታና የፌሽታ መድረክ ላይ ትግራይን ለመውረር ቀደም ብለው ዝግታቸው እንደጨረሱና ጦርነቱም በአማራና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች በምሽት እንዴት እንደ ጀመሩት ነጥብ በነጥብ ሲያስረዳ ተናጋሪውና ተጋባዥ ባለ ስልጣናቱ “ሰሜን ዕዝ ስለ ተጠቃ ነው” በሚለው የዐቢይ አህመድ ዓሊ የተፈበረከ ትርክትና ሐሰተኛ ውንጀላ ክት ብለው እየሳቁ ነው። ይህ ብቻም አይደለም፥ አንድ የዐቢይ አህመድ ዓሊ ከፍተኛ መኮነን (ኮረኔል) በፊናው ኢትቪ ወቅታዊ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ያለው ደግሞ ይህን ነበር “ሠራዊቱ (የኢትዮጵያ ሠራዊት) የተዘጋጀ መሆኑን የምታውቀው የመጀመሪያ ጥይት ከወያነ ቡድን ጋር ሶሮቃ አከባቢ የኮማንዶ አሃዱና በዚያ አከባቢ የነበሩ የአማራ ክልል ሚኒሻና ልዩ ኃይል ጋር ነው ውጊያ የጀመረው” በማለት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ትግራይን ለመውረርና ለማውደም አስቀድሞ መዘጋጀቱ ብቻ ሳይሆን የጦርነቱ ጀማሪም የኢትዮጵያ ሰራዊት እንደሆነና ጦርነቱም ሶሮቃ የሚባል አከባቢ እንደ ተጀመረ፤ በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ግፍና በደል የማይገልጸው የዘር ጭፍጨፋም በሚገባ የታሰበበት ለመሆኑ ከዚህ በላይ መረጃና ማስረጃ ሊኖር አይችልም። እንግዲህ፥ በጥቂቱ ይህን ካነበቡ በኋላ ዐቢይ አህመድ ዓሊ በትግራይ ላይ የፈጸመው ወረራና ይህን ተከትሎም በሰውና በንብረት ላይ ያደረሰው ውድመትና የዘር ጭፍጨፋ አሁንም “የፖለቲካ ልዩነት” የፈጠረው ችግር ነው/ነበር፤ አንድም፥ “ሰሜን ዕዝ ስለ ተነካ ነው” ብለው የሚያምኑ ከሆነ ሰበአዊነት እንዲሰማዎትና የሚሸጥ ልብ ካለም ነፍስዎን ሽጠውም ቢሆን ልብ እንዲገዙ ብቻ ነው ልጠይቆት የምችለው።

እውን የትግራይ ህዝብ የህልውና ትግልና ጥያቄ፥ የፖለቲካ ልዩነት ነውን?

የፖለቲካ ልዩነት ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲካ ሲባል በጽርእ ይጻፍ በላቲን፣ በአማርኛ ይነገር በእንግሊዝኛ የኃይለ ቃሉ ፍቺና አንድምታ ዜጎች በጋራ ለሚሰሩት ስራ የሚያደርጉት ውሳኔ አንድም ህዝባዊ አስተዳደር ነው። በመሆኑም፥ የፖለቲካ ልዩነት ሊባል የሚችለው ከሞላ ጎደል የሃሳብና የምልከታ ልዩነት ነው። ይህ ማለት ግን የፖለቲካ ልዩነት እንዲሁ በደፈናው የአመላካከትና የአስተሳሰብ ወይም የሃሳብና የምልከታ ልዩነት ተብሎ እንዲሁ በቀላሉ ተድበስብሶ የሚታለፍ ሳይሆን ልዩነቱ፥ ከባድና ቀላል ተብሎ በደረጃ የሚቀምጥ ከዚህም አልፎ ፈጽሞ የማይታረቅ የራዕይ ልዩነት ጭምር የሚያስከትል ልዩነት የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። ለምሳሌ ያህል፥ ከሰው ኪስ አስር ብር የሰረቀ ሌባ (ሌብነት ወንጀል ነውና) ሌባ ተብሎ ነው የሚታወቀው። የሌብነት አንዱ ትርጉም ያንተ ያልሆነ፣ ላንተ ያልተገባ፣ ያላስቀመጥከውን በክፉ ምክርና ምኞች መመንተፍና መውሰድ ነውና። በተመሳሳይ፥ ዓለም ልታበረክተው የምትችል የላቀና የረቀቀ የጥበቃ ቴክኖሎጂ የታጠረ ምስጢራዊ የመንግስት ግምዣ ቤት ዘልቆ የአገር ሀብትና ምስጢር (ሰነድ) የሚሰርቅ ድርጊቱ ስርቆት ስለሆነ በተመሳሳይ ሌባ ነው። እነዚህ ሁለት ዓይነት ሌቦች ግን እኩል ሌቦች አይደለም። በርግጥ የመጀመርያው፥ ሌባ የፈጸመው ድርጊት እንዲፈጽም የተገደደበት ምክንያት ቢጠየቅ፥ ስለ ራበው የፈጸመው ድርጊት መሆኑን ከተረዳን በኋላ በምክርና በተግሳጽ መግባባት ላይ ተደረሶ አብልተንና አጠጥተን ቀድሞ ከውሰደብን ገንዘብ ሁለት እጥፍ ጨምረን በፍቅር በሰላም ሂድ ብለን ሁላ ልናሰናብተው እንችላለን። የሁለተኛው ሌባ ድርጊት ዓላማ ተልእኮ ግን እጅግ የላቀና የተለየ በመሆኑ፤ ማለትም፥ በአንድ ሰው ብቻ የተፈጸመ ድርጊት አለ መሆኑ፥ የሚመለከተው አካል አገሪቱ ያፈራቻቸው የተዋጣላቸው የወንጀል መርማሪዎችና ባለሞያዎች አሰልፎ በሚያደረገው ምርመራ በከፍተኛ አመራር ላይ የተቀመጡ የአገር መሪዎችና ባለ ሥልጣናት ምክርና ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለበት ድርጊት ሆኖ ሲገኝ ፈጻሚውና ተባባሪዎቹ እንዲሁ በቀላሉ ሌባ ተበለው ሳይሆን የሚታወቁ በአገር ክህደትና ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌለው የወንጀል ዓይነት ተጠቅሶ በሞት ካልሆነ ደግሞ በዕድሜ ይፍታ የእስር ቅጣት ነው የሚቀጡ።     

የአማራ ልሒቃን፥ ለኢትዮጵያ ከፈጣሪ የተሰጠ መንግስታዊ አስተዳደር መለኮታዊ የሆነ ሥርዓተ መንግስት አሃዳዊ ነው ሲሉ፤ ትግራይ ደግሞ፥ የለም ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አገር ናት፣ እንደ አገር አብረን መኖር የምንችለው ደግሞ የፌደራል ሥርዓት የገነባን እንደሆነ ነው ብላ ታምናለች። ይህ እውነትም ልዩነት ነው። ይህ ዓይነቱ ልዩነት ታድያ ተራ ልዩነት ሳይሆን መሰረታዊ የራዕይ ልዩነት ነው። ለሁሉም የሚበጀውና የሚሻለው የፌደራል ሥርዓት ነው ሲባል ይህን ያለ ሁሉ ልዩ ልዩ ታፔላዎች እየተለጠፈበት መጥፋትና መክሰም አለበት ተብሎ በአገርና በህዝብ ስም አንድን ህዝብ እንደ ህዝብ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት መነሳት፣ ኢትዮጵያ ያለ የሌለ አቅሟን ማሰባሰብዋ ሳያንስ የጎረቤት አገራትና መንግስታት ይዛ መጥታ በሰማይና በምድር በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመችው ታሪክ የማይረሳውና ይቅር የማይለው አረማዊ ድርጊት ምክንያትና መንስኤ የሆነ ችግር “በድርድር የሚፈታ የፖለቲካ ልዩነት” ሳይሆን በትግራይ ህዝብ ህልውና      ላይ የተቃጣ ከፖለቲካ ልዩነት ያለፈ ጠላትነት ነው። በህልውና ላይ የሚቃጣ ጠላትነት የሚፈታው ደግሞ አንዱ ሰሜንን ሲመርጥ ሌላኛው ደቡብን፥ ሌላኛው ምዕራብን ሲመርጥ አንደኛውን ወደ ምስራቅ በማሰናበት ብቻ ይሆናል።   

እውነት ነው፥ የፖለቲካ ምልከታና የሃሳብ ልዩነት ያለና በውይይትና በድርድር ለመፍታት የሚገባ ልዩነትም ነው።  የፖለቲካ ምልከታና የሃሳብ ልዩነት በውይይትና በድርድር ለመፍታት አዳጋች የማይሆንበት ምክንያት አንዱ ታድያ፥ ግራ ዘመም ይሁን ቀኝ ዘመም ሁለቱም በልዩ ልዩ ቃላት የሚገልጹት፣ የሚያንጸባርቁትና የሚያራምዱት የፖለቲካ አቋም የተለያየ ቢመስልም የጋራ የሆነ፣ ሁለቱም በእኩልነት የሚያስማማና የሚያግባባ አገር የምትባል መድረክ ስላለ ልዩነቶቻቸው በሰለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት አይቸገሩም። ኋላቀር የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአንጻሩ፥ ባላንጣዎቹ አንድ የሚያደረግ የጋራ የሚባል ነገር አንድስኳ የላቸውም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ፥ ግብዝነት የሞላበት፣ የማታለልና የማስመሰል ክፉ በሽታ የወረረው፣ በኃይማኖት ተሸፋፈነ የበከተ የሌብነት ፖለቲካ በመሆኑ ‘ኮምፕሮማይዝ’ በማድረግ በዘላቂነት የሚፈታ ችግር አይደለም። ዘልአለም ከጦርነትና ከድህነት መላቀቅ ተስኖን እየተዳማንና እየተገዳደልን ያለንበትና የምንገኝበት ምክንያትም ይህ ነው። አሁን ባለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታም የኢትዮጵያ ችግር ሊፈታና ዕልባት ሊያገኝ የሚችለው፥ አንዱ ለሌላኛው ሲሰግድና ራዕዩን ጥሎ ለመኖር የተስማማ እንደሆነ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ የሚሰፋና የሚበጃጀው ጥብቆ ሁሉ እንደ ገና ሦስት አስር ዓመታት ጊዜያዊ ዕረፍት ያስገኝልን ይሆን እንደሆነ ነው እንጅ የመቻቻል ባህል የሌላት አገር የራዕይ ልዩነት ተጨምሮበት በዝግ በር በምስጢር በሚደረግ ድርድር ዘለቄታ ያለው መፍትሔ ያመጣል ብሎ መጠበቅ ሲበዛ የዋህነት ነው። አንድም፥ የችግሩ ምንጭ በአገርና በህዝብ ስም በር ዘግተው የሚወይዩ ያሉ ግለሰቦች ችግር ካልሆነ በቀር፥ በሌላ አባባል፥ ለዚህ ሁሉ ሞትና እልቂት የዳረገን ጦርነት መንስኤው፥ በግለሰቦች መካከል የተፈጠረ የሥልጣንና የጥቅም መተላለፍ ከሆነና ሰዎቹ ያጣላቸው ሥልጣንና ጥቅም አስመልክተው በር ዘግተው በሚስጥር በሚያደርጉት ድርድር መግባባት ላይ ሲደርሱ ጦርነቱ በሴኮንዶች ውስጥ ያበቃል። ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራትና መንግስታት ጋር ግንባር ፈጥራ በትግራይ ህዝብ ላይ ያካሄደውችው ወረራና ይህን ተከትሎም የፈጸመችው በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸውም የጦርና የዘር ማጥፋት ወንጀል ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ነው።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ለማድረግ እወዳለሁ፤ ይኸውም፥ በፖለቲካ አሳቢዎችና ልሒቃን እንዲሁም በህዝቦች መካከል የሃሳብ ልዩነት መታየና መፈጠር አዲስ ነገር እንዳይደለና የሃሳብና የምልከታ ልዩነት ባህሪያዊና ነባራዊ እንደሆነ ልናሰምርበት ይገባል። የራዕይ ልዩነት የተፈጠረ ዕለት፣ እንዲሁም፥ ፍርሃት የሚወልደው ቅናትና ምቀኝነት ወደ ጠላትነት አድጎ በአንድ ህዝብ ህልውናና ደህንነት ላይ በዚህ ደረጃ ሲገለጥ ታድያ ነገሩ እንዲሁ “የፖለቲካ ልዩነት” ተብሎ ዘወትር ሲነገር የምንሰማው ዓይነት ችግር እንዳይደለና የዚህ ዓይነቱ ችግር የችግሮች ሁሉ መሰረትና ምንጭ መሆኑን በተመሳሳይ መንገድ ልናሰምርበት ይገባል። የኢትዮጵያ ችግር፥ አንተም ተው – አንችም ተዪ ተብሎ እንዲሁ የሚፈታ ዓይነት ልዩነት አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር፥ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ እንደማይወጣ እንዲሁ የየራስህ መንገድ በመጠብጠብ የሚፈታ የራዕይ ልዩነትና ቀደም ሲል እንደ ገለጽኩት ፍርሃት የሚወልደው የቅናትና የምቀኝነት ድምር ውጤት የሆነው ጠላትነት ነው ያለው። በሌላ አገላለጽ፥ ማንነት መሰረት አድርጎ በአንድ ህዝብ ህልውና ላይ አነጣጥሮ የሚሰበቅ፣ የሚቃጣና የሚወረወር ጦር፥ ግራ ዘመም – ቀኝ ዘመም ተብሎ የሚመደብም “የፖለቲካ የምልከታና የሃሳብ ልዩነት” ሳይሆን ጸበኞች የየራሳቸው ይዘው እንዲሄዱ የሚያስገድድ ጠላትነት ነው።

ከዚህ ቀደም “ልዩነቶቻችን አቻችለን አንድ በሚያደርገን ነገር አብረን እንስራ” ስንል አንድ የሚያደርገን የጋራ ጥቅም የሚመለከት እንጅ አንድ የሚያደርገን ነገር ኖሮ አይደለም። በተጨማሪም ልዩነት በራሱ መለያየት አለ መሆኑና ለአንድ የጋራ ዓላማ ከመቆም ስለ ማያግድ ነው። ሰው – ሰው ከመሆኑ የዘለለ ሰው ሁሉ መልኩም አሻራውም ልዩ ልዩ ነው፤ የሚያግባባ የጋራ ጥቅም የለውም፤ ይህ ማለት ግን ለጋራ ጥቅም አብሮ መስራት አይችልም ማለት አይደለም። ተወደደም ተጠላም፥ ትግራይ፥ ከአማራ ጋር የሥነ ልቦና፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሥልጣኔ፣ የፖለቲካ፣ የልዩ ልዩ ወጎችና ልማዶች ልዩነት ያለን ህዝቦች መሆናችን ብቻ ሳይሆን የራዕይ ልዩነት ያለን ህዝቦች ጭምር ነን። ሐቁ፥ አንድ ገጽ ብቻ ሳይሆን የሌለነው ፈጽመን የተለዩ መጻህፍት ላይ ያለን ህዝቦች ነን። መጋባትና መውለድ እንደሆነ ትግራይም አማራም ከሱዳናውያን ከቻይናውያን እየተጋባና እየተዋለደ ነው። በመሆኑም፥ ኢትዮጵያ ተባላ ከበቀለችና ከተቀረቆረች ጊዜ ጀመሮ ሲወርድ ሲዋረድ ትውልድ እያዋረደ የሚገኝ የኢትዮጵያ ችግር በዘላቂነት መፍትሔ ሊያገኝ የሚችል ሁሉም የየራሱ ሲይዝ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ችግር የፌዴራል ሥርዓት ካልፈታው አገሮች በመሆን ይፈታል። ይህ የመፍትሔ ሃሳብ ደግሞ ለአማራ ወይም ለትግራይ የሚያደላ፤ አንድም፥ የጥላቻና የመራራነት ሃሳብ ሳይሆን ለሁላችን በፍትሓዊነት የሚዳኝ የመፍትሔ ሃሳብ ነው። ልዩነቶቻችን አቻችለን በእኩልነትና በፍትሓዊነት በአብሮነት መኖር ያቃተን ህዝቦች መሆናችን ብቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ስመ ዝክሩ ለማጥፋት የተኬደው ርቀት ዘልአለም የማይረሳ ታሪክ ነው። በመሆኑም፥ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የወደደውን መንገድ ይምረጥ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከህልውናችንና ከደህንነታችን በላይ አብልጠን የምናየው ሆነ የምናስቀድመው ሌላ ምንም ነገር የለምና ለትግራይ የሚበጅ የመፍትሔ ሃሳብ ትግራይ አገር ሆና መቆም ነው።

ትክክለኛ የመፍትሔ ሃሳብ ለማመንጨት ሆነ ለማስቀመጥ ከምንም በላይ ችግሩን በትክክል ማወቅና ማግኘት እንዲሚጠይቅ እንዲሁ፥ የምንሊክ ዘር ነኝ እያለ እያወከን በሚገኝ ኃይልና በትግራይ ህዝብ መካከል ያለው ገደል፥ ከፖለቲካዊ የሃሳብና የምልከታ ልዩነት ያለፈ የራዕይ ልዩነት ያለን ሁለት ሕዝቦች መሆናችን ሊገባን ይገባል። በትግራይና በአማራ ልሒቃን መካከል ያለው ዘመናት ያስቆጠረ ችግር የማይገልጸው መቆራቆስ በፖለቲካ መደረክ በውይይትና በድርድር የሚፈታ ቢሆን ኖሮ የፌዴራል ሥርዓት በፈታው ነበር። የአማራ ልሒቃን ጭምር ተስማምተው የፈረሙበትና የጸደቀ የፌዴራል ሥርዓት የውሸት (ፌክ) ነበር ቢባል እንኳ፥ የአማራ ልሒቃን ዕድሉን ሲያገኙ፥ ሲያራግቡት ያየነው የፌዴራል ስርዓት የሚባል ነገር ማየትም መስማትም የማይፈልጉ መሆናቸው ነው። ይህ ደግሞ መብታቸው ነው። በኢትዮጵያዊነት፣ በፍቅርና በአንደነት ስም ግን የሰው አገር ሰው የመንካት ሆነ የመግደል መብት ግን የላቸውም። በትግራይ ህዝብ ላይ ለፈጸሙት በደልና ግፍ ተጠያቂዎች ሳይሆኑ እንዲሁ ያመልጣሉ ብሎ የሚያምን ካለ ደግሞ ተሳስቷል፤ በጊዜው በሰፈሩት መስፈሪያ ይሰፈርላቸዋል።

አሁን እርስበርሳችን መሸናገል ተትን እውነት እውነቱ ብቻ እንነጋገር ከተባለ፥ የኢትዮጵያ ችግር ተራ “የፖለቲካ ልዩነት” ሳይሆን ልዩነቱ፥ እኖራለሁ – አትኖርም ነው። ኢትዮጵያ በትግራይ ላይ የፈጸመችው ግፍና በደል ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የበከተ ምንሊካዊ አስተሳሰብ ተከትሎ የመጣ ችግር “ሰሜን ዕዝ ተነካ ተብሎ” ሕዳር አራት በትግራይ ላይ የተፈጸመ ወረራ ተከትሎ የተፈጠረ ችግር አይደለም። እኖራለሁ – አትኖርም የፈጠረው ሞትና ዕልቂት፥ በፖለቲካ መድረክ በውይይት የሚፈታ የፖለቲካ ልዩነት የፈጠረው ችግር ነው ብሎ ማመን ቀርቶ ማሰብ በራሱ ታድያ፥ “ዘይስንኻ ሑፃ ቆርጥመሉ” ወደ አማርኛ ሲመለስ፥ “አለ ጥርስህ አሸዋ ፍጭበት” እንደ ማለት ነው። ወጣም ወረደ፥ ኢትዮጵያ የውስጥም የውጭም አገራትና መንግስታት ጋብዛ በጠራራ ጸሐይ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመችው የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ መጥራትና ሳይሸቃቅጡ በትክክል ማስቀመጥ ካልተቻለ ዘላቂነት ያለው መፍትሔ ይገኛል ብሎ ማሰብ ራስህን ማታለል ብቻ ሊሆን የሚችለው።

ምንሊክ፣ ኃይለስላሴ፣ መንግስቱ ኃይለማሪያም፣ አሁን ደግሞ ዐቢይ አህመድ ዓሊ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸሙትና እየፈጸመው ያለ ለሰሚ ጆሮ እጅግ የሚሰቀጥጥ ግፍና በደል በውይይት የሚፈታ የፖለቲካ ልዩነት ነው ተብሎ የሚታመን ከሆነ፥ ምን አለፋዎት ችግሩ ያለው ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር ሳይሆን ችግሩ ያለው እኛው ጋር ነው። ተወደደም ተጠላም፥ ትናንትም ዛሬም በትግራይ ሰማያት ላይ ያጠላው ጥቁር የሐዘን መጋረጃ፣ ትግራይ በታሪኳና በሥልጣኔዋ ልክ የሚገባት የከፍታ ስፍራ እንዳትቀመጥ ቁልቁሊት ደፍቶ የድህነት መናገሻ ያደረጋት ከዛሬ ያለፈ የነገ ትውልድ አሻግሮ ማየት የተሳነው “ክሳብ ሰማይ ንብላዕ ስንዳይ” ብሎ የሚያምን የትግራይ የፖለቲካ አመራር ነው።

ኢትዮጵያ የፈጸመችብን ግፍና በደል “የፖለቲካ ልዩነት” የፈጠረው ችግር ነው ብሎ የሚያምን ትግራዋይ ካለ፥ በእውነቱ ነገር ኢትዮጵያ ሦስትና አራት ጊዜ እየደጋግመች ባትጨፈጭፈን ነው የሚደንቀኝ። ቀለል ባለ አማርኛ፥ የትግራይ ህዝብ፥ ትግራዋይ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ትግራይዋይ ኢታማጆር ሹም፣ የባንክና የደህንነት ዳይሬክተር ሲሾምና ትግራዋይ ቁልፍ ቁልፍ የፌዴራል ሥልጣን መቆጣጠር ሲችል ብቻ ነው ግፍና በደል የማይፈጸምበት ብለን የምናምን ከሆነ፥ አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይኸውም፥ ስንገፋ አምርረን እየታገልን፣ ታግለን ስናሸንፍ ደግሞ የተከፈለ ዋጋ እንደ ልጣጭ እየጣልን በሄድን ቁጥር ከመቶና ከመቶ አምሳ ዓመታት በኋላ ትግራይ የሚል ግዛት ሆነ የትግራይ ህዝብ የሚባል ህዝብ ሊኖር እንደማይችል ልንጠራጠር አይገባም። የዛሬ መቶ አምሳ ዓመት ስለሚሆን ነገር እኛን አይመለከት ባዮች ከሆነ ደግሞ መፍትሔው ተሸራርፈህ እስክታልቅ ድረስ እያጭበረበርክና እየተጭበረበርክ መኖር ነው።

የትግራይ ህዝብ፥ የገጠመው ችግር ከምንጩ ለማድረቅ ችግሮቹን በሚገባ አጢኖ በትክክል በማስቀመጥ ትክክለኛ መፍትሔ ለማፈላለግና ለመስጠት ካልቆረጠ አሁንም፥ ከጥቂት አስርት ዓመታት በኋላ እንደ ገና መቸገራችን፣ መራባችን፣ መሰደዳችንና መገደላችን የማይቀር ነው የሚሆነው። በማኸል ለጥቂት ዓመታት እያረፍን እንደገና መቁሰላችን፣ ደም መቀባታችንና መገደላችን ይቀጥላል፥ አንድ ቀን ደግሞ እንዲሁ ፈጽመን መጥፋችን የማይቀር ነው። የአንድ ትውልድ ዕድሜ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በተደጋጋሚ ደም እየተቃባን፣ እየተገዳደልን፣ የተወልደ ሁሉ ያለ ቀባሪ አፈር ሲበላው ለማየት እየተገደድን ያለነው በውል የሚታወቀው የኢትዮጵያ ችግር እልባት እንዲያገኝ ከማድረግ ይልቅ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች የትግራይ ህዝብ መስዋዕትነት በማቀጨጭ ጥቅማቸው ሲያሳድዱ እያየን ቁመን መመልከት ስለ መረጥን ነው። ጎበዝ፥ የትግራይ ችግር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የፈጠረው ችግር ብቻ ነው ብል ውሸታም ያደርገኛል።

የኢትዮጵያ ችግር የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ችግር ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ችግር ደግሞ ከብዙ በጥቂቱ የፖለቲከኞቹ የመጨረሻ የፖለቲካ ዓላማና ግብ፥ ህዝብና አገር እንዴት ይጠቀማሉ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ሳይሆን በአንጻሩ፥ በህዝብና በአገር ስም እንዴት ጥቅም አገኛለሁ፣ እንዴት የስልጣን ባለቤት እሆናለሁ የሚል ስስተኝነትና ራስ ወዳድነት የማይገልጸው የአውሬ ባህሪይ የነገሰበት ፖለቲካ የፈጠረው ችግር ነው። እየተባለ ያለ ታድያ፥ እኛም ጋር ችግር አለ ነው። ለዚህ ሁሉ ሞትና እልቂት ያበቃን የበከተ የኢትዮጵያ የትምክህትና የጠላቻ ፖለቲካ ብቻ አይደለም። የእኛ የራሳችን ፖለቲካም ቢሆን መሰረቱ የጣለ (አደራው የበላ) የጥቅም ፖለቲካ ከሆነ ዘመናት ተቆጥሯል። ከዚህ የተነሳም ችግር ውስጥ ገብተናል። ለእኔና ለቤተሰቤ ከደላንና ከተመቸን ጎረቤቴ ለምን በችጋር አያልቅም የምንል ዓይነት ሰዎች ካልሆን በቀር ወደድንም ጠላንም ችግር አለብን። ችግራችን መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው ታድያ የእኛ ችግር ደብቀን የሌላው ችግር እያጎላን በማውራት ሳይሆን እጅ የመቆረጥ ያህል ቢያመንም ችግራችን ለይተን በማወቅ፣ መጠየቅና ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አካል በተጨባጭ ተጠያቂ እንዲሆን በማድረግ፣ የራሳችን ችግር ልንፈታና ወደ ፊት ልንሄድ ይገባል (የትግራይ ችግር በተመለከተ፥ የትግራይ ችግር ምንድ ነው? በሚል በሌላ ርዕስ በስፋት እዳስሰዋለሁ)።

የተጀመረው የተናጠል ውይይት ሆነ ይደረጋል እየተባለ ያለ አገር አቀፍ ውይይት

ዓላማና ግብ ምንድ ነው?

ተስማሙ ሲባል ተታኮሱ፣ እየተታኮሱ ነው ሲባል ተስማሙ! የሚለው ነገር አዲስ ነገር አይደለም። ይህን ዓይነቱ አዙሪት የነበረና ያለ ነው። ሰው ዘላአለም ጦርነት ውስጥ ስለማይኖርም በአንድም በሌላም መልኩ አሁን ያለው ሁኔታ የሚያሳልፍ ሁኔታ መፈጠሩ ግድ ነው። ግድ የሆነው/የሚሆነው ውይይት የሚባለው ነገር ጦርነትን ተክቶ የሚከሰተውም እዚህ ላይ ነው። በዚህ መልኩ የሚካሄድ ውይይትም ቢሆን በአንድ ጊዜ የሚፈጥረው መፍትሔ ኖሮ ሳይሆን ውይይቱ የአንድ አካል ብቻ ፍላጎት ሳይሆን የሁሉም ተሳታፊ አካላት ፍላጎትና ግዴታ እስኪሆን ድረስ ሰጣ-ገባው የሚጠበቅ ይሆናል። ቁም-ነገሩ፥ ወደው ነው ተገደው፣ በሦስተኛ አካል ነው በሌላ መንገድ፥ ሰዎች ለድርድር ሆነ ለውይይት ሲቀመጡ የሚደራደሩና የሚወያዩ አካላት በየፊናቸው የያዙት አንድን ነገር አሳካለሁ ብለው ነው። በሌላ አባባል፥ በሰጥቶ መቀበልም ቢሆን ጥቅማቸው ለማስጠበቅ ነው። ባይሆን ኖሮ፥ ያለውን ለማጣትና ለማስረከብ ለድርድርና ለውይይት የሚቀመጥ ባላንጣ ባልተገኘ ነበር።

ትናንት በፓርላማው ፊት ቀርቦ አንገቴን ለካራ ሲል የነበረ ሰው (ዐቢይ አህመድ ዓሊ) ውስልትናው እየመረረውም ቢሆን ዛሬ እየመሰከርነው ላለነው መድረክ ሊገባ ይቻለ ወዶና ፈቅዶ ሳይሆን ነፍሱን ለማትረፍ ነው። በሶማሌ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሞ፣ በጋምቤላ ወዘተ የለመደው ግድያና ግልበጣ በትግራይ ላይ ሊደግመው ስላልተቻለውና ስለ ከሸፈበት፤ አሁን ባለው ሁኔታም ከቀጠለ አገሪቱ ካለችበትና ከምትገኝበት የኢኮኖሚና ማህበራዊ መቃወስ ከገጠመው ወታደራዊ ሽንፈትና ኪሳር ተደማምሮ እመራዋለሁ የሚለው ህዝብ ሲሳይ መሆኑ ስለማይቀር ከዚህ ለመትረፍም ሳይቸግረው ጎረቤት አገራትና መንግስታት አስተባብሮ በትግራይ ላይ የፈጸመው ወረራና ጦርነት በውይይት አንዲፈታ አጥብቆ ይሻል፤ ይህን ከማድረግም ሌላ አማራጭ አይኖረውም። ከአንድ ዓመት በኋላ፥ ውይይት ድርድር ለማለት የተደረሰም እንዲሁ ሳይሆን በቁጥራቸውና በታጠቁት የጦር መሳሪያ ተማምነው የወረሩንና የጨፈጨፉን የውስጥም የውጭም ኃይሎች ዳግም ደህና አድርገን ስለሰባበርናቸውና ስላንበረከክናቸው እንጅ የጎረቤት አገራትና መንግስታት ይዛ መጥታ ዘር ማንዘራችን ቆጥራ ልታጠፋን የተነሳችና የቻለቸው ሁሉ ያደረገች ኢትዮጵያ ወዳና ፈቅዳ አይደለም። ሲጀመር ነገሩ በውይይት ለመፍታትም አልወረሩንም። የከፈቱብን ጦርነት ስመ ዝክራችን ሊያጠፉና ሊያንበረክሩን ነበር። ይህ ሳይሳካላቸው ሲቀር ደግሞ ዓለም እያየች ካሽመደመድናሸውና ካጥመለመልናቸው “ችግራችን” በውይይት እንፈታለን ተባለ። እንግዲያውስ ምን እንላለን? ጎበዝ፥ እዚህ የተደረሰ፥ በተራራዎች መካከል የሰፈረ፣ ክህነትና ብረት ከደሙና ከዘሩ የማይታጣ፣ በሰላማዊነቱ የተመሰከረለት የትግራይ ህዝብ፥ ትግራይ ትስዕር! ብሎ ከበባው ሳይበግረው በአህጉሪቱ ትላላቅ የሚባሉ ሰራዊት ቆርጦ ሊጥላቸው ቆርጦ በመታገሉ ነው።

ጥያቄው፥ ትግራይዋይ ለውይይት ተስማምቶ ሲቀመጥ ምን ለማግኘትና ለማሳከት ነው? ምስረታ አገረ ትግራይ በሰላማዊ መንገድ እውን ለማድረግ ወይስ በዝግ ቤት በምስጢር በሚደረገው ድርድር ስምምነት ላይ ደርሰናል ተብሎ የትግራዋይ ደም ጠጥታ የሰከረች ጋለሞታይቱ ኢትዮጵያ ሌላ ካባ አልብሶ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል አድርጎ ለማስቀጠል ነው? ስለ አፍሪንና ስለ አዛዝ የተጠየቀ ይመስል ላሊበላና ኮምቦሊቻ በማን ቁጥጥር ስር እንደሆኑ መረጃው የለኝም በማለት በይፋ የሚሸመጥጥ የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ/ም በሰጠው መግለጫ “የውይይቱ ፍሬ ነገር ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚገባው ማይክራፎን ላይ ስምምነት አትጠብቁ” ብሏል። የዚህ አባባል አደገኝነት ለኢትዮጵያዊያን የሚተው ቢሆንም፥ አገር የጠፋችው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከህዝብ ደብቆ ዐረብ አገራት ድረስ በመሄድ ከኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር የተፈራረመው ሰነድ ነው እዚህ ሁሉ እልቂት ወስጥ ያስገባን በማለት ተቃውሞውን በማሰማት የሚታወቀው የትግራይ አመራር የዚህ ውይይት በመሆኑ የተናጠል ውይይትም ቢሆን ምን እየሰራ እንዳለ በግልጽ የማሳወቅ፣ ለህልውናውና ለማንነቱ የህይወት መስዋዕትነት እየለፈለ የሚገኝ የትግራይ ህዝብ የማወቅ መብት አለው።

በጦርነቱ ማግስት የትግራይ አመራር ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገው ውይይት፥ የትግራይ ህዝብ ጥያቄና መሻት በሰላማዊ ሂደትና አሰራር መልስ የሚያገኝበት መድረክ የሚያመቻች (ለማመቻቸት) ከሆነ እውነትም ከቀድሞ ስህተታችን መማራችን ብቻ ሳይሆን የትግራዋይ ሞትና የህይወት መስዋዕትነት ፍሬ አፈራ ማለት ነው። አባሳንጆ መጣ ሄደ እገሌ ተጨመረ እየተባለ የሚደረግ ሽርጉድ፥ ትግራይ በኪሳራ ከተንኮታኮተች ኢትዮጵያ ጋር ለማስቀጠል ሌላ መልኩን የለወጠ አደረጃጀትና መዋቅር ለማመቻቸት ከሆነ ግን ትግራዋይ ሁለት ሞት እንዲሞት መፍረድ ብቻ ሳይሆን ይህን ዓይነቱ መድረክ ተከትሎ ነገ ሊታይ የሚችለው ሰላም የሚመስል የዕረፍት ጊዜ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ሳይሆን እንደ መስቲካ ስኳሩ ሲያልቅ እንጨት እንጨት የሚል፣ ተመልሶ የሚቀጣጠል፣ የጠፋ የሚመስል የተደጎለ እሳት ነው ሊሆን የሚችለው። ለምን? የነገ “ሰላም” ኢትዮጵያ ወድዳና ፈቅዳ የምትገባበት ኪዳን ሳይሆን በኢትዮጵያ ስም የሚነግድ ትምክህተኛ ኃይል ዛሬም እንደ ትናንት ድጋሜ አከርካሪው ስለ ሰበርነው የተገኘ ዕረፍት ስለሆነ ነው። በተጨማሪም፥ ይህ ዓይነቱ ሰላም የሚመስል የዕረፍት ጊዜ እውነተኛ ሰላም ስላይደለ በዕረፍት ጊዜ አብልተንና አጠጥተን ስናወፍራቸው ከሆነ ዘመን በኋላ የበረቱና የጠነከሩ ስለሚመስላቸውና ሆኖ ስለሚሰማቸው ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ሊጨምሩን እንደሚችሉ ግልጽ ስለሆነ ነው። ቀለል ባለ አማርኛ፥ ከታሪካችን እንደምንረዳው ኢትዮጵያ ግልጽ የሆነ የትግራይ ህዝብ የእኩልነትና የፍትሓዊነት ጥያቄ ፈጽሞ ሊገባት ስለማይችል፣ እኩልነት መሰረት ያደረገ የአብሮነት ህይወት ለእኔ አይጥመኝም ባይ ስለሆነች፣ ይህ የምትልበት ምክንያት ደግሞ የትግራይ ህዝብ ህልውና ከመፈታተን ያለፈ ጠንቅ በመሆኑ ለእኛም ለእነሱም የሚጠቅም መፍትሔ በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት የራሳችን መያዝና ራሳችን ችለን መቆም ነው።

መፍትሔው፥ ምስረታ አገረ ትግራይ እውን ማድረግ ነው! የሚል ከአድልዎ የጸዳ የመፍትሔ ሃሳብ፥ ኢትዮጵያ በትግራይ ላይ የተፈጸመችው ወረራና ይህን ተከትሎም በትግራይ ህዝብ ላይ ያካሄደችው የዘር ጭፍጨፋ ብቻ መሰረት ሳይሆን የትግራይ ህዝብ አገር የመሆን ጥያቄ ኢትዮጵያ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመችው ተደጋጋሚ ግፍና በደል እንድትፈጽም ትናንትም ዛሬም ገፊ ምክንያት በመሆን ያገለገለ የበከተ ምንሊካዊ እምነትና አስተሳሰብ ለአንዴና ለመጨረሻ ከትግራይ ህዝብ ትክሻ ላይ ተቆርጦ ወደ እሳት መጣል ስላለበት ነው። አንድም፥ ኢትዮጵያ በቀጣይነት በትግራይ ህዝብ ላይ እፈጠረችው ያለ ችግር የሚፈታ ችግሩን በሚገባ በማጤን መፍትሔው አገር መሆን ነው በማለት የተነሳ የትግራይ ህዝብ ጥያቄና መሻት በመመለስ ስለሆነ ነው። አሁንም ይህን የምለው፥ ኢትዮጵያ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሰው ልጆች ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብና የማታመን ግፍና በደል ስለ ፈጸመችብን፣ የትግራይ ህዝብ ጥያቄ አገር መሆን ከሆነ ህገ-መንግስቱ ይፈቅድላቸዋል ሀገር መሆን ይችላሉ የሚለውና ይህን ብናደርግ ከተጠያቂነት እናመልጣለን ብለው የሚያልሙ የኢትዮጵያ ባለ ሥልጣን ፍርሃትና ጭንቀት የወለደው ዝሩው ቃል መሰረት ያደርገ ሳይሆን ትግራይ በተደጋጋሚ የመቃብር ስፍራ ያደረገ መሰረታዊ የአገሪቱ ችግር በተጨባጭ ማዕከል ያደረገና ያገናዘበ የመፍትሔ ሃሳብ ስለሆነ ነው። በተጨማሪም፥ ይገንጠሉ ሲባል እንቆያለን፤ አትሄዱም ሲባል እንገለጠላለን ዓይነቱ አንጻራዊ እልህም አይደለም። የተሸነፈችው ኢትዮጵያ ታግሎ በጅግንነቱ እዚህ ለደረሰ የትግራይ ህዝብ አቅጣጫ የምትሰጥበት አንዳች የሞራልም የሌላም መብት ሆነ አቅም የላትም። አንድም፥ የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የመፍትሔ ሃሳብ የትግራይ ህዝብ አገር መስርቶ በአገሩ እንዲኖር ከሆነ የማንም ፈቃድና ይሁንታ ሳያስፈልገው ምርጫውና ፍላጎቱ ያለ ከልካይ እናደርገዋለን፥ ከትግራይ አመራር የሚጠበቀው የትግራይ ህዝብ ምርጭና ፍላጎት አክብሮ መንገዱን መጥረግ ብቻ ነው። ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ዛሬ በዝግ በር ሊደረስ የሚችለው የትግራይ ህዝብ ጥቅምና መሻት ያላማከለ ማንኛውም ዓይነት ስምምነት ነገ አንድ ትውልድ ባማይሞላ ጊዜ ውስጥ እልቂቱ ተመልሶ የሚመጣና የትግራይ ህዝብ እየበላ ህልውናው ወደ ማክሰም የሚደርስ የተደጎለ እሳት ሆኖ የሚቀጥል የማይድን ጭንቁር ነው የሚሆነው።

በዚህ አጋጣሚ ማንሳት የምፈልገው ነጥብ ቢኖር፥ በሁሉም ግንባሮች ሽንፈትና ኪሳራ እየተከናነበች ያለችው ኢትዮጵያ በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ለማጽናናት፣ የሌለ አጀንዳ ለመፍጠርና ለማስቀየስ አፍጥጦ የመጣ የአዳነች አበቤ ፍርሃትና ጭንቀት የወለደው ንግግር በዓይነቱ ለየት ያለና አዲስ አነጋገር ሳይሆን ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከበርካታ ወራት በፊት ቀደም ብሎ ትግራይን ለቀን የወጣነው እንዲሁ ሳይሆን በሻሻና አድርገናት ነው የወጣነው! ሲል ባደረገው ንግግሩ ላይ ሙሉ የንግግሩ ይዘት ከአሁን በኋላ ስለ ትግራይ አይመለከተንም፤ የትግራይ ህዝብ የፈለገው መሆን ይችላል፤ ከዚህ ቀደም ከእነሱ ጋር የነበረን ግኑኝነት ሁሉ ሙሉ በሙሉ አቋርጠናል፤ ፈልገውን ከመጡ በራችን ክፍት ነው በዛው እንሄዳለን ካሉ ደግሞ ምርጫቸው ነው፣ እኛም መንገዳቸው ጨርቅ ያርግላቸው እንናለን እያለ በይፋ ያደረገው ንግግር ትርጉምና ፍቺ ነው። ጥጉ፥ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ሊኖረው የሚችል ፖለቲካዊ ሆነ ማህበራዊ አስተሳሰቦችና ልዩነቶቹ አቻችሎ በወንድማማችነት መንፈስ ለመኖር ያለው ጽኑ ፍላጎት ጥያቄ ላይ የሚገባ ሳይሆን የህይወት መስዋዕትነት በመክፍል ያረጋገጠ ህዝብ ነው። ቢሆንም ግን፥ የትግራይ ህዝብ – እኩልነትና ፍትሓዊነት መሰረት ያደረገ በአብሮነት የመኖር መሻት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን (ለምንሊካውያን) ቀልድ ሆኖ ያመጣብን ጣጣና ያስከፈለን ዋጋ አይተነዋል። በመሆኑም፥ ለትግራዋይ የነበረው አማራጭ አንድም ምንሊካውያን በኢትዮጵያዊነት ስም በላዩ ላይ የሚጭኑበት ኋላቀር እምነትና አስተሳሰብ ሲጭኑት ለመጫን መንበርከክ ነው ካለሆነ ደግሞ ለክፉዎች ሴራና ተንኮል አልገዛም፣ እንቢ! በማለት መታገልና ራሱን ችሎ መቆም ነው። እውነት ነው የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ባንዴራ እያውለበለበ ለመጣ ግፈኛ ወራሪ ኃይል እምቢ! ብሎ በደሙና በመስዋዕትነቱ ህልውናው አረጋግጧል። ይህ፥ ትግራዋይ ለክብሩና ለነጻነቱ፣ ለህልውናውና ለማንነቱ ያደረገው ትግልና የከፈለው የህይወት መስዋዕትነት ታድያ የጉዞው ግማሽ መንገድ ብቻ ነው። የሚቀረው ግማሽ መንገድ፥ በመስዋዕትነቱ ያፈሰውና የተቀዳጀው ድል በፖለቲካ አሸናፊነትና ብልጫ በማተም ፈጽሞ ከእርግማን መገላገልና አገር ሆኖ መቆም ነው። ለመሆኑ፥ የትግራይ አገር መሆን የሚያከስራቸው አካላት እነማን ናቸው? ምክንያታቸውስ ምንድ ነው?

የትግራይ አገር መሆን የሚያከስራቸው እነማን ናቸው?

ምክንያታቸውስ ምንድ ነው?

በቀጠናው፥ የተፈጥሮ ሀብት፣ የኢኮኖሚ፣ የመልክዓ መድሩ አቀማመጥ ተከትሎም የጸጥታና የደህንነት ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው ርዕሰ ኃያላኑ ልዩ ልዩ ወቅታዊ አጀንዳዎች ለጊዜው አቆይተን፥ የትግራይ አገር መሆን የሚያከስራቸው አካላት በጥቂቱ ሦስት አካላት ናቸው። ሦስቱ እነማን ናቸው? ምክንያታቸውስ ምንድ ነው? ለሚለው ጥያቄ እጅግ በጥቂቱ የተመልከትን እንደሆነ፥ 

  1. ጥሮ ግሮ ሰርቶ ሳይሆን ትግራይን የዋጠች ኢትዮጵያ በመፍጠር ኢትዮጵያን እያለበ፣ እየመዘበረና እየዘረፈ የመኖር ህልም ያለው የኤርትራ መንግሥት ነው። ዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ልሒቃን ሥልጣናቸው ለመጠበቅና ለማስቀጠል የሄዱበት ርቀት እዚህ ድረስ ነው። እነዚህ በነጋ በጠባ ቁጥር፥ ኢትዮጵያ አገሬ፣ ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ ኢትዮጵያ መቃብሬ! እና ሌሎች በርካታ ሐሰተኛ መፈክሮች እያስተጋቡና የአዞ እምባ እያነቡ በኢትዮጵያዊነት ስም እየተማማሉ ኢትዮጵያን የገዘገዙና የአገሪቱ ህዝቦች ወደ መቀመቅ የጨመሩ ሰዎች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሳይቀር ምንኛ ቀልድ እንደሆነባቸው፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር በዚህ ደረጃ ማጠልሸታቸው ሳያንስባቸውም ለኢሳይያስ አፈወርቂ አሳልፈው እንደሰጧት ፍንትው አድርጎ የሚሳይ ነው። ባይሆን ኖሮ፥ ኤርትራ በዚህ ደረጃ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እጇን ሰዳ ባልፈተፈተችና የራስዋ ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን በደም ባላጨቀየች ነበር። እዚህ ላይ ኤርትራን በተመለከተ አንድ ነገር ማወቅ ይጠበቅብናል፤ ይኸውም፥ የኢሳይያስ አፈወርቂ ከሳላሳ ዓመታት በፊት የከሰመ የቀጠናው አያቶላህና ሲንጋፖር የመሆን እቅድና ምኞች የኤርትራና ኤርትራውያን አቅምና ጉልበት መሰረት ያደረገ ሳይሆን፥ በስርቆት፣ በዝርፊያና በማጭበርበር ከኢትዮጵያ በሚገኝ ሀብት መሰረት ያደረገ በመሆኑ ኤርትራ እንደ አገር መቀጠል የምትችለው ትግራይን የዋጠች ኢትዮጵያ የተፈጠረለት እንደ ሆነ ብቻ ስለሆነ ኢሳይያስ አፈወርቂና ደጋፊዎችና ምስረታ ሀገረ ትግራይ መስማት ሆነ ማየት የሞት ያህል ነው የሚከብዳቸው። ሐቁ፥ ኤርትራ ከትግራይ ጋር ያላት ግኑኝነት ካላስተካከለች፣ ለዚህ ሁሉ ውድቀትና ድቀት ችጋርና ድህነት የማገዳት ትዕቢትና እብሪት ወጥቶላት ጸባይዋ ካላሳመረች፣ ከትግራይ ጋር ካልተስማማችና ሰላም ካላወረደች በቀር የኤርትራ መንግስትና ህዝብ አሁን የሚገኝበት የጨለማ ህይወት የምጡ መጀመሪያ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። በዓመት ከሣላሳ ተማሪ በላይ አስተምራ ለማስመረቅ የተሳናት ኤርትራ ራስዋ የቻለች አገር ብትሆንም አሁንም ከትግራይ ጋር ያላት ግኑኝነት ካላስተካከልች ሲም ካር በሌለው (ኔትዎር በሌለው) የስልክ ቆፎ የማውራት ያህል ሆኖባት የምትገኝበት የመቃብር ህይወት እንደኖረች እንዲሁ ትኖራለች። በመሆኑም፥ የኤርትራ መንግሥት ትግራይ አይደለም አገር ሆና ሊያይ ቀርቶ የትግራይ ህዝብ ህልውና እንዳይኖረው፥ ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከአማራና ከኢምሬት ጋር መክሮና ዘክሮ ከአርባ በላይ ክፍለ ጦሮች በመላክ ትግራይን ወረዋል፣ ሀብት ንብረቱ ዘርፏል፣ ከዚህም በላይ በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽሟል።
  • በይፋ በአደባባይ በተሰጠው መንግስታዊ መግለጫ፥ የትግራይ ህዝብ ጠላት ህዝብ ነው! በማለት በትግራይ ህዝብ ላይ የጦርነት አዋጅ ያወጁ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ፖለቲካ እያራገቡ በግርግር የምንሊክ ዘውድ ለመጫን የሚቋምጡ የጸሐይ ብርሃን/እውነት የሚያጠፋቸው ቫምፓየሮች (vampire) የአማራ ልሒቃን ናቸው። ይህ ሲባል፥ እንዴ ነው ነገሩ? ሐሰተኛ ወሬና አሉባልታ በማናፈስ ህዝቡን በትግራይ ጠል ፖለቲካቸው አጥምቀው አገሪቱ የደም ምድር ያደረጉ ሰዎች እንዴት ነው ትግራይ ተገንጥላ እንድትሄድላቸው የማይፈልጉ? ከእነሱ በላይ የትግራይ መገንጠል ለማየት የሚሻና የሚናፍቅ ሌላ ማን ቢኖር ነው? አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ባንዴራ እንደ ልብስ አሰፍተው፥ እምዬ፣ እናቴ፣ መቃብሬ እያሉ የአዞ እምባ እያነቡ ሲያለቃቅሱ፣ ሲመጻድቁብንና በአደባባይ ወጥተው የትግራይ ህዝብ ጠላት ህዝብ ነው፣ ከዚህ ህዝብ ጋር ፈጽመን ልንቆራረጥ ይገባል፣ ጥላቻ በሚገባ መሰበክ አለበት! እያሉ የክተትና የዝመት ነጋሪት እየመቱ እሳቱን ያነዳዱና በቀጥይነት እያያዙት የሚገኙ የአማራ ልሒቃን አይደሉም ወይ? በማለት በርካታ ጥያቄዎች በማንሳት ራሱን የሚጠይቅ ቁጥሩ የማይናቅ አንባቢ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ። እውነት ነው፥ የአማራ ልሒቃን እነሱ ብቸኛ የኢትዮጵያ ተቆርቋሪዎችና ጠበቆች ሌላውን ማህበረሰብ ደግሞ አፍራሽ እንደሆነ በማስመሰል የሚያራግቡት ትርክት ለረጅም ዘመን የተሰበከ ዲስኩር በመሆኑ የዚህ ዓይነቱ ጥያቄ ባይነሳ ነው ሊያገርም የሚችለው። የአማራ ልሒቃን በየ አደባብዩ እየወጡ፥ የማትሞት መርዛም ምላሳቸው እየወለወሉ “ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት አንሞታለን! ኢትዮጵያ ወይ ሞት!” እያሉ ሲፎክሩ፣ ሲያቅራሩና ሲሸልሉ የሚያይና የሚሰማ ሰው፥ ሰዎቹ በእውነት ስለ ኢትዮጵያ የሚጨነቁ ሰዎች ናቸው ብሎ ቢገምትና ቢያስብ አይፈረድምበት። ከነተረቱ፥ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለው ግን ይህ ሁሉ የአማራ ልሒቃን ሐሰተኛ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በማደናገርና በማወናበድ ትምክህተኛ ምንሊካዊ የአገዛዝ ስርዓት ዳግም ለመትከልና በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጫንቃ ላይ ለመጫን የሚጠቀሙት ስልት፣ የሚያስነሱት አቧራና ፕሮፓጋንዳ፤ አንድም፥ የሚፈልጉት ለማግኘት እንደ መሰላል (means) የሚጠቀሙበት ታክቲክ እንጅ በተለይ በአሁን ሰዓት ትግራይ ጥሏቸው የሄደች እንደሆነ የአማራ ልሒቃን የሚጠብቃቸው ምን እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች ናቸው። የአማራ ልሒቃን በአሁን ሰዓት፥ የምንሊክ፣ የጃንሆይና የደርግ ዘመን ተመልሶ እንደማይመጣና ዘመናቸው እንዳበቃ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ቀለል ባለ አማርኛ፥ የአማራ ልሒቃን አይደለም የአገር ተቆርቋሪዎች፣ ጠበቆችና ጠባቂዎች ሊሆኑ ቀርቶ መቀመጫቸው የማይጠብቁ ቢራቢሮ እንደ መሆናቸው መጠን መርዛም ምዋርተኛ ምላሳቸው እየወለወሉ በትግራይ ላይ የሚያናፍሱት አሉባልታና ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የተነሳ በሚፈጠር ግርግር ሾልኮው የምንሊክ ዘውድ ለመትከል እንጅ በልባቸው ኢትዮጵያ ማለት በባህል፣ በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በፖለቲካና በሥልጣኔ ትግራይ ማለት እንደሆነች፤ በተመሳሳይ፥ ትግራይን አውጥተህ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ትኖራለች ብለው አይደለም በውናቸው በህልማቸውም አያልሙትም። የአማራ ልሒቃን የኢትዮጵያ ባንዴራ እያውለበለቡ፣ በኢትዮጵያዊነት ስም የሚመጻደቁበት ታሪክ ሁሉ ካርቦን ኮፒ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በተጨማሪም፥ የኢትዮጵያ ታሪክ እያሉ በተውሶ የሚያወሩት ታሪክ ሁሉ ብሉ-ፕሪንቱ ትግራይ መሆንዋን አሳምረው ያውቃሉ። ትግራይ አገር የሆነች ዕለትም የአማራ ልሒቃን ፍሬ አልባ በለስ ሆነው በቁማቸው ደርቀው እንደሚቀሩ፣ ያለ የትግራይ ክብር፣ ታሪክና ህልውና ሊኖራቸው እንደማይችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። ትናንት፥ ጋላ ሻንቅላ እያሉ ልዩ ልዩ ስም እየሰጡ ሲያሸማቅቁት የኖሩት፣ የናቁትና የተጸየፉት የኦሮሞ ህዝብ “ኦሮ-ማራ” እያሉ ሊደልሉት ቢሞክሩም አሁን እንዴት ሿሿ ሊሰራቸውና ሰጥ ለጥ አድርጎ ሊገዛቸው እንደሚችል በቂ ትምህርት ቀስመዋል ብቻ ሳይሆን አርፈው ከመቀመጥ ውጪ ሌላ አማራጭ እንዴ ሌላቸው በሚገባ በርቶላቸዋል። በመሆኑም፥ የአማራ ልሒቃን “ኢትዮጵያ አትፈርስም” የሚል መፈክር እያውለበለቡ ካልሆኑ በቀር ጠላት ህዝብ ነው፣ ፈጽመን ልንቆራረጥ ይገባል ያሉት ህዝብ ማለትም የትግራይ አገር መሆን በቀጥታ አይቃወሙም። ለምን? የዋሉት እንደሆነ አቅመ ቢስነታቸውና ሽንፈታቸው በይፋ ስለሚገልጥና ስለሚያረጋግጥ ነው። “ኢትዮጵያ አትፈርስም!” እያሉ ሲጮኹ የሰማን እንደሆነም የሰዎቹ ጨኸት አገር ወዳዶች ስለሆኑ ሳይሆን ያለ ትግራይ በስም ብቻ የያዘች ኢትዮጵያ ካልሆነች በቀር ኢትዮጵያ የምትባል አገር ልትኖር እንደማትችል ስለሚያውቁ ነው። ሌላው፥ ለትግራይ ህዝብ የሚያስቡ በመምሰልና የትግራይ ህዝብን ለማሸማቀቅ በማሰብም፥ ቢገነጠሉ ምን ይበላሉ? ማለትን ያበዛሉ። ለምን? ያልን እንደሆነ የትግራይ አገር መሆን ራቁታቸው ስለሚያስቀራቸውና እንደ ወላጅ አልባ ህጻን ተንከራታች መሆናቸው ስለሆነ ነው እንጅ ለእኛ አስበውልን አይደለምና። “ምን ይበላሉ” የሚለው የልሃጫሞቹ የአማራ ልሒቃንና ከበሮ መቺዎቻቸው አባባል የሚመነጨው የትግራይ አገር መሆን ሰዎቹ ምን ያህል እንደ ሚያስጨንቃቸው፣ እንደ ሚያስበረግጋቸውና እንደ ሚያበሽቃቸው ሁነኛ ማሳያ ነው። ተሓጓሚ ተሎስ ተሓዚ!
  • በስንዴ መካከል እንክራዳድ እንደማይታጣ እንዲሁ፥ ህዝባዊ አጀንዳ የሌለውና መቀላወጥ የለመደ፣ በትግራይ ህዝብ ስም መነገድ የሚችሉበት፣ ግን ደግሞ የተመናመኑና ሞራል የሌላቸው በጣት የሚቆጠሩ የእኛ ሰዎች ወይም የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ዐቢይ አህመድ ዓሊ ተዋጊ ጀቶች እየላከ የትግራይ ህጻናትና እናቶች ሲጨፈጭፍ በሚኒስትር ማዕረግ የመከላኪያ ሚኒስትር ሆኖ የተቀመጠ አሻንጉሊት አብርሃም በላይ የተባለ ግለሰብ ትግራዋይ ነው። አዲስ አበባ ተቀምጦ ትግራዋይ በማንነቱ እያደነ እያሰረና እያሳሰረ ያለ አረጋዊ በርሀ የተባለ ግለሰብም ቢሆን ትግራዋይ ነው። የትግራይ ህዝብ ስቃይና ህመም የማይሰማቸው፣ በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግዱ፣ የትግራይ ህዝብ ጠላቶች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም። ጠላትነት ለራስ ጥቅም ተብሎ የህዝብ ጥቅምና ፍላጎት መጉበጥ ተብሎ ከተተረጎመ ትግራይ ውስጥ ተቀምጦ በትግራይ ህዝብ እየተማማለ የትግራይ ህዝብ ዓቅሙና ጉልበቱ ተጠቅሞ ሰው የደረሰበት እንዳይደርስ በራሱ ሚዛን እየመዘነ አይሰራ አያሰራ ሆኖ ማነቆ የሆነና ትግራይ ቁልቁል የደፋ የወዳጅ መሳይ ጠላት እንዳለ ማወቅ ለራስ ነው።

የትግራይ አገር መሆን የሚያከስረው ትግራዋይ ማን ነው?

አሁን በዚህ ሰዓት፥ የትግራይ ህዝብ ውክልና አለኝ የሚል በትግራይ ህዝብ ስም በህቡእ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና እንድትቀጥል የሚፈልግና የሚሰራ መኖሩ ስንሰማ  ለብዙዎቻችን ልብ የሚሰብር ዜና ሊሆንብን እንደሚችል ይታመናል። የዚህ ንባብ ዓላማ ታድያ ይህን ዓይነቱ ህቡእ አቋም የሚያራምዱ ሰዎች ለማውገዝ ሳይሆን፥ ሌላው ይቅር ልጆቹ እያጣ ያለ ህዝብ የልጆቹ ሞት በከንቱ እንዳይደለ አውቆ ይጽናና ዘንድ ዕድል እንዲሰጠው ነው። በንኡስ ርዕሳችን ለተነሳ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠቴ በፊት ግን ለወዳጅም ለጠላትም አንድ ነገር ግልጽ ለማድረግ እወዳለሁ። ይኸውም፥ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆኖ የምትቀጥለው ለኢትዮጵያ ተብሎ ሳይሆን ለትግራይ ጥቅም ነው፤ አገር በመሆን ከሚገኝ “ጥቅም” (ጥቅም የሚለው ቃል ለጸሐፊው የህልውናችንና ደህንነታችን ዋስት ማረጋገጥ ነው) ይልቅ በመቆየት የምናገኘው ጥቅም ይበልጣል ብሎ በምክንያትና በተጨባጭ የሚሞግትና የሚያሳምነኝ ግለሰብ ይሁን ቡድን የተገኘ እንደሆነ አሁንኑ ሃሳቡን ደግፌ እቆማለሁ። ምክንያቱም፥ በትግራይ ጉዳይ ስንመካመርና ስንሟገት ቀዳሚና ተከታይ የሌለው የርዕሳችን ማዕከል ትግራይና የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነት ስለሆነች ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ እዚህ ሞገት ውስጥ ስፍራም ዕድልም የላቸውምና። ይህ ማለትም ሌላው ገደል ይግባ የሚል “የእኔነት” አንድምታ ፈጽሞ የለውም። አንድም፥ ትግራዋይ ባለንጀራውን እንደ ራሱ አድርጎ የሚመለከትና የሚቀበል እንጅ ከራሱ በታችም በላይም አድርጎ አይመለከትምና።  አሁን ወደ ተነሳው ጥያቄው ለመለስ፥   

ይህ፥ ለትግራይ የሚጠቅም “ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና የቀጠለች እንደሆነ” ብሎ በውስጡ የሚያምነውን እምነት በእውነት የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሃሳብ ነው ብሎ የሚያምን ከሆነ በይፋ አቋሙን የማያስውቅበት ምክንያት ለሁላችን ትንግርት ነው። በርግጥ፥ ይህ ቡድን ለትግራይ ህዝብ የሚበጀውና የሚረባው “ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና የቀጠለች እንደሆነ ነው” ብሎ በተጨባጭ የሚሞግትበት ምክንያታዊ ምልከታና አመክንዮ ቢኖሮው ኖሮ ይህን ያህል ባልተቸገረ ነበር።  በአንድ በኩል፥ ምስረታ ሀገረ ትግራይ በይፋ የሚቃወም የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲ ሳይኖር በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየታችን በራሱ ችግሩ ስለሌለ ሳይሆን ችግሩ በይፋ ያልተገለጠና ከብዙዎች እይታ የተሰወረ በመሆኑ ነው። ታድያ፥ በትግራይ ህዝብ ስም ሲማማል ጸሐይ የምትጠልቅበት፣ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና እንድትቀጥል በብርቱ የሚሰራና የሚያሴር ቡድን የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችለው አቅም ሆነ ፍላጎት የሌለው ሸማቂ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጸረ ትግራይ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል። የስልጣኔ መሰረት የሆነችው ትግራይ ራስዋን ችላ እንደ አገር እንዳትቆም በራሱ ሚዛን እየመዘነ ጸረ የትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት የቆመ ኃይል ደግሞ ሌላ ማንም ሳይሆን፥  

  • በህዝብና በአገር ስም በመነገድ በአቋራጭ የሚገኝ ጥቅምና ሥልጣን ከማሳደድ ውጪ ሌላ ራዕይና ተልዕኮ የሌለው፤
  • በህዝብ ስም ያልላበበት የህዝብ ሀብትና ንብረት ማግበስበስ የለመደ፤
  • የትግራይ ህዝብ ልጆቹ እየገበረና የህይወት መስዋዕነት እየከፈለ በሚያበራው ችቦ ስልጣኑን አደላድሎ ለመኖር የሚቋምጥ፤
  • አሁንም በትግራይ ወጣቶች ሞትና መስዋዕትነት በትግራይ ህዝብ ስም ክላሱን ጠብቆ የመኖር ፍላጎት ያለው፤
  • ትግራዋይ በማንነቱ ግፍ እየፈጸመችበት የምትገኝ አዲስ አበባ፥ ሥልጣን ለሚፈልግ ሥልጣን ሀብት ለሚፈልግ ሀብት ለመስጠትና ለማጋራት በሮችዋን የከፈተች ዕለት የትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ጥቅምና ጥያቄ ጉዳዩ ያይደለ፤
  • የህዝብ ጥያቄ ይዘው የሚነሱትን ሁሉ ያለ ስማቸው ስም እየሰጠ ብረቱን ወልውሎ ከመረሸን የማይመለስ፤
  • የሥልጣንና የጥቅም ጥያቄው በትግራይ ህዝብ ስም ደጉሶ ዘመኑ ያለፈበት የለበጣ ጨዋታ እየተጫወተ የሚያነክስና የልቡን የሰመረለት ዕለት ደግሞ የትግራይ ህዝብ ጥያቄ የሞኝ ጥያቄ ነው እያለ የሚሳለቅ ኃይል ነው። መልካም ዜናው፥ ይህ ዕንቅፋት የሆነ  ኃይል መናደፊው የተመነገለ በሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከስም ኃይል መሆኑ ነው።

E-mail: [email protected]

By aiga